አምላክን በአንድነት የሚያገለግሉ ብዙ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች
መዝሙራዊው “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፣ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው። በኃያል እጅ እንዳሉ ፍላጾች፣ የጎልማስነት ልጆች እንዲሁ ናቸው። ከእነርሱ ዘንድ ምኞቱን የሚፈጽም [“የቀስት መያዣ ኮረጆውን በእነርሱ የሞላ፣” NW] ብፁዕ ሰው ነው” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 127:3-5
አዎን፣ ልጆች ከይሖዋ የተገኙ በረከት ሊሆኑ ይችላሉ። አንድ ቀስት ወንጫፊ በኮረጆው የያዛቸውን ቀስቶች በትክክል መወንጨፍ ሲችል እርካታ እንደሚያገኝ ሁሉ ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዙ ማድረግ ሲችሉ ይደሰታሉ።—ማቴዎስ 7:14
ጥንት በነበሩ የአምላክ ሕዝቦች መካከል ‘ኮረጆዎቻቸው’ በልጆች ‘የተሞሉ’ በርካታ ቤተሰቦች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ግዞተኛ ሆነው በግብፅ አገር ያሳለፏቸውን ዓመታት አስብ:- “የእስራኤልም ልጆች አፈሩ፣ እጅግም በዙ፣ ተባዙም፣ እጅግም ጸኑ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ሞላች።” (ዘጸአት 1:7) ወደ ግብፅ የገቡት እስራኤላውያን ብዛት አገሩን ለቅቀው ከወጡት ጋር ሲነጻጸር አሥር ልጆች ያለው ቤተሰብ መጠነኛ እንደነበር ይጠቁማል!
ኢየሱስ ያደገው ዛሬ ባለው አመለካከት ብዙ ልጆች እንዳሉት በሚቆጠር ቤተሰብ ውስጥ ነው። የበኩር ልጅ የነበረውን ኢየሱስ ጨምሮ ዮሴፍና ማርያም ሌሎች አራት ወንዶች ልጆችና የተወሰኑ ሴቶች ልጆች ነበሯቸው። (ማቴዎስ 13:54-56) ማርያምና ዮሴፍ ከኢየሩሳሌም ለመመለስ ጉዞ ሲጀምሩ ኢየሱስ አብሯቸው አለመኖሩን ሳያስተውሉ የቀሩት በርካታ ልጆች ስለነበሯቸው ሊሆን ይችላል።—ሉቃስ 2:42-46
በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች
በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ቤተሰባቸውን ለመመጠን ወስነዋል። ሆኖም በብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድ ብዙ ልጆች ያሉት ቤተሰብ አሁንም የተለመደ ነው። ዘ ስቴት ኦቭ ዘ ዎርልድስ ችልድረን 1997 እንዳመለከተው ከፍተኛ የመራባት ሂደት የሚታየው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ነው። በእነዚህ አካባቢዎች የምትኖር አንዲት እናት በአማካይ እስከ ስድስት የሚደርሱ ልጆች ትወልዳለች።
ሰፊ ቤተሰብ ያላቸው ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ አድርጎ ማሳደግ ቀላል አይደለም። ሆኖም ብዙዎች ተሳክቶላቸዋል። ልጆችን በማሳደግ ረገድ ስኬታማ ለመሆን ቤተሰቡ በንጹህ አምልኮ የተባበረ መሆን አለበት። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኘው ጉባኤ በላከው ደብዳቤ ውስጥ የሚገኙት ቃላት በዛሬው ጊዜ ላሉ ቤተሰቦችም በእኩል ደረጃ ይሠራሉ። ጳውሎስ “ነገር ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ . . . እለምናችኋለሁ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 1:10) እንዲህ ያለው አንድነት ሊደረስበት የሚችለው እንዴት ነው?
ወላጆች መንፈሳዊ መሆን አለባቸው
አንዱ ቁልፍ ነገር ወላጆች ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደሩ መሆን አለባቸው። ሙሴ ለእስራኤላውያን የተናገራቸውን ቃላት ልብ በሉ:- “እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።”—ዘዳግም 6:4-7
ሙሴ የአምላክ ትእዛዛት በወላጆች ‘ልብ ውስጥ’ መቀመጥ እንዳለባቸው ማመልከቱን ልብ በሉ። ወላጆች ለልጆቻቸው ያልተቋረጠ መንፈሳዊ መመሪያ መስጠት የሚችሉት እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው። እንዲያውም ወላጆች ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ነገሮች በማስተማር ረገድ ትጉዎች የሚሆኑት እነሱ ራሳቸው በመንፈሳዊ ጠንካራ ሲሆኑ ነው።
መንፈሳዊ ሰው ለመሆንና በሙሉ ልብ ይሖዋን ለመውደድ የአምላክን ቃል አዘውትሮ ማንበብ፣ በእርሱ ላይ ማሰላሰልና በሥራ ላይ ማዋል እጅግ አስፈላጊ ነው። መዝሙራዊው በይሖዋ ሕግ ደስ የሚለውና “ቀንና ሌሊት” የሚያነበው “በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 1:2, 3
አንድ ዛፍ ያለማቋረጥ ውኃ ካገኘ ጥሩ ፍሬ እንደሚያፈራ ሁሉ በመንፈሳዊ በሚገባ የተመገበ ቤተሰብም አምላካዊ የሆኑ ፍሬዎችን ያፈራል። ይህም ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣለታል። በምዕራብ አፍሪካ የሚኖረው የኡዋሚግዉ ቤተሰብ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። ኡዋሚግዉ እና ሚስቱ ስምንት ልጆች ያሏቸው ቢሆንም ሁለቱም የዘወትር አቅኚዎች ወይም የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው። ኡዋሚግዉ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ቤተሰባችን ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ያልተቋረጠ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። ልጆቻችንን ከሕፃንነታቸው ጀምረን በቤተሰብ ጥናት ወቅት ብቻ ሳይሆን አገልግሎት በምንወጣበት ጊዜና በሌሎች ጊዜያት የአምላክን ቃል ዘወትር እናስተምራቸዋለን። ልጆቻችን በሙሉ የመንግሥቱ ምሥራች አዋጅ ነጋሪዎች ሲሆኑ የስድስት ዓመት ልጅ ከሆነችው ከመጨረሻ ልጃችን በስተቀር ሁሉም ተጠምቀዋል።”
በቡድን ሆኖ መሥራት
መጽሐፍ ቅዱስ “ቤት በጥበብ ይሠራል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 24:3) እንዲህ ያለው ጥበብ በቤተሰብ ውስጥ በቡድን የመሥራት ሁኔታ ይፈጥራል። የቤተሰቡ የቡድን “አምበል” አባትየው ሲሆን እርሱም በአምላክ የተሾመ የቤት ራስ ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ሐዋርያው ጳውሎስ አንድ የቤት ራስ ያለበት ኃላፊነት ከባድ መሆኑን በመንፈስ ተነሳስቶ ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 5:8
ክርስቲያን ባሎች የአምላክ ቃል ከሚሰጠው ከዚህ ምክር ጋር በመስማማት የሚስቶቻቸውን መንፈሳዊነት መንከባከብ ይኖርባቸዋል። ሚስቶች የቤት ውስጥ ሥራ ከበዛባቸው መንፈሳዊነታቸው ይዳከማል። በአንዲት አፍሪካ አገር የሚኖር በቅርቡ የተጠመቀ አንድ ክርስቲያን ሚስቱ ለመንፈሳዊ ነገሮች ግድ የለሽ መሆኗን ለጉባኤው ሽማግሌዎች ይነግራቸዋል። ሽማግሌዎቹም ሚስቱ ተግባራዊ የሆነ እርዳታ እንደሚያስፈልጋት ነገሩት። ስለዚህም ባልየው የቤት ውስጥ ሥራዎችን አብሯት በመሥራት ያግዛት ጀመር። በተጨማሪም የማንበብ ችሎታዋንና የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቷን እንድታሻሽል በመርዳት አብሯት ጊዜ ያሳልፍ ጀመር። እርሷም ጥሩ ምላሽ በመስጠቷ አሁን መላው ቤተሰብ በአምላክ አገልግሎት አንድ ለመሆን በቅቷል።
በተጨማሪም አባቶች የልጆቻቸው መንፈሳዊነት ሊያሳስባቸው ይገባል። ጳውሎስ “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 6:4) ወላጆች ልጆቻቸውን እንዳያስቆጡ የተሰጣቸውን ምክርም ሆነ እነርሱን እንዲያሠለጥኑ የተሰጣቸውን መመሪያ ሲከተሉ ልጆች የቤተሰቡ ቡድን ክፍል እንደሆኑ ይሰማቸዋል። በውጤቱም ልጆች እርስ በርሳቸው የሚረዳዱና አንዳቸው ሌላውን የሚያበረታቱ ሊሆኑ ይችላሉ።
የቡድን ሥራ የልጆችን እድገት እያዩ መንፈሳዊ ኃላፊነቶች መስጠትንም ያጠቃልላል። አሥራ አንድ ልጆች ያሉት አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ወደ ሥራ ከመሄዱ በፊት ሁልጊዜ ማለዳ እየተነሳ ለሁለት ሦስት ልጆቹ ጥናት ይመራል። ትልልቆቹ ልጆች ከተጠመቁ በኋላ ተራ ገብተው መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማርን ጨምሮ ታናናሽ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ይረዷቸዋል። አባትየው ሁኔታውን በቅርብ በመከተታል ለጥረታቸው ያመሰግናቸዋል። ከልጆቹ መካከል ስድስቱ የተጠመቁ ሲሆን ሌሎቹም ወደ እዚያ ግብ ለመድረስ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
ጥሩ የሐሳብ ግንኙነትና የጋራ ግቦችን ማውጣት
በፍቅር ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግና መንፈሳዊ ግቦችን ማካፈል ለቤተሰብ አንድነት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። በናይጄርያ የሚኖር ጎርደን የተባለ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ከ11 እስከ 27 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰባት ልጆች አሉት። ስድስቱ ልጆች እንደ ወላጆቻቸው አቅኚዎች ናቸው። በቅርቡ የተጠመቀው የሁሉም ታናሽ ከቀሩት የቤተሰቡ አባላት ጋር ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ አዘውትሮ ይካፈላል። በሃያዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ወንዶች ልጆቹ የጉባኤ አገልጋዮች ናቸው።
ጎርደን ለእያንዳንዱ ልጅ በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመራ ነበር። በተጨማሪም መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያካሂድበት ፕሮግራም አለው። በየቀኑ በማለዳ ሁሉም ይሰባሰቡና በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ከተወያዩ በኋላ ለጉባኤ ስብሰባዎች ይዘጋጃሉ።
ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ከወጣው የጋራ ግብ አንዱ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጡትን ትምህርቶች በሙሉ አንብቦ መጨረስ ነው። በቅርቡ ደግሞ በዕለታዊ ፕሮግራማቸው ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አክለውበታል። ባነበቧቸው ነገሮች ላይ በመነጋገር በዚሁ ልማዳቸው መቀጠል ይችሉ ዘንድ አንዱ ሌላውን ያበረታታል።
ሳምንታዊው የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ሁልጊዜ ቋሚ ስለሆነ ማንም ሰው አስታዋሽ አያስፈልገውም፤ እንዲያውም ሁሉም በጉጉት ይጠባበቁታል። ላለፉት በርካታ ዓመታት የቤተሰብ ጥናቱ ይዘት፣ አደረጃጀትና የሚፈጀው ጊዜ እንደ ልጆቹ ዕድሜና ፍላጎት ይቀያየር ነበር። የቤተሰቡ አባላት ከሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ጋር በጣም የሚቀራረቡ ሲሆን ይህም በልጆቹ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል።
በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነው ነገሮችን ያከናውናሉ እንዲሁም ለመዝናኛ የሚሆን ጊዜ ይመድባሉ። ጥያቄ መጠያየቅ፣ አስቂኝ ቀልዶች፣ የፒያኖ ጨዋታ፣ ተረትና ሌሎች አዝናኝ የሆኑ ጨዋታዎችን ያካተተ “የቤተሰብ ምሽት” የሚባል ሳምንታዊ ፕሮግራም አላቸው። አልፎ አልፎም ወደ ባሕር ዳርቻና ማራኪ ወደ ሆኑ ሌሎች ቦታዎች ይሄዳሉ።
በይሖዋ ላይ መደገፍ
ከላይ የቀረቡት ሐሳቦች ብዙ ልጆች ያሉት አንድ ቤተሰብ ማስተዳደር ምንም ችግር እንደሌለው አድርገው የሚገልጹ አይደሉም። አንድ ክርስቲያን “ጥሩ አባት ሆኖ ስምንት ልጆችን ማሳደግ በጣም ተፈታታኝ ነገር ነው” ሲል ተናግሯል። “እነርሱን ለመንከባከብ የተትረፈረፈ ቁሳዊና መንፈሳዊ ምግብ ማቅረብ ይጠይቃል። ቤተሰቤን ማስተዳደር የሚያስችለኝ በቂ ገንዘብ ለማግኘት ጠንክሬ መሥራት አለብኝ። ትልልቆቹ ልጆች በአሥራዎች የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ስምንቱም ተማሪዎች ናቸው። መንፈሳዊ ስልጠና እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ባውቅም አንዳንዶቹ ልጆቼ አስቸጋሪዎችና ዓመፀኞች ናቸው። የሚያደርጉት ነገር ያሳዝነኛል። ይሁን እንጂ እኔም አንዳንድ ጊዜ የይሖዋን ልብ የሚያሳዝኑ ነገሮች ስፈጽም ይቅር እንደሚለኝ አውቃለሁ። ስለዚህ ወደ ልባቸው እስኪመለሱ ድረስ ልጆቼን በትዕግሥት ማስተካከሌን መቀጠል አለብኝ።
“ይሖዋ ሁሉም ሰው ወደ ንስሐ እንዲደርስ እንደሚታገሠን ሁሉ እኔም የእርሱን ምሳሌ ለመከተል እጥራለሁ። ከቤተሰቦቼ ጋር አጠናለሁ፣ ከልጆቼ መካከል አንዳንዶቹ ለመጠመቅ ግብ አውጥተው ወደዚያው እያመሩ ናቸው። ውጤታማ ለመሆን በራሴ ችሎታ ላይ አልመካም። በራሴ ኃይል ላከናውን የምችለው በጣም ጥቂት ነው። በጸሎት ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ‘በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል’ የሚለውን ምሳሌ በሥራ ላይ ለማዋል እጣጣራለሁ።”—ምሳሌ 3:5, 6
ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጡ!
ልጆችን ማሠልጠን አንዳንድ ጊዜ እንዲያው ከንቱ ልፋት ሊመስል ይችላል። ሆኖም ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጡ! በጽናት ወደፊት ግፉ! ለምታደርጉት ጥረት ልጆቻችሁ አሁን ጥሩ ምላሽ ባይሰጡ ወይም አመስጋኝ ባይሆኑ ወደፊት እንደዚያ ሊያደርጉ ይችላሉ። አንድ ልጅ የመንፈስ ፍሬዎችን የሚያፈራ ክርስቲያን እንዲሆን ለማድረግ ረዥም ጊዜ ይወስዳል።—ገላትያ 5:22, 23
በኬንያ የምትኖረው ሞኒካ ከአሥር ልጆች መካከል አንዷ ናት። እንዲህ ትላለች “ወላጆቼ ከሕፃንነታችን ጀምረው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አስተምረውናል። አባባ በየሣምንቱ ከእኛ ጋር ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ያጠናል። በሥራው ጠባይ የተነሳ ጥናቱ በተወሰነ ቀን የሚካሄድ አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ ከሥራ ወደ ቤት ሲመለስ ውጪ ስንጫወት ያገኘንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ በአምስት ደቂቃ ውስጥ እንድንሰባሰብ ይነግረናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በኋላ ጥያቄ እንድንጠይቅ ወይም ማንኛውንም ዓይነት ችግር አንስተን እንድንወያይ ያበረታታን ነበር።
“አምላክን ከሚፈሩ ልጆች ጋር መዋላችንን ይከታተል ነበር። አባባ ስለ ጠባያችን አስተማሪዎችን ለመጠየቅ ሲል ወደ ትምህርት ቤት አዘውትሮ ይሄድ ነበር። በአንድ ወቅት፣ ወደ ትምህርት ቤት መጥቶ በነበረ ጊዜ ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቼ ከሌሎች ልጆች ጋር እንደተደባደቡና አንዳንድ ጊዜም እንደሚያስቸግሩ ሰማ። አባባ መጥፎ ጠባይ በማሳየታቸው ምክንያት ቀጣቸው። ከዚህም በተጨማሪ አምላካዊ የሆነ ጠባይ ማሳየት ያለባቸው ለምን እንደሆነ ጊዜ ወስዶ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሰ አስረዳቸው።
“ወላጆቻችን ከእኛ ጋር የስብሰባ ክፍሎችን በመዘጋጀት በስብሰባዎች ላይ መገኘት ያለውን ጠቀሜታ አሳይተውናል። ቤት ውስጥ በሚደረግ የልምምድ ፕሮግራም ላይ አገልጋይ መሆን የምንችልበትን ሥልጠና ሰጥተውናል። ከሕፃንነታችን ጀምረን ከወላጆቻችን ጋር ወደ መስክ አገልግሎት እንወጣ ነበር።
“ዛሬ ሁለቱ ታላላቅ ወንድሞቼ ልዩ አቅኚዎች ሲሆኑ አንደኛዋ እህቴ ደግሞ የዘወትር አቅኚ ናት። አግብታ ልጆች የወለደችው ሌላኛዋ እህቴ ደግሞ ቀናተኛ ምሥክር ናት። 18 እና 16 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለቱ ታናናሽ እህቶቼ የተጠመቁ አስፋፊዎች ናቸው። ሁለቱ ትንንሽ ወንድሞቼ ሥልጠና በማግኘት ላይ ናቸው። እኔም ኬንያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ማገልገል ከጀመርኩ አሁን ሦስት ዓመት ሆኖኛል። ወላጆቼ መንፈሳዊ ሰዎች በመሆናቸው እወዳቸዋለሁ እንዲሁም አደንቃቸዋለሁ። ጥሩ ምሳሌ ትተውልናል።”
ያሏችሁ ልጆች ብዙም ይሁኑ ጥቂት ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲሄዱ ከመርዳት ፈጽሞ ወደኋላ አትበሉ። ይሖዋ ጥረታችሁን ሲባርክላችሁ ሐዋርያው ዮሐንስ መንፈሳዊ ልጆቹን በማስመልከት “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም” በማለት የተናገራቸውን ቃላት እናንተም ታስተጋባላችሁ።—3 ዮሐንስ 4