የሆሎኮስት ሙዚየምና የይሖዋ ምሥክሮች
የናዚ አገዛዝ በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች በተለይ ደግሞ የአይሁድና የስላቭ ዝርያ ባላቸው ላይ አሰቃቂ የሆነ ጭፍጨፋ አካሂዷል። ይሁን እንጂ አንድ ሃይማኖታዊ ቡድን ማለትም የይሖዋ ምሥክሮች በዘራቸው ወይም በብሔራቸው ምክንያት ሳይሆን ሕሊናቸው ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚገዛ በመሆኑ ለናዚ አገዛዝ ለመንበርከክ እምቢተኞች ሆነዋል።—ዮሐንስ 17:14, 16
የናዚ መንግሥት የስደት ዒላማው በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እንዲያነጣጥር በማድረግ ከብዛታቸው ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን ጭፍጨፋ ፈጽሞባቸዋል። ለምን? ምሥክሮቹ በሃይማኖታዊ ምክንያቶች የተነሣ የጀርመን ሌበር ፍሮንት አባሎች ለመሆንም ሆነ በግንባሩ ውስጥ ለማገልገል እምቢተኛ በመሆናቸውና የሂትለርን አመራር የሚያወድስ መፈክር ለማሰማት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነበር። በዚህ ምክንያት ናዚዎች በሚያዝያ 1933 የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት እንዲታገድ አደረጉ። ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ ዓመፅ ፈጽመዋል ተብለው በመከሰሳቸው ወደ ማጎሪያ ካምፖች ለመወርወር የመጀመሪያዎቹ ቡድኖች ሆኑ። አንድ የሙዚየም በራሪ ጽሑፍ እንደሚለው “ከ30,000 በላይ ምሥክሮች በናዚዎች ተሰደዋል።”
በዋሽንግተን ዲ ሲ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የሆሎኮስት መታሰቢያ ሙዚየም የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ ናዚዎች ያሳደዷቸውን ቡድኖች ታሪክ ለማሳየት የተቋቋመ ነው። አንድ ምንጭ እንዳለው ሙዚየሙ “በተለይ የሂትለር አገዛዝ የዘር ማጥፋት ዘመቻ የተነጣጠረባቸውን አይሁዳውያንና የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ አሜሪካውያንም ሆኑ የውጭ አገር ጎብኚዎች ትኩረት የሚስብ ይሆናል።” በሙዚየሙ ኤግዚብሽን፣ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ውስጥ በጦርነቱ ዓመታት ግፍ በተፈጸመባቸው የተለያዩ ቡድኖች ላይ የደረሰውን መከራ የሚያሳዩ የእጅ ሥራ ውጤቶች፣ ሰነዶች፣ በቪዲዮ ክር የተነሱ የዐይን ምሥክሮች የምሥክርነት ቃሎች፣ ታሪካዊ ፎቶ ግራፎችና ፊልሞች ይገኛሉ። በሙዚየሙ ውስጥ የናዚ አገዛዝ ግፍ ፈጽሞባቸው ለነበሩ 74 የይሖዋ ምሥክሮች የተደረጉ ቃለ መጠይቆች የሚገኙባቸው የቪዲዮ ክሮች ይገኛሉ። ሙዚየሙ ለሕዝብ ክፍት የሆነው በሚያዝያ ወር 1993 ነው።
[ምንጭ]
Courtesy of United States Holocaust Memorial Museum