‘ቤተሰብ የሚያስፈልገውን ማሟላት’ በታዳጊ አገሮች ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ መወጣት
“ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖትን ከካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” ይህን የተናገረው ሐዋርያው ጳውሎስ ነበረ። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ቤተሰብን የማስተዳደሩ ጉዳይ በበለጸጉት አገሮች ጭምር ከዕለት ወደ ዕለት አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ ሲሆን በታዳጊ አገሮች ደግሞ ጭራሹኑ ሊወጡት የማይችሉት ፈታኝ ኃላፊነት ሆኗል።
ለምሳሌ ያህል በአፍሪካ ውስጥ የኢኮኖሚ ችግር ከመጠን በላይ ተስፋፍቷል። ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ ቢገኝም እንኳ ለቤተሰቡ መደጎሚያ የሚሆን ጥቂት ነገር ለማምጣት ባልም ሚስትም ሁለቱም መሥራት ያስፈልጋቸው ይሆናል። የቤተሰብ ራሶች ሥራ ፍለጋ ከትዳር ጓደኛቸውና ከልጆቻቸው ተለይተው ለወራት ወይም ለዓመታት ራቅ ወዳለ ቦታ መሄድ ይኖርባቸው ይሆናል። በቂ መኖሪያ ቤት ማግኘትም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። አብዛኞቹ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች የቤተሰብ አባሎቻቸው ቁጥር ብዙ ነው፤ በዚህም ምክንያት መኖሪያቸው የተጨናነቀና መሠረታዊ የሆኑት ነገሮች ያልተሟሉለት ይሆናል። ብዙውን ጊዜም ጤና ማጣት ያጠቃቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የአካባቢው ባሕሎች፣ ጥንታዊ የሆኑት ወጎችና በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው አመለካከቶች የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይቃረኑ ይሆናል። ትዳርንና ልጆችን በሚመለከት ከሰፈኑት አመለካከቶች አንዳንዶቹን ልብ በል። አንዳንድ የቤተሰብ ራሶች የእነርሱ ግዴታ የቤት ኪራይና የትምህርት ቤት ወጪዎችን መክፈል ብቻ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ብዙውን ጊዜ እንደ ምግብና ልብስ ያሉትን መሠረታዊ ነገሮች የማሟላቱ ኃላፊነት የሚጫነው በሚስቶችና አንዳንድ ጊዜም በትላልቆቹ ልጆች ላይ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ባሎች “የእኔ ገንዘብ የእኔ ነው፤ የአንቺ ገንዘብ ግን የእኔም ጭምር ነው” የሚል አመለካከት አላቸው። ይህም ብዙውን ጊዜ ሥራ ያላቸውን ሚስቶች ቅር ያሰኛል። አንድ ታንዛኒያዊት ሴት እንዲህ ስትል አማርራለች፦ “ገንዘቡ የሚጠፋው ለእኛ ወይም ለልጆች አንድ ነገር ተደርጎበት ሳይሆን በመጠጥ ነው። ሥራውን የምንሠራው እኩል ነው ወይም የሚበልጠውን እንሠራ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ገንዘቡ የእርሱ እንደሆነ በሌላ አባባል እርሱ እንዳመጣው ይነግረንና ሁሉንም ይወስደዋል።”
ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ከአካባቢው ባሕል ወይም በኅብረተሰቡ ዘንድ በሰፊው ከተለመደው አመለካከት ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጡት ለአምላክ ቃል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ቤተሰብን መንከባከብን በሚመለከት ጠቃሚ መመሪያ ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል “ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውም” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 12:14) በመሆኑም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወንዶች መሥራት እየቻሉ በስንፍና ምክንያት ለቤተሰቡ ምግብና ልብስ የማቅረቡን ኃላፊነት በሚስቶቻቸው ወይም በትላልቅ ልጆቻቸው ላይ አይጥሉም፤ ይህን ኃላፊነት መሸከም ያለበት የቤተሰቡ ራስ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም።—1 ቆሮንቶስ 11:3
የባልየው ገቢ የቤተሰቡን ፍላጎት ሁሉ ለማሟላት በቂ ሳይሆን የሚቀርበት ጊዜ እንደሚኖር አይካድም። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ወንድ ሚስቱ ተቀጥራ ገንዘብ ብታመጣ ቅር አይሰኝም። ከዚህ ይልቅ እንደ ተከበረች “ባልንጀራው” አድርጎ ይይዛታል። (ሚልክያስ 2:14) በመሆኑም እርሷ ላቧን አንጠፍጥፋ ያገኘችውን ገንዘብ ለእርሷ ስሜት ግዴለሽ በመሆን እንዳሻው አያባክነውም። ከዚህ ይልቅ እርሱና ሚስቱ ‘ተመካክረውበት’ ያገኙትን ገንዘብ መላውን ቤተሰብ በሚጠቅም መንገድ በተሻለ ሁኔታ መጠቀም የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይወስናሉ። (ምሳሌ 13:10) አንድ ባል የሚቻል ሆኖ ሲያገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንደነበረችው “ልባም ሴት” ሚስቱ በገንዘብ አጠቃቀም ረገድ የተወሰነ ነፃነት እንዲኖራት ያደርጋል። (ምሳሌ 31:10, 11, 16) በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር መከተል በቤተሰብ ውስጥ ደስታና እርካታ እንዲሰፍን ያስችላል።
ሥራ አጥነት የሚያስከትላቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ማሸነፍ
ሥራ አጥነት የሚያስከትለውን ችግር ተመልከት። በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ብዙ የቤተሰብ ራሶች ሥራ በሚጠፋበትና ክፍያውም ዝቅተኛ በሚሆንበት ጊዜ ሥራ ፍለጋ ከመኖሪያቸው ርቀው ወደሚገኙ የማዕድን ማውጫዎች፣ ፋብሪካዎች፣ የከብት እርባታና የእርሻ ቦታዎች ሄደዋል። አንድ ክርስቲያን ወንድ ተመሳሳይ ሁኔታ ከገጠመው ከመሰል አማኞች ሊለይና ለመጥፎ ባልንጀርነት ሊጋለጥ ይችላል። (ምሳሌ 18:1፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) ቤተሰቡ ችግሮቹን ለመወጣት የቱንም ያህል ቢጥር በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ የሚረዳቸው ወይም የሞራል ድጋፍ የሚሰጣቸው አባት ባለመኖሩ ምክንያት ሊጎዱ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ለረጅም ጊዜ ከቤተሰቡ መለየቱም እንዳሰበው የገንዘብ ችግሩን የሚያቃልል ሳይሆን የሚያባብስ ይሆናል።
አንድ እናት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ወደ ወርቅ ቁፋሮ ሄደ። ዕቅዱ ከአንድ ወር ወይም ግፋ ቢል ከሁለት ወር በኋላ ለመመለስ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ዓመት ሙሉ አልመጣም! ብቻዬን ስድስት ልጆች መንከባከብ ነበረብኝ። በዚያ ላይ ኪራይ መክፈል አለብኝ። ጤና ስላልነበረኝ ለሆስፒታል እገፈግፋለሁ። ልብስ ያስፈልገን ነበር፤ በየዕለቱም ምግብ ያስፈልገናል። ሥራ አልነበረኝም። በጣም ከባድ ነበር። ከሁሉ በላይ ይበልጥ አስቸጋሪ የነበረው ደግሞ የቤተሰብ ጥናት በማድረግ፣ ወደ ስብሰባ በመሄድና በመስክ አገልግሎት በመካፈል በኩል የልጆቹን መንፈሳዊነት መንከባከብ ነው። የሆነ ሆኖ በይሖዋ እርዳታ እንደምንም ተወጣነው።”
አንዳንድ እናቶች እንኳ ሳይቀሩ ሥራ ለመሥራት ሲሉ ቤተሰቦቻቸውን ለረጅም ጊዜ ተለይተው ለመሄድ ተገደዋል። አንዳንዶች ኑሯቸውን የሚገፉት ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በመነገድ ስለሆነ ቤታቸው የሚገኙት ከስንት አንዴ ነው። በዚህም ምክንያት ትላልቆቹ ልጆች ወላጆቻቸው ሊይዙት ይገባ የነበረውን ምግብ የማዘጋጀት፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የማከናወንና ታናናሾቻቸውን የመገሠጹን ኃላፊነት ሳይቀር ይሸከማሉ። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ይዳከማል። አዎን፣ በቤተሰቡ ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ውጥረት እንዲህ እንደዋዛ የሚታይ አይሆንም!
እርግጥ ነው፣ የኤኮኖሚው ሁኔታ በጣም የከፋ ከሆነ አንድ ወላጅ ለቤተሰቡ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ራቅ ወዳለ ቦታ ሄዶ ሥራ መፈለግ ግድ ሊሆንበት ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም የያዕቆብ ልጆች ከግብጽ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማምጣት ሲሉ የግድ ቤተሰባቸውን ትተው መሄድ አስፈልጓቸው እንደነበር ግልጽ ነው። (ዘፍጥረት 42:1-5) ስለዚህ ዛሬም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የቤተሰብ ራሶች ራቅ ብለው ሄደው የሚሠሩት ሥራ ሊያስገኝላቸው የሚችለውን ቁሳዊ ጥቅም ለረጅም ጊዜ መለያየታቸው ከሚያስከትለው መንፈሳዊና ስሜታዊ ጉዳት ጋር በማነፃፀር ጥቅምና ጉዳቱን ማመዛዘን ይኖርባቸዋል። ብዙ ቤተሰቦች ለረጅም ጊዜ ከመለያየት የኤኮኖሚ ችግሩን ችሎ መኖርን ይመርጣሉ። በ1 ጢሞቴዎስ 6:8 ላይ የሚገኙትን “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” የሚሉትን ቃላት ያስታውሳሉ።—ከምሳሌ 15:17 ጋር አወዳድር።
ብዙውን ጊዜ ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ከመጓዝ ይልቅ ሌሎች አማራጮች ይኖራሉ። አንዳንዶች በራሳቸው በመነሣሳትና ብልሃተኛ በመሆን ጠቃሚ አገልግሎት የሚያበረክቱባቸውን ሥራዎች መፍጠር ችለዋል።a (ከምሳሌ 31:24 ጋር አወዳድር።) ወይም ደግሞ ሌሎች ዝቅተኛ እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቷቸውን ሥራዎች በትሕትና የመቀበል ጉዳይ ብቻ ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 4:28) ሐዋርያው ጳውሎስ ገንዘብ ነክ በሆኑ ነገሮች ረገድ ለሌሎች ሸክም ላለመሆን ራሱ “ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት” ይሠራ ነበር። (2 ተሰሎንቄ 3:8) ዛሬም ክርስቲያን ወንዶች ይህን ምሳሌ ሊከተሉ ይችላሉ።
የትምህርት ችግር
ሌላው ችግር ደግሞ ከትምህርት ጋር የተያያዘ ነው። ራቅ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚኖሩ ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ ሲሉ ረዘም ላለ ጊዜ ከእነርሱ ተለይተው ከዘመዶቻቸው ጋር እንዲቆዩ መላካቸው የተለመደ ነገር ነው። ብዙውን ጊዜ ከወላጆቻቸው የተለዩት እነዚህ ልጆች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትም ሆነ በመስክ አገልግሎት በመሳተፍ ረገድ ይዳከማሉ። አስፈላጊውንም ተግሣጽ ስለማያገኙ በቀላሉ በመጥፎ ባልንጀርነት ወጥመድ ይያዛሉ። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ከክርስትና መንገድ ወጥተዋል።
ሰብዓዊ ትምህርት የራሱ ጥሩ ጎኖች እንዳሉት አይካድም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ቅድሚያ የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ትምህርት ሲሆን አምላክ ለልጆቻቸው እንዲህ ዓይነቱን ትምህርት የመስጠቱን ኃላፊነት የጣለው በወላጆች ላይ ነው። (ዘዳግም 11:18, 19፤ ምሳሌ 3:13, 14) ይሁን እንጂ አንድ ልጅ ረዘም ላለ ጊዜ ከወላጆች ርቆ እንዲሄድ ማድረግ ወላጆች እርሱን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያኮላሽ ነው።—ኤፌሶን 6:4b
በአካባቢው ለመማር ያለው አጋጣሚ ጠባብ ከሆነ ወላጆች አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ያክል ለልጆቻቸው መሠረታዊ የሆኑ የእጅ ሙያዎችን ከማስተማር ውጭ ሌላ አማራጭ አይኖራቸው ይሆናል። ‘ታላቁ አስተማሪያችን’ ይሖዋም ይረዳናል። (ኢሳይያስ 30:20 አዓት) በየአካባቢው ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችም በርካታ የትምህርት ዝግጅቶች አሏቸው። ብዙ ጉባኤዎች ማንበብና መጻፍ የማይችሉ አባሎቻቸውን ያስተምራሉ። የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤትም በተመሳሳይ አንድ ልጅ የማንበብና ጥርት አድርጎ የመናገር ችሎታውን እንዲያሻሽል ሊረዳው የሚችል ጠቃሚ ዝግጅት ነው።
ልጅ ስለመውለድ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
በተለይ ልጆች ሲበዙ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ማሟላት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ አፍሪካውያን ወላጆች ልጅ እንደሚወዱ ይናገራሉ፤ ከዚህም የተነሣ የቻሉትን ያህል ብዙ ልጆች ይወልዳሉ! ልጆች የኢኮኖሚ ምንጭ እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩ ቢችሉም እንኳ ብዙ ወላጆች እነዚህ ሁሉ ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት አይችሉም።
እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስም “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው” ይላል። (መዝሙር 127:3) ይሁን እንጂ እነዚህ ቃላት የተጻፉት በእስራኤል ውስጥ የተመቻቸ ሁኔታ በነበረበት ዘመን መሆኑን ልንዘነጋው አይገባም። ከጊዜ በኋላ የከፋ ረሃብና ጦርነት ልጅ መውለድን ፈታኝ አድርጎት ነበር። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:11, 20፤ 4:10) በበርካታ ታዳጊ አገሮች ውስጥ ሰፍኖ ከሚገኘው አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር በኃላፊነት ላይ ያሉ ክርስቲያኖች በትክክል ምን ያህል ልጆች መመገብ፣ ማልበስ፣ በቤታቸው ማኖርና ማሠልጠን እንደሚችሉ በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል። ብዙ ባልና ሚስቶች ወጪአቸውን ካሰሉ በኋላ የአካባቢውን ወግ አለመከተልና የልጆቻቸውን ቁጥር መገደቡ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ይወስናሉ።c—ከሉቃስ 14:28 ጋር አወዳድር።
የምንኖረው “አስጨናቂ” በሆነ ዘመን ላይ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ይህ የነገሮች ሥርዓት ወደማይቀረው ፍጻሜው እያሽቆለቆለ በሄደ መጠን በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች የሚገጥማቸው ተጽዕኖ እንደሚጨምር የታወቀ ነው። ይሁንና የቤተሰብ ራሶች በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ በመከተል የቤተሰቦቻቸውን ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎት በማሟላት ረገድ ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ይሖዋ እርሱን በታማኝነት ለሚያገለግሉት ሁሉ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” ሲል ቃል ገብቷል። (ዕብራውያን 13:5) አዎን፣ ድህነት ባጠቃቸው አገሮች ውስጥም ቢሆን ክርስቲያኖች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር በማሟላት ረገድ የሚገጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ መወጣት ይችላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የዚህ መጽሔት ተጓዳኝ በሆነው የንቁ! መጽሔት የሚያዝያ—ሰኔ 1995 እትም ላይ የወጣውን “በታዳጊ አገሮች ሥራ መፍጠር” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b ተጨማሪ ዝርዝር ሐሳብ ለማግኘት በነሐሴ 15, 1982 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባብያን ጥያቄዎች” አምድ ተመልከት።
c የየካቲት 22, 1993 ንቁ! መጽሔት እትም “የቤተሰብ ምጣኔ በዓለም ዙሪያ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል” በሚል ርዕስ ጠቃሚ ሐሳቦች ይዞ ወጥቷል።