ስለ ጥንቆላ የምታውቀው ነገር አለ?
ጥንቆላ! ይህን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው?
ለብዙዎች ጥንቆላ በቁም ነገር መታየት የሌለበት አጉል እምነትና ቅዠት ብቻ ነው። ለእነዚህ ሰዎች፣ ጠንቋይ ሲባል የሚታያቸው ተጥዶ በሚፍለቀለቅ ድስት ውስጥ የሌሊት ወፍ ክንፎችን የሚጨምሩ፣ ሰዎችን ወደ እንቁራሪትነት ይለውጣሉ የሚባሉ በመጥረጊያ እንጨት ላይ ሆነው እያሽካኩ የሌሊቱን ሰማይ የሚያስሱ ካባ የለበሱ ያረጁ ጠንቋዮች ስለሆነ ጥንቆላ በምናባዊው ዓለም ብቻ ያለ ነገር እንደሆነ ያስባሉ።
ለሌሎች ደግሞ ጥንቆላ እንዲያው የሚፌዝበት ነገር አይደለም። አንዳንድ ተመራማሪዎች ከዓለም ሕዝብ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ጠንቋዮች በእርግጥ እንዳሉና በሌሎች ሕይወት ላይ ተጽእኖ ማሳደር እንደሚችሉ እምነት እንዳለው ተናግረዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጥንቆላ መጥፎና አደገኛ እንዲሁም በጣም ሊፈራ የሚገባው ነገር እንደሆነ ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል ስለ አፍሪካ ሃይማኖት የሚናገር አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ሌሎችን ለማጥቃት የሚደረግ አስማት፣ ሟርትና ጥንቆላ ኃይልና አደጋ አለው የሚለው እምነት በአፍሪካውያን ሕይወት ውስጥ እጅግ ሥር የሰደደ ነው . . . ጠንቋዮችና ሟርተኞች በሚኖሩበት ኅብረተሰብ ውስጥ በጣም የተጠሉ ናቸው። በዛሬው ጊዜም እንኳ ተወግረው የሚገደሉባቸው ቦታዎችና አጋጣሚዎች አሉ።”
በምዕራቡ ዓለም ግን ጥንቆላ መልካም የሚያስመስለውን አዲስ ገጽታ እየተላበሰ ነው። መጻሕፍት፣ ቴሌቪዥንና ፊልሞች ሰዎች ለጥንቆላ ያላቸውን ፍራቻ በማርገብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በመዝናኛ ስም የሚዘጋጁትን ነገሮች የሚገመግሙት ዴቪድ ዴቪስ እንዲህ ብለዋል:- “ጠንቋዮች ድንገት በአንድ ጀምበር ልጅ እግርና የደስ ደስ ያላቸው እንደሆኑ ተደርገው መታየት ጀምረዋል። ሆሊዉድ አዳዲስ አዝማሚያዎችን በማስተዋል ረገድ ፈጣን ነው። . . . ጠንቋዮችን የደስ ደስ ያላቸውና ይበልጥ ማራኪ አድርጎ በማቅረብ ሴቶችንና ትንንሽ ልጆችን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካች መማረክ ችሏል።” ሆሊዉድ ማንኛውንም የሰዎች ዝንባሌ በምን መልኩ ገንዘብ ማስገኛ ምንጭ አድርጎ እንደሚለውጠው ያውቅበታል።
አንዳንዶች ጥንቆላ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ካሉት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ። በበለጸጉ አገሮች ባጠቃላይ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሰዎች የሴቶች ንቅናቄ ባሳደረባቸው ግፊት እንዲሁም ነባር በሆኑ ሃይማኖቶች ቅር በመሰኘታቸው በተለያዩ የጥንቆላ ዓይነቶች መንፈሳዊ እርካታ ለማግኘት ይጥራሉ። እንዲያውም በርካታ የጥንቆላ ዓይነቶች ከመኖራቸው የተነሳ ሰዎች “ጠንቋይ” ለሚለው ቃል በሚሰጠው ትርጉም እንኳ አይስማሙም። ይሁን እንጂ ጠንቋይ እንደሆኑ የሚቆጠሩ ሰዎች በአብዛኛው ዊካ በሚል መጠሪያ የሚታወቁ ሲሆን በአንድ መዝገበ ቃላት መሠረት ይህ ቃል “አመጣጡ ከቅድመ ክርስትና ምዕራባዊ አውሮፓ ሆኖ አረማዊ ባሕርይ የተላበሰና በ20ኛው መቶ ዘመን በማንሰራራት ላይ የሚገኝ ሃይማኖት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል።a ከዚህ የተነሳ ብዙዎች አረማውያን ወይም ዘመናዊ አረማውያን እንደሆኑም ይናገራሉ።
በታሪክ ዘመናት በሙሉ ጠንቋዮች ይጠሉ፣ ይሰደዱና ይደበደቡ አልፎ ተርፎም ይገደሉ ነበር። ዘመናዊ ጠንቋዮች መልካቸውን ቀይረው ለመቅረብ መጣራቸው ምንም አያስገርምም። በአንድ ጥናት ላይ በደርዘን የሚቆጠሩ ጠንቋዮች በአንደኛ ደረጃ ለኅብረተሰቡ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት ምን እንደሆነ ተጠይቀው ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት የሚያካሂዱት ማርጎ ኤድለር ጠንቋዮቹ የሰጡትን መልስ ጠቅለል አድርገው ሲያቀርቡ እንዲህ ብለዋል:- “እኛ ለክፋት የቆምን አይደለንም። ዲያብሎስን አናመልክም። ሰዎችን አንጎዳም ወይም አናታልልም። አደገኞች አይደለንም። እንደ እናንተው ሰዎች ነን። ቤተሰብና ሥራ አለን እንዲሁም ተስፋ የምናደርጋቸውም ሆነ የምንመኛቸው ነገሮች አሉ። መናፍቃን አይደለንም። ልዩ ፍጡር አይደለንም። . . . ልትፈሩን አይገባም። . . . እንዲያው ከምትገምቱት በላይ እኛ ልክ እንደ እናንተ ነን።”
ይህ መልእክት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። ታዲያ ይህ ማለት የጥንቆላ ሥራን በተመለከተ ምንም የሚያሳስበን ጉዳይ የለም ማለት ነው? እስቲ ቀጥሎ በቀረበው ርዕስ ላይ ይህን ጥያቄ እንመርምር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ዊችክራፍት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ሴትና ወንድ ጠንቋዮችን ለማመልከት ከሚሠራበት “ዊሲ” እና “ዊካ” ከሚሉት የድሮ እንግሊዝኛ ቃላት የተወረሰ ነው።