የሕይወት ታሪክ
‘ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ዕንቁ’ አገኘን
ዊንስተን እና ፓሜላ (ፓም) ፔን የሚያገለግሉት በአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ነው። አብረው ያሳለፉት ሕይወት አስደሳች ቢሆንም አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል፤ ከተለያዩ ባሕሎች ጋር መላመድ ያስፈለጋቸው ከመሆኑም ሌላ ልጃቸው ገና ሆድ ውስጥ ሳለ ሞቶባቸዋል። ሆኖም በዚህ ሁሉ ጊዜ፣ ለይሖዋና ለሕዝቡ ያላቸውን ፍቅር እንዲሁም ከአገልግሎታቸው የሚያገኙትን ደስታ ይዘው መቀጠል ችለዋል። በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ፣ ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉን ጠይቀናቸዋል።
ዊንስተን፣ አምላክን ለማወቅ ስላደረግከው ፍለጋ እስቲ ንገረን።
ያደግኩት በኩዊንስላንድ፣ አውስትራሊያ በሚገኝ አንድ እርሻ ውስጥ ነው፤ ቤተሰባችን ሃይማኖተኛ አልነበረም። የምንኖረው ራቅ ባለ ስፍራ ስለነበር ከቤተሰቤ ውጭ ከሌሎች ሰዎች ጋር ብዙም አልገናኝም ነበር። አምላክን መፈለግ የጀመርኩት 12 ዓመት ገደማ ሲሆነኝ ነው። አምላክ ስለ እሱ እውነቱን እንዲያሳውቀኝ ጸልዬ ነበር። ከጊዜ በኋላ የእርሻ ቦታውን ለቅቄ በአደሌድ፣ ደቡብ አውስትራሊያ መሥራት ጀመርኩ። በ21 ዓመቴ ለእረፍት ወደ ሲድኒ በሄድኩበት ወቅት ከፓም ጋር ተዋወቅኩ፤ እሷም የብሪታንያ እስራኤል ስለሚባለው ሃይማኖታዊ ቡድን ነገረችኝ። የዚህ ሃይማኖታዊ ቡድን ተከታዮች የብሪታንያ ሕዝብ፣ የጠፉት የእስራኤል ነገዶች ዝርያ እንደሆኑ ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች፣ የጠፉት የእስራኤል ነገዶች በ8ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በግዞት የተወሰዱት የሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት አሥር ነገዶች እንደሆኑ ያምናሉ። ወደ አደሌድ ተመልሼ ስሄድ፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምሮ ለነበረ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ስለዚህ ሃይማኖታዊ ቡድን የሰማሁትን ነገርኩት። የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ከእሱ ጋር ለጥቂት ሰዓታት ያህል ከተወያየን በኋላ በልጅነቴ ያቀረብኩት ጸሎት መልስ እንዳገኘ ተሰማኝ። ስለ ፈጣሪዬና እሱ ስላቋቋመው መንግሥት እውነቱን ማወቅ ቻልኩ! ‘ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ዕንቁ’ ያገኘሁት በዚህ መንገድ ነበር።—ማቴ. 13:45, 46
ፓም፣ አንቺም ይህን ዕንቁ መፈለግ የጀመርሽው ገና በልጅነትሽ ነው። እንዴት ልታገኚው እንደቻልሽ ትነግሪናለሽ?
ያደግኩት በኮፍስ ሃርበር፣ ኒው ሳውዝ ዌልስ ነው፤ ቤተሰቦቼ ሃይማኖተኛ ነበሩ። ወላጆቼና አያቶቼ የብሪታንያ እስራኤል የሚባለው ሃይማኖታዊ ቡድን የሚያስተምራቸውን ትምህርቶች ተቀብለው ነበር። እኔ፣ ታናሽ ወንድሜ፣ ታላቅ እህቴ እንዲሁም የአክስቶቼና የአጎቶቼ ልጆች አምላክ የብሪታንያ ተወላጆችን ከሁሉ አብልጦ እንደሚመለከት ከልጅነታችን አንስቶ ተምረናል። ሆኖም የቀረቡት ማስረጃዎች ስላላሳመኑኝ መንፈሳዊ ጥማቴ ሊረካ አልቻለም። የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ ባፕቲስትን፣ አንግሊካንንና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትን ጨምሮ በአካባቢው ወደሚገኙ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ሄጃለሁ። ይሁን እንጂ አንዳቸውም ስለ አምላክ እንዳውቅ አልረዱኝም።
ከጊዜ በኋላ ቤተሰቤ ወደ ሲድኒ ተዛውሮ መኖር የጀመረ ሲሆን በዚያም ለእረፍት ከመጣው ከዊንስተን ጋር ተዋወቅሁ። ከእሱ ጋር ስለ ሃይማኖት ተወያይተን ነበር። ዊንስተን ቀደም ሲል እንደጠቀሰው፣ በዚህ ውይይት ምክንያት እሱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረ። ከዚያ በኋላ የሚልክልኝ ደብዳቤዎች ሁሉ በጥቅሶች የተሞሉ ነበሩ! እውነቱን ለመናገር መጀመሪያ ላይ ጉዳዩ አሳስቦኝ አልፎ ተርፎም አበሳጭቶኝ ነበር። ቀስ በቀስ ግን፣ የሚጽፈው ነገር እውነት እንደሆነ ማስተዋል ቻልኩ።
ዊንስተን ወዳለበት ቀረብ ብዬ ለመኖር ስል በ1962 ወደ አደሌድ ተዛወርኩ። እሱም በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሚስዮናዊ ሆነው ያገለግሉ ከነበሩት ቶማስና ጃኒስ ስሎማን የተባሉ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ጋር እንድኖር ዝግጅት አደረገልኝ። እነዚህ ባልና ሚስት አስደናቂ ደግነት አሳይተውኛል፤ በወቅቱ ገና የ18 ዓመት ወጣት የነበርኩ ቢሆንም ስለ ይሖዋ ብዙ ነገር እንዳውቅ ረድተውኛል። በመሆኑም የአምላክን ቃል ማጥናት የጀመርኩ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ እውነትን እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ። እኔና ዊንስተን ከተጋባን በኋላ ወዲያውኑ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርን፤ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በዚህ አገልግሎት መካፈላችን ብዙ በረከት አስገኝቶልናል። ይህም ላገኘነው ውድ ዕንቁ ያለንን አድናቆት አሳድጎልናል።
ዊንስተን፣ በይሖዋ አገልግሎት ስላሳለፍካቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት እስቲ ንገረን።
ሀ. በወረዳ ሥራችን ላይ የተጓዝንባቸውን ቦታዎች የሚያሳይ ካርታ
ለ. ከአንዳንዶቹ ደሴቶች የተወሰዱ የፖስታ ቴምብሮች። ኪሪባቲና ቱቫሉ ቀደም ሲል ጊልበርትና ኤሊስ ደሴቶች ተብለው ይጠሩ ነበር
ሐ. በቱቫሉ ግዛት ውስጥ ያለው የፉናፉቲ ውብ ደሴት። ሚስዮናውያን ከመመደባቸው በፊት ከጎበኘናቸው በርካታ ደሴቶች መካከል አንዱ ነው
እኔና ፓም ከተጋባን ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ እሱን ለማገልገል የሚያስችል “ትልቅ የሥራ በር” ከፈተልን፤ ይህ ምድብ በእሱ አገልግሎት ካገኘናቸው በርካታ አስደሳች የአገልግሎት መብቶች የመጀመሪያው ነበር። (1 ቆሮ. 16:9) ይህን የሥራ በር የጠቆመን፣ አነስተኛ የሆነችውን ጉባኤያችንን የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግል የነበረው ወንድም ጃክ ፖርተር ነው። (አሁን በአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ ውስጥ አብረን እያገለገልን ነው።) ጃክና ባለቤቱ ሮዝሊን በዘወትር አቅኚነት እንድናገለግል ያበረታቱን ሲሆን በዚህ የአገልግሎት መስክ ለአምስት ዓመታት ተካፍለናል። ሃያ ዘጠኝ ዓመት ሲሆነኝ እኔና ፓም በወቅቱ በፊጂ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር በነበሩት የደቡብ ፓስፊክ ደሴቶች ላይ በወረዳ ሥራ እንድናገለግል ተጠየቅን። ደሴቶቹ ቱቫሉ፣ ቶንጋ፣ ቶክላው፣ ኒዩዌ፣ ናኡሩ፣ አሜሪካን ሳሞአና ሳሞአ፣ ኪሪባቲና ቫንዋቱ ናቸው።
በዚያ ወቅት፣ ይበልጥ ርቀው በሚገኙት ደሴቶች ላይ የሚኖሩት ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን በጥርጣሬ ዓይን ይመለከቱ ስለነበር ጠንቃቆችና አስተዋዮች መሆን ነበረብን። (ማቴ. 10:16) ጉባኤዎቹ አነስተኛ ከመሆናቸውም ሌላ ለእኛ ማረፊያ ቦታ ማዘጋጀት ይከብዳቸው ነበር። ስለዚህ የአካባቢው ሰዎች እንዲያሳርፉን እንጠይቃለን፤ ደግሞም ሰዎቹ ሁሌም ደግነት ያሳዩን ነበር።
ዊንስተን፣ ለትርጉም ሥራ ለየት ያለ ትኩረት ትሰጣለህ። ምክንያቱን ልትነግረን ትችላለህ?
በሳሞአ የሽማግሌዎች ትምህርት ቤት ላይ ሳስተምር
በዚያን ጊዜ፣ በቶንጋ ደሴት የሚኖሩት ወንድሞች በቶንጋኛ ማግኘት የሚችሉት ጥቂት ትራክቶችንና ቡክሌቶችን ብቻ ነበር። በአገልግሎት ላይ የሚጠቀሙት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ እንግሊዝኛ ቅጂ ነበር። ስለዚህ አራት ሳምንት የሚፈጀው የሽማግሌዎች ትምህርት ቤት በተደረገበት ወቅት፣ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑና ውስን የእንግሊዝኛ ችሎታ ያላቸው ሦስት ሽማግሌዎች እውነት የተባለውን መጽሐፍ ወደ ቶንጋኛ ለመተርጎም ተስማሙ። ፓም በእጅ የተጻፈውን ጽሑፍ ታይፕ ካደረገች በኋላ ለሕትመት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ላክነው። ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ስምንት ሳምንታት ገደማ ፈጅቷል። የትርጉሙ ጥራት የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በርካታ የቶንጋኛ ተናጋሪዎች እውነትን እንዲማሩ ረድቷል። እኔና ፓም ተርጓሚዎች ባንሆንም ይህ አጋጣሚ ለትርጉም ሥራ ልዩ ትኩረት እንድንሰጥ አድርጎናል።
ፓም፣ በደሴቶቹ ላይ ያለው ሕይወት በአውስትራሊያ ከነበረው ጋር ሲወዳደር እንዴት ነው?
በወረዳ ሥራ ላይ ሳለን ለመኖሪያነት ከተጠቀምንባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ይህ መኪና ነበር
በጣም የተለየ ነው! ሁኔታው ከደሴት ወደ ደሴት ሊለያይ ቢችልም በወባ ትንኞች፣ ከፍተኛ በሆነ ሙቀትና እርጥበት፣ በአይጦች፣ በበሽታ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በምግብ እጦት ምክንያት እንቸገር ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ላይ፣ በሳሞአ ሰዎች አጠራር ፌል ከሚባለው ቤታችን ሆነን ውቅያኖሱን ስንመለከት መንፈሳችን ይታደሳል፤ ፌል በፖሊኔዥያ አካባቢ የተለመደ የቤት አሠራር ሲሆን የሣር ክዳን ያለው ሆኖም ግድግዳ የሌለው ቤት ነው። የጨረቃ ብርሃን ባለባቸው ሌሊቶች የዘንባባ ዛፎቹ ጥላ እንዲሁም በውቅያኖሱ ላይ ያረፈው የጨረቃዋ ነጸብራቅ ይታየናል። እንዲህ ያሉት አስደሳች ወቅቶች ለማሰላሰልና ለመጸለይ አመቺ ስለሆኑ አሉታዊ አስተሳሰብን አስወግደን አዎንታዊ አስተሳሰብ እንድናዳብር ረድተውናል።
በእነዚህ ደሴቶች ላይ የምናገኛቸውን ልጆች በጣም እንወዳቸው ነበር፤ ልጆቹ ደስ የሚሉ ናቸው። ነጭ የቆዳ ቀለም ስላለን በትኩረት ይመለከቱን ነበር። ኒዩዌን ስንጎበኝ አንድ ትንሽ ልጅ በዊንስተን እጅ ላይ ያለውን ፀጉር እየደባበሰ “ላባዎችህ ደስ ይላሉ” አለው። ልጁ ይህን ያለው ከዚያ በፊት እንዲህ ያለ ፀጉራም እጅ አይቶ ስለማያውቅ ምን ብሎ እንደሚገልጽ ቸግሮት ነው!
አብዛኞቹ ሰዎች ይኖሩበት የነበረውን የተጎሳቆለ ሁኔታ ስናይ በጣም እናዝን ነበር። የሚያምር አገር ያላቸው ቢሆንም በቂ ሕክምናና የመጠጥ ውኃ አያገኙም። ሆኖም ወንድሞቻችን በዚህ ያን ያህል አይጨነቁም። ይህ ዓይነቱ ሕይወት ለእነሱ የተለመደ ነበር። በቤተሰባቸው ተከበው በመኖራቸው፣ ለአምልኮ የሚሰበሰቡበት ቦታ በማግኘታቸውና ይሖዋን ማወደስ በመቻላቸው ደስተኞች ነበሩ። እነሱ የተዉት ምሳሌ እኛም ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገቡ ነገሮች ላይ እንድናተኩርና ኑሯችንን ቀላል እንድናደርግ ረድቶናል።
ፓም፣ ከጉድጓድ ውኃ ለመቅዳትና እሳት አቀጣጥለሽ ምግብ ለማብሰል የተገደድሽባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ሰምተናል። ሁኔታው ለአንቺ አዲስ ከመሆኑ አንጻር እንዴት ተወጣሽው?
ቶንጋን እየጎበኘን በነበርንበት ወቅት ፓም ልብሳችንን ስታጥብ
በዚህ ረገድ አባቴን አመሰግነዋለሁ። አባቴ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን አስተምሮኛል፤ እሳት አቀጣጥዬ ምግብ ማብሰልም ሆነ ያለኝን አብቃቅቼ መኖር የምችለው እንዴት እንደሆነ አሠልጥኖኛል። በአንድ ወቅት ኪሪባቲን ስንጎበኝ ያረፍንበት ቤት፣ የሣር ክዳንና የቀርከሃ ግድግዳ ያለው እንዲሁም ወለሉ ላይ ዛጎል የተነጠፈበት ትንሽ ቤት ነበር። ቀለል ያለ ምግብ ማብሰል ስለፈለግኩ ወለሉን ቆፍሬ ምድጃ ሠራሁ፤ ከዚያም የኮኮናቱን ቅርፊት እንደ ማገዶ አድርጌ ተጠቀምኩ። ውኃ ለመቅዳት ደግሞ ወደ አንድ የውኃ ጉድጓድ ሄጄ ከአካባቢው ሴቶች ጋር ተሰለፍኩ። እነዚህ ሴቶች ከጉድጓዱ ውኃ ለመቅዳት ወደ ሁለት ሜትር ገደማ ርዝመት ያለውና ጫፉ ላይ ቀጭን ገመድ የታሰረበት እንጨት ይጠቀሙ ነበር። እንጨቱ ከዓሣ ማጥመጃ በትር ጋር ይመሳሰላል፤ ሆኖም የገመዱ ጫፍ ላይ የታሰረው መንጠቆ ሳይሆን የቆርቆሮ ባልዲ ነበር። ሁሉም ሴቶች ተራቸው ሲደርስ ገመዱን ከወረወሩ በኋላ ትክክለኛው ጊዜ ላይ ባልዲውን ገልበጥ ያደርጉታል። በዚህ ጊዜ ባልዲው ወደ ጎን ዘንበል ይልና ውኃው መሙላት ይጀምራል። ተራዬ ደርሶ እስክሞክረው ድረስ በዚህ መንገድ ውኃ መቅዳት ቀላል መስሎኝ ነበር። ሆኖም ገመዱን በተደጋጋሚ ብወረውረውም ባልዲው ውኃውን መትቶ ከመንሳፈፍ በቀር ውኃ አልይዝ አለ! ሁሉም ስቀው ከጨረሱ በኋላ ከመካከላቸው አንዷ ረዳችኝ። የአካባቢው ሰዎች ሁሌም ቢሆን ተባባሪና ደግ ናቸው።
ሁለታችሁም በደሴቶቹ ላይ እንድታገለግሉ የተሰጣችሁን ምድብ ትወዱት ነበር። የማትረሷቸውን አንዳንድ ገጠመኞች እስቲ ንገሩን።
ዊንስተን፦ አንዳንድ ባሕሎችን ለመረዳት የተወሰነ ጊዜ ወስዶብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ወንድሞች ቤታቸው ሲጋብዙን አብዛኛውን ጊዜ የሚያቀርቡት ያላቸውን ምግብ በሙሉ ነበር። መጀመሪያ ላይ፣ ለእነሱ ማስተረፍ እንዳለብን አላወቅንም ነበር። ስለዚህ የቀረበልንን በሙሉ ጥርግ አድርገን እንበላ ነበር! እርግጥ ነው፣ ይህን ካወቅን በኋላ ለእነሱም ምግብ ማስቀረት ጀመርን። አንዳንድ ስህተቶችን እንሠራ የነበረ ቢሆንም ወንድሞቻችን ሁኔታችንን ይረዱልን ነበር። በወረዳ ሥራችን በየስድስት ወር ገደማ ልንጎበኛቸው ስንሄድ እኛን በማየታቸው በጣም ይደሰታሉ። በዚያን ጊዜ ከአካባቢው ወንድሞች ውጭ የሚያውቁት የይሖዋ ምሥክር እኛን ብቻ ነበር።
በኒዩዌ ደሴት ላይ ከአንድ ቡድን ጋር ለአገልግሎት ስንሰማራ
በተጨማሪም ጉብኝታችን በማኅበረሰቡ ውስጥ ጥሩ ምሥክርነት ሰጥቷል። ብዙ የመንደሩ ነዋሪዎች፣ የወንድሞች ሃይማኖት እዚያው የተመሠረተ ሃይማኖት እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። ስለዚህ የአካባቢው ሰዎች አንድ የሃይማኖት አገልጋይና ባለቤቱ ከውጭ አገር መጥተው ወንድሞችን እንደጎበኙ ሲያዩ አመለካከታቸውን ከማስተካከላቸውም ባሻገር በጣም ይደነቁ ነበር።
ፓም፦ ኪሪባቲ ውስጥ ጥቂት ወንድሞችና እህቶች ብቻ ያሉበትን አንድ ጉባኤ ስንጎበኝ ያጋጠመንን ነገር መቼም ቢሆን አልረሳውም። በዚህ ጉባኤ ውስጥ ብቸኛ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል የነበረው ስቲንካይ ማቴራ የተባለ ወንድም እኛን ለመንከባከብ የቻለውን ሁሉ አድርጓል። አንድ ቀን አንዲት እንቁላል ብቻ የያዘ ቅርጫት ይዞ መጣ። ከዚያም “ይህን ያመጣሁት ለእናንተ ነው” አለን። የዶሮ እንቁላል በዚያን ጊዜ በቀላሉ የማይገኝ ልዩ ግብዣ ነበር። ከፍተኛ ልግስና የተንጸባረቀበት ይህ አነስተኛ ስጦታ ልባችንን በጥልቅ ነክቶታል።
ፓም፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ልጃችሁ ገና ሆድ ውስጥ እያለ በሞተባችሁ ጊዜ ሐዘኑን ለመቋቋም የረዳሽ ምንድን ነው?
በ1973 እኔና ዊንስተን በደቡብ ፓስፊክ ሳለን ልጃችንን ፀነስኩ። በመሆኑም ወደ አውስትራሊያ ለመመለስ ወሰንን። ይሁንና ከአራት ወር በኋላ ልጃችን ሆዴ ውስጥ ሳለ ሞተ። እኔም ሆንኩ ዊንስተን በተፈጠረው ነገር በጣም አዘንን። በጊዜ ሂደት የልቤ ሐዘን እየቀነሰ ቢሄድም የሚያዝያ 15, 2009ን መጠበቂያ ግንብ እስካነብ ድረስ ሙሉ በሙሉ አልተጽናናሁም ነበር። ይህ መጽሔት “የአንባቢያን ጥያቄዎች” በሚለው ዓምድ ሥር “በእናቱ ማህፀን ውስጥ የሞተ ሕፃን የትንሣኤ ተስፋ አለው?” የሚል ጥያቄ ይዞ ነበር። ይህ ርዕስ፣ የልጃችን ጉዳይ ምንጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር በሚያደርገው በይሖዋ እጅ ውስጥ እንዳለ በመግለጽ አጽናንቶናል። ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ ልጁ ‘የሰይጣንን ሥራዎች እንዲያፈርስ’ ትእዛዝ የሚያስተላልፍ ሲሆን በዚያን ጊዜ፣ ይህ ክፉ ዓለም ካስከተለብን ቁስሎች በሙሉ ፈውስ እናገኛለን። (1 ዮሐ. 3:8) በተጨማሪም ይህ ርዕስ የይሖዋ ሕዝቦች በመሆናችን ያገኘነውን ውድ “ዕንቁ” ይበልጥ እንድናደንቅ አስችሎናል! የመንግሥቱ ተስፋ ባይኖረን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር?
ልጃችን ከሞተ በኋላ እንደገና ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተመለስን። በአውስትራሊያ ቤቴል ውስጥ ለጥቂት ወራት ካገለገልን በኋላ የወረዳ ሥራችንን ቀጠልን። ለአራት ዓመታት ያህል በገጠራማው ኒው ሳውዝ ዌልስና በሲድኒ ካገለገልን በኋላ በ1981 በአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ (በወቅቱ ይጠራ የነበረው በዚህ ስም ነው) እንድናገለግል ተጋበዝን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ እዚያው እያገለገልን ነው።
ዊንስተን፣ በደቡብ ፓስፊክ ደሴቶች ስታገለግል ያካበትከው ተሞክሮ የአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል ሆነህ ለምታከናውነው ሥራ እንደጠቀመህ ይሰማሃል?
አዎ፣ በብዙ መንገዶች ጠቅሞኛል። አንደኛ፣ የአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ በአሜሪካን ሳሞአና በሳሞአ የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት እንዲከታተል ተጠይቆ ነበር። ከዚያም የኒው ዚላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ከአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር ተቀላቀለ። በአሁኑ ጊዜ የአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ቲሞር ሌስተን፣ ቶንጋን፣ ቶክላውን፣ ኒው ዚላንድን፣ ኒዩዌን፣ አሜሪካን ሳሞአንና ሳሞአን፣ አውስትራሊያን እንዲሁም ኩክ ደሴቶችን የሚያካትት ሲሆን ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹን የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ ሆኜ የመጎብኘት መብት አግኝቻለሁ። በደሴቶቹ ላይ ከሚኖሩት ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ጋር ሳገለግል ያገኘሁት ተሞክሮ አሁን ከቅርንጫፍ ቢሮው ሆኜ እነዚህኑ ወንድሞች ሳገለግል በጣም ጠቅሞኛል።
ዊንስተንና ፓም በአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ
በማጠቃለያው ላይ መናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር፣ እኔና ፓም ከብዙ ዓመታት በፊት በራሳችን ተሞክሮ እንዳየነው አምላክን ማወቅ የሚፈልጉት አዋቂዎች ብቻ አይደሉም። ወጣቶችም ቢሆኑ ሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ምንም ፍላጎት ባያሳዩ እንኳ ‘ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ዕንቁ’ ለማግኘት ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ። (2 ነገ. 5:2, 3፤ 2 ዜና 34:1-3) ይሖዋ ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ሕይወት እንዲያገኙ የሚፈልግ አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን!
እኔና ፓም ከ50 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት አምላክን መፈለግ ስንጀምር ፍለጋችን ወዴት እንደሚመራን የምናውቀው ነገር አልነበረም። የመንግሥቱ እውነት እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ዕንቁ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም! እስከ መጨረሻው ድረስ ይህን ውድ ዕንቁ ይዘን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል!