የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g95 4/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው የሚወልዱ ወጣቶች
  • አፍሪካን በማውደም ላይ የሚገኘው ኤድስ
  • ለአይሮቢክስ ስፖርት አዘውታሪዎች ማስጠንቀቂያ
  • “አስተማማኝ ወሲብ”፣ ለሴቶች ግን ላይሆን ይችላል
  • ቴሌቪዥን በማይገኝበት ደሴት የሚኖሩ ልጆች
  • በሽተኞች የሚፈጽሙት ወሲባዊ ጥቃት
  • የጃንደረቦች ኑፋቄ
  • በጉዞ ላይ በምትሆኑበት ጊዜ ጥንቃቄ አድርጉ
  • ወንጀል የሚያስከትለው ኪሣራ
  • ማር ለሆድ ዕቃ ቁስል?
  • የኤድስ መድኃኒት በቅርብ ጊዜ ይገኛል ተብሎ አይታሰብም
  • አንግሊካን ቄሶችና ሰው ሠራሽ የሆነው አምላካቸው
  • ጾታዊ ትንኮላን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2000
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—2005
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1999
  • ብዙዎች በፍርሃት የሚኖሩት ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2005
ንቁ!—1995
g95 4/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው የሚወልዱ ወጣቶች

ፖፑሊ የተባለው የተባበሩት መንግሥታት የሕዝብ ጉዳይ ድርጅት መጽሔት በየዓመቱ በመላው ዓለም ከ15 ሚልዮን የሚበልጡ ከ15 እስከ 20 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች ልጅ እንደሚወልዱ ገምቷል። ይህ ግምት ከ15 ዓመት በታች የሆኑትን ሴቶችና የሚያስወርዱትን አይጨምርም። በአፍሪካ ብቻ 28 በመቶ የሚያክሉት ሴቶች የሚወልዱት 18 ዓመት ሳይሞላቸው ነው። በዚህች አህጉር በአፍላ ወጣትነት ዕድሜ የሚያረግዙ ሴቶች ቁጥር እየበዛ ከሄደባቸው ምክንያቶች መካከል ስለ ጾታ ጉዳዮች በቂ እውቀት አለማግኘት፣ አለዕድሜ ማግባት፣ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ወጣት ሴቶች በዕድሜ የሚበልጧቸው ባለጠጋ ወንዶች ቅምጥ ለመሆን መፈተናቸው እንደሆነ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች በወሊድ ምክንያት የመሞታቸው ዕድል ከ20–34 ዕድሜ ከሚገኙት ሴቶች በእጥፍ የሚበልጥ ከመሆኑም ሌላ የሚወልዷቸው ልጆችም የመሞት አጋጣሚያቸው በጣም ከፍተኛ ነው” ሲል ፓፑሊ ዘግቧል።

አፍሪካን በማውደም ላይ የሚገኘው ኤድስ

በዓለም የጤና ድርጅት ግምት መሠረት በመላው ዓለም በኤድስ እንደተያዙ ከሚታወቁት ከ15 ሚልዮን ከሚበልጡ ሰዎች መካከል 10 ሚልዮን የሚያክሉት የሚገኙት በአፍሪካ ውስጥ ነው። ይህም በኤድስ በመጠቃት ረገድ አፍሪካ ከዓለም አህጉራት በሙሉ በአንደኛ ደረጃ እንድትገኝ አድርጓታል። ፕሮፌሰር ናታን ክሉሜክ ይህን የኤድስ ወረርሽኝ ለማስወገድ በመደረግ ላይ ስለሚገኘው ጥረት ሲናገሩ “ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የሚሄድን ጎርፍ ለመገደብ አነስተኛ የአሸዋ ክምር እንደመጨመር ይቆጠራል” ብለዋል። ፕሮፌሰር ክሉሜክ ለ ሞንድ ለተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የአፍሪካ ርዕሳነ ብሔሮች ቫይረሱ በአፍሪካ ላይ ሊያስከትል ስለሚችለው ውድመት ሙሉ በሙሉ የተገነዘቡ አይመስልም ብለዋል። ፕሮፌሰር ክሉሜክ በ1987 ከአህጉሪቱ ነዋሪዎች 10 በመቶ የሚሆኑት በኤድስ እንደሚለከፉ በገመቱ ጊዜ ብዙዎች ከልክ በላይ የተጋነነ ግምት መስሏቸው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ከአፍሪካ ሕዝቦች መካከል ከ20 እስከ 40 በመቶ የሚደርሱት በዚህ ቀሳፊ ቫይረስ እንደሚለከፉ ተገምቷል።

ለአይሮቢክስ ስፖርት አዘውታሪዎች ማስጠንቀቂያ

የለንደኑ ታይምስ መጽሔት “ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚጠይቁ የአይሮቢክስ እንቅስቃሴዎችን የሚያዘወትሩ ሰዎች” የጆሯቸው ውስጠኛ ክፍል ሊጎዳባቸው እንደሚችል ሪፖርት አድርጓል። ለበርካታ ጊዜያት በተደጋጋሚ የሚደረግ ጠንከር ያለ ዝላይ በውስጠኛው የጆሮ ክፍል በሚገኙት ጥንካሬ የሌላቸው ሕዋሶች ላይ ትልቅ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ግልጽ ነው። በዚህ ምክንያት የሚደርሰው ጉዳት ከሚያስከትላቸው የሕመም ስሜቶች መካከል ማዞር፣ ሚዛን መጠበቅ አለመቻል፣ የማቅለሽለሽ ስሜትና የጆሮ ጩኸት ይገኝበታል። በቅርቡ በቀን ሁለት ጊዜ ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ የአይሮቢክስ ስፖርት በሚያስተምሩ ሴቶች ላይ በተደረገ ጥናት 83 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ እርግብግቦሽ ያላቸውን ድምፆች የመስማት ችግር እንዳለባቸው ተደርሶበታል። ሌላው አሳሳቢ ነገር ደግሞ አንዳንድ ሴቶች ጠንከር ያለ “አካላዊ እንቅስቃሴ የማድረግ” ሱስ ያደረባቸው መሆኑ ነው። ዘ ታይምስ እንዳለው ይህ ዓይነቱ ሱስ የያዛቸው ሴቶች “ጡንቻዎቻቸው ዝለው እስከ መዝለፍለፍና አጥንታቸው እስከ መሰበር ይደርሳል። ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ የሚለማመዱ ከሆነ ደግሞ ሚዛናቸውን የመጠበቅ ችግር ያጋጥማቸዋል።”

“አስተማማኝ ወሲብ”፣ ለሴቶች ግን ላይሆን ይችላል

ስለ “አስተማማኝ ወሲብ” ብዙ የተነገረና በኤድስ ላለመያዝ በኮንዶም መጠቀም በጣም ጥሩ ዘዴ እንደሆነ ብዙ የተባለ ቢሆንም ዶክተሮች የዚህ ዓይነቱን ምክር ጠቃሚነት መጠራጠር ጀምረዋል። ለ ፊጋሮ በተባለ አንድ የፖሪስ ጋዜጣ ላይ የወጣ የሕክምና ሪፖርት ኮንዶም ወንዶችን እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ በኤድስ ከመያዝ ሊከላከልላቸው ቢችልም የኮንዶም ውጫዊ ክፍሎች ኤድስ በተያዘ የወሲብ ጓደኛ በቀላሉ ሊበከሉ ስለሚችሉ ለሴቶች የሚሰጠው መከላከያ በጣም አነስተኛ ነው። በተጨማሪም ሴቶች በተለይ በወር አበባቸው ወቅትና ማንኛውም ዓይነት የአባለ ዘር በሽታ ወይም ፈሳሽ በሚኖራቸው ጊዜ በኤድስ የመያዝ ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ ኮንዶም ሴቶችን ከኤድስ ለመጠበቅ ያለው ችሎታ ከ69 በመቶ ያነሰ ሆኗል። አንድ ዶክተር የኮንዶም የመከላከል ችሎታ “አስተማማኝነቱ” አነስተኛ ስለመሆኑ ሲናገሩ “በዓመት ውስጥ ሳይጋጭ በደህና የማረፍ ዕድሉ 69 በመቶ ብቻ ስለሆነ አውሮፕላን ምን ለማለት እንችላለን?” ብለዋል።

ቴሌቪዥን በማይገኝበት ደሴት የሚኖሩ ልጆች

በምዕራብ አፍሪካና በደቡብ አሜሪካ መካከል በሚገኘው ውቅያኖስ ከምዕራብ አፍሪካ በአንድ ሦስተኛ ርቀት ላይ በምትገኘው ሴይንት ሔለና በተባለች ደሴት ላይ የሚኖሩ ልጆች “በዓለም ከሚኖሩ ልጆች በሙሉ ሚዛኑን የጠበቀ ባሕርይ ያላቸው” እንደሆኑ ዘ ታይምስ የተባለው የለንደን ጋዜጣ ሳፖርት ፎር ለርኒንግ የተባለው እውቅ የትምህርት መጽሔት ያቀረበውን ሪፖርት እንደ ዋቢ በመጥቀስ ገልጿል። የሪፖርቱ ጸሐፊ የሆኑት ዶክተር ቶኒ ቻርልተን ከ9 እስከ 12 በሚደርስ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት የደሴቲቱ ልጆች መካከል ከበድ ያለ የባሕርይ ችግር ያለባቸው 3.4 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እንደሆኑ ተገንዝበዋል። ይህ ቁጥር “እስከዛሬ ድረስ በማንኛውም የዓለም ክፍል በማንኛውም የዕድሜ ክልል ከተመዘገበው በጣም ያነሰ” እንደሆነ ዘ ታይምስ ገልጿል። ይህን የመሰለ ሚዛናዊ ባሕርይ ያላቸው ልጆች ሊኖሩ የቻሉበት ምክንያት ምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ልጆቹ ከፍተኛ ጥራት ያለው ትምህርት በቀላሉ የሚያገኙ መሆናቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ቻርልተን አንድ ሌላ ምክንያት ለመመርመር እቅድ አላቸው። አንድ የሳተላይት መቀበያ ጣቢያ እስከተሠራበት ቅርብ ጊዜ ድረስ በደሴቲቱ ላይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም የሚያስተላልፍ ጣቢያ አልነበረም። በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት በደሴቲቱ ከሚኖሩት 1, 500 ቤተሰቦች 1, 300 የሚያክሉት የራሳቸው ቴሌቪዥን እንደሚኖራቸው ይገመታል። ቻርልተን በዚህ ምክንያት በደሴቲቱ ልጆች ላይ የሚደርሰውን የባሕርይ ለውጥ ማጥናት ይጀምራሉ።

በሽተኞች የሚፈጽሙት ወሲባዊ ጥቃት

አንድ በቅርቡ የተደረገ ጥናት በሥራ ቦታ ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ መዳፈር ለብዙ ሴት ሐኪሞች አሳሳቢ ችግር እየሆነባቸው እንደመጣ ገልጧል። ዘ ሜዲካል ፖስት እንደገለጸው በዚህ ጥናት ጥያቄ ቀርቦላቸው መልስ ከሰጡት ሴት ሐኪሞች 77 በመቶ የሚሆኑት “ከበሽተኞች አንድ ዓይነት ወሲባዊ መዳፈር እንደተሰነዘረባቸው ተናግረዋል።” ብዙዎች የዚህ ችግር መፍትሔ በራሳቸው በዶክተሮች እጅ የሚገኝ እንደሆነ ያምናሉ። በሥራቸውና በሞያ ግዴታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ፣ በሽተኞችን በሚያክሙበት ጊዜ የሥራ ጋውን እንዲለብሱና የጋብቻ ቀለበታቸውን እንዲያደርጉ ይመክራሉ። ሌሎች ደግሞ በሴት ዶክተሮች ላይ የሚሰነዘረውን ወሲባዊ መዳፈር ማስወገድ የሚቻልበት መንገድ የለም ይላሉ። ፖስት “ሴት ዶክተሮች ወሲባዊ መዳፈርና በዚህም ምክንያት የሚፈጠረው ሥጋት በሴቶች ላይ የነገሠበት ማኅበረሰብ ክፍል ናቸው” በማለት ይህንን አመለካከት አንጸባርቋል።

የጃንደረቦች ኑፋቄ

ኢንድያን ኤክስፕሬስ የተባለው የቦምቤ ጋዜጣ በሕንድ አገር ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ጃንደረቦች እንዳሉ ሪፖርት አድርጓል። ከእነዚህ መካከል ጃንደረባ ሆነው የተወለዱት ከ2 በመቶ ያነሱ ናቸው። የቀሩት የተሰለቡ ናቸው። ኤክስፕሬስ ጋዜጣ እንደዘገበው ጥሩ መልክ ያላቸው ወንድ ልጆች ተታልለው ወይም ተጠልፈው በሕንድ አገር ከሚገኙት በርካታ የጃንደረቦች መፍጠሪያ ካምፖች ወደ አንዱ ይወሰዳሉ። በዚያም ልጆቹ “መስፍናዊ አያያዝ” የሚጨምር ሥርዓተ አምልኮ ከተፈጸመላቸው በኋላ የአባለ ዘራቸው ፍሬ እንዲወጣ ይደረጋል። ከዚያ በኋላ አዲሱ ጃንደረባ በዕድሜ ከፍ የሚል ሌላ ጃንደረባ ልጅ እንዲሆን ይደረግና በመካከላቸው “የእናትነትና የሴት ልጅነት” ዝምድና ይፈጠራል። እነዚህ ጃንደረቦች የሴት ስም የሚሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ከዚያ በኋላ ጠባያቸውም ሆነ አለባበሳቸው ልክ እንደ ሴት ይሆናል። አብዛኞቹ ጃንደረቦች በተለያዩ አማልክት ሥር በኑፋቄዎች ይደራጃሉ። በሕንድ አገር ጃንደረቦች በየዓመቱ በሚደረጉ በዓሎች የሚከበሩባቸውና መለኮታዊ እንደሆኑ ተቆጥረው የሚመለኩባቸው በርካታ ቤተ መቅደሶች አሉ።

በጉዞ ላይ በምትሆኑበት ጊዜ ጥንቃቄ አድርጉ

ጉዞ በምታደርጉበት ጊዜ ነቃ ብላችሁ በአካባቢያችሁ የሚሆነውን ነገር መከታተል ይኖርባችኋል። በብራዚል አገር የሚታተመው ክለውዲያ መጽሔት “የሻንጣ ሌቦችና ኪስ አውላቂዎች ምንጊዜም ሐሳባቸው የተከፋፈለባቸውን መንገደኞች ይመርጣሉ” ይላል። በተመሳሳይም “አንድ ሰው ቢገጫችሁ ወይም ልብሳችሁ ላይ አንድ ነገር ቢያፈስ ተጠንቀቁ። እነዚህ ድርጊቶች ሰዎችን ለማዘናጋት የሚደረጉ ናቸው።” በተጨማሪም አንድ ሰው አንድ ነገር እንድትነግሩት ወይም እንድትረዱት ሲጠይቃችሁ ጠንቀቅ በሉ። ለአንድ አፍታ እንኳን ትኩረታችሁ ከተወሰደ ሻንጣችሁ ሊሰረቅባችሁ ይችላል። የሳኦ ፓውሎ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባልደረባ የሆኑት አድሪያኖ ካሌይሮ እንደተናገሩት ከሆነ ሻንጣችሁን በአውሮፕላን ጣቢያዎች ለማስፈተሽ በምታቀርቡበት ጊዜ፣ በመኪና መከራያ ቦታዎች ወረቀቶች በምትፈርሙበት ጊዜ፣ የሆቴል ክፍል በምትይዙበት ወይም ለቃችሁ በምትሄዱበት ጊዜ፣ ልጆች ታክሲ ውስጥ በምታስገቡበት ጊዜ፣ በሱቆች መስኮት ሆናችሁ ዕቃ በምታዩበት ጊዜ፣ ወይም ቡና በምትጠጡበት ጊዜ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባችኋል። ይኸው መጽሔት ቁልፋችሁ ከተሰረቀባችሁ ወዲያው ቁልፉን እንድታስለውጡ ያስጠነቅቃል። ሌባው የጠፋባችሁን ሻንጣ እንዳገኘላችሁ ሊነግራችሁና የተወሰደባችሁንም በሙሉ መልሶ ሊሰጣችሁ ይችላል። ይሁን እንጂ ቆየት ብሎ ሙሉ ቤታችሁን ለመመዝበር እንዲያስችለው ሌላ ተመሳሳይ ቁልፍ አሠርቶ ይሆናል።

ወንጀል የሚያስከትለው ኪሣራ

ዘ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ በዘገበው መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ 163 ቢልዮን ዶላር በወንጀል ምክንያት ትከስራለች። ይህ ጋዜጣ ለገንዘብ ዋጋ መቀነስ ተገቢ ማስተካከያ ከተደረገ በኋላ እንኳን ይህ ገንዘብ በ1965 ከወጣው በአራት እጥፍ እንደሚበልጥ ዘግቧል። ጋዜጣው በወንጀል ምክንያት የሚደርሰውን ኪሣራ እንደሚከተለው ይተነትናል። “በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ደረጃ ለፖሊሶች ከ31.8 ቢልዮን ዶላር በላይ፣ ለወንጀለኞች ማረሚያ 24.9 ቢልዮን ዶላር፣ በችርቻሮ ንግድ ለሚደርሱ ኪሳራዎች 36.9 ቢልዮን ዶላር፣ በተጭበረበረ ኢንሹራንስ ምክንያት 20 ቢልዮን ዶላር እንዲሁም በግለሰቦች ላይ በሚደርስ የንብረት ጥፋትና የሕክምና ወጪ ምክንያት 17.6 ቢልዮን ዶላር ይወጣል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ግለሰቦች ራሳቸውን ከወንጀል ለመጠበቅ ለሚያደርጉት መከላከያ 15 ቢልዮን ዶላር፣ ለፍርድ ቤት ወጪዎች 9.3 ቢልዮን ዶላር፣ ለአቃቤ ሕጎችና ለተከላካይ ጠበቆች 7.2 ቢልዮን ዶላር ይወጣል።” ፖስት በወንጀል ምክንያት የሚደርሰውን ኪሣራ በምሳሌ ሲያስረዳ በዋሽንግተን ዲ ሲ አካባቢ በአንድ ሰው ላይ ጥይት ቢተኮስ ከተኩሱ በኋላ ባሉት ጥቂት ሰዓቶች ብቻ ቁስለኛውን ለማከም በአማካይ 7, 000 ዶላር ወጪ ይሆናል። ቁስለኛው ከሞት ከተረፈ ወጪው እስከ 22, 000 ዶላር ይደርሳል። መንግሥት ተኳሹን ሰው አሳድዶ ለመያዝና ለፍርድ ለማቅረብ ሙከራ ቢያደርግ ወንጀለኛውን በእስር ቤት ለማቆየት በየዓመቱ 22, 000 ዶላር ወጪ ያደርጋል።

ማር ለሆድ ዕቃ ቁስል?

ዶክተር ቤሲል ጄ ኤስ ግሮጎኖ በካናዳ ሜዲካል ፖስት ጋዜጣ ላይ ሲጽፉ በአንጀትና በጨጓራ ቁስል ለሚሠቃዩ በሽተኞች ከአነስተኛዋ ፍጥረት ከንብ የሚገኘው ማር ባለፉት ዘመናት ሐኪሞች ያከናውኑት ከነበረው ቀዶ ሕክምና የተሻለ ጥቅም ሳያስገኝ አይቀርም ብለዋል። ብዙ ሊቃውንት ሄሊኮባክተር ፓይሎሪ የምትባለው በዓይን የማትታይ በጣም አነስተኛ ፍጥረት የአንጀትና የጨጓራ ቁስል በማምጣት ረገድ የምታበረክተውን የሥራ ድርሻ መገንዘብ እንደጀመሩ ገልጸዋል። አንዳንዶች ይህችን ሚክሮብ በመድኃኒት መዋጋት እንደሚገባ ቢናገሩም እነዚህ መድኃኒቶች ሌላ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከመሆናቸውም በላይ ሚክሮቦቹ የራሳቸውን መከላከያ ሠርተው ሊቋቋሙት እንደሚችሉ ግሮጎኖ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ግን በቅርቡ በጆርናል ኦቭ ዘ ሮያል ሶሳይቲ ኦቭ መዲሲን ላይ የወጣን ማር ባክቴሪያዎችን ለመግደል ያለው ኃይል የተሞከረበትን አንድ ጥናት ጠቅሰዋል። በኒው ዚላንድ ከሚገኝ ማኑካ የተባለ ተክል ከተመገቡ ንቦች የተገኘ ማር አልሰር አምጭ የሆነውን ሚክሮብ የመግደል ችሎታ እንዳለው ታውቋል።

የኤድስ መድኃኒት በቅርብ ጊዜ ይገኛል ተብሎ አይታሰብም

አምና በነሐሴ ወር በጃፓን አገር ተደርጎ የነበረው 10ኛው ዓለም አቀፍ የኤድስ ጉባኤ ኤድስን የሚከላከል ክትባት ወይም ከበሽታው የሚፈውስ መድኃኒት ለመሥራት የተደረገው ጥረት በአብዛኛው ውድቅ እንደሆነ ገልጿል። እስከዚህ አሥርተ ዓመት መጨረሻ ድረስ ይገኛል ተብሎ አይታሰብም። በአትላንታ፣ ጆርጅያ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ጀምስ ኩራን “አሁን የምንገኘው በዓለም የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ መጀመሪያ ላይ ነው” ብለዋል። በመላው ዓለም 17 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በበሽታው እንደተለከፉ የተነገረ ሲሆን ይህ ቁጥር ከአምናው በ3 ሚልዮን ይበልጣል። ከእነዚህ መካከል አንድ ሚልዮን የሚያክሉት ሕፃናት መሆናቸው ያሳዝናል። የበሽታው መዛመት በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ በ2000 ዓመት ከ30 እስከ 40 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በበሽታው እንደሚያዙ የዓለም ጤና ድርጅት ገምቷል። የኤድስ በሽታ ምልክቶች ሙሉ በሙሉ የታዩባቸው ሰዎች ቁጥር በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ 60 በመቶ ጨምሯል። ይህም እስከ 1994 አጋማሽ ድረስ ያለውን ቁጥር፣ የሞቱትን ጨምሮ ወደ አራት ሚልዮን ከፍ አድርጎታል። አንድ ሰው በኤች አይ ቪ ቫይረስ በተለከፈበትና የበሽታው ምልክቶች ሊታይበት በጀመረበት ጊዜ መካከል እስከ አሥር ዓመት የሚደርስ ጊዜ ሊያልፍ ይችላል። ይህን እየጨመረ የሄደውን ወረርሽኝ ለመግታት የሚደረገው ጥረት በጣም አዝጋሚ ከመሆኑ የተነሣ ይህ የኤድስ ጉባኤ በየዓመቱ መሆኑ ቀርቶ በየሁለት ዓመቱ እንዲደረግ ተወስኗል። የሚቀጥለው ስብሰባ በሐምሌ ወር በ1996 በቫንኩቨር ከተማ በብሪትሽ ኮሎምቢያ ካናዳ አገር እንዲደረግ ፕሮግራም ወጥቷል።

አንግሊካን ቄሶችና ሰው ሠራሽ የሆነው አምላካቸው

በቅርቡ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አንድ ቄስ አባራለች። ይህ ቄስ በዓይን የማይታይ ሁሉን ቻይ አምላክ ስለመኖሩ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ስለመሆኑና ኢየሱስ አዳኝ ስለመሆኑ ጥርጣሬ የሚያሳድር ትምህርት በይፋ ይሰብክ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችና የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርቶችን በግልጽ የሚቃወም ሰው እንደሆነ ቢታወቅም የእርሱ መባረር የሌሎች ቄሶችን ተቃውሞ አስነስቷል። ሰባ አምስት የሚያክሉ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ይህ ሰው በቅስና ሥራው እንዲቀጥል የሚጠይቅ ማመልከቻ ፈርመዋል። አንዳንድ ቄሶች ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት መካከል በዓይን የማይታይ ሁሉን ቻይ አምላክ መኖሩን የማያምኑ በመቶ የሚቆጠሩ ቄሶች እንዳሉ ይናገራሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ