ስለ ጥንቆላ ማወቅ ያለብህ ነገር
ዘመናዊ ጥንቆላ እንዲህ ነው ብሎ ለመግለጽ ያስቸግራል። ይህ የሆነበት ምክንያት የተለያዩ ሰዎች በተለያየ መንገድ ስለሚያካሂዱት ነው። ሁሉም የሚመሩበት አንድ መመሪያ ወይም ሃይማኖታዊ ሕግ ወይም ቅዱስ መጽሐፍ የላቸውም። በተጨማሪም በባሕል፣ በአወቃቀር፣ በአምልኮ ሥርዓትና የትኞቹ አማልክት መከበር እንዳለባቸው ባላቸው አመለካከት ረገድ ይለያያሉ። አንዲት ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል:- “ምሥጢራዊው ዓለም ለግለሰቡ የግል አመለካከቶች የሚስተናገዱበት ‘ነፃ ገበያ’ ያቀርባል።” ሌላዋ ጸሐፊ ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “አብዛኞቹ ዘመናዊ አረማውያን በሁሉም ነገር ማለት ይቻላል ይቃረናሉ።”
ለብዙዎች ቅራኔዎቹ ችግር አይፈጥሩባቸውም። ጠንቋይ መሆን ለሚፈልጉ የተዘጋጀ አንድ መመሪያ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “እርስ በርሱ የሚቃረን የሚመስል መረጃ ሲደቀንብህ ይህን መረጃ መርምርና የትኛውን እንደምትከተል ወስን። ቀልብህ የሚነግርህን አዳምጥ። በሌላ አባባል በጽሑፍ ከወጡት የአምልኮ ሥርዓቶችና የአምልኮ ሥርዓት መጻሕፍት መካከል ትክክል መስሎ የሚሰማህን አንዱን ለመምረጥ ነፃነት ይሰማህ።”
የእውነትን ባሕርይ ለሚገነዘቡ ሰዎች እነዚህ ቅራኔዎች ችግር ይፈጥሩባቸዋል። እውነት ተጨባጭ የሆነ ሐቅ ነው። አንድ ሰው አንዳንድ ነገሮች እውነት እንደሆኑ ስለተሰማው ወይም ስለተመኘ ወይም ስላመነ ብቻ እውነት ሊሆኑ አይችሉም። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት ሐኪሞች አንድ በሕይወት ያለን ዶሮ ሁለት ቦታ ቆርጠው ቁራጮቹን የበሽተኛው ደረት ላይ በማስቀመጥ የሳንባ ምች በሽታን ማዳን እንደሚችሉ ያምኑ ነበር። ብዙ በሽተኞች ይህ የሕክምና ዘዴ ፈውስ እንደሚያስገኝላቸው በቅንነት እንዳመኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም እምነታቸውና ተስፋቸው በሐቅ ላይ የተመሠረተ አልነበረም። እንዲህ ዓይነት የሕክምና ዘዴ የሳንባ ምች ሊያድን አይችልም። ሰዎች እውነትን ለመረዳት ይጥራሉ እንጂ እውነትን መፍጠር አይችሉም።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች የሚያስረዳ እውነት እንደያዘ ይናገራል። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት “ቃልህ እውነት ነው” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:17) ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱስ መጽሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16፣ የ1980 ትርጉም ) የጥንቆላ ተግባር የሚፈጽሙ ብዙ ሰዎች በዚህ አይስማሙም። ከዚህ ይልቅ መንፈስ እንዲሞላባቸውና አመራር እንዲያገኙ አፈ ታሪኮችን፣ ጥንታዊ የሆኑ ሃይማኖቶችንና አልፎ ተርፎም ሳይንሳዊ ልብ ወለዶችን ይመለከታሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ቢያንስ መመርመሩ ምክንያታዊ አይደለምን? ደግሞም በዓለም አቀፍ ደረጃ ማለት ይቻላል እንደ ቅዱስ መጽሐፍ ይታያል። በተጨማሪም እስካሁን ድረስ ተጠብቀው ከቆዩት ሃይማኖታዊ ጽሑፎች መካከል ረጅም እድሜ ያለው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ 1, 600 ዓመታት በፈጀ ጊዜ ውስጥ የተጻፈ ቢሆንም በውስጡ የያዘው ትምህርት ከዳር እስከ ዳር እርስ በርስ ይደጋገፋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸውን ነገሮች በአሁኑ ጊዜ ጠንቋዮች ከሚያስፋፏቸው አንዳንድ የተለመዱ እምነቶች ጋር እስቲ እናወዳድር።
በመንፈሳዊው ዓለም የሚኖረው ማን ነው?
መንፈሳዊ ማስተዋል ለማግኘት በምናደርገው ፍለጋ፣ በመንፈሳዊው ዓለም የሚኖረው ማን ነው? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ይነሳል። ምንም እንኳ አብዛኞቹ ዘመናዊ ጠንቋዮች በዋነኛነት ለተፈጥሮ ትኩረት የሚሰጥ ብዙ አማልክትን ያቀፈ እምነት ተከታዮች ቢሆኑም አንዳንዶች መሠረታዊ የሆኑትን የሕይወት ደረጃዎች ማለትም የልጃገረድነት፣ የእናትነትና የአሮጊትነት ሦስት ሚና እንዳላት ተደርጋ የምትቆጠር አንዲት ታላቅ እናት አምላክ ያመልካሉ። ባለ ቀንድ አምላክ የሆነ ፍቅረኛ አላት። ሌሎች ጠንቋዮች ደግሞ ጣምራ የሆኑ ወንድና ሴት አማልክት ያመልካሉ። አንድ ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ሴትና ወንድ አማልክቱ አንስታይ እና ተባዕታይ የሆኑ የተፈጥሮ ኃይሎች መግለጫ ተደርገው ይታያሉ። እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የሆኑ ባሕርያት ያሏቸው ሲሆን በሚዋሃዱበት ጊዜ ስምምነት ያለው ሕይወት ያስገኛሉ።” ሌላ ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “በጥንቆላ ሥራ ላይ ካሉህ እጅግ ወሳኝ ምርጫዎች አንዱ የምትገናኛቸውን አማልክት (ወንድ/ሴት አማልክት) መምረጥ መቻልህ ነው። . . . የምትጠቀምበት ጥበብ መለኮታዊ አድርገህ የምትመለከታቸውን የግልህ የሆኑ መግለጫዎች የመምረጥና ከዚያም የማምለክ ነፃነት ይሰጥሃል።”
መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ አመለካከቶች ውስጥ የትኛውንም አይደግፍም። የኢየሱስ ክርስቶስ መላ አገልግሎት ያተኮረው ‘ብቸኛ እውነተኛ አምላክ’ ስለሆነው ስለ ይሖዋ በማስተማር ላይ ነበር። (ዮሐንስ 17:3) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ታላቅ፣ ምስጋናውም ብዙ ነውና፤ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነው። የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው።”—1 ዜና መዋዕል 16:25, 26
ስለ ዲያብሎስስ ምን ማለት ይቻላል? ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጂየት ዲክሽነሪ ጥንቆላ ተብሎ የተተረጎመውን ዊችክራፍት የሚለውን ቃል “ከዲያብሎስ ጋር የሚደረግ የሐሳብ ግንኙነት” ሲል ይፈታዋል። በዛሬው ጊዜ ይህን ፍቺ የሚቀበል ጠንቋይ ማግኘት በጣም አዳጋች ነው። ምክንያቱም አብዛኞቹ ሰይጣን ዲያብሎስ ሕልውና እንዳለው እንኳ አይቀበሉም። ዚ አይሪሽ ታይምስ “ከፍተኛ ቦታ ያላት ጠንቋይና አየርላንድ ውስጥ ካሉት የጠንቋዮች ማኅበራት እጅግ እውቅ የሆነው ማኅበር መሪ” እንደሆነች የገለጻት አንዲት ወጣት ሴት እንዲህ በማለት መከራከሪያ አቅርባለች:- “የዲያብሎስን ሕልውና ማመን ማለት ክርስትናን መቀበል ይሆናል . . . አምላክ በሌለበት ዓለም ውስጥ [ዲያብሎስ] ሊኖር አይችልም።”
መጽሐፍ ቅዱስ የዲያብሎስን ሕልውና የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ በምድር ላይ ላለው ለአብዛኛው መከራና ሁከት ተጠያቂ ያደርገዋል። (ራእይ 12:12) ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ ሕልውና እንዳለው ማስተማር ብቻ ሳይሆን ሳያውቁት የዲያብሎስን ፈቃድ ማድረግም እንዳለ ገልጿል። ለምሳሌ ያህል በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ራሳቸውን እንደ ጻድቃን የሚቆጥሩ ሃይማኖታዊ መሪዎች በተወሰነ መጠን የአምላክ ልጆች እንደሆኑና የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ እንዳሉ እንደሚያምኑ በእርግጠኝነት ተናግረዋል። በልባቸው ያለውን ነገር ማስተዋል የሚችለው ኢየሱስ ሁኔታቸው ከዚህ የተለየ መሆኑን አውቋል። እንዲህ ሲል በግልጽ ነግሯቸዋል:- “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ።” (ዮሐንስ 8:44) በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው ራእይ፣ ዲያብሎስ ‘ዓለሙንም ሁሉ እያሳተ መሆኑን’ ይናገራል።—ራእይ 12:9
ምንም ክፋት የሌለባቸው አንዳንድ የአስማት ድርጊቶች አሉን?
እርግጥ ነው፣ አስማት ምንጊዜም ከምትሃታዊ ኃይል ጋር ሲዛመድ ቆይቷል።a ጥንትም ሆነ ዛሬ ብዙ ሰዎች ጠንቋዮች የሚሠሩት አስማት በሌሎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚደረግ እንደሆነ ያምናሉ። ጠንቋዮች በመተት አማካኝነት ሰዎችን የማሰቃየት አልፎ ተርፎም የመግደል ኃይል እንዳላቸው ይታመናል። በተለምዶ ጠንቋዮች በሽታ፣ ሞትና የሰብል ውድመትን ጨምሮ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው መጥፎ አጋጣሚዎች ተጠያቂ ይሆኑ ነበር።
በዛሬው ጊዜ ጠንቋዮች እነዚህን ክሶች አይቀበሉም። ምንም እንኳ አልፎ አልፎ መጥፎ ዓላማ ያለው መሰሪ ጠንቋይ እንደማይታጣ ቢቀበሉም አብዛኞቹ የሚሠሩት አስማት ጥቅም ለማስገኘት እንጂ ለጉዳት እንዳልሆነ ይናገራሉ። ዊካ የሚባለው የጥንቆላ እምነት ተከታዮች የአስማት ድርጊቱ ውጤት በአስማተኛው ላይ ሦስት እጥፍ ሆኖ እንደሚደርስ ያስተምራሉ። ሰዎችን ከመርገም የሚቆጠቡበት ዋነኛው ምክንያትም ይህ እንደሆነ ይናገራሉ። በጎ ነገር ያስገኛል ለሚባልለት ለዚህ የአስማት ድርጊት በምሳሌነት ከሚጠቀሱት ነገሮች መካከል ራስህን ለመጠበቅ፣ ከአንተ በፊት ይኖርበት የነበረው ሰው ትቶት ከሄደው ክፉ መንፈስ ቤትህን ለማንጻት፣ አንድ ሰው እንዲያፈቅርህ ለማድረግ፣ ፈውስና ጤና ለማግኘት፣ ከሥራህ እንዳትፈናቀል ለመከላከልና ገንዘብ እንድታገኝ ለማድረግ የሚደገሙ ድግምቶች ይገኙበታል። ጥንቆላ የማይገባበት ጉዳይ እንደሌለ ስለሚነገር በጣም ተወዳጅ መሆኑ ምንም አያስገርምም።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ጎጂና ጠቃሚ ጥንቆላ ብሎ አይለይም። አምላክ ለሙሴ በሰጠው ሕግ ላይ አቋሙን ግልጽ አድርጓል። “አስማትም አታድርጉ” ብሏቸዋል። (ዘሌዋውያን 19:26) ከዚህ በተጨማሪ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ሞራ ገላጭም፣ አስማተኛም፣ መተተኛም፣ በድግምት የሚጠነቁልም፣ መናፍስትንም የሚጠራ . . . በአንተ ዘንድ አይገኝ።”—ዘዳግም 18:10, 11
አምላክ እንዲህ ያለበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚጠቅመንን ነገር የመንፈግ ዓላማ ስላለው አይደለም። ይሖዋ ለሕዝቡ እነዚህን ሕጎች የሰጠው ይወዳቸው ስለነበረና የፍርሃትና የአጉል እምነት ባሪያ እንዳይሆኑ ስለፈለገ ነው። ከዚህ ይልቅ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች እንዲጠይቁት ያበረታታቸዋል። “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት” የሚገኘው ከእሱ ነው። (ያዕቆብ 1:17) ሐዋርያው ዮሐንስ ለመሰል አማኞች እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል:- “ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለ ሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከ[አምላክ] እናገኛለን።”—1 ዮሐንስ 3:22
ስለ ክፉ መናፍስትስ ምን ማለት ይቻላል?
ብዙ ጠንቋዮች ክፉ መናፍስት መኖራቸውን ስለሚያምኑ በዚህ ረገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይስማማሉ። አንድ የጥንቆላ አራማጅ በአንድ ጽሑፍ ላይ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “በሕያዋን ፍጥረታት ከተሞላው ዓለማችን ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ እነሱም በዓይን በማይታየው ዓለም ውስጥ ይኖራሉ። . . . ‘ክፉ መንፈስ’ እና ‘ጋኔን’ የሚሉት ቃላት ጉዳዩን በትክክል ይገልጻሉ። በጣም ጠንካሮች ናቸው። . . . ከፍተኛ ማስተዋል አላቸው . . . (አንድ ሰው በሩን በመክፈት ከተባበራቸው) እኛ ወዳለንበት ዓለም መግባት ይችላሉ። ሰውነታችሁ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ . . . እንዲያውም በተወሰነ መጠን እናንተን የመቆጣጠር ሥልጣን ይኖራቸዋል። አዎን፣ ይህ በአጋንንት ስለ መያዝ ከሚነገሩ የቆዩ ታሪኮች በምንም አይለይም።”
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በአጋንንት የተያዙ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ስቃይ ይደርስባቸው ነበር። በአጋንንት የተጠቁ አንዳንድ ሰዎች ልሳናቸው ይዘጋ፣ አንዳንዶች ዓይነ ስውር ይሆኑ፣ ሌሎች እንደ እብድ ያደርጋቸው የነበረ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ከሰው የተለየ ኃይል ነበራቸው። (ማቴዎስ 9:32፤ 12:22፤ 17:15, 18፤ ማርቆስ 5:2-5፤ ሉቃስ 8:29፤ 9:42፤ 11:14፤ ሥራ 19:16) አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ላይ ብዙ አጋንንት አብረው ሲሰፍሩበት ስቃዩ ይባባስ ነበር። (ሉቃስ 8:2, 30) ይሖዋ ሰዎች ከጥንቆላና ከሌሎች ምትሃታዊ ተግባሮች እንዲርቁ ያስጠነቀቀው አለምክንያት እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው።
በእውነት ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት
ዛሬ ብዙዎች ወደ ጥንቆላ የሚሳቡት ጉዳት የሌለው፣ ደግነት የሚታይበትና በተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት ስለሚመስላቸው ነው። በአንዳንድ ኅብረተሰቦች ውስጥ ጥንቆላ ተቀባይነት ከማግኘቱ የተነሳ ሰዎች ፍርሃት አይሰማቸውም። እንዲያውም በአብዛኛው እንደ ተራ ነገር ይታያል። በሃይማኖት ተቻችሎ የመኖር መንፈስ በሰፈነበት አካባቢ የሚኖሩ ብዙዎቹ ሰዎች እንደ ጥንቆላ የመሳሰለውን ግራ የሆነ እምነት እንኳ እስከመቀበል አድርሷቸዋል።
በእርግጥም የሃይማኖቱ ዓለም አንድ ሰው የሚስማማውን ጫማ መርጦ እንደሚገዛ ሁሉ ሰዎች ፍላጎታቸውን የሚያሟላላቸውን ሃይማኖት እንዳሰኛቸው የሚመርጡበት የገበያ ማዕከል ሆኗል። ከዚህ በተቃራኒው ግን ኢየሱስ ያሉት ሁለት ምርጫዎች ብቻ መሆናቸውን ተናግሯል። እንዲህ ብሏል:- “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” (ማቴዎስ 7:13, 14) በየትኛው ጎዳና እንደምንሄድ የመምረጥ ነፃነት እንዳለን ግልጽ ነው። ሆኖም ዘላለማዊ ደኅንነታችንን የሚመለከት ስለሆነ የምናደርገው ምርጫ በጣም ወሳኝነት አለው። መንፈሳዊ ማስተዋል ለማግኘት በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ የሚገኘውን የእውነት መንገድ መከተል አለብን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በእንግሊዝኛ አንዳንዶች ድብቅ የሆነውን፣ መድረክ ላይ ከሚቀርበው አስማት ለይቶ ለማመልከት “magick” የሚለውን አጻጻፍ ይጠቀማሉ። ንቁ! ሐምሌ-መስከረም 1994 በገጽ 28 ላይ የወጣውን “አስማት መሥራት የሚያስከትለው አደጋ አለን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዛሬ ብዙዎች ጥንቆላን ጉዳት የሌለው በተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት አድርገው ይመለከቱታል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አስማት ምንጊዜም ምትሃታዊ ከሆነ ነገር ጋር ሲያያዝ ቆይቷል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጥንቆላ ተግባር የተሠማሩ ሰዎች ሳያውቁት የዲያብሎስን ፈቃድ እያደረጉ ይሆን?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ የእውነትን መንገድ ያሳያል