የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አስማት መሥራት የሚያስከትለው አደጋ አለን?
‘አካባቢው ለአስማት ማሳያነት ተመቻችቶ ተዘጋጅቷል። በድንገት የአካባቢው ፀጥታ በከበሮ ድምፅ ተናጋ። የሁሉም ሰዎች ዓይን የደንብ ልብስ በለበሱና ጠመንጃ በያዙ ሁለት ሰዎች ላይ አተኮረ። ጠመንጃቸውን አንስተው በትከሻቸው ላይ ከደገኑ በኋላ የሚያብረቀርቅ ልብስ በለበሰ አንድ ቻይናዊ አስማተኛ ላይ አነጣጠሩ። አስማተኛው ሰው በደረቱ ላይ የሸክላ ሳህን ይዟል። ከጠመንጃዎቹ አፈሙዝ ታላቅ ድምፅና እሳት ወጣ። አስማተኛው ወዲያው በቅጽበት ወለሉ ላይ ተዘርሮ በደም ተነከረ። የተተኮሰ ጥይት ለመያዝ የሚቻል ለማስመሰል የተደረገው ሙከራ አሳዛኝ ውጤት አስከተለ።’ በአንደኛው ጠመንጃ ላይ የተገጠመው የመቆጣጠሪያ መሣሪያ ተበላሽቶ ኖሮ ጥይትዋ አምልጣ የአስማተኛውን ደረት በስታ ገባች። ይህን የተረከው ሄንሪ ጎርደንስ ወርልድ ኦቭ ማጂክ የተባለው መጽሐፍ ነው።
ይህ ዓይነቱ አስማት ለሚያስገኘው የልብ መሰቀል፣ ደስታና መዝናኛ ሲባል ብቻ ሕይወትን በመሰለ ታላቅ ስጦታ ላይ የደረሰ ኪሳራ ነው። አንተስ እንዲህ ሆኖ ይሰማሃል? ወይስ እንዲህ ያለውን ትርዒት ከማሳየት ጋር ሊመጣ የሚችል ተራ አደጋ ነው ብለህ ታስባለህ? ምንም ዓይነት ስሜት ቢሰማህ እንዲህ ያለው የማስመሰል ሙከራ በሚከሽፍበት ጊዜ ሕይወት ሊያሳጣ የሚችል ታላቅ አደጋ ያስከትላል። ይህም አስማት ከማድረግ ጋር የተያያዘ ይበልጥ ስውር የሆነ አደጋ ይኖር ይሆን? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። የዚህን መልስ ለማግኘት የዚህን ጥንታዊ ጥበብ አመጣጥ እንመልከት።
አስማት በታሪክ ዘመናት የነበረው ቦታ
ታሪክ መመዝገብ ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ የሰው ልጅ የአስማትን ምሥጢር ለማወቅ ሲጓጓ ኖሯል። የአስማት ድርጊቶች በሰው ልጅ ሕይወት ላይ በተለያየ ሁኔታ ተጽዕኖ አሳድረዋል። “አስማት” ተብሎ የተተረጎመው “ማጂክ” የተባለ የእንግሊዝኛ ቃል “ማጂ” ከሚለው የፋርስ ቃል የመጣ ነው። “ማጂ” በምትሐታዊ ሥራዎቻቸው የታወቁት የጥንታዊት ፋርስ ቀሳውስት የሚጠሩበት ስም ነው። አስማት በመሠረቱ የተፈጥሮ ወይም ከተፈጥሮ በላይ የሆኑትን ኃይሎች ተቆጣጥሮ ወይም አስገድዶ የሰውን ፈቃድ እንዲፈጽሙ ማድረግ ነው። በ18ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በግብጽ አገር አስማተኛ ቀሳውስት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር። በተጨማሪም በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አስማት በከለዳውያን የባቢሎን ሃይማኖት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት ነበር። (ዘፍጥረት 41:8, 24፤ ኢሳይያስ 47:12–14፤ ዳንኤል 2:27፤ 4:7) አስማት ከጥንታውያን ግሪኮችና ሮማውያን ጀምሮ እስከ መካከለኛው ዘመንና አስከ አሁኑ 20ኛ መቶ ዘመን ድረስ የነበረውን ከፍተኛ ቦታ አላጣም።
ልዩ ልዩ የአስማት ዓይነቶችን በተለያየ መንገድ መከፋፈል ይቻላል። ሮበርት ኤ ስቴቢንስ ዘ ማጂሽያን በተባለው መጽሐፋቸው አስማትን በሦስት ዓይነት ክፍሎች መድበዋል።
ሦስት የአስማት ዓይነቶች
መናፍስታዊ አስማት “ም ትሐት የሚገለጥበት አንዱ መንገድ ነው። ከተለመደው ወይም ከሳይንሳዊ እውቀት በሚጻረር መንገድ የሚፈጸሙ ድርጊቶችና ሁኔታዎች እውነተኛና ትክክል” ናቸው ይላል። ስቴቢንስ ማብራሪያቸውን በመቀጠል “መናፍስታዊ አስማት የምትሐት፣ . . . የጥንቆላ፣ የአልኬሚና በአንዳንድ ሁኔታዎች የሃይማኖት ጭምር ደንገጡር ነው” ብለዋል።
የማሳሳቻ አስማት “አስማተኞቹ ተመልካቾቹ የተደረገውን ነገር ወይም እውነታውን እንዳይመለከቱ በማድረግ ድንቅ ነገር እንዳደረጉ ሆነው እንዲታዩ ያደርጋሉ።” ተመልካቹን ሕዝብ እንደሚያታልሉ ያውቃሉ። ይሁን እንጂ ስቴቢንስ እንደሚሉት “ተመልካቾቹ እንደተታለሉ ሆኖ እንዳይሰማቸውና በአስማተኝነታቸው ተራ ሰው የሌለው ዓይነት ኃይል እንዳላቸው ወይም ከሰው የበለጠ ኃይል ካላቸው አካላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው እንዲያምኑ ያበረታታሉ።”
የመዝናኛ አስማት ግራ የሚያጋቡ የማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀም ተመልካቾች እንዲደነቁ ለማድረግ ይሞክራል። ይህ ዓይነቱ አስማት በአምስት መሠረታዊና አንዳንድ ጊዜ አንዳቸውን ከሌላው ለመለየት በሚያስቸግሩ ዘዴዎች ይከፈላል:- “የመድረክ አስማት፣ በቅርብ የሚታይ አስማት፣ በእጅ ቅልጥፍና የሚሠራ አስማት፣ በማደናገር የሚሠራ አስማትና አእምሮን በመቆጣጠር የሚሠራ አስማት ናቸው።
በአንድ ክርስቲያን ላይ የሚያስከትለው አደጋ ይኖራልን?
በመጀመሪያ ስለ መናፍስታዊ አስማት እንመልከት። መናፍስታዊ አስማት የሚሠራው በተለያዩ መንገዶች ነው። ለምሳሌ ያህል ሰይጣናውያን “ጥቁር” እና “ነጭ” በሚባል አስማት ይጠቀማሉ። “ጥቁር” አስማት የሚባለው በድግምት፣ ልዩ በሆነ እርግማንና ጠላቶች በቡዳ እንዲበሉ በማድረግ የሚሠራ አስማት ነው። “ነጭ” አስማት ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ሲሆን ድግምቶችንና አስማቶችን በማክሸፍ ጥሩ ውጤቶች ለማምጣት የሚደረግ አስማት ነው። ይሁን እንጂ ሁለቱም ቢሆኑ የመናፍስታዊ ወይም የምትሐታዊ ድርጊቶች መግለጫዎች ናቸው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ጥሩ አዝመራ ለማግኘት ወይም በስፖርት ውድድሮች ላይ የአሸናፊነት ውጤት ለማግኘት የምትሐታዊ አስማት እርዳታ ይፈለጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ስላለው መናፍስታዊ አስማት ግልጽ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። “አስማትም አታድርጉ፣ ሞራ ገላጭም አትሁኑ።”—ዘሌዋውያን 19:26፤ ዘዳግም 18:9–14፤ ሥራ 19:18, 19
የማሳሳቻ አስማት አደገኛ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? የእጅ አሻራ አንባቢዎች፣ ጠንቋዮች፣ ተአምራዊ ፈዋሾችና እነዚህን የመሰሉ ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማራመድ ሲሉ በማሳሳቻ አስማት ይጠቀማሉ። በሚሠሩት ሥራ የውሸት ኑሮ መኖራቸው አይደለምን? የአምላክ ቃል “አትካዱም፣ ከእናንተም እርስ በርሳችሁ ሐሰት አትነጋገሩ” ይላል።—ዘሌዋውያን 19:11
ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና “በአንዳንድ ሁኔታዎች አስማታዊ ድርጊቶች መናፍስት ለመሳብ ሊያገለግሉ ይችላሉ” ይላል። ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ እንኳን እንዲህ ባለው ክልል ውስጥ ስንገባ አጋንንታዊ መናፍስት ችግር እንዲያመጡብን መጋበዛችን አይደለምን? አጋንንት አጋጣሚውን ካገኙ እኛን መጠቀሚያ ሊያደርጉ ይችላሉ፣ ያደርጋሉም። ሁልጊዜ ‘የሚያመቻቸውን ጊዜ’ ይጠብቃሉ። ጥረታቸውንም ለአንድ አፍታ እንኳን አያቆሙም።—ሉቃስ 4:13፤ ያዕቆብ 1:14
ዋነኛው የማታለያና የማደናገሪያ ጥበብ ምንጭ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። በኤደን የአትክልት ቦታ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ካሳመፀበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ የማታለል ጥበቡ ከመጠቀም ወደ ኋላ ያለበት ጊዜ የለም። (ዘፍጥረት 3:1–19) እንደ ሰይጣን ለመሆን የሚፈልግ ክርስቲያን ሊኖር ይችላልን? ከዚህ ይልቅ ክርስቲያኖች ‘እግዚአብሔርን የሚመስሉ እንዲሆኑ”፣ ‘ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያስገዙና ዲያብሎስን ግን እንዲቃወሙ’ ተመክረዋል።—ኤፌሶን 5:1፤ ያዕቆብ 4:7
ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሰዎች “አስማት” የሚለውን ቃል የሚያዛምዱት ከመዝናኛ ጋር ነው። አንድ ሰው አብዛኛውን ጊዜ የእጅ እንቅስቃሴ ከዓይን እንደሚፈጥን በመገንዘብ በቀልጣፋ እጆቹ ሰዎችን ለማደናገር ይችል ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ላይከለክል ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ምሥጢራዊ አስማት እንደሚሠራ በማስመሰል ከሰው በላይ የሆነ ወይም ምንነቱ የማይታወቅ ኃይል እንዳለው ሆኖ መታየት ይኖርበታልን? ሌሎች ሰዎችስ “አስማቱን” በመመልከት የተሳሳተ ግንዛቤ የሚያድርባቸው ከሆነ ክርስቲያኑ ሌሎችን ላለማደናቀፍ ሲል እንዲህ ያለውን መዝናኛ መተው አይኖርበትምን? (1 ቆሮንቶስ 10:29, 31–33) በተጨማሪም ይበልጥ ጥልቅ ወደሆኑት የጥንቆላ ጥበቦች ለመግባት የመፈተን አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል።
ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከመናፍስት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው አስማቶች ጋር ምንም ዓይነት ተካፋይነት እንዲኖራቸው አይፈልጉም። ከዚህም በላይ አንድ ክርስቲያን በማንኛውም የሕይወቱ ክፍል በሥራውም ሆነ በመዝናኛው ጭምር በአምላክም ሆነ በሰው ላይ ምንም ዓይነት በደል እንዳልፈጸመ የሚሰማው “በጎ ሕሊና” እንዲኖረው ይፈልጋል።—1 ጴጥሮስ 3:16፤ ሥራ 24:16
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ምንጭ]
The Bettmann Archive