የወጣቶች ጥያቄ . . .
በሐሳብ መመሰጥ ስህተት ነውን?
የሒሳብ አስተማሪህ አሰልቺ ስለሆኑ ስሌቶች ሲናገር እንደነበረ ትዝ ይልሃል። ከዚያ በኋላ ግን በክፍሉ ውስጥ አልነበርክም። አእምሮህ ባለፈው ዓመት ከቤተሰቦችህ ጋር ወደ ጎበኘኸው የባሕር ዳርቻ ሄዷል። የፀሐዩና የአሸዋው ሙቀት ትዝ ይልሃል። የባሕሩ ሞገድ ከባሕሩ ዳርቻ ጋር ሲላተም፣ ሕፃናት ሲቦርቁ . . . የክፍል ጓደኞችህ ሲስቁ ይሰማሃል። አዎን፣ አሁን አስደሳች የነበረው የአእምሮ ሽርሽር አብቅቶ በቦታው በጣም የተቆጣ አስተማሪ ሽንጡን ይዞ ያልሰማኸውን ጥያቄ መልስ እንድትነግረው አፋጦሃል።
በሐሳብ መመሰጥ፣ በሁሉም ዓይነት ሰዎች ላይ፣ በአረጋውያንም ሆነ በወጣቶች ላይ የተለመደ በመሆኑ አንድ የታወቁ ተመራማሪ “የሰው ልጅ ሕይወት ዋነኛ ገጽታ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው” ብለዋል። አንዳንዶች ከእንቅልፍ ሰዓት ውጪ ከምናሳልፈው ጊዜ ውስጥ ሲሶ የሚሆነውን የምናሳልፈው በአንድ ዓይነት ሐሳብ ተውጠን እንደሆነ ያምናሉ። እንደነዚህ ያሉት ብቅ ብለው የሚጠፉ ሐሳቦች የሚፈጠሩት ለምንና እንዴት ነው? በሚለው ጉዳይ ላይም ሆነ በሐሳብ መመሰጥ ራሱ ምንድን ነው? በሚለው ጉዳይ ላይ የሳይንስ ሊቃውንት አንድ ዓይነት አቋም የላቸውም። አንድ መዝገበ ቃላት በሐሳብ መመሰጥን “በምናባዊ ግምት የሚፈጠር . . . አስደሳች ሕልም ነው” ይለዋል። ይሁን እንጂ ብዙ ተመራማሪዎች ትርጉሙን ሰፋ በማድረግ አስደሳች ይሁንም አይሁን ማንኛውንም ዓይነት የቁም ቅዠት ወይም ከፈቃድ ውጭ የሚመጣ ሐሳብ በሙሉ ያጠቃልላል ይላሉ። በዚህ ጽሑፍ በሐሳብ መመሰጥ በሚለው ሐረግ የምንጠቀመው ከፈቃድ ውጭ የሆኑትን ምናባዊ ሐሳቦች ብቻ ሳይሆን ሆን ተብሎ የሚታሰቡትንም ጭምር በሚያጠቃልለው ሰፋ ያለ ትርጉሙ ነው።
ስለዚህ በሐሳብ መመሰጥ ሲባል ሁልጊዜ ልዩና በጣም ደስ የሚሉ ነገሮችን የምናውጠነጥንበት የቁም ቅዠት ማለት ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በሐሳብ ስንወሰድ የምናስበው ቀደም ባለው ጊዜ ያሳለፍነውን ነገር ነው። ፓረንትስ በተባለ መጽሔት በወጣ አንድ ጽሑፍ ዶክተር ጀምስ ካመር የራሳቸውን ተሞክሮ አስፍረዋል። በቢሮአቸው ሲያከናውኑ በዋሉት ሥራ ደክመው ወደ ቤታቸው መኪና እየነዱ በሚጓዙበት ጊዜ በሐሳባቸው ወደ ወጣትነት ዘመናቸው ይመለሱና በቅርጫት ኳስ ጨዋታ እንዴት ያለ ጥሩ ግብ እንዳስገቡ ያስታውሳሉ። “ይህን ያህል አስፈላጊ ሆኖ ሊታወስ የሚገባ ነገር ላይሆን ይችላል። ቢሆንም ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋል” ብለዋል። ሌሎች ደግሞ በሐሳብ የሚመሰጡት የወደፊት ኑሯቸውን ለመቀየስ ነው። አንድ የታወቀ የጃዝ ሙዚቃ ተጫዋችና ቀማሪ የሆነ ሰው “ብዙ ጊዜ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘሁ ሙዚቀኛ ስለመሆን አልምና አስብ ነበር” ብሏል።
ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ሐሳቦች የሚያተኩሩት እንደ ትምህርት ቤት፣ ማኅበራዊ ስብሰባዎችና የቤት ሥራዎች ባሉ ተራ የዕለት ተዕለት ጉዳዮች ነው። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በሐሳብ የሚመሰጡት እየተከታተሉት ያሉት ትምህርት ወይም በቤት ውስጥ የሚያከናውኑት ሥራ አሰልቺ ሲሆንባቸው ነው። ሳይፈለጉ በራሳቸው የሚመጡ ሐሳቦችም አሉ። አንድ ቃል፣ ድምፅ ወይም የሚታይ ነገር አንድ የሚያሳስባቸውን ነገር፣ ቀደም ሲል ያሳለፉትን አስደሳች ሁኔታ ወይም ወደፊት ሊያገኙ የሚፈልጉትን ነገር በድንገት ያስታውሳቸዋል። ከዚያ በኋላ አእምሮአቸው ሽርሽሩን ይጀምራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕልም በሥራ ብዛት ይታያል” ይላል። (መክብብ 5:3) በእርግጥም ስለራሱ በመጨነቅ ወይም ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ በመመኘት የተወጠረ ሰው ቁሳዊ በሆኑ ሐሳቦች መዋጡ አይቀርም።
ይሁን እንጂ በሐሳብ መመሰጥ እውን እንደሆነ ሽርሽር ደስ የሚያሰኝበት ጊዜ ቢኖርም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ በትምህርት ቤትና በሥራ ቦታ ሊኖራችሁ የሚገባውን ትኩረት ሊያጠፋባችሁ ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ሐሳቦች ተገቢ ካለመሆናቸውም በላይ ጎጂዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ በሐሳብ መመሰጥ ልታስወግዱት የሚገባ ልማድ ነውን?
ለአእምሮ ጤንነት አደገኛ ነውን?
ቀደም ባሉት ዓመታት የአእምሮ ጤና አማካሪዎች፣ ዶክተሮችና የትምህርት ባለሞያዎች በሐሳብ መመሰጥ ጥሩ አይደለም የሚል አመለካከት ነበራቸው። በዚህም ምክንያት አንድ የሥነ ልቦና ሐኪም ለአንድ ወጣት “ይህን በሐሳብ የመመሰጥ ልማድ ማቆም እንድትችል ልንረዳህ ይገባል” ብሎ ነበር። ዶክተር ኤሪክ ክሊንገር እንዳሉት እንዲህ ያለው ምክር በሐሳብ መመሰጥ የጨቅላነትና የአእምሮ ቀውስ ምልክት ነው የሚል አስተሳሰብ በነበረውና የሳይኮአናሊስስ አባት በመባል በሚታወቀው በሲግመንድ ፍሩድ መላ ምት ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ ምክንያት አንድ የሳይኮሎጂ መማሪያ መጽሐፍ “በሐሳብ መመሰጥ አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው ባለበት ሁኔታ ባለመርካቱና ከሕልውና ለመሸሽ በመፈለጉ ምክንያት የሚመጣ ነው” ብሏል። በርካታ የአእምሮ ጤና አማካሪዎችና የትምህርት ባለሞያዎች በሐሳብ መመሰጥ ጨርሶ መወገድ ያለበት ነገር እንደሆነ ሲማሩ ኖረዋል። እንዲያውም ከመጠን በላይ በሐሳብ መመሰጥ ስኪዞፍሪንያ የሚባለውን የአእምሮ በሽታ ያመጣል ይባል ነበር።
ይሁን እንጂ የፍሩድ መላ ምቶች በምርምር በተገኙ ማስረጃዎች ተሸንፈዋል። ዶክተር ኤሪክ ክሊንገር ዴይድሪሚንግ በተባለው መጽሐፋቸው ተመራማሪዎች ከሌሎች በርካታ ነገሮች በተጨማሪ የሚከተሉትን እንደሚያምኑ ጽፈዋል:-
በሐሳብ መመሰጥ ጤናማና የተለመደ ነገር ነው።
በአማካይ ሲታይ ብዙ ጊዜ በሐሳብ የሚመሰጡ ሰዎች እምብዛም በሐሳብ ከማይመሰጡ ጋር እኩል ጤናማ አእምሮ ያላቸው ናቸው።
በሐሳብ መመሰጥ የሌለ ነገር ወደ ማየትና መስማት አያመራም።
በሐሳብ መመሰጥ ስኪዞፍሪንያ የሚባለውን የአእምሮ በሽታ አያመጣም። ስኪዞፍሪንያ ያለባቸው ሰዎች ከማንኛውም ጤነኛ ሰው የበለጠ በሐሳብ የመመሰጥ ልማድ የላቸውም።
ምናባዊ ችሎታህን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በምናባዊ ችሎታ ጤናማ በሆነ መንገድ መጠቀምን ፈጽሞ የማያወግዝ መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም። እንዲያውም አእምሮአችን ሊገምትና በምናብ ሊመለከት መቻሉ መዝሙራዊው እንዳለው “ግሩምና ድንቅ” ሆነን መፈጠራችንን ያረጋግጣል። (መዝሙር 139:14) ይህን ችሎታ ፍሬያማ በሆነ መንገድ ከተጠቀምንበት ትልቅ ዋጋ ያለው ንብረት ሊሆንልን ይችላል። ክርስቲያኖች “የማይታየውን እንጂ የሚታየውን” እንዳይመለከቱ ተነግሯቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:18) ይህም አዲሱ የአምላክ የጽድቅ ሥርዓት ምን እንደሚመስል ለማየት መሞከርን ይጨምራል። በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ምድር አቀፍ ገነት የሚሰጠው መግለጫ ምናባችንን ሊቀሰቅስልን ይችላል!— ኢሳይያስ 35:5– 7፤ 65:21–25፤ ራእይ 21:3, 4
በተጨማሪም አንድ ከባድ ሥራ የምታከናውን ከሆነ ሥራህን ለማከናወን ምናብህ ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑት ወጣቶች መካከል በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ንግግር እንዲሰጡ ይመደባሉ። አንተም እንዲህ ያለ ንግግር እንድትሰጥ ስትመደብ ጮክ ብለህ ከመለማመድ በተጨማሪ ንግግርህን በአእምሮህ ለመለማመድ ሞክር። አድማጮችህ የምታቀርበውን ትምህርትና ንግግር እንዴት እንደሚቀበሉት በሐሳብህ ለማየት ሞክር። ይህም በአቀራረብህ ላይ ተገቢ ማስተካከያ እንድታደርግና ይበልጥ በራስህ እንድትተማመን ሊረዳህ ይችላል።
ከዚህም በላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት እንደምትወጣ በአእምሮህ ልትለማመድ ትችላለህ። ምናልባት አንድ ክርስቲያን በአንተ ላይ ቅሬታ እንዳለው ትገነዘብና በጉዳዩ ላይ ተነጋግራችሁ ችግሩ እንዲፈታ ለማድረግ ትፈልግ ይሆናል። (ማቴዎስ 5:23, 24) ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ሳታደርግ ግለሰቡን ከማነጋገር ይልቅ ሁኔታውን በአእምሮህ በመሳል ችግሩን ልትፈቱ የምትችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች በሐሳብህ ልትለማመድ ትችላለህ። ይህም “የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይስማማል።— ምሳሌ 15:28
ያስቀየመህ ወይም ያስቆጣህ ሰው ይኖራልን? መዝሙር 4:4 ላይ የተሰጠውን ምክር ልብ በል:- “ተቆጡ፣ ነገር ግን ኃጢአትን አታድርጉ። በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፤ ዝም በሉ።” ይህ ማለት የተቀየማችሁበትን ነገር በአእምሮአችሁ ውስጥ ስታወጡና ስታወርዱ ኑሩ ወይም ያስቀየማችሁን ሰው እንዴት እንደምትበቀሉ አውጠንጥኑ ማለት አይደለም። እንዲያውም ኢየሱስ “በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤” በተመሳሳይም “ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው” ፍርድ እንደሚገባው አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 5:22) ከዚህ ይልቅ ያስቀየመህን ሰው ይቅር ብሎ መተውን ጨምሮ ያሉህን አማራጮች በሙሉ በአእምሮህ ማውጣትህና ማውረድህ ዝግ ባለና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሰላም ለመፍጠር ሊረዳህ ይችላል።
በተጨማሪም በሐሳብ መመሰጥ አንድን ችግር በመፍታት ረገድ ጠቃሚ ድርሻ ሊያበረክት ይችላል። ዶክተር ክሊንገር እንዲህ ብለዋል:- “በሐሳብ መመሰጥ በፈጠራ ችሎታችን ተጠቅመን ለችግሮች መፍትሔ ለማግኘት ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ነው። በምናባቸው ተጠቅመው በሐሳብ የሚመሰጡ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በቀጥታ ችግራቸውን ለመፍታት ጥረት ቢያደርጉ ሊያገኙ የማይችሉትን መፍትሔ ያገኛሉ።”
እንዲያውም በሐሳብ መመሰጥ በጉልበት የሚሠሩ ሥራዎችን የምታከናውንበትን ሁኔታ ሊያሻሽል እንደሚችል የሚያረጋግጥ ማስረጃ ተገኝቷል። ለምሳሌ ያህል አንድ በበረዶ ላይ የመንሸራተት ስፖርት የሚያስተምሩ ሰው ተማሪዎቻቸው በአንድ የሸርተቴ ውድድር ላይ ወደ ግራና ወደ ቀኝ ሲታጠፉ እንዲሁም ሲወጡና ሲወርዱ በሐሳባቸው እንዲመለከቱ ይነግሯቸዋል። ተመራማሪዎች እንዲህ ማድረግ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን የሚቆጣጠረውን የአእምሮ ክፍል እንደሚያንቀሳቅስና ለሥራ እንደሚያነሳሳ ያምናሉ። አካላዊ ልምምድ ማድረግን የሚተካ ነገር ባይኖርም የአእምሮ ልምምድ ማድረግ የሙዚቃ መሣሪያ የመጫወት ወይም ታይፕ የመምታት ችሎታህን ሊያሻሽልልህ ይችላል። ዶክተር ጀምስ ካመር “በአጭር አነጋገር በሐሳብ መመሰጥ ጊዜ ማባከን ሳይሆን የተሻለ ሥራ እንድንሠራ የሚያስችል አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው” ብለዋል።
አደጋዎቹ
ይሁን እንጂ “ለሁሉ ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:1) በራስህ ክፍል ውስጥ ሆነህ ስትዝናና በሐሳብ መመሰጥ ጥሩ ሊሆን ቢችልም ተገቢ የማይሆንበት፣ እንዲያውም ጎጂ የሚሆንበት ጊዜ አለ። መኪና እየነዳህ ነውን? ከሆነ አደጋ እንዳይደርስብህ ተጨማሪ ንቃትና ትኩረት ሊኖርህ ያስፈልጋል። ፈተና እየወሰድህ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር እያዳመጥክ ከሆነስ? “የጠራ የማሰብ ችሎታ” ሊኖርህ ያስፈልጋል።— 2 ጴጥሮስ 3:1 አዓት
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አሉታዊ በሆኑ ሐሳቦች ላይ እንዳናተኩር ያስጠነቅቀናል። አንድ ወሳኝ የሆነ ፈተና ስትወስድ ወይም ለሥራ ቃለ መጠይቅ ስትቀርብ በመጠኑ መጨነቅ የማይቀር ነገር ቢሆንም እወድቃለሁ ወይም ተቀባይነት አላገኝም ብሎ አስፈሪ የሆኑ ሐሳቦችን በአእምሮ ውስጥ መሳል የሚያስገኘው ውጤት አይኖርም። (ከመክብብ 11:4 ጋር አወዳድር።) ምሳሌ 12:25 [አዓት] “ጭንቀት የሰውን ልብ ይሰብራል” በማለት ያስጠነቅቃል። ኢየሱስ ክርስቶስ አድማጮቹን “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል” ሲል መክሯል።— ማቴዎስ 6:34
ከመጠን በላይ ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር እያውጠነጠኑ በሐሳብ መመሰጥ የሚያስከትለው ሌላ ችግርም አለ። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ወጣቶች ወሲባዊ ድርጊቶችን ያልማሉ። ሌሎች ደግሞ በሐሳብ በመመሰጣቸው ምክንያት በምንም ነገር ላይ ማተኮር ያቅታቸዋል። በሚቀጥለው እትማችን ላይ በዚህ ርዕስ የሚወጣው ጽሑፍ እንደዚህ ያለውን ችግር እንዴት ልታስወግድ እንደምትችል አንዳንድ ሐሳቦችን ይሰጣል።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአእምሮ ልምምድ አንድ ሰው ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን ሊረዳው ይችላል