ባልና ሚስት ሐሳባቸውን በመግለጥ ረገድ ልዩነት አላቸውን?
ጌታቸው ወደ አበበ ቢሮ ዘው ብሎ ገባ። አንገቱን ስላቀረቀረ የተጨነቀበት ነገር እንዳለ በግልጽ መመልከት ይቻላል። አበበ ወዳጁን በአክብሮት ከተመለከተ በኋላ የሚናገረውን ለመስማት ተዘጋጀ። “ይህን የገባሁትን የሥራ ውል በተሳካ ሁኔታ የምጨርስ አይመስለኝም” በማለት ጌታቸው በረጅሙ ተነፈሰ። “ብዙ ያልጠበቅኳቸው ችግሮች አጋጥመውኛል፣ ዋናው መሥሪያ ቤት ደግሞ በጣም እያጣደፈኝ ነው።” “ለምንድን ነው የምትጨነቀው ጌታቸው?” በማለት አበበ በተረጋጋ መንፈስ ይጠይቀዋል። “ለዚህ ሥራ ከአንተ የተሻለ ሰው እንደማይገኝ ታውቃለህ። እነርሱም ቢሆኑ ይህን ያውቃሉ። እስቲ በቂ ጊዜ ስጠው። የሚሻል አይመስልህም? እኔም እኮ ባለፈው ወር . . .” በማለት የሠራውን ስህተት ይነግረውና አብረው ይስቃሉ። ጌታቸው ጭንቀቱ ቀልሎት ከቢሮው እየሳቀ ይወጣል። አበበም ጓደኛውን ለመርዳት በመቻሉ ደስ ይለዋል።
አሁን ደግሞ አበበ በዚያው ምሽት ቤቱ እንደገባ ሚስቱ አልማዝ አንድ የተበሳጨችበት ነገር እንዳለ በቀላሉ ተመለከተ። ከወትሮው በተለየ ሞቅ ያለ ስሜት ሰላምታ ከሰጣት በኋላ ያስጨነቃት ነገር ምን እንደሆነ እንድትነግረው መጠበቅ ጀመረ። በዝምታ ተውጠው ከቆዩ በኋላ አልማዝ “አሁንስ ፈጽሞ መቋቋም አልቻልኩም! ይህ አዲስ አለቃ በጣም ጨቋኝ ነው” ትለዋለች። አበበ ቁጭ እንድትል ካደረገ በኋላ እጁን ትከሻዋ ላይ አድርጎ “አትበሳጪ የኔ ቆንጆ። ይህ በሥራ ዓለም ያለ ነገር ነው። አለቆች ሲባሉ እንዲህ ናቸው። የእኔም አለቃ ዛሬ እንዴት እንደጮኸብኝ ልነግርሽ አልችልም። ቢሆንም ይህን ያህል የሚያበሳጭሽ ከሆነ ሥራውን ልትተይ ትችያለሽ” ይላታል።
አልማዝ “ስለ እኔ ስሜት ፈጽሞ ግድየለህም!” ስትል በቁጣ ትመልስለታለች። “ፈጽሞ አታዳምጠኝም! ሥራውን ልተው አልችልም! አንተ የምታመጣው ገንዘብ አይበቃንም!” ወደ መኝታ ቤት ሮጣ ከገባች በኋላ በሩን ዘግታ ስቅስቅ ብላ ማልቀስ ትጀምራለች። አበበ ደንግጦ ምን እንደሆነች በመገረም ከውጭ ቆሞ ይጠብቃል። አበበ ሊያጽናናት ብሎ የተናገረው ቃል ይህን የመሰለ ያልተጠበቀ ውጤት ያስከተለው ለምን ይሆን?
በወንድና በሴት መካከል የባሕርይ ልዩነት ስላለ ነውን?
በእነዚህ ምሳሌዎች ልዩነት የተፈጠረው ጌታቸው ወንድ፣ አልማዝ ሴት ስለሆነች ነው የሚል ቀላል መልስ የሚሰጡ ሰዎች ይኖራሉ። የሥነ ልሳን ተመራማሪዎች በጋብቻ ውስጥ ሐሳብ ለሐሳብ የመግባባት ችግር የሚፈጠረው በጾታ ልዩነት ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ። እንደ ዩ ጀስት ዶንት አንደርስታንድ (ፈጽሞ አይገባህም) እና ሜን አር ፍሮም ማርስ፣ ውመን አር ፍሮም ቬነስ (ወንዶች ከማርስ፣ ሴቶች ደግሞ ከቬነስ የመጡ ናቸው) ያሉት መጻሕፍት ወንዶችና ሴቶች አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ ቢሆኑም በግልጽ ሊታይ የሚችል የአነጋገር ስልት ልዩነት አላቸው የሚለውን አስተሳሰብ ያራምዳሉ።
ይሖዋ ሴትን ከወንድ በፈጠረ ጊዜ በጥቂቱ ብቻ ከወንድ ለየት ያለች እንድትሆን አድርጎ እንዳልፈጠራት የታወቀ ነው። ወንድና ሴት አንዱ የሌላውን አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች እንዲያሟሉ በጥሩ ማስተዋል ውብ ሆነው የተፈጠሩ ናቸው። በእነዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑ የባሕርይ ልዩነቶች ላይ የአስተዳደግና የሕይወት ተሞክሮ ልዩነቶች፣ ባሕል፣ የአካባቢ ሁኔታና ማኅበረሰቡ ለወንድነትና ለሴትነት ያለው አመለካከት በባሕርይ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ሲጨመር ሁኔታው በጣም የተወሳሰበ ይሆናል። እነዚህን ተጽእኖዎች በሙሉ ግምት ውስጥ በማስገባት ወንዶችና ሴቶች ሐሳባቸውን በመግለጽ ረገድ ያላቸውን ልዩነት ለይቶ ማስቀመጥ ይቻል ይሆናል። ይሁን እንጂ “አይነተኛው ወንድ” ወይም “አይነተኛዋ ሴት” የሚገኙት በሥነ ልቦና መጻሕፍት ብቻ ነው።
ሴቶች ስሜታውያን እንደሆኑ ይነገራል። ይሁን እንጂ ከሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ርህሩህና ስሜታዊ የሆኑ ብዙ ወንዶች አሉ። በምክንያታዊነት የማሰብ ባሕርይ ያላቸው በአብዛኛው ወንዶች ናቸው ቢባልም ጥሩ የማመዛዘንና የማስተዋል ችሎታ ያላቸው ብዙ ሴቶች አሉ። ስለዚህ ይህ ባሕርይ ሙሉ በሙሉ የሴቶች ወይም የወንዶች ነው ለማለት አይቻል እንጂ አንድ እርግጠኛ የሆነ ነገር አለ። ነገሮችን በሌላው ግለሰብ አመለካከት ለማየት መቻልና አለመቻል በተለይ በትዳር ውስጥ ተስማምቶ በሰላም ለመኖር ወይም ለግጭትና ለጦርነት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ወንዶችና ሴቶች በጋብቻ ውስጥ ሐሳብ ለሐሳብ ለመግባባት ባለመቻላቸው ምክንያት በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ችግሮች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። ብዙ አስተዋይ የሆኑ ባሎች ሊያረጋግጡ እንደሚችሉት “የፀጉሬ አሠራር እንዴት ነው?” እንደሚሉት ያሉ ቀላል የሚመስሉ ጥያቄዎች አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ጥበበኛ የሆኑ ሚስቶች በሚጓዙበት ጊዜ ባላቸው መንገዱ ከጠፋው “ለምን ቆም ብለህ ሰው አትጠይቅም?” እያሉ በተደጋጋሚ መጠየቅ ጥሩ እንዳልሆነ ተምረዋል። አፍቃሪ የሆኑ የትዳር ጓደኞች የባላቸውን ወይም የሚስታቸውን ልዩ ባሕርይ አቃልለው “ጠባዬ ነው፣ ምንም ማድረግ አልችልም” በማለት ከራሳቸው ጠባይ ጋር የሙጥኝ ከማለት ይልቅ የትዳር ጓደኛቸውን ውስጣዊ ባሕርይ ለማስተዋል ይጥራሉ። እንዲህ ሲባል አንዳቸው የሌላውን የሐሳብ አገላለጽ በቀዝቃዛ ስሜት ይመረምራሉ ማለት ሳይሆን አንዳቸው የሌላውን ልብና አእምሮ ለማስተዋል በፍቅር ይገፋፋሉ ማለት ነው።
አንዱ ሰው ከሌላው የተለየ እንደሆነ ሁሉ እያንዳንዱ የጋብቻ ጥምረትም በዓይነቱና በባሕርዩ የተለየ ነው። እውነተኛ የሆነ የአእምሮና የልብ ስምምነት የሚገኘው በአጋጣሚ አይደለም። ሰብዓዊ ባሕርያችን ፍጽምና የጎደለው በመሆኑ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል ሌሎች ስለ አንድ ነገር ያላቸው አመለካከት ከእኛ አመለካከት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ማሰብ በጣም ቀላል ነው። ብዙ ጊዜ ለእኛ ሊደረግልን የምንፈልገውን ነገር ለሌሎች እናደርጋለን። ምናልባት “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚለውን ወርቃማ ሕግ የፈጸማችሁ ሊመስላችሁ ይችላል። (ማቴዎስ 7:12) ይሁን እንጂ ኢየሱስ እናንተ የምትፈልጉት ነገር ሁሉ ለሌላውም ሰው ጥሩ እንደሚሆን አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ሌሎች እናንተ የሚያስፈልጋችሁን ወይም የምትፈልጉትን ነገር እንዲሰጧችሁ እንደምትመኙ ማመልከቱ ነበር። ስለዚህ እነሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር መስጠት አለባችሁ ማለት ነው። በተለይ በትዳር ውስጥ ባልና ሚስት አንዳቸው የሌላውን ፍላጎት ለመፈጸም ቃለ መሐላ የፈጸሙ በመሆናቸው ይህን መፈጸም በጣም አስፈላጊ ነው።
አልማዝና አበበ ይህን መሐላ ፈጽመዋል። ተጋብተው ያሳለፏቸው ሁለት ዓመታት አስደሳች ነበሩ። ይሁን እንጂ እርስ በርሳቸው በሚገባ እንደሚተዋወቁ ቢሰማቸውም በበጎ ፈቃድ ብቻ ሊወገድ የማይችል ሰፊ የመግባባት ክፍተት በመካከላቸው መኖሩን የሚያሳዩ ሁኔታዎች የሚፈነዱባቸው ጊዜያት አሉ። ምሳሌ 16:23 (አዓት) “የጠቢብ ሰው ልብ አፉ አስተዋይ እንዲሆን ያደርጋል” ይላል። አዎን፣ ሐሳብ ለሐሳብ በመግባባት ረገድ አስተዋይ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። አስተዋይነት ለአበበና ለአልማዝ ምን ዓይነት በር ሊከፍትላቸው እንደሚችል እንመልከት።
የወንድ አመለካከት
አበበ የሚኖረው እያንዳንዱ ሰው የበታችነትም ሆነ የበላይነት ደረጃ ቢኖረው ድርሻውን ለመፈጸም በሚገደድበት የፉክክር ዓለም ውስጥ ነው። ደረጃውን፣ ብቃቱን፣ ችሎታውንና ጠቃሚነቱን የሚያሳየው በመናገር ነው። ነጻነቱን እንደ ውድ ነገር ይመለከታል። ስለዚህ አበበ እንዲህ አድርግ ተብሎ ከታዘዘ ትእዛዙን ለመቀበል እምቢተኛ ይሆናል። የቀረበለት ጥያቄ ምክንያታዊ ቢሆንም “ሥራህን እንደሚገባ አልፈጸምክም” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ከሆነ እምቢተኛ ለመሆን ይገፋፋል።
አበበ ከሰዎች ጋር የሚነጋገርበት መሠረታዊ ምክንያት መረጃ ለመለዋወጥ ነው። ስለተማራቸው አዳዲስ ነገሮች፣ ስለ አንዳንድ ሐሳቦችና ተጨባጭ ሁኔታዎች መናገር ይወዳል።
አበበ በሚያዳምጥበት ጊዜ የሚነገረውን ነገር ከራሱ ጋር ለማዋሃድ ስለሚፈልግ በተናጋሪው ንግግር ጣልቃ ለመግባት “እህ! አዎ!” እንደሚሉት ባሉት ቃላት እንኳን ለማቋረጥ አይፈልግም። የማይስማማበት ነገር ከኖረ ግን በተለይ የቅርብ ወዳጁ ከሆነ ተቃውሞውን ለመግለጽ ወደኋላ አይልም። ወዳጁ የሚነግረውን ነገር ከተለያዩ ገጽታዎች ለማስተዋል ጥረት ያደርጋል፣ ይህም ለሚያዳምጠው ነገር ፍላጎት ያለው መሆኑን ያሳያል።
አበበ ችግር ካጋጠመው ብቻውን ሆኖ የችግሩን መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግ ይመርጣል። ስለዚህም ከማንኛውም ሰውም ሆነ ነገር ይርቃል። አለበለዚያም ችግሩን የሚያስረሳው ነገር ለማድረግና ለመዝናናት ይፈልጋል። ችግሩን ለሰው የሚያዋየው ምክር ሲፈልግ ብቻ ነው።
አበበ እንደ ጌታቸው ችግር አጋጥሞት ወደ እርሱ የሚመጣ ሰው ካጋጠመው ወዳጁን ብቃት እንደጎደለው ሳይሰማው የመርዳት ኃላፊነት እንዳለበት ይገነዘባል። በሚሰጠው ምክር ላይ አክሎ ራሱ ያጋጠመውን ችግር በመናገር ችግሩ በወዳጁ ላይ ብቻ የደረሰ እንዳልሆነ እንዲገነዘብ ያደርጋል።
አበበ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ አንዳንድ ነገሮችን መሥራት ያስደስተዋል። ለእርሱ ጓደኝነት ማለት አንዳንድ ነገሮች አብሮ ማድረግ ነው።
ለአበበ ቤቱ ማንነቱን ለማሳየት ለመናገር የማይገደድበት፣ በእሱነቱ ብቻ የሚታመንበት፣ የሚወደድበት፣ የሚደነቅበትና ተቀባይነት የሚያገኝበት፣ ከአደባባይ ኑሮ እፎይ የሚልበት ቦታ ነው። ቢሆንም አበበ ብቻውን መሆን የሚፈልግበት ጊዜ ይኖረዋል። አልማዝን ወይም እርስዋ የምታደርጋቸውን ነገሮች ለመሸሽ ብሎ ላይሆን ይችላል። የፈለገው ብቻውን ለመሆን ብቻ ነው። አበበ ስጋቱን፣ ጭንቀቱንና በውስጡ ያለውን ያለመረጋጋት መንፈስ ለሚስቱ መግለጽ ያስቸግረዋል። እንድትጨነቅ አይፈልግም። እርስዋን መንከባከብና መጠበቅ ግዴታው እንደሆነና አልማዝም ይህን ግዴታውን እንደሚወጣ እንድትተማመንበት ይፈልጋል። አበበ ድጋፍ እንዲሰጠው ቢፈልግም የማንንም አዘኔታ አይፈልግም። ሰዎች እንደሚያዝኑለት ሲናገሩ ብቃት እንደሌለውና ዋጋ ቢስ እንደሆነ ይሰማዋል።
የሴት አመለካከት
አልማዝ ራስዋን የምትመለከተው ማኅበራዊ ግንኙነቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ እንዳለች አንዲት ግለሰብ ነው። ለእርስዋ እነዚህን ግንኙነቶችና ዝምድናዎች ማጠናከር በጣም አስፈላጊ ነው። ከሌሎች ጋር ቅርርብ ለመፍጠርና የተፈጠረውን ቅርርብ ለማጠንከር መነጋገር ያስፈልጋታል።
ለአልማዝ የሌሎች ጥገኛ መሆን የተፈጥሮ ባሕርይ ነው። አበበ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት የእርስዋን አስተያየት ቢጠይቅ እንደምትወደድ ይሰማታል። ቢሆንም ባልዋ ነገሮችን በቀዳሚነት እንዲያከናውን ትፈልጋለች። ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ ባልዋን ማማከር ትወዳለች። ይህን የምታደርገው ቅርበትዋንና በእርሱ የምትታመን መሆንዋን ለማሳየት እንጂ ምን ማድረግ እንደሚገባት እንዲነግራት ላይሆን ይችላል።
አልማዝ ይህን እፈልጋለሁ ብላ በቀጥታ መናገር በጣም ያስቸግራታል። አበበን ለመጨቅጨቅ ወይም ደስተኛ እንዳልሆነች እንዲሰማው ለማድረግ አትፈልግም። ከዚህ ይልቅ የሚያስፈልጋትን እንዲያስተውል ትፈልጋለች ወይም ስለሚያስፈልጋት ነገር ፍንጭ የሚሰጥ ነገር ታደርጋለች።
አልማዝ ከሌሎች ጋር በምትጨዋወትበት ጊዜ ዝርዝር ነገሮችን ለማወቅ ትፈልጋለች፣ ብዙ ጥያቄዎችም ትጠይቃለች። ይህም ለሰዎችና ከሰዎች ጋር ላላት ግንኙነት በጣም አሳቢ ከመሆን የተፈጥሮ ባሕርይዋ የሚመነጭ ነው።
አልማዝ በምታዳምጥበት ጊዜ ተናጋሪውን እንደምትከታተል ወይም ስለሚናገረው ወይም ስለምትናገረው ነገር ፍላጎት ያላት መሆኑን ለማሳየት በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ትጠይቃለች፣ ወይም ራስዋን ትነቀንቃለች ወይም የቃለ አጋኖ ቃላት ታሰማለች።
ሰዎች ስለሚፈልጉት ነገር ገና ሳይናገሩ ለማወቅ ትጣጣራለች። ለእርስዋ ሳትጠየቅ እርዳታ መስጠት ፍቅርዋን ለመግለጽ የሚያስችላት ግሩም መንገድ ነው። በተለይ ባልዋ እድገት እንዲያደርግና እንዲሻሻል ለመርዳት ትፈልጋለች።
አልማዝ ችግር ሲያጋጥማት ትደናገጣለች። መፍትሔ ለማግኘት ባይሆንም ስሜትዋን መግለጽና ለሰው መናገር ትፈልጋለች። ችግርዋን የሚረዳና የሚያስብላት ሰው መኖሩን ለማወቅ ትፈልጋለች። ስሜትዋ በሚረበሽበት ጊዜ ጥፋተኛውንና ጥፋተኛ ያልሆነውን የማይመርጥ ከባድ ንግግር ትናገራለች። “ፈጽሞ አትሰማኝም!” ስትል ቃል በቃል አትሰማኝም ማለትዋ አይደለም።
አልማዝ ዘወትር የምታስታውሳት የልጅነት ጓደኛዋ አብራት ብዙ ነገር የሠራች ጓደኛዋ ሳትሆን ስለ ብዙ ነገሮች አብራት ያወራችዋ ናት። ስለዚህ በትዳርዋም ስሜትዋን የምታካፍለው ጥሩ አድማጭ የማግኘትን ያህል በውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አያስደስቷትም።
ለአልማዝ ቤትዋ የሚተቻት ሳይኖር እንደልብዋ ልትናገር የምትችልበት ቦታ ነው። ስጋትዋንና ጭንቀትዋን ለአበበ ለመግለጽ ወደ ኋላ አትልም። እርዳታ የሚያስፈልጋት ከሆነ ምን ጊዜም ባልዋ ከጎንዋ እንደሚሆንና እንደሚያዳምጣት ስለምትተማመንበት እርዳታውን መጠየቅ አያሳፍራትም።
አልማዝ አብዛኛውን ጊዜ እንደምትወደድ ይሰማታል፣ ስለትዳርዋም አትሰጋም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ምንም ግልጽ ምክንያት ሳይኖራት ስጋትና ያለመወደድ ስሜት ተሰምቷት በአጣዳፊ ማጽናኛና ባልንጀራ ማግኘት ትፈልጋለች።
አዎን፣ አበበና አልማዝ አንዳቸው የሌላው ማሟያ ሲሆኑ የተለያየ ባሕርይ አላቸው። ሁለቱም የትዳር ጓደኛቸውን ለመውደድና ለመደገፍ ልባዊ ፍላጎት ያላቸው ቢሆኑም በመካከላቸው ያለው ልዩነት ከባድ አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከላይ በጠቀስነው ሁኔታ እያንዳንዳቸው ከራሳቸው አመለካከት አንጻር የተሰማቸውን ሲናገሩ ለመስማት ብንችል ምን ይሉ ይሆን?
በራሳቸው ዓይን የተመለከቷቸው ነገሮች
“ወዲያው በሩን ከፍቼ እንደገባሁ አልማዝ የተበሳጨችበት ነገር እንዳለ ለማየት ችዬአለሁ” ይላል አበበ። “በጊዜው የተበሳጨችበትን ምክንያት የምትነግረኝ መስሎኝ ነበር። ለኔ ይህን ያህል ከባድ ችግር ሆኖ አልታየኝም። ይህን ያህል መበሳጨት እንደማይኖርባትና መፍትሔውም ቀላል እንደሆነ እንድትገነዘብ ከረዳኋት ብስጭቷ ይሻላታል ብዬ አሰብኩ። ሳዳምጣት ከቆየሁ በኋላ ‘ፈጽሞ አትሰማኝም!’ ስትለኝ በጣም አዘንኩ። ለብስጭትዋ ሁሉ እኔን ምክንያት እንዳደረገች ሆኖ ተሰማኝ።”
አልማዝ የበኩሏን ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “ቀኑን ሁሉ ስበሳጭ ነበር የዋልኩት። ስህተቱ የአበበ እንዳልነበረ አውቃለሁ። በጣም ደስ ብሎት ሲገባ ግን የኔን መበሳጨት ከጉዳይ ያልቆጠረው ሆኖ ተሰማኝ። ምን እንደሆንኩ ለምን አልጠየቀኝም? ችግሬን ስነግረው የሰጠኝ ምላሽ የማልረባና ትንሹን ነገር የማጋንን መሆኔን የሚያሳይ ነበር። መፍትሔ ፈላጊው አበበ ስሜቴን እንደሚረዳልኝ ከመናገር ይልቅ እንዴት ችግሬን መወጣት እንደሚኖርብኝ ነገረኝ። እኔ የፈለግሁት ስሜቴን እንዲረዳልኝና እንዲያዝንልኝ እንጂ መፍትሔ እንዲሰጠኝ አልነበረም!”
አበበና አልማዝ ይህን የመሰለ ጊዜያዊ አለመግባባት ቢያጋጥማቸውም በጣም ይዋደዳሉ። ይህን ፍቅራቸውን ለመግለጽ የሚችሉት ምን ነገር ቢያስተውሉ ነው?
ነገሮችን በሌላው ሰው ዓይን ማየት
አበበ፣ አልማዝ ምን እንደሆነች ቢጠይቃት በግል ጉዳይዋ ውስጥ መግባት የሚሆንበት መስሎ ተሰማው። ስለዚህም ሰዎች ሊያደርጉለት የሚፈልገውን ነገር አደረገላት። ራስዋ አውጥታ እስክትናገር ድረስ ጠበቃት። አልማዝ ግን ካጋጠማት ችግር በተጨማሪ አበበ ሊረዳት ዝግጁ አለመሆኑ አበሳጫት። ዝም ማለቱን አክብሮት እንደሆነ ሳይሆን ግድየለሽነት እንደሆነ ቆጠረች። አልማዝ መናገር ስትጀምር ደግሞ አበበ ምንም ነገር ሳይናገር አዳመጣት። እርስዋ ግን ስሜቷን የማያዳምጣት ሆኖ ታያት። ካዳመጠ በኋላ ደግሞ አዘኔታውን ሳይሆን መፍትሔ ነገራት። ይህም ‘ያንቺ ስሜት ግምት ሊሰጠው የሚገባ አይደለም፣ ይህን ችግር መፍታት ምን ያህል ቀላል እንደሆነ እይ’ የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ነበር።
ሁለቱም ራሳቸውን በሌላው ቦታ አድርገው ችግሩን ቢያዩት ኖሮ እንዴት ያለ የተለየ ውጤት ይገኝ ነበር! እንደሚከተለው ሊሆን ይችል ነበር።
አበበ ቤቱ ሲገባ አልማዝን ተበሳጭታ ያገኛታል። ቀስ ብሎ “አልማዝዬ፣ ምን ሆነሻል?” ብሎ ይጠይቃል። እንባዋ እየተናነቃት መናገር ትጀምራለች። አልማዝ “ጥፋቱ ያንተ ነው” ማለትዋ ወይም አበበ የሚገባውን እንደማያደርግ መናገርዋ አይደለም። አበበ እቅፍ ያደርጋትና በትዕግሥት ያዳምጣታል። ስትጨርስ “በጣም ስለተበሳጨሽ አዝናለሁ። ይህን ያህል የተበሳጨሽው ለምን እንደሆነ ገብቶኛል” ይላታል። አልማዝም “ስላዳመጥኸኝ በጣም አመሰግናለሁ። ስሜቴን እንደተረዳኽልኝ በማወቄ በጣም ቀለል ብሎኛል” ትለዋለች።
ብዙ ባለ ትዳሮች በመካከላቸው የሚነሳውን አለመግባባት ከመፍታት ይልቅ ለመፋታት ይመርጣሉ። ለብዙ ቤቶች መፍረስ ምክንያቱ ሐሳብ ለሐሳብ አለመግባባት ነው። የትዳራቸውን መሠረት የሚያናጋ ጭቅጭቅ ይነሳል። እንዲህ ያለው ጭቅጭቅ የሚነሳው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ጭቅጭቅ የሚነሳው እንዴት እንደሆነና እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ይነግረናል።