ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ከመጠን በላይ በሐሳብ የመመሰጥን ልማድ ማቆም የምችለው እንዴት ነው?
ጆናታን የተባለ አንድ ወጣት “ከባድ ችግር ውስጥ ወድቄአለሁ። በሥራ ላይ ሳለሁ፣ በእግሬ ስጓዝ፣ ከመተኛቴ በፊትና ሌላው ቀርቶ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ሆኜ እንኳ በሐሳብ እመሰጣለሁ። ብዙውን ጊዜ የማውጠነጥነው ስለ ሴቶች፣ የጾታ ፍላጎት ስለሚቀሰቅስ ሐሳብ ወይም እንደ አንዳንድ ታዋቂ ወይም የኪነት ሰዎች ስለ መሆን ነው” በማለት ተናግሯል።
በሐሳብ መመሰጥ በወጣቶችም ሆነ በዕድሜ በገፉ ሰዎች ዘንድ የተለመደ ነው። ከልኩ ካላለፈ ሁሉም ሰው የሚያደርገውና ጤናማ ነገር ሊሆን ይችላል።a ሆኖም ጥሩ ነገር እንኳ በጣም ከበዛ ጎጂ ሊሆን ይችላል። (ከምሳሌ 25:16 ጋር አወዳድር።) በተለይ በሐሳብ ተመስጠን የምናውጠነጥናቸው ነገሮች መጥፎ ከሆኑ በሐሳብ መመሰጥ ጎጂ ይሆናል።
ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ የምትወደውን ዘፋኝ እንደሆንክ አድርገህ ታስባለህ እንበል። በመጀመሪያ መድረክ ላይ ሆነህ ብዙ ሕዝብ አድናቆቱን ሲገልጽልህ በማየት በየቀኑ ጥቂት ደቂቃዎች ታሳልፍ ይሆናል። ሳምንታት እያለፉ ሲሄዱ ግን የሙዚቃ ትርዒት ስታሳይ፣ ቃለ ምልልስ ስታደርግ፣ ስትቀረጽ እየታየህ በፈጠርከው የቅዠት ዓለም ውስጥ ብዙ ሰዓታት ማሳለፍ ትጀምራለህ። የምትቃዠው ነገር ደስ ስለሚያሰኝህ ማቆም ያስቸግርሃል።
‘ታዲያ ያልሆኑትን እንደሆኑ አድርጎ ማሰብ ምን ጉዳት አለው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አንዱ ጉዳት ምን እንደሆነ ምሁራን ሲናገሩ ከመጠን በላይ በሐሳብ መመሰጥ የሚያጠቃቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ “በገሃዱ ዓለም አይሳካላቸውም” ብለዋል። (ዘ ፓሬንትስ ጋይድ ቱ ቲንኤጀርስ) በቅዠት ዓለም ውስጥ መኖር የእድገት ሂደቶችን ያደናቅፋል። ሕፃናዊ ባሕርያትን ከመተው ይልቅ እነኚህን ባሕርያት የሙጥኝ እንድትል ያደርግሃል። (1 ቆሮንቶስ 13:11) ስለ ሕይወት ያለህ አመለካከት በገሃዱ ዓለም ላይ ሳይሆን በቅዠት ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ለችግሮች መፍትሔ እየፈለግህ “የማስተዋል ችሎታህን” ከማዳበር ይልቅ ወደ ቅዠት ዓለም እየሸሸህ እድገቱን ታቀጭጨዋለህ። (ዕብራውያን 5:14 አዓት) በዚህ የተነሳ ሕይወትህ በሙሉ በሐሳብህ ስለሚዋጥ በገሃዱ ዓለም ከሰዎች ጋር የሚኖሩህ ግንኙነቶችና ቅድሚያ የምትሰጣቸው ነገሮች ስለሚመሰቃቀሉብህ ሕይወትህ ይበላሽብሃል።
በዶክተር ኤሪክ ኪንገር የተዘጋጀው ዴይድሪሚንግ የተባለ መጽሐፍ በሐሳብ መመሰጥ የሚያስከትለውን ከሁሉ ሊከፋ የሚችል አደጋ ሲጠቁም “ማድረግ የሌለብህን ነገር የምታሰላስል ከሆነ ያንን ነገር ከማድረግ መቆጠብ አስቸጋሪ ይሆንብሃል” ብሏል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሁኔታ “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል” ብሏል። (ያዕቆብ 1:14) ከማንኛውም ድርጊት የሚቀድመው ሐሳብ ነው። አልፎ አልፎ ታዋቂ ዘፋኝ ስለመሆን በማሰላሰልህ ብቻ የዕፅ ሱሰኛ የሆንክ ታዋቂ ዘፋኝ ባትሆንም ‘ለሥጋ ምኞትና ለዓይን አምሮት’ መጥፎ ፍላጎት ልትኮተኩት ትችላለህ።— 1 ዮሐንስ 2:16
የቁም ቅዠትን ማስወገድ
ታዲያ ከእነዚህ የቁም ቅዠቶች እንዴት ልትላቀቅ ትችላለህ? በመጀመሪያ ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ቅዠት የምትቃዠው ለምን እንደሆነ ራስህን ብትጠይቅ ጥሩ ይሆናል።b ሌሎች እንዲወዱህ ስለምትፈልግ ነውን? እነዚህን ታዋቂ ሰዎች ተወዳጅ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ዓይነት ውበት ወይም ችሎታ እንዳለህ ማሰብ ያስደስትሃልን? ወይም ምንም ዓይነት ጭንቀት ወይም ችግር የሌለበት ኑሮ የሚኖሩ መስሎህ በእነርሱ አኗኗር ስለምትቀና ይሆናል። አንድ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያ ታዋቂ ዘፋኝ ስለሆነችው ማዶና ሲናገሩ “አድናቂዎቿ የገንዘብ፣ የትምህርት ቤትና የብቸኝነት ችግር ፈጽሞ የማያውቃት እንደሆነች አድርገው ይመለከቷታል” ብለዋል። በዚህ የተነሳ አንዳንዶች እንደ እርሷ ለመሆን ያልማሉ።
እውነተኛውን ሁኔታ በምክንያታዊነት መመልከት እንዲህ ካለው የቅዠት አስተሳሰብ ሊያላቅቅ ይችላል። በፊልጵስዩስ 4:8 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ሥራበት። እዚህ ጥቅስ ላይ እውነተኛ የሆነውንና ምስጋና ያለበትን ነገር እንድናስብ ተመክረናል። በእርግጥ ዝነኛ ሰዎች ጭንቀት የሌለበት ኑሮ ይኖራሉን? ምግባራቸው ብዙውን ጊዜ የሚያስመሰግን ነውን? በሩጫ የተሞላው ሕይወታቸው የአብዛኞቹን አካላዊና ስሜታዊ ጤና አቃውሷል። ብዙዎቹ ዝነኛ ሰዎች ሀብታም ከመሆን ይልቅ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ ደርሶባቸዋል። ትዳራቸው ያልፈረሰባቸው ጥቂቶች ናቸው። እንደዚህ ዓይነት ሕይወት ለመኖር ማሰብ ትፈልጋለህን?
እርግጥ ነው ለመወደድና ለመደነቅ የማይፈልግ ሰው የለም። የአሥራ ስድስት ዓመቷ ኦሊቭያ “ሁሉ ሰው የሚወዳት ልዩ ሰው” እንደሆነች አድርጋ ታስብ ነበር። ቢሆንም የሕልም እንጀራ እንደማያጠግብ ሁሉ አንድ ሰው በሐሳቡ የሚያውጠነጥነው ነገር ምንም ያህል እውነተኛ ወይም የሚጨበጥ መስሎ ቢታይ ፍላጎቱን ሊያረካለት አይችልም። (ኢሳይያስ 29:8) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም” በማለት ያስጠነቅቃል። (መክብብ 11:4) ስለዚህ ሁሉ ሰው ይወደኛል ብለህ በሐሳብ ከመቃዠት ይልቅ ራስህን ተወዳጅ ለማድረግ ጥረት አድርግ።— በዚህ መጽሔት በኅዳር 22, 1988 (በእንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . ሰዎች እንዲወዱኝ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ወሲባዊ ቅዠቶች
አለን (እውነተኛ ስሙ አይደለም) በአፍላ የጉርምስና ዕድሜው እስካሁን ከተጠቀሱት የተለየ ጉዳይ ያውጠነጥን ነበር። “ወሲባዊ ሐሳቦችን በአእምሮው መፍጠር ይችል” ስለነበር አብዛኛውን ጊዜውን እነዚህን ሐሳቦች በማውጠንጠን ያሳልፍ ነበር። ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን ሆኖ ራሱን ለአምላክ ወሰነ። “ይሁን እንጂ ራሴን መወሰኔ ምንም ዓይነት ለውጥ አላመጣልኝም። ወሲባዊ ሐሳቦችን ማሰብና ማሰላሰል የሕይወቴ ክፍል ሆኖ ቆየ” በማለት አለን እውነቱን ተናግሯል።
አንተስ ወሲባዊ ሐሳቦችን ከማውጠንጠን መላቀቅ አስቸግሮሃልን?c የጾታ ፍላጎት በሚያይልበት “አፍላ የጉርምስና” ዕድሜ ላይ የምትገኝ ከሆነ ይህ ሁኔታ ያልተለመደ ነገር ላይሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 7:36) ቢሆንም ሆነ ብለህ ወሲባዊ ሐሳቦችን የምትኮተኩትና የምታሳድግ ከሆነ ራስህን ትጎዳለህ። መጽሐፍ ቅዱስ በቆላስይስ 3:5 ላይ ‘በምድር ያሉትን ብልቶቻችሁን ግደሉ፤ እነርሱም ዝሙት፣ ርኩሰትና ፍትወት ናቸው’ በማለት ይናገራል። ወሲባዊ ቅዠቶችን ማሰላሰልና ማውጠንጠን በውስጣችን መጥፎ ፍላጎቶች እንዲያድጉ ያደርጋል። ማስተርቤሽን ወይም ዝሙት ወደ መፈጸም ሊመራን ይችላል።
ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ድርጊቶችን የማለም ልማድ ለመቅጨት የሚቻለው እንዴት ነው? አለን እንዲህ በማለት የሚያስታውሰውን ይናገራል:- “በወሲባዊ ሐሳቦች ምትክ ሌላ ነገር ለማውጠንጠን ወሰንኩ። ትኩረቴ ሌላ ነገር ላይ ካረፈ ወሲባዊ ሐሳብ ማውጠንጠን አልችልም።” አለን በዚህ መንገድ ራሱን መጎሰም ተማረ። (1 ቆሮንቶስ 9:27) የሚያንጹ ነገሮችን ማሰላሰልና ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ሐሳቦች ሲመጡበት ወዲያውኑ ከአእምሮ ማስወገድ ተማረ። (መዝሙር 77:12 የ1980 ትርጉም) አለን “በመጨረሻ ተሳክቶልኛል!” በማለት ተናግሯል።
በሐሳብ የምንመሰጠው ሥራ ስንፈታ እንደሆነ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ስለዚህ በሥራ በተለይም ‘በጌታ ሥራ’ መጠመድ መጥፎ ሐሳቦች ሥር እንዳይሰዱ መከላከል የምንችልበት ሌላኛው መንገድ ነው።— 1 ቆሮንቶስ 15:58
አእምሮህ እንዲዋልል አትፍቀድ
በብዙዎቹ ወጣቶች ላይ ችግር የሚያስከትለው አእምሯቸው የሚመሰጥበት ሐሳብ ዓይነት ሳይሆን በሐሳብ መመሰጣቸው በትምህርት ቤት እንቅስቃሴያቸውና በጥናታቸው ላይ እንቅፋት መሆኑ ነው። “ሐሳቤን ሰብሰብ አድርጌ በትኩረት መከታተል አልችልም” በማለት የ16 ዓመቷ ካሪን ችግሯን ትናገራለች። “አእምሮዬ በአንድ ነገር ላይ እንዲረጋ ማድረግ ፈጽሞ አልችልም።” የምትሰማውን ነገር በትኩረት መከታተል የምትችለው እንዴት ነው? (ከማርቆስ 4:24 ጋር አወዳድር።) በሐሳብ ተመስጠህ የምታሳልፈው ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ብታውቅ ይህን ልማድ ለመቆጣጠር ሊረዳህ እንደሚችል አንዳንድ ተመራማሪዎች ያምናሉ። ክፍል ውስጥ ተቀምጠህ በሐሳብ ጭልጥ ብለህ መሄድህን ባወቅህ ቁጥር በብጣሽ ወረቀት ላይ ምልክት ልታደርግ ትችላለህ። ጥናት የተደረገባቸው ተማሪዎች ከላይ የተጠቀሰውን በማድረጋቸው በሐሳብ የመመሰጥ ልማዳቸው በከፍተኛ መጠን ቀንሷል።
በተጨማሪም ለምትማረው ትምህርት ያለህን ፍላጎት ለማሳደግ ጥረት አድርግ። ሒሳብ አሰልቺ ነው ወይም ታሪክ ችክ ያለ ነው ብለህ ከደመደምክ እነዚህ ትምህርቶች በሚሰጡበት ክፍለ ጊዜያት ሐሳብህን ሰብሰብ አድርገህ በትኩረት መከታተል አስቸጋሪ ይሆንብሃል። ትምህርቱ እንዴት ሊጠቅምህ እንደሚችል የምትገነዘብ ከሆነ ለትምህርቱ የተሻለ ፍቅር ይኖርሃል። መማርህ ቢያንስ “የማሰብ ችሎታህን” ለማዳበር ይረዳሃል። (ምሳሌ 1:4 አዓት) አስፈላጊ የሆኑ ችሎታዎችንም ልትቀስም ትችላለህ። ለምሳሌ የሒሳብ ትምህርት በመሥሪያ ቤት፣ ቤተሰብ በማስተዳደርና አንዳንድ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶችን በመወጣት ረገድ ይጠቅምሃል። የታሪክ እውቀት የተለያዩ ሕዝቦችንና ዜናዎችን ለመረዳት ያስችልሃል። የይሖዋ ምሥክር የሆነው የአሥራ አራት ዓመቱ ዳንኤል እንዲህ ብሏል:- “ሁልጊዜ የቤት ሥራዬን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ለማዛመድና ትምህርቱን በስብከቱ ሥራ እንዴት ልጠቀምበት እንደምችል ለመመልከት እጥራለሁ። እንዲህ ማድረጌ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብዬ ስለ ኳስ ጨዋታ ከማሰብ ጠብቆኛል፤ የቤት ሥራዬንም ቶሎ ለመጨረስ አልጣደፍም።” አዎን፣ ለምትማረው ነገር ከፍተኛ ዋጋ በሰጠህ መጠን አዲስ ነገር ለማወቅ በንቃት ትከታተላለህ።— ከምሳሌ 2:4 ጋር አወዳድር።
በተለይ እንደ ምግብ ማብሰል፣ እንደ ጽዳት ወይም እንደ ፋይል ማደራጀት የመሳሰሉትን የተለመዱ የዕለት ተዕለት ሥራዎች ስታከናውን ሐሳብህን ሰብሰብ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። ሸርተት ብሎ በሐሳብ ጭልጥ ለማለት በጣም ቀላል ነው! ሆኖም ከፍተኛ እርካታ የሚገኘው አንድን ሥራ ጥሩ አድርጎ በመሥራት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መክብብ 2:24) በተጨማሪም ‘ሁሉን ነገር ለይሖዋ እንደምንሠራ አድርገን እንድናከናውን’ ያበረታታናል። (ቆላስይስ 3:23) እንዲህ ያለው ገንቢ አመለካከት ትኩረትህን ሰብሰብ ለማድረግ ያስችልሃል። የ12 ዓመቱ ሳሙኤል “ትኩረቴን በምሠራው ነገር ላይ ሳደርግ ሥራው ቶሎ ያልቅልኛል” ብሏል።
በሐሳብ መመሰጥ አስደሳች ሊሆን ቢችልም ለገሃዱ ዓለም ምትክ ሊሆን አይችልም። ይህ ልማድ ሕይወትህን እንዲቆጣጠር አትፍቀድለት። አእምሮህን ጎስመው። ጠቃሚ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርግ። እንዲህ ካደረግህ ከመጠን በላይ በሐሳብ የመመሰጥን ልማድ ከማስወገድህም በላይ ‘እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀህ ትይዛለህ።’— 1 ጢሞቴዎስ 6:19 አዓት
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በጥቅምት— ታኅሣሥ 1995 እትማችን ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . በሐሳብ መመሰጥ ስህተት ነውን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b ችግሮችን ከመጋፈጥ ይልቅ ወደ ቅዠት ዓለም ገብቶ ለማምለጥ መሞከር ከበስተጀርባው ከባድ ችግር መኖሩን የሚያመለክትበት ጊዜ አለ። የቁም ቅዠት በሚያዘወትሩ አዋቂ ሰዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኞቹ በልጅነታቸው ተጎሳቁለዋል ወይም በጾታ ተነውረዋል። የቁም ቅዠትን ከችግር ማምለጫ መንገድ አድርገው ይጠቀሙበታል። አንድ በደል የተፈጸመበት ወጣት እምነት ሊጥልበት የሚችል አዋቂ ሰው እርዳታ ያስፈልገዋል።
c ሰዎች በአጠቃላይ ወሲባዊ ሐሳቦችን በማውጠንጠን የሚያሳልፉት ጊዜ ሌሎች ሐሳቦችን ከሚያውጠነጥኑበት ጊዜ ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ሆኖም በዶክተር ኤሪክ ክሊንገር የተዘጋጀው ዴይድሪሚንግ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ስሜታችንን ያነሳሱ ነገሮች ይበልጥ ጉልህ ሆነው ይታወሱናል። ወሲባዊ ሐሳቦችን ማውጠንጠን የጾታ ፍላጎት ስለሚቀሰቅስ ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ሐሳቦች ይልቅ የምናስታውሰው ወሲባዊ ሐሳቦችን ነው።”
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁሉ ሰው ይወደኛል ብለህ በሐሳብ ከመቃዠት ይልቅ ራስህን ተወዳጅ ለማድረግ ጥረት አድርግ