የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g95 10/8 ገጽ 3-4
  • ዘር ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዘር ምንድን ነው?
  • ንቁ!—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሰው ልጆችን በዘር በመከፋፈል ረገድ ያለው ችግር
  • “የሰው ልጅ የፈጠረው እጅግ አደገኛ የሆነ መሠረተ ቢስ እምነት”
  • ሁሉም የሰው ዘሮች በሰላም አንድ ላይ የሚኖሩበት ጊዜ
    ንቁ!—1995
  • የዘር ኩራትን በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል?
    ንቁ!—1998
  • የሰው ዘሮች
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • አምላክ አንድን ዘር ከሌላው አስበልጦ ይመለከታል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1995
g95 10/8 ገጽ 3-4

ዘር ምንድን ነው?

ዘር! ይህን ቃል ስንሰማ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው ምንድን ነው? አንዳንዶች ዘር የሚለውን ቃል ሲሰሙ ወደ አእምሮአቸው የሚመጣው አድልዎና ጭቆና ነው። ሌሎች ደግሞ ጥላቻ፣ ረብሻና ግድያ ይታወሳቸዋል።

የዘር ጉዳይ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚካሄደው የዘር ብጥብጥ አንስቶ በደቡብ አፍሪካ ተንሠራፍቶ እስከቆየው አፓርታይድ፣ በምሥራቅ አውሮፓ በተለያዩ ጎሣዎች መካከል ከሚደረገው ጦርነት አንስቶ እንደ ስሪላንካና ፓኪስታን ባሉት አገሮች እስከሚደረገው የጎሣዎች የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ በሰው ልጆች ላይ ለደረሰው ይህ ነው የማይባል ውድመትና መከራ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ እንዲህ የሆነው ለምንድን ነው? ሰዎች በማንኛውም ሌሎች ጉዳዮች እርስ በርስ ተቻችለው በሚኖሩባቸው አገሮች እንኳን የዘር ጉዳይ ሲነሣ ፀጉራቸው የሚቆመው ለምንድን ነው? የዘር ጉዳይ ታላቅ ብጥብጥና ግፍ የሚያቀጣጥል ደማሚት የሆነው ለምንድን ነው? በአጭሩ፣ የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች እርስ በርሳቸው ተስማምተው ለመኖር የማይችሉት ለምንድን ነው?

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ዘር ምን እንደሆነና የተለያዩ ዘሮች በምን መንገዶች እንደሚለያዩ ማወቅ ብቻ አይበቃንም። በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ዘሮች መካከል ባለው ግንኙነት ረገድ ታሪክ ምን ዓይነት ተጽእኖ እንዳሳደረ መረዳት ያስፈልገናል። በመጀመሪያ ግን ሳይንስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚነግረን እንመልከት።

የሰው ልጆችን በዘር በመከፋፈል ረገድ ያለው ችግር

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎች በቁመናቸውና በአካላዊ ቅርጻቸው ይለያያሉ። የቆዳቸው ቀለም፣ የፊታቸው ገጽታ፣ የፀጉራቸው ዓይነት፣ ወዘተ ይለያያል። እንደነዚህ ያሉት አካላዊ ገጽታዎች አንዱን ዘር ከሌላው ይለያሉ።

በዚህም ምክንያት ሰዎች በአብዛኛው ነጮችና ጥቁሮች እያሉ ሲናገሩ ይሰማል። የቆዳ ቀለም ልዩነት የሚያመለክቱ ቃላት ናቸው። ይሁን እንጂ ሰዎች ሂስፓኒኮች፣ እስያውያን፣ ስካንዲኔቭያውያን፣ አይሁዳውያንና ሩሲያውያን እያሉም ይናገራሉ። እነዚህ አጠራሮች ግን የሚያመለክቱት ከመልክና ከአካላዊ ቁመና ይልቅ ጂኦግራፊያዊ፣ ብሔራዊ ወይም ባሕላዊ ልዩነቶችን ነው። ስለዚህ ለአብዛኞቹ ሰዎች የዘር ልዩነት የሚወሰነው በአካላዊ ገጽታዎች ብቻ ሳይሆን በባሕል፣ በቋንቋ፣ በልማድ፣ በሃይማኖትና በብሔራዊ ማንነት ጭምር ነው።

ይሁን እንጂ ስለዚህ ጉዳይ የሚጽፉ አንዳንድ ደራሲያን እስከናካቴው “ዘር” በሚለው ቃል ለመጠቀም አይፈልጉም። ቃሉን በሚጽፉበት ጊዜ በትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ ፈጽሞ በቃሉ አይጠቀሙም፤ በዚያ ፋንታ “የጎሣ ክፍል፣” “ቡድኖች፣” “ሕዝቦች” እና “ለየት ያሉ” እንደሚሉት ባሉ ቃሎችና ሐረጎች ይጠቀማሉ። እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? “ዘር” የሚለው ቃል በሚሰጠው የተለምዶ ትርጉም መሠረት የሚያስተላልፈው ስሜትና እንድምታ ተገቢ የሆነ ማብራሪያ ካልተሰጠው አብዛኛውን ጊዜ ለማስረዳት የተፈለገው ነጥብ እንዲሰወር ስለሚያደርግ ነው።

ዘር የሚባለው ባዮሎጂስቶችና አንትሮፖሎጂስቶች በሚሰጡት ትርጉም መሠረት “አንዱን የሕዝብ ክፍል ከሌላው የሚለይ አካላዊ ባሕርይ የወረሰ አንድ ንዑስ የሕዝብ ክፍል ነው።” ይሁን እንጂ እዚህ ላይ የሰው ልጆችን በተለያዩ ዘሮች ለመከፋፈል የሚያስችሉት አካላዊ ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው? የሚል ጥያቄ ይነሳል።

የቆዳ ቀለም፣ የፀጉር ቀለምና ዓይነት፣ የዓይንና የአፍንጫ ቅርጽ፣ የጭንቅላት መጠን፣ የደም ዓይነትና እነዚህን የመሳሰሉት ነገሮች መለያ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ሐሳብ ቀርቧል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ የሰው ልጆችን በዓይነት ለመከፋፈል የሚያስችሉ አጥጋቢ መለያዎች ሆነው አልተገኙም። ምክንያቱም ከእነዚህ መለያዎች መካከል አንዱን እንኳን በእኩል መጠን የሚጋሩ አንድ ዓይነት ሰዎች ሊገኙ አልቻሉም።

የቆዳ ቀለምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ብዙ ሰዎች የሰው ልጅ በቆዳ ቀለሙ ነጭ፣ ጥቁር፣ ቡና፣ ቢጫና ቀይ ተብሎ በአምስት ዘሮች ሊከፈል ይችላል ይላሉ። የነጮች ዘር በአብዛኛው ነጭ ቆዳ፣ ነጣ ያለ ፀጉርና ሰማያዊ ዓይን አለው ተብሎ ይታሰባል። ይሁን እንጂ የነጭ ዘሮች በሚባሉት ሕዝቦች መካከል ብዙ ዓይነት የፀጉር፣ የዓይንና የቆዳ ቀለም ልዩነት አለ። ዘ ሂዩማን ስፒሽስ የተባለው መጽሐፍ “በዛሬው ጊዜ በአውሮፓ ውስጥ አንድ ዓይነት ሕዝቦች ያሉበት አገር የለም፤ ኖሮም አያውቅም” ብሏል።

በእርግጥም ዘ ካይንድስ ኦቭ ማንካይንድ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው የሰውን ዘር በዓይነቱ መከፋፈል በጣም አስቸጋሪ ነው። “ልንል የምንችለው የሚከተለውን ብቻ ነው:- ሁሉም የሰው ልጆች እርስ በርሳቸው የማይመሳሰሉ ቢሆኑና ሰዎች በብዙ መንገዶች እርስ በርሳቸው እንደሚለያዩ ልንመለከት ብንችልም ቅሉ የሳይንስ ሊቃውንት ስንት ዓይነት የሰው ዘሮች እንዳሉ ሊስማሙ አልቻሉም። እንዲያውም ሰዎችን በተለያዩ ዘሮች ለመመደብ በምን መስፈርቶች መጠቀም እንደሚቻል ውሳኔ ላይ ሊደርሱ አልቻሉም። አንዳንድ ተመራማሪዎች ችግሩ ምንም ዓይነት መፍትሔ የለውም በማለት የሚያደርጉትን ምርምር እርግፍ አድርገው ሊተውት ይፈልጋሉ!”

ይህ ሁሉ ግራ የሚያጋባ መስሎ ሊታይ ይችላል። የሳይንስ ሊቃውንት እንስሳትንና ዕፀዋትን አለ ብዙ ችግር በተለያዩ ዘሮችና ንዑስ ዘሮች ለመከፋፈል ሲችሉ የሰው ልጆችን ግን በዘሮች ለመከፋፈል ይህን ያህል የተቸገሩት ለምንድን ነው?

“የሰው ልጅ የፈጠረው እጅግ አደገኛ የሆነ መሠረተ ቢስ እምነት”

አንትሮፖሎጂስት አሽሊ ሞንታጉ እንደሚሉት ብዙ ሰዎች “አካላዊና አእምሮአዊ ባሕርያት እርስ በርሳቸው የተዛመዱ እንደሆኑ፣ ከአካላዊ ልዩነቶች ጋር የሚቀናጁ ግልጽ የሆኑ የአእምሮ ችሎታ ልዩነቶች እንዳሉና እነዚህም ልዩነቶች የማሰብ ችሎታን መጠን ለመለካት በሚያስችሉ መስፈርቶችና (አይ ኪው ቴስት) በሕዝቦች ባህላዊ እድገቶች ሊለኩ እንደሚችሉ” ያምናሉ።

ስለዚህ ብዙ ሰዎች እያንዳንዱ ዘር ከሌላው የሚለይበት አካላዊ ገጽታዎች ስላሉት በአእምሮአዊ ችሎታ አንዱ ዘር ከሌላው ይበልጣል ወይም አንደኛው ከሌላው ያንሳል ብለው ያምናሉ። ሞንታጉ ግን ይህን አስተሳሰብ “የሰው ልጅ የፈጠረው እጅግ አደገኛ የሆነ መሠረተ ቢስ እምነት” ብለውታል። ሌሎች ሊቃውንትም በዚህ ይስማማሉ።

ሞርተን ክላስና ሃል ሄልማን ዘ ካይንድስ ኦቭ ማንካይንድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል “ግለሰቦች ይለያያሉ፣ በማንኛውም ሕዝብ ውስጥ በጣም ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ ችሎታ ያላቸውና ደካማ የአእምሮ ችሎታ ያላቸው ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ምርምር ከተደረገ በኋላ ታላላቅ ምሁራን በሕዝቦች መካከል በዘር ልዩነት ሳቢያ የተከሰተ የአእምሮም ሆነ የችሎታ ልዩነት እንዳለ የሚያሳምን ማስረጃ አላገኙም።”

ታዲያ ብዙ ሰዎች አሁንም ቢሆን ውጪያዊ የሆኑ የመልክ ልዩነቶች በተለያዩ ዘሮች መካከል መሠረታዊ የሆነ ልዩነት እንዳለ ያመለክታሉ ብለው የሚያምኑት ለምንድን ነው? የዘር ጉዳይ ይህን ያህል አወዛጋቢ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው? እነዚህን ጉዳዮች በሚቀጥለው ርዕስ እንመረምራለን።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ