የዘር ጉዳይ ይህን ያህል አወዛጋቢ የሆነው ለምንድን ነው?
ታሪክ መመዝገብ ከጀመረበት ዘመን አንስቶ “እኛ” እና “እነርሱ” ብሎ መነጣጠል በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ነግሦ ቆይቷል። ብዙ ሰዎች ማንኛውንም ነገር በትክክል የሚያደርጉና ትክክለኛ የሆኑ ሰዎች እነርሱ ብቻ እንደሆኑ አድርገው ያምናሉ። ይህ ዓይነቱን አስተሳሰብ የሳይንስ ሊቃውንት ኤትኖሴንትሪስዝም ብለው ሲጠሩት ከራሴ አሠራርና ሕዝብ በስተቀር ትክክለኛ የለም ብሎ ማመንን የሚያመለክት ቃል ነው።
ለምሳሌ ያህል የጥንቶቹ ግሪኮች ማንኛውንም ግሪካዊ ያልሆነ ሕዝብ “ባርባርያን” ብለው በመጥራት በንቀት ይመለከቱ ነበር። “ባርባርያን” የሚለው ቃል የመጣው ባዕዳኑ ይናገሩ የነበረው ቋንቋ ለግሪካውያኑ ጆሮ “ባር ባር” የሚል ድምፅ ከማሰማት በስተቀር ምንም ዓይነት ትርጉም የማይሰጥ ስለነበረ ነው። ከግሪካውያን በፊት የዓለም ኃያላን የነበሩት ግብጻውያንም ሆኑ ከግሪካውያን በኋላ የተነሱት ሮማውያን ሌሎች ሕዝቦችን የበታች አድርገው ይመለከቱ ነበር።
ቻይናውያን ለበርካታ መቶ ዓመታት አገራቸውን ዦንግ ጉዎ ወይም መካከለኛው መንግሥት ብለው ይጠሩ ነበር። እንዲህ ብለው ይጠሩ የነበረው ቻይና፣ ሲሆን የመላው ጽንፈ ዓለም፣ አለበለዚያም የመላው ዓለም እምብርት እንደሆነች ያምኑ ስለነበረ ነው። ቀይ ፀጉር፣ ቀላ ያለ ፊትና፣ አረንጓዴ ዓይን የነበራቸው አውሮፓውያን የሆኑ ሚስዮናውያን ወደ ቻይና በመጡ ጊዜ ቻይናውያን “ባዕዳን ዲያብሎሶች” ብለው ጠሯቸው። በተመሳሳይ ደግሞ የሩቅ ምሥራቅ ሰዎች በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታዩ በዓይናቸው ቀዳዳ ጠባብነትና ለየት ባለው ባሕላቸው ምክንያት በንቀትና በጥርጣሬ መታየት ጀመሩ።
ይሁን እንጂ ዘ ካይንድስ ኦቭ ማንካይንድ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሌላ ቁምነገር አለ። “የራሴ [ዘር] ከማንኛውም ሌላ ዘር ይበልጣል ብሎ ማመን አንድ ነገር ሲሆን ይህን በሳይንሳዊ ግኝቶች አማካኝነት ለማረጋገጥ መሞከር ግን ሌላ ነገር ነው።” በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አንደኛው ዘር ከሌላው የሚበልጥ መሆኑን በማስረጃ ለማረጋገጥ የተለያዩ ሙከራዎች ማድረግ የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። አንትሮፖሎጂስቱ አሽሊ ሞንታጉ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “በአእምሮም ሆነ በአካላዊ ባሕርያት እርስ በርሳቸው የሚለያዩ ሥነ ፍጥረታዊ ወይም ባዮሎጂያዊ የሰው ዘሮች አሉ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ እስከ አሥራ ስምንተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ድረስ ፈጽሞ የማይታወቅ ነገር ነበር።”
በዘር የበላይነት ረገድ የተነሳው አወዛጋቢ ጉዳይ በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመናት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ለምን ነበር?
የባሪያ ንግድና ዘር
ዋነኛው ምክንያት ከፍተኛ ትርፍ ያስገኝ የነበረው የባሪያ ንግድ በዚያ ወቅት እጅግ በጣም ተስፋፍቶና ዳብሮ የነበረ መሆኑና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ተገደው በመወሰድ በአውሮፓና በአሜሪካ ባሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ መደረጉ ነበር። ብዙ ጊዜ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ተነጣጥለው ሁለተኛ ሊተያዩ ወደማይችሉባቸው የተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይወሰዱ ነበር። ታዲያ በአብዛኛው ክርስቲያኖች ነን ይሉ የነበሩት ባሪያ አሳዳሪዎችና ባሪያ ፈንጋዮች ይህን ኢሰብዓዊ ድርጊታቸውን እንዴት ትክክለኛ ለማስመሰል ይችላሉ?
ጥቁር አፍሪካውያን በተፈጥሮአቸው ከነጮች ያነሱ ናቸው የሚለውን አስተሳሰብ በማሰራጨት ነው። ዴቪድ ሂዩም የተባሉት የ18ኛው መቶ ዘመን ስኮትላንዳዊ ፈላስፋ “በአጠቃላይ ሌሎች ዘሮች በሙሉ፣ በተለይ ደግሞ ጥቁሮች ከነጮች ያነሱ ናቸው የሚል ግምት አለኝ” ሲሉ ጽፈዋል። እንዲያውም ሂዩም “በጥቁሮች ዘንድ ምንም ዓይነት የጥበብ ሥራ ወይም ኪነ ጥበብ ወይም ሳይንስ ማግኘት አይቻልም” እስከማለት ደርሰዋል።
ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አባባል ፈጽሞ ስህተት ነው። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ (1973) “በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች በጣም የሰለጠኑ የጥቁሮች መንግሥታት ነበሩ። . . . ከ1200 እስከ 1600 [እዘአ] በነበሩት ዘመናት በምዕራብ አፍሪካ ቲምቡክቱ በተባለው ቦታ በጣም የተደራጀ የጥቁሮችና የአረቦች ዩኒቨርሲቲ የነበረ ሲሆን በስፔይን፣ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ በጣም ከፍተኛ የሆነ ዝና አትርፎ ነበር” ብሏል። ቢሆንም በባሪያ ንግድ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ሰዎች እንደ ሂዩም የመሰሉትን ፈላስፎች መከተልና ጥቁሮች ከነጮች ያነሱ፣ እንዲያውም ከሰውነት ደረጃ ዝቅ ያሉ እንደሆኑ ማመንና መቀበል ፈለጉ።
ሃይማኖትና ዘር
ባሪያ ፈንጋዮች በዘረኛ አመለካከታቸው ረገድ ከሃይማኖት መሪዎች በቀላሉ የማይገመት ድጋፍ አግኝተው ነበር። ከ1450ዎቹ ዓመታት ጀምሮ የሮማ ካቶሊክ ሊቃነ ጳጳሳት ድንጋጌዎች “የአረማውያንና የማያምኑ” ሰዎች “ነፍሳት” ድነው “ወደ አምላክ መንግሥት” እንዲገቡ እነርሱን ባሪያ አድርጎ መግዛት ትክክል እንደሆነ ይገልጹ ነበር። የጥንቶቹ አውሮፓውያን አገር አሳሾችና ባሪያ ፈንጋዮች የቤተ ክርስቲያን ቡራኬ ተለይቷቸው ስለማያውቅ ባሪያ አድርገው ይገዟቸው በነበሩት ሰዎች ላይ የጭካኔ ድርጊት በመፈጸማቸው ሕሊናቸው አልቆረቆራቸውም።
ስሌቨሪ ኤንድ ሂውማን ፕሮግረስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “በ1760ዎቹ ዓመታትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩት በርካታ አሥርተ ዓመታት ጥቁሮችን ባሪያ አድርጎ መግዛት የካቶሊክ፣ የአንግሊካን፣ የሉተራንና የፕሪስቢቴሪያን አብያተ ክርስቲያናትን እንዲሁም የተሐድሶ ሃይማኖታውያንንና የሃይማኖት ምሁራንን ድጋፍ አግኝቶ ነበር። አባሎቹ ባሪያ አሳዳሪዎች ወይም አስተላላፊዎች እንዳይሆኑ ለማድረግ የሞከረ አንድም ዘመናዊ ቤተ ክርስቲያን ወይም ኑፋቄ የለም።”
አንዳንዶቹ አብያተ ክርስቲያናት ስለ ዓለም አቀፋዊ የክርስቲያኖች ወንድማማችነት ቢናገሩም የዘር ልዩነቶችንና ግጭቶችን የሚያፋፍሙ ትምህርቶችን አስፋፍተዋል። ለምሳሌ ያህል ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ እንዲህ ይላል:- “ስፔናውያን በአሜሪካ ምድር ያገኟቸውን የአገሩን ተወላጆች ነፍስ እንዳላቸው ሰዎች አድርገው መቀበል የጀመሩት ረዥም ትግልና ሰፊ የሆነ ሃይማኖታዊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው።”
ይህ ሁሉ እነዚህ የአገሩ ተወላጆች የሆኑት ሰዎች ወደ ክርስትና በመለወጣቸው ምክንያት “ነፍሳቸው” “እስከ ዳነ” ድረስ ምንም ዓይነት አካላዊ ጉስቁልና ቢደርስባቸው ምንም አይደለም የሚል አስተሳሰብ ያስተላልፋል። ብዙ ሃይማኖታዊ መሪዎች ምንም ቢሆን ጥቁሮች በአምላክ የተረገሙ ሕዝቦች ናቸው ብለው ይከራከራሉ። ይህንንም ክርክራቸውን ለማሳመን ጥቅሶችን አጣምመው በማስረጃነት ያቀርባሉ። ሮበርት ጃመሰን፣ ኤ አር ፎሰት እና ዴቪድ ብራውን የተባሉት ቀሳውስት በጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንታኔ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ከነዓን ርጉም ይሁን [ዘፍጥረት 9:25]— ይህ እርግማን ከነዓናውያን ፈጽመው በመጥፋታቸው፣ ግብጽ በመዋረድዋና የካም ዝርያዎች የሆኑት አፍሪካውያን ባሪያዎች በመሆናቸው ተፈጽሟል።”— ኮመንተሪ፣ ክሪቲካል ኤንድ ኤክስፕላነተሪ፣ ኦን ዘ ሆል ባይብል
የጥቁሮች አባት ተረግሟል የሚለው ትምህርት ፈጽሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኝ ትምህርት ነው። የጥቁር ዘር የመጣው ከኩሽ እንጂ ከከነዓን አይደለም። በ18ኛው መቶ ዘመን ጆን ውልመን በዚህ እርግማን በመጠቀም ጥቁሮችን ባሪያ አድርጎ መግዛትና የተፈጥሮ መብታቸውን መንፈግ ትክክለኛ ነው ብሎ መከራከር “ጠንካራ መሠረት ባላቸው ሥርዓቶች ለመገዛት ከልቡ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደ አእምሮው ሊያስገባው የማይገባ መናኛ አስተሳሰብ ነው” በማለት ተከራክረዋል።
የውሸት ሳይንስና ዘር
የውሸት ሳይንስም ጥቁሮች ከነጮች ያነሱ ናቸው የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ለመደገፍ የበኩሉን ድምፅ አሰምቷል። ዦዜፍ ደ ጎቢኖ በተባሉት የ19ኛው መቶ ዘመን ፈረንሳዊ ደራሲ የተጻፈው ኤሴይ ኦን ዘ ኢንኢኳሊቲ ኦቭ ሬስስ የተባለ መጽሐፍ ከእርሱ በኋላ ለተጻፉ በርካታ ተመሳሳይ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መሠረት ጥሏል። ጎቢኖ በዚህ መጽሐፋቸው የሰው ዘሮችን ነጭ፣ ቢጫና ጥቁር በማለት በሦስት ክፍሎች ከከፈሉ በኋላ እንደ ቅደም ተከተላቸው እንደሚበላለጡ ገልጸዋል። የእያንዳንዱ ዘር ባሕርያት በደም ስለሚተላለፉ በተለያዩ ዘሮች መካከል በሚደረግ ጋብቻ አማካኝነት መደባለቅ የዘር የበላይነትን ያሳጣል ወይም ያረክሳል ብለዋል።
ጎቢኖ ክርክራቸውን በመቀጠል በአንድ ዘመን ነጭ ቆዳ፣ ረዥም ቁመት፣ ነጣ ያለ ፀጉርና ሰማያዊ ዓይን ያላቸው አርያውያን የሚባሉ ንጹሕ ዘር የነበራቸው ሕዝቦች ነበሩ ይላሉ። የሕንድን ሥልጣኔና ሳንስክሪት የተባለውን የጥንት ቋንቋ ያስተዋወቁት፣ የጥንቶቹን ግሪካውያንና ሮማውያን ሥልጣኔዎች የመሠረቱት፣ አርያውያን ነበሩ በማለት ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ አርያውያን ከእነርሱ ከሚያንሱት የየአገሩ ተወላጆች ጋር ተጋብተው ዘራቸውን በማበላሸታቸው ምክንያት እነዚህ ታላላቅ ሥልጣኔዎች አርያውያን ከነበሯቸው ግሩም ባሕርያትና ጥበብ ጋር አብረው ጠፉ። አሁንም ቢሆን ንጹሕ ለሆነው የአርያውያን ዘር የሚቀርቡት ሕዝቦች የሚገኙት በሰሜን አውሮፓ፣ በተለይም በኖርዲክ እና በጀርመናውያን ሕዝቦች መካከል ነው በማለት ጎቢኖ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ።
የጎቢኖ መሠረታዊ ሐሳቦች፣ ማለትም የሰው ልጅ በሦስት ዘሮች የሚከፈል መሆኑ፣ በደም የሚወረስ ልዩ የዘር ባሕርይ መኖሩና፣ አርያውያን የሚባሉ ዘሮች መኖራቸው ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ማረጋገጫ የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ የዘመናችን ሳይንሳዊ ማኅበረሰብ ፈጽመው ውሸት መሆናቸውን አረጋግጧል። ቢሆንም እነዚህን አስተሳሰቦች ወዲያውኑ የተቀበሉ ሰዎች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል እንግሊዛዊው ሂውስትን ስቲዋርት ቻምበርሌይን ይገኛሉ። እኚህ ሰው በጎቢኖ ሐሳቦች ከመጠን በላይ በመመሰጣቸው ምክንያት መኖሪያቸውን በጀርመን አድርገው የአርያውያንን ንጹሕ ዘር ከጥፋት ጠብቆ ለማቆየት የሚቻለው በጀርመናውያን አማካኝነት ብቻ ነው የሚለውን አስተሳሰብ በሰፊው ማሠራጨት ጀመሩ። የቻምበርሌይን ጽሑፎች በጀርመን አገር በብዛት ተነበዋል። ይህም በጣም አስከፊ ውጤት አስከትሏል።
ዘረኝነት ያስከተለው አስከፊ ውጤት
አዶልፍ ሂትለር ማይን ካምፍ (ትግሌ) በተባለው መጽሐፉ ዓለምን የመግዛት መብት የተሰጠው የአርያውያን ምርጥ ዘር፣ ማለትም የጀርመናውያን ዘር ነው በማለት በእርግጠኝነት ጽፏል። ለዚህ እንቅፋት የሆኑት በጀርመን ኢኮኖሚ ላይ ደባ የሚፈጽሙት አይሁዳውያን ናቸው ብሎ ያምን ነበር። በዚህም ምክንያት አይሁዳውያንንና ሌሎች የአውሮፓ አናሳ ዘሮችን የማጥፋት ዘመቻ ተካሄደ። ይህ ደግሞ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጣም ጥቁር የሆነው ምዕራፍ እንደሆነ ሊክድ የሚችል ሰው የለም። የጎቢኖንና የቻምበርሌይንን ጨምሮ፣ ማንኛውም ዘረኛ አስተሳሰብ፣ ይህን የመሰለ አደገኛ ውጤት ያስከትላል።
ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አስከፊ ነገር የታየው በአውሮፓ ብቻ አይደለም። ከውቅያኖስ ባሻገር ባለው አዲሱ ዓለም ተብሎ ይጠራ በነበረው አህጉርም ይኸው መሠረተ ቢስ አስተሳሰብ በንጹሐን ሰዎች ላይ በቃላት ተነግሮ የማያልቅ መከራ አስከትሏል። በዩናይትድ ስቴትስ ከተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ አፍሪካውያን ባሮች ነጻ የወጡ ቢሆንም በብዙ ክፍለ አገሮች ጥቁሮች ሌሎች ዜጎች ከሚያገኟቸው በርካታ መብቶች ተካፋይ እንዳይሆኑ የሚያግዱ ሕጎች ወጥተዋል። ለምን? ጥቁሮች በሕዝባዊና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ለመካፈል የሚያስችል በቂ የአእምሮ ችሎታ የላቸውም ብለው ነጮቹ ያስቡ ስለነበረ ነው።
እነዚህ የዘረኝነት ስሜቶች ምን ያህል ሥር የሰደዱ መሆናቸውን ለመረዳት አንድ በጥቁሮችና በነጮች መካከል ጋብቻ እንዳይኖር በሚያግደው ሕግ መሠረት የተሰጠ ብይን እንመልከት። አንድ ዳኛ ይህን ሕግ በጣሱ ወንድና ሴት ላይ ባስተላለፉት የፍርድ ውሳኔ እንዲህ ብለዋል:- “ሰዎችን ነጭ፣ ጥቁር፣ ቢጫ፣ ማሌዥያዊና ቀይ አድርጎ የፈጠረውና በተለያዩ አህጉራት እንዲኖሩ ያደረገው ሁሉን ቻይ አምላክ ራሱ ነው። ሰዎች ይህን የአምላክን ዝግጅት ባይጥሱ ኖሮ እንደነዚህ ያሉ ጋብቻዎች የሚኖሩበት ምክንያት አይኖርም ነበር።”
እኚህ ዳኛ ይህን ያሉት በ19ኛው መቶ ዘመን ወይም ከሥልጣኔ በራቀ ኋላ ቀር አካባቢ አይደለም። በ1958 የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ምክር ቤት ከሚገኝበት ሕንፃ ከ100 ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ ከሚገኝ ቦታ ነው! እንዲያውም የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተለያየ ዝርያ ያላቸው ሰዎች እርስ በርስ እንዳይጋቡ የሚከለክሉትን ሕጎች በሙሉ የሻረው በ1967 ነበር።
በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች በርካታ አገሮች ሕዝባዊ ዓመፅ፣ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍና ጠብ የዕለት ተዕለት ጉዳዮች የሆኑት እንደነዚህ ያሉ ፍርደ ገምድል ሕጎችና በትምህርት ቤቶች፣ በአብያተ ክርስቲያናት፣ በሕዝባዊ ድርጅቶች፣ በሥራና በመኖሪያ ቤት ድልድል አድልዎ በመኖሩ ነው። በሕይወትና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ለጊዜው ብንተው እንኳን በዚህ ምክንያት የሚደርሰው ብጥብጥ፣ ጥላቻ፣ መከራና ውርደት ሰለጠንኩ የሚለውን ማኀበረሰብ የሚያሳፍር ነው።
ዘረኝነት የሰውን ልጅ የሚከፋፍል ታላቅ ኃይል ሆኗል። በእርግጥ ሁላችንም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳችንን በመጠየቅ ልባችንን መመርመር ይኖርብናል:- አንዱን ዘር ከሌላው አስበልጦ የሚመለከትን ማንኛውም ትምህርትና አስተሳሰብ እቃወማለሁን? ምንም ዓይነት የዘረኝነት ስሜት እንዳይኖርብኝ እጥራለሁን?
በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኘው የዘር ጥላቻና ግጭት ይጠፋል ብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላልን? የተለያየ ብሔር፣ ቋንቋና ባሕል ያላቸው ሰዎች አንድ ላይ ተስማምተው ሊኖሩ ይችላሉን? ብለን መጠየቃችን ተገቢ ይሆናል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ ነጮች ጥቁሮችን ከሰው ያነሱ ፍጥረታት አድርገው ይመለከቱ ነበር
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሥዕሉ የተወሰደው:- DESPOTISM—A Pictorial History of Tyranny
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዘረኝነት አስተሳሰቦች ካስከተሏቸው አስከፊ ውጤቶች አንዱ የናዚ የእልቂት ካምፕ ነው
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
U.S. National Archives photo