ሁሉም የሰው ዘሮች በሰላም አንድ ላይ የሚኖሩበት ጊዜ
እግዚአብሔር “በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ።” (ሥራ 17:26) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጅ አመጣጥ ይህን ቀላልና ግልጽ መግለጫ ይሰጣል።
ይህም ማለት የሰው ልጆች በየትኛውም የምድር አካባቢ ቢኖሩ፣ ምንም ዓይነት ቁመናና መልክ ቢኖራቸው ከአንድ የዘር ግንድ የመጡ ናቸው ማለት ነው። በተጨማሪም በሰው ልጆች መካከል በገሐድ የሚታዩ ልዩነቶች ቢኖሩም “የሰው ወገኖች ሁሉ” እኩል የሆነ ችሎታቸውንና እውቀታቸውን የማዳበር አቅም አላቸው። አዎን፣ በአምላክ ዓይን የማንኛውም ብሔርና ዘር አባሎች እኩል ናቸው።— ሥራ 10:34, 35
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ትክክለኛ ከሆነ በዘር ልዩነት ላይ የተመሠረተ ጥላቻና ግፍ በሙሉ እንደሚወገድ ተስፋ አለ ማለት ነው። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰብዓዊው ቤተሰብ አመጣጥ የሚሰጠው መግለጫ እውነት ከሆነ ይኸው መጽሐፍ መላው የሰው ዘር በሰላምና በአንድነት ሊኖር የሚችልበትን መመሪያ ሊሰጥ ይችላል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።
ታዲያ መረጃዎቹ ምን ያመለክታሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጆች አመጣጥ የሚሰጠው መግለጫ በሳይንስ ተረጋግጧልን?
ሳይንሳዊ ማስረጃ
አር ቤነዲክትና ጂ ዌልትፊሽ በተባሉት አንትሮፖሎጂስቶች የተዘጋጀው ዘ ሬስስ ኦቭ ማንካይንድ የተባለ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “የመላው ሰብዓዊ ዘር አባትና እናት ስለሆኑት ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረው በርካታ መቶ ዓመታት የቆየ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የዘመናችን ሳይንስ ካረጋገጠው ሐቅ ጋር አንድ ነው። የምድር ሕዝቦች በሙሉ ከአንድ የዘር ግንድ የተገኙና አንድ ቤተሰብ ናቸው።” በተጨማሪም እነኚሁ ጸሐፊዎች “በጣም ውስብስብ የሆነው የሰው አካል አሠራር . . . አንድ ዓይነት የሆነው ሁሉም የሰው ዘሮች ከአንድ አባትና እናት የተገኙ በመሆናቸው እንጂ እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ አይደለም” ብለዋል።
በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የዙዎሎጂ ፕሮፌሰር በሆኑት በኤል ኬ ዱን የተዘጋጀው ሬስ ኤንድ ባዮሎጂ የተባለ በራሪ ጽሑፍ “ሁሉም ሰዎች መሠረታዊ በሆኑት አካላዊ ገጽታዎች ተመሳሳይ በመሆናቸው አንድ ዘር እንደሆኑ ግልጽ ነው። ከየትኛውም ወገን የሆኑ ሰዎች ከማንኛውም ሌላ ወገን ጋር ሊጋቡ ይችላሉ፣ ይጋባሉም” ይላል። ከዚያም በመቀጠል “ቢሆንም እያንዳንዱ ሰው ከሌላው የተለየና በጥቃቅን መንገዶች ከማንኛውም ሌላ ሰው ጋር የማይመሳሰል ነው። ይህም የሚሆነው በከፊል ሰዎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች የተለያዩ በመሆናቸውና በከፊልም በዘር የወረሷቸው ባሕርያት (ጂን) የተለያዩ በመሆናቸው ነው” በማለት ያብራራል።
የተገኘው ሳይንሳዊ ማስረጃ ፈጽሞ የማያሻማ ነው። በባዮሎጂያዊ አነጋገር የበላይ ወይም የበታች የሆነ፣ ንጹሕ ወይም የተከለሰ ዘር የለም። አንዳንዶች በዘር ልዩነት ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጧቸው እንደ ቆዳ፣ ፀጉር ወይም የዓይን ቀለም ያሉት ልዩነቶች ከአንድ ሰው የማሰብ ችሎታ ወይም ብቃት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም። ከዚህ ይልቅ በዘር ውርሻ የሚገኙ ባሕርያት ናቸው።
በእርግጥም ሃምፕተን ኤል ካርሰን ኸረዲቲ ኤንድ ሂውማን ላይፍ በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደጻፉት በተለያዩ ዘሮች መካከል ያለው ልዩነት በጣም አነስተኛ ነው። “አሁን ያጋጠመን እንቆቅልሽ እያንዳንዱ የሰው ልጆች ዘር በውጪ ሲታይ የተለያየ ሆኖ በውስጡ ግን መሠረታዊ ተመሳሳይነት ያለው መሆኑ ነው።”
ታዲያ የሰው ልጆች በሙሉ አንድ ቤተሰብ ከሆኑ የዘር ጥላቻና ግጭት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?
ይህ ችግር ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?
ዘረኝነት ሊኖር የቻለበት መሠረታዊ ምክንያት የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ወላጆች ለልጆቻቸው መጥፎ ጅምር ማውረሳቸው ነው። አዳምና ሔዋን ሆን ብለው በአምላክ ላይ በማመፃቸው ፍጽምና የጎደላቸው እንከን ያለባቸው ሆኑ። በዚህም ምክንያት ሰዎች ወደ መጥፎ ድርጊት እንዲያዘነብሉ የሚያደርገው ይህ የአዳም አለፍጽምና ዝንባሌ ለዘሮቹ በሙሉ ተላለፈ። (ሮሜ 5:12) ስለዚህም ሁሉም የሰው ልጆች ከዕለተ ልደታቸው ጀምረው ራስ ወዳድና ኩሩዎች መሆን ይቀናቸዋል። ይህም የዘር ግጭትና ውዝግብ አስከትሏል።
ዘረኝነት የኖረበት ሌላም ምክንያት አለ። አዳምና ሔዋን ከአምላክ አገዛዝ ባፈነገጡ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ወይም ዲያብሎስ ብሎ በሚጠራው ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ቀንበር ሥር ወደቁ። ይህ ‘መላውን ምድር የሚያስተው’ መንፈሳዊ ፍጡር በሚያሳድረው ተጽእኖ ምክንያት ሕዝቦች ስለ ዘር ትክክለኛ አመለካከት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ብዙ ጥረት ተደርጓል። (ራእይ 12:9፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) ዘረኝነት፣ ማለትም የራሴ ዘር ከሌላው ሁሉ ይበልጣል የሚለው አስተሳሰብ፣ የሰዎችን ስሜት እንደ እሳት የሚያቀጣጥል ሆኗል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በዚህ የስሜት ግንፋሎት መነዳታቸው አስከፊ ውጤት አስከትሏል።
በግልጽ ለመናገር ከዘረኝነት ጋር ለተያያዙ ችግሮች ምክንያት የሆነው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያሉት ራስ ወዳድ የሆኑትና ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ዘርን አስመልክቶ የሐሰት ትምህርቶችን ማስፋፋታቸው ነው።
ስለዚህ የሰው ዘር አንድ እንዲሆን ከተፈለገ ሰዎች ሁሉ አንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ መሆናችንንና አምላክ “በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ” መፍጠሩን ማመን ይኖርባቸዋል። (ሥራ 17:26) ከዚህም በላይ የሰው ዘሮች በሙሉ አንድ ላይ በሰላም እንዲኖሩ ከተፈለገ ሰይጣን በሰው ልጆች ጉዳዮች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ መወገድ ይኖርበታል። እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? እንዲህ ይሆናል ብለን የምናምንበትስ ምክንያት ይኖር ይሆን?
የዘር ጥላቻ መጥፋት
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን እርሱ እንደወደዳቸው እነርሱም ‘እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ’ ባዘዛቸው ጊዜ የዘር ጥላቻ የሚወገድበትን መንገድ አመልክቷል። (ዮሐንስ 13:34, 35) ይህ ፍቅር ለአንድ የተለየ ዘር ወይም ለተወሰኑ ዘሮች ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ “ለመላው የወንድማማቾች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ” በማለት መክሯል።— 1 ጴጥሮስ 2:17 አዓት
ይህ ክርስቲያናዊ ፍቅር የሚገለጸው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” ይላል። (ሮሜ 12:10) ሁሉ ሰው እርስ በርሱ ሲከባበር እንዴት ያለ ሁኔታ እንደሚኖር ገምቱ! እያንዳንዱ ሰው ሌሎች ምንም ዓይነት ዘር ወይም ብሔር ቢኖራቸው ‘ከእርሱ እንደሚበልጡ አድርጎ በመመልከት’ ሳይንቃቸው በእውነተኛ አክብሮት ይይዛቸዋል ማለት ነው። (ፊልጵስዩስ 2:3) ይህን የመሰለ ልባዊና ክርስቲያናዊ ፍቅር ሲኖር የዘር ጥላቻ ችግር መፍትሔ ያገኛል።
እርግጥ ነው፣ አእምሮአቸው በዘር ጥላቻ ተቀርጾ ያደጉ ሰዎች ከዚህ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ለመላቀቅ ከባድ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ አስተሳሰብ መላቀቅ ይቻላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ የታቀፉ ሰዎች በሙሉ ከዚያ በፊት ታይቶ የማያውቅ አንድነት አግኝተው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ አንድነት ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።” (ገላትያ 3:28) በእርግጥም የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ከልብ የመነጨ የወንድማማችነት መንፈስ ነበራቸው።
ሆኖም አንዳንዶች ‘ይህ በዛሬው ጊዜ ሊሆን የማይችል ነገር ነው’ ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ አምስት ሚልዮን በሚያክሉት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል በአሁኑ ጊዜ ተፈጽሟል። ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ከአምላክ የራቀ ዓለም ከተማሩት የዘር ጥላቻ ሙሉ በሙሉ ጸድተዋል ለማለት አይቻልም። አንዲት ጥቁር አሜሪካዊ የይሖዋ ምሥክር ስለ ነጭ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚከተለው በማለት በሐቀኝነት ተናግራለች:- “አንዳንዶቹ በውስጣቸው ገና ሙሉ በሙሉ ያልጠፋ የዘር የበላይነት ስሜት እንዳለ እመለከታለሁ። አንዳንድ ጊዜ ከእነርሱ የተለየ ዘር ካላቸው ሰዎች ጋር መቀራረብ እንደሚያስቸግራቸው አስተውያለሁ።”
ቢሆንም ይህች ሴት የሚከተለውን አምናለች:- “የይሖዋ ምሥክሮች፣ በምድር ላይ ከሚኖር ከማንኛውም ሕዝብ ይበልጥ ራሳቸውን ከዘር ጥላቻ አጽድተዋል። በዘር የተለያዩ ቢሆኑም እርስ በርሳቸው ለመፋቀር ጥረት ያደርጋሉ። . . . በአንድ ወቅት ነጮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ባሳዩኝ እውነተኛ ፍቅር ልቤ ተነክቶ እስከ ማልቀስ ደርሻለሁ።”
ታዲያ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ የዓለም ሰዎች ሰይጣናዊ በሆነው የዘር የበላይነት ሐሳብ ተመርዘው እያሉ በጥቂት ሚልዮኖች በሚቆጠሩት በእነዚህ ሰዎች መካከል የዘር አንድነት መኖሩ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? የእነዚህ ሰዎች መለወጥ ለዘር ጥላቻ መፍትሔ እንደማይሆን እናምናለን። የሰው ልጅ በራሱ ጥረት የዘር ጥላቻን ሊያስወግድ አይችልም። ይህን ለማድረግ የሚችለው ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው።
በቅርቡ ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚተዳደረው መንግሥት አማካኝነት ማንኛውንም ዓይነት ግፍና በዘር ላይ የተመሠረቱትንም ሆነ ሌሎች የአድልዎ ዓይነቶችን በራስ ወዳድነት የሚያስፋፉትን ሰዎች ከምድረ ገፅ ያጠፋል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) በዚያ ጊዜ በክርስቶስ አስተዳደር ሥር በሚሰጠው ፍጹም የሆነ የትምህርት ፕሮግራም ሁሉም ዘሮች አንድ ይሆናሉ። ይህ የትምህርት ፕሮግራም ወደፊት እየገፋ ሲሄድ የሰው ልጆች ማንኛውንም የዘር ጥላቻና የአድልዎ ርዝራዥ አስወግደው ፍጹም በሆነ አንድነት መኖር ይጀምራሉ። በመጨረሻም “የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና . . . እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” የሚለው የአምላክ ተስፋ ይፈጸማል።”— ራእይ 21:4, 5
እውነተኛ ወንድማማችነት ሰፍኖ፣ ሁሉም የሰው ዘሮች በሰላምና በአንድነት የሚኖሩበትን ጊዜ ለማየት ትጓጓለህን? ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ዘወትር ወደሚሰበሰቡበት በአካባቢህ የሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ሄደህ በስብሰባቸው ላይ እንድትገኝ እንጋብዝሃለን። ለሁሉም ዘሮች ልባዊ የሆነ ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየትና አለማሳየታቸውን ራስህ አይተህ ፍረድ።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅርቡ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩ ዘሮች በአንድነትና በሰላም ይኖራሉ