በታዳጊ አገሮች ሥራ መፍጠር
ሴኔጋል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
የወጣትዋ አባት እናቷንና ስምንት ልጆቹን ጥሎ የሞተው ገና በሕፃንነትዋ ነው። አሁን ግን እናትዋ እርጅና እየተጫጫናት ስለመጣ ሥራ አግኝታ ቤተሰቦችዋን መርዳት ሊኖርባት ነው። ትምህርትዋን ለመጨረስ የነበራት ምኞት ከንቱ ሆኗል። ችሎታም ሆነ መደበኛ ትምህርት ባይኖራትም መሥራት ግዴታዋ ነው።
እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች በታዳጊ አገሮች የተለመዱ ናቸው። የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ያላቸው እንኳን ሥራ ለማግኘት ይቸገራሉ። ይሁን እንጂ ብዙዎች በቆራጥነትና በፈጠራ ችሎታቸው በመጠቀም የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር ችለዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ሥራዎች የተቀናጣ የምቾች ኑሮ ላያስገኙ ይችላሉ። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ጢሞቴዎስ 6:8 ላይ “ምግብና ልብስ ካገኘን እርሱ ይበቃናል” ይላል።
እንዲህ ያለው ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን የሚያስችለንን ምክር በአእምሯችን ይዘን በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ኑሯቸውን ሊያሸንፉ የቻሉባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።
በአፍሪካውያን የአዘገጃጀት ዘዴ ምግብ እየሠሩ መሸጥ
ምንጊዜም ቢሆን ምግብ ይፈለጋል። ይህን ማወቃቸው በዚህ በምዕራብ አፍሪካ ጥሩ የንግድ ችሎታ ያላቸው ሴቶች ትርፍ ለማግኘት የሚያስችላቸው ብዙ የተለያየ መንገድ ፈጥረዋል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች የሕንፃ ግንባታ በሚካሄድባቸው ቦታዎች አጠገብ ትንሽ ዳስ ሠርተው ለሠራተኞቹ ምሳ ያዘጋጃሉ። ሌሎች ማለዳ ወደ ሥራቸው ለሚሄዱ ሠራተኞች ምግብ ያዘጋጃሉ። ትንሽ ጠረጴዛና አግዳሚ ወንበር አስቀምጠው በከሰል ማንደጃ ላይ ውኃ በማፍላት ከትኩስ ዳቦና ቅቤ ጋር እንዲሁም ቡና እያዘጋጁ ቀላል ቁርስ ያቀርባሉ። ምሽት ላይ ደግሞ ወደሚያበስሉበት ቦታ ተመልሰው ከሥራ ለሚመለሱ ሰዎች መክሰስ ያዘጋጃሉ። ይህን ዓይነቱን የምግብ ቤት ንግድ ማካሄድ ከባድ ፕሮግራም የሚጠይቅ ቢሆንም ተግተው ከሠሩ ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን ያስችላቸዋል።
በተጨማሪም ቀላል ምግቦችን ለመሸጥ የሚያስችል አጋጣሚ አለ። አንዳንድ ሴቶች በገበያ አካባቢዎች ሰው የሚበዛባቸውን ቦታዎች ይመርጡና ለውዝ ወይም ኦቾሎኒ ይቆላሉ። ፋታያስ የሚባሉት በትኩስ ወጥ ውስጥ ተጨምረው የሚቀርቡት ትናንሽ የሥጋ ጥብሶችም ቶሎ ቶሎ ይሸጣሉ። ቅመም ካለው የሥጋ ወጥ የሚዘጋጁ ሳንድዊቾችም ቢሆኑ ብዙ ገዥ አላቸው። ሳይውሉ ሳያድሩ የሚሸጡት እንዲህ ያሉት ምግቦች እንደ ጋምቢያና ማሊ ባሉት የአፍሪካ አገሮች በጣም ተፈላጊነት አላቸው።
በጊኒ ቢሳውና በሴኔጋል ቁጥራቸው በዛ ያሉ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ትናንሽ ኬክ ጋግረው በመሸጥ ራሳቸውን እያስተዳደሩ ሙሉ ጊዜ ያገለግላሉ። የሴኔጋል ዋና ከተማ በሆነችው በዳካር የሚኖረው ሞሰስ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “እኔና ባለቤቴ ልጅ መውለድ በጀመርንበት ጊዜ ልዩ አቅኚዎች [የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን] ሆነን እናገለግል ነበር። እነርሱን የማስተዳድርበት ሥራ ማግኘት ነበረብኝ። ትናንሽ ኬኮች አዘጋጅቶ የመሸጥ ሐሳብ መጣልኝ።
“ሥራውን ለመጀመር የሚያስችል በቂ ገንዘብ ስላልነበረኝ ትርፌ ነው ብዬ የማስቀምጠውንና እንደ ዱቄትና እንቁላል የመሰሉትን ዕቃዎች በመግዛት መልሼ ንግዴ ላይ ማዋል የሚኖርብኝን ገንዘብ በጥንቃቄ መለየት ነበረብኝ። አሁን ለትንሹ ቤተሰቤ ከሚያስፈልጉት ነገሮች አብዛኞቹን ለማሟላት የሚያስችለኝን ያህል ኬኮች መሸጥ ችዬአለሁ።
“ባለቤቴ አስቴርም እቤት ሆና ልብስ በመስፋት ትረዳኛለች። ይህም እቤት ውላ ሁለቱን ልጆቻችንን ለመጠበቅ አስችሏታል። የምንኖርበት ዘመን አስቸጋሪ ቢሆንም በዚህ መንገድ ሁለታችንም እየተረዳዳን ቤተሰባችንን በሚገባ ለመንከባከብ ችለናል።”
አነስተኛ ንግድ ለመጀመር የሚያስችል ሌላም ሐሳብ አለ:- ሥራ ላይ የሚውሉ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሥራ ስለሚበዛባቸውና ራቅ ወዳለ ገበያ ሄደው ለመሸመት ጊዜ ስለማያገኙ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን አጠገባቸው ከሚገኙ ጉልቶች ይገዛሉ። እንዲያውም አንዳንድ ባለጉልቶች ሸቀጦቻቸውን ወደ ደንበኞቻቸው ቤት ወስደው ይሸጣሉ። ሐቀኞችና ጥሩ ዕቃ የምትሸጡ መሆናችሁ በፍጥነት ሊሰማ ይችላል። ይሁን እንጂ ዋጋችሁን እንዳታበዙ መጠንቀቅ አለባችሁ። ደንበኞቻችሁ ወደ መደበኛው ገበያ ሊሄዱባችሁ ይችላሉ።
አገልግሎት ሰጪ የሆኑ ሥራዎች
ዕቃ መሸጥ የማያስደስታችሁ ወይም የማይሆንላችሁ ከሆነ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ትችላላችሁ። እንደ ማጽዳት፣ ምግብ ማብሰል፣ ልብስ ማጠብና መተኮስ የመሰሉት ሥራዎች ምን ጊዜም ተፈላጊዎች ናቸው። ሌሎች ብዙ አጋጣሚዎችም አሉ።
ለምሳሌ የምትኖሩት በባሕር አጠገብ ወይም ዓሣ በሚሸጥበት አካባቢ ነውን? ለምን በተቀላጠፈ መንገድና ቀለል ባለ ዋጋ ዓሦቹን ለማጠብ አትጠይቁም? የሚያስፈልጋችሁ ጥሩ ጠፍጣፋ እንጨትና የዓሣ ቢላዋ ብቻ ነው። መኪና ማጠብ ሌላው አትራፊ ሥራ ነው። ለሥራው የሚያስፈልጉ ነገሮች ምንድን ናቸው? ባልዲ፣ ትንሽ ውሃ፣ ሳሙናና ጥሩ ጨርቅ። በዳካር ጥሩ የንግድ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች በሁሉም የመኪና ማቆሚያዎችና ጥላ ባላቸው ብዙ ጎዳናዎች ይህን አገልግሎት ሲሰጡ ይታያሉ።
በምትኖሩበት አካባቢ የቧንቧ ውሃ ማግኘት ያስቸግራልን? አንዳንድ ጊዜ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት በምንጭ ወይም የጋራ መቅጃ በሆኑ ቧንቧዎች አጠገብ ለበርካታ ሰዓት ተሰልፈው ይቆማሉ። ከዚያም ከባድ እንስራ ተሸክመው ወደቤታቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። በዚህ ምክንያት ውሃ ቀድቶ ለሚያመጣላቸው ሰው የአገልግሎቱን ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ የሚሆኑ ብዙ ናቸው። ዘዴው ማለዳ ተነስቶ ውሃውን በዕቃዎች ሞልቶ በእጅ በሚገፋ ወይም በአህያ በሚሳብ ጋሪ መጫን ነው። ከዚህ በኋላ ውሃውን በየቤቱ ወይም በየሥራ ቦታው ለማድረስ ዝግጁ ሆናችኋል ማለት ነው።
መጠነኛ የሆነ መደበኛ ትምህርት አላችሁን? ምናልባት ቅዳሜና እሁድ ትናንሽ ልጆችን ለማስተማር ልትጠይቁ ትችላላችሁ። በታዳጊ አገሮች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እጅግ የተጣበቡ ስለሆኑ ወላጆች ለልጆቻቸው የግል አስተማሪ ለመቅጠር ይፈልጋሉ።
ሌላው ጠቃሚ ችሎታ ሽሩባ መሥራት ነው። ሽሩባ በአፍሪካውያን ሴቶች ዘንድ በጣም የተለመደ የፀጉር አሠራር በመሆኑ ይህ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ተፈላጊዎች ናቸው።
ዘዴኛ መሆን
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ብልሃተኛ ሴት ገቢ የምታገኝባቸውን ዘዴዎች ለማግኘት ትችል ነበር። ምሳሌ 31:24 (የ1980 ትርጉም ) “ልብሶችና ቀበቶዎች እየሠራች ለነጋዴዎች ትሸጣለች” ይላል። በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ሰዎችም በተመሳሳይ የራሳቸውን የጎጆ ኢንዱስትሪ ወይም አነስተኛ ንግድ በማካሄድ የተሳካ ውጤት አግኝተዋል። ለምሳሌ አንድ አናጢ ቀለል ያሉ መቀመጫዎች፣ አግዳሚ ወንበሮችና ሌሎች የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎችን እየሠራ ሊሸጥ ይችላል። ለዚህ ሥራ የሚያስፈልገው በጣም መሠረታዊ የሆኑ የእንጨት ሥራ ዕቃዎች ናቸው። የእርሻ ችሎታ ካላችሁ ደግሞ የዶሮ እርባታ ልትጀምሩና እንቁላልና ዶሮ ልትሸጡ ትችላላችሁ።
አነስተኛ ኢንዱስትሪ ለመጀመር የሚያስፈልገው ዋነኛ ነገር ዘዴኛ መሆን ነው። አንዳንዶች ከተጣሉ ቆርቆሮዎች የሚያምሩ ሣጥኖች ለመሥራት ችለዋል። ሌሎች ደግሞ ከመኪና ጎማ ነጠላ ጫማ ሠርተዋል። አሁንም ሌሎች በመኪና ጎማ ፕላስቲክ የውኃ መቅጃ ባልዲ ሠርተዋል። ዘዴዎቹ በጣም ብዙ ናቸው።
በታዳጊ አገሮች ኑሮን አሸንፎ ለመግፋት ችሎታና ዘዴኛነት የሚጠይቅ ቢሆንም ትዕግሥትና ይቻላል የሚል አመለካከት መያዝም ያስፈልጋል። በቀላሉ ተስፋ አትቁረጡ። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሥራ ለመለወጥና እንደ ሁኔታው ለመሆን ዝግጁዎች ሁኑ። ንግድ ወይም አንድ ዓይነት ሥራ ለመጀመር አስባችሁ ከሆነ ስለ አካባቢው ሕግና ደንብ አስቀድማችሁ አጣሩ። ክርስቲያኖች የአገሩን ሕግ የማክበር ግዴታ አለባቸው።— ሮሜ 13:1–7
አንድ ዓይነት ምርት ወይም አገልግሎት ለማቅረብ ከመሞከራችሁ በፊት ራሳችሁን እንደሚከተለው ብላችሁ ጠይቁ:- ‘በአካባቢው የሚፈለጉት ነገሮችና ልማዶች ምንድን ናቸው? የአካባቢው የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዴት ያለ ነው? ደንበኞቼ የማቀርብላቸውን ነገር ለመግዛት ይችላሉን? የእኔን የመሰለ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚያቀርቡ ምን ያህል ሰዎች አሉ? ይህን ሥራ ለማካሄድ የሚያስፈልገው ችሎታ፣ ጉልበት፣ የግል ተነሳሽነት፣ ፍላጎትና ዝግጅት አለኝን? ለመነሻ ምን ያህል ገንዘብ ያስፈልጋል? መበደር ያስፈልገኛልን? ብድሩንስ መልሼ መክፈል እችላለሁን?’
ኢየሱስ በሉቃስ 14:28 ላይ “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቆጥር ማን ነው?” በማለት ያቀረበው ጥያቄ በዚህ ጉዳይ ላይ አግባብነት ያለው ነው።— ጋደል ባሉ ፊደላት የጻፍናቸው እኛ ነን።
ሁሉ ሰው የራሱን ሥራ ለመፍጠር የሚያስችለው ችሎታም ሆነ ዝንባሌ ሊኖረው እንደማይችል የታወቀ ነው። ሆኖም ትክክለኛ ዝንባሌ ኖሯችሁ የምታደርጉትን ልባዊ ጥረትና የራስ ተነሳሽነት ይሖዋ አምላክ ይባርካል። (ከ2 ጴጥሮስ 1:5 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ ራሳችሁ መፍጠር የሚኖርባችሁ ቢሆን እንኳን ሥራ ለማግኘት የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ!
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልብስ መስፋት፣ መኪና ማጠብ፣ ውሃ መቅዳትና ዓሣ ማጠብ ሰዎች የሚተዳደሩባቸው አንዳንድ መንገዶች ናቸው