የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 10/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አሰልቺ ሥራ ጤናን ያቃውሳል
  • ከቤት እንስሳት ጋር መወዳጀት ለጤና ይበጃል?
  • የውኃ ሀብት መመናመን
  • ንዴት ማብረጃ
  • አስመሳይ ለማኝ
  • የወፍ አንጎልና እንቅልፍ
  • ምንም ጥቅም የለውም
  • መንገደኞች የሚሰማቸውን የወገብ ሕመም መቀነስ
  • በሕፃናት ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ በደል ትኩረት እያገኘ መጥቷልን?
  • “የባቤል ግንብ”
  • ፈገግታ ማሳየትን መማር
  • ሰውነትህ እንቅልፍ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—1995
  • በዛሬው ጊዜ ያለው ሥነ ምግባር ምን ይመስላል?
    ንቁ!—2000
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1994
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1995
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 10/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

አሰልቺ ሥራ ጤናን ያቃውሳል

ጀርመን በሚኖሩ 50,000 ሠራተኞች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው ብዙ ነገር የማይጠይቅ ቀላል ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ሥራ ከሚበዛባቸው ሰዎች ይልቅ ለሕመም የተጋለጡ ናቸው። ኦግስበርገ አልጌማይነ የተባለው ጋዜጣ እንደገለጸው “ድግግሞሽ የበዛበት ሥራ የሚሠሩና በሌሎች ጫንቃ ላይ ተደግፈው የሚሠሩ ሠራተኞች የመታመም አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ጥሮሽ የሚጠይቅ ሥራ ከሚሠሩ ሠራተኞች ከሁለት እጥፍ በላይ እንደሆነ” ተረጋግጧል። ብዙ ነገር የማይጠይቅ ቀላል ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞችን ያክል ከሥራ ጋር በተያያዘ ውጥረት በተደጋጋሚ ለረዥም ጊዜ ከሥራ ገበታው የሚቀር ሠራተኛ የለም። በዘገባው መሠረት ሥራቸው ብዙም ጥረት የማይጠይቅባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ “በደም ግፊት፣ በጨጓራና በአንጀት እንዲሁም በጀርባና በመገጣጠሚያ አካላት ሕመም ይሠቃያሉ።”

ከቤት እንስሳት ጋር መወዳጀት ለጤና ይበጃል?

“አንድ ሰው ከቤት እንስሳት ጋር መወዳጀቱ የሐኪም ቤት ደንበኛ እንዳይሆን ሊረዳው ይችላል” በማለት ዘ ቶሮንቶ ስታር ተናግሯል። ባለፈው አሥርተ ዓመት የተካሄዱ በርካታ ጥናቶች እንዳመለከቱት “የእንስሳት ወዳጆች የሚሰማቸው ውጥረት አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ለምርመራም ወደ ሐኪም ዘንድ የሚሄዱት አልፎ አልፎ ነው። ሌላው ቀርቶ ከድንገተኛ የልብ ድካም ሕመም ማገገም የሚችሉበት አጋጣሚ የሰፋ ሆኖ ተገኝቷል። አንድ እንስሳ በስትሮክ ሳቢያ የታመሙ ሰዎች ኃይላቸው እንዲታደስና የአእምሮ ሕመምተኛ የሆኑት ደግሞ ከጭንቀታቸው ማረፍ እንዲችሉ ሊረዳ ይችላል። እንስሳት ሰዎችን ያዝናናሉ። የሰዎቹ ትኩረት በእንስሳቱ ላይ ያርፋል፤ አዘውትረውም ይደባብሷቸዋል” ሲሉ በኢንዲያና አሜሪካ የሚገኘው የፐርዱ የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አለን ቤክ ተናግረዋል። እንስሳው ቤተሰቡ የሚያሳድገው ባይሆንም እንኳ እንዲህ ያለው ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። በዚህም የተነሳ “በእንስሳት የሚታገዝ ሕክምና” የመስጠት ሥራ እንዲጀመር በር ከፍቷል። በመሆኑም አንዳንድ የአእምሮ ጤና ባለ ሙያዎች የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ከእንስሳት ጋር ጊዜ እንዲያሳልፉ ያበረታቱ ሲሆን ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።

የውኃ ሀብት መመናመን

“በአሁኑ ወቅት በነፍስ ወከፍ ሊደርሰን የሚችለው የውኃ መጠን ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ከነበረው በግማሽ ያነሰ ነው” በማለት ዘ ዩኔስኮ ኮሪየር ገልጿል። እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ያለው የውኃ መጠን እየቀነሰ እንደሚሄድ ይጠበቃል። የውኃው መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ እያደገ ባለው የሕዝብ ብዛት፣ በግብርናው መስክ ያለው ፍላጎት በመጨመሩና በኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ሳቢያ ጨው አልባ ውኃ የማግኘት ፍላጎት ማሻቀቡን የሚያመለክት ነው። የውኃ እጥረት ያለበትን አካባቢ በካርታ የሚያመለክቱ ሳይንቲስቶች አንዳንድ አካባቢዎችን “አደገኛ” በማለት ሰይመዋቸዋል። እንደ ኮሪየር አባባል ይህ ማለት በአሁኑ ወቅት በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የውኃ መጠን “እንደ ድርቅ ያለ ከፍተኛ ቀውስ በሚከሰትበት ጊዜ አንድን ሕዝብ ጠብቆ የሚያኖር አይመስልም።” አክሎም “የዛሬ 50 ዓመት በዓለም ላይ ከፍተኛ የውኃ ችግር የገጠመው አንድም አገር አልነበረም። ዛሬ 35 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በእንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ ይገኛል።”

ንዴት ማብረጃ

“ንዴትን ለማብረድ ተብሎ እንደ ትራስ ወይም አሸዋ የተሞሉ ጆንያዎች ያሉ ግዑዝ ነገሮችን በቡጢ መደብደብ የጠበኝነትን ባሕርይ ከማባባስ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም” በማለት የካናዳው ናሽናል ፖስት ዘግቧል። በአዮዋ ግዛት ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ብራድ ጄ ቡሽማን “የታመቀን ስሜት የማስወጫ ዘዴ በጥናታዊ ጽሑፎች ካገኘው ድጋፍ ይበልጥ በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ያልተቋረጠ ድጋፍ አግኝቷል” ሲሉ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ “ግዑዝ የሆኑ ነገሮችን በቡጢ በመደብደብ ንዴትን ማብረድ ጥሩ ዘዴ እንደሆነ አድርገው የሚናገሩ መጻሕፍትና አምዶች ሰዎች ራሳቸውን እንዳይገዙ በር በመክፈት የጠብ አጫሪነትን ጠባይ ሊያባብሱ እንደሚችሉ” ተመራማሪዎች የደረሱበት መሆኑን ፖስት ገልጿል።

አስመሳይ ለማኝ

በሕንድ በሚታተም ዘ ዊክ የተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ዘገባ እንደገለጸው ብዙዎቹ ለማኞች ምንም የሌላቸው ምስኪኖች ቢሆኑም አንዳንዶቹ ግን እንደዚያ አይደሉም። ማሃራሽትራ በሚባል በአንድ የሕንድ ግዛት በምርኩዝ የሚሄድ አንድ ለማኝ የትራፊክ መብራት ወዳስቆመው ወደ አንድ መኪና ጠጋ ብሎ መለመን ጀመረ። የመኪናው አሽከርካሪ ለማኙን ችላ ብሎ ከሴት ጓደኛው ጋር ማውራቱን ቀጠለ። ስለዚህ ለማኙ ድምፁን ከፍ አድርጎ መለመኑን ቀጠለ። በዚህ ጊዜ የመኪና አሽከርካሪው መስኮቱን ወደ ታች ዝቅ አድርጎ ለማኙን ሲገፈትረው የያዘው ሳንቲም ተበተነ። “ሽባው” ለማኝ ድንገት ጤነኛ ሆኖ በያዘው ምርኩዝ የመኪናውን የፊት መስተዋት መሰባበር ጀመረ። “ወደ ሌሎች መኪናዎች ሄደው ይለምኑ የነበሩ ‘ዓይነ ስውር፣’ ‘አንካሳ’ እና ‘ሽባ’ የሆኑ ጓደኞቹ እርሱን ለማገዝ ድንገት ግልብጥ ብለው መጡና” ድንጋይ፣ ዱላና ምርኩዝ መወርወር ጀመሩ። በመጨረሻም ወጣቱን ሰው ከመኪናው ውስጥ ጎትተው አወጡት በማለት ዘ ዊክ ተናግሯል። አጋጣሚ አንድ የፖሊስ መኪና በቦታው በመድረሱ ለማኞቹ እግሬ አውጪኝ ብለው አምልጠዋል።

የወፍ አንጎልና እንቅልፍ

በቶሮንቶ ስታር ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደገለጸው ወፎች ራሳቸውን ከአዳኞቻቸው ለመጠበቅ ሲሉ አንድ ዓይናቸውን ገልጠው እንደሚተኙ ከታወቀ ሰነባብቷል። አሁን የተገኙ የምርምር ውጤቶች እንደሚያሳዩት ወፎች አንጎላቸው ሙሉ በሙሉ እንዲተኛ ማድረግ ወይም አንድ ዓይናቸውን ገልጠው ለመተኛት ግማሹን የአንጎላቸውን ክፍል ንቁ ለማድረግ ይችላሉ። በረድፍ በተኙ ዳክዬዎች ላይ የተደረገ ምርምር እንዳረጋገጠው በረድፉ መጨረሻ ላይ የተኙት ዳክዬዎች ሦስት አራተኛውን የእንቅልፍ ጊዜያቸውን ያሳለፉት ግማሽ አንጎላቸውን ንቁ አድርገው ነው። በረድፉ መካከል ላይ ያሉት በከፊል ንቁ የነበሩት ከጠቅላላው የእንቅልፍ ሰዓታቸው መካከል 12 በመቶውን ብቻ ነበር። “ወፎች በአደገኛ አካባቢ በሚሆኑበት ወቅት ብዙውን ጊዜ የሚተኛው ከፊሉ አንጎላቸው ብቻ” ሳይሆን እንደማይቀር የኢንዲያና ግዛት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ኒልስ ራተንቦርግ ተናግረዋል።

ምንም ጥቅም የለውም

“ማጨስ ሰዎች ቀጠን ያለ ሰውነት እንዲኖራቸው አይረዳቸውም” በማለት የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ባርክሌይ ዌልነስ ሌተር ሪፖርት አድርጓል። “በተለይ ብዙ ወጣት ሴቶች ሰውነታቸው ቀጭን እንዲሆንላቸው በማሰብ ሲጋራ ማጨስ ጀምረዋል።” ይሁን እንጂ ከ18 እስከ 30 ዓመት ዕድሜ ባላቸው 4,000 ሰዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው “ሰዎቹ አጨሱም አላጨሱ በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ (በዓመት በአማካይ በግማሽ ኪሎ ግራም) ውፍረት መጨመር የተለመደ ነገር ነው።” አምዱ ሲደመድም “ማጨስ ውፍረትን ለመቆጣጠር የሚሰጠው ጥቅም የለም። ምንም ጥቅም አይሰጥም።”

መንገደኞች የሚሰማቸውን የወገብ ሕመም መቀነስ

ከባድ የወገብ ሕመም ያለባቸው መንገደኞች ጉዞ ማድረግ ሊከብዳቸው ይችላል። ሆኖም ዘ ቶሮንቶ ስታር የሚከተሉትን ጠቃሚ ሐሳቦች ይለግሳል:- በእግር ስትሄዱ “ምቹ ጫማ አድርጉ። ረዥም ተረከዝ ያለው ጫማ ሰውነታችሁን ስለሚያናጋው በአከርካሪ አጥንታችሁ ላይ ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል። . . . በመኪና የምትጓዙ ከሆነ አልፎ አልፎ መኪናችሁን አቁማችሁ ተንጠራሩ እንዲሁም ወዲያ ወዲህ ተንሸራሸሩ። . . . ደገፍ የምትሉበት ትራስ ነገር ከጀርባችሁ አድርጋችሁ” ተቀመጡ። በተጨማሪም አልፎ አልፎ እየተሸራሸህ ተቀመጥ። ሻንጣ በመሸከም የሚደርሰውን ሕመም ለመቀነስ ይቻላል፤ ምክንያቱም ስታር እንደገለጸው “ሻንጣዎችን ተሸክሞ ከመውሰድ ይልቅ ተሽከርካሪ ጎማ ያላቸው በቀላሉ እየተጎተቱ የሚወሰዱ በተለያየ መጠንና ቅርጽ የተዘጋጁ ሻንጣዎች ማግኘት ይቻላል። ሻንጣዎችህ ላይ ያለው መጎተቻ በቂ ርዝመት ያለው መሆን አለበት። አጫጭር መጎተቻ ያላቸውን ሻንጣዎች የምትጠቀም ከሆነ ለወገብህ ብዙም የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።”

በሕፃናት ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ በደል ትኩረት እያገኘ መጥቷልን?

በካራካስ የሚታተመው ኤል ዩኒቨርሳል የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በቬንዙዌላ በጾታ የሚነወሩ ልጆች ቁጥር በእጅጉ ያደገ ሲሆን በ1980 በፆታ የተነወሩት ልጆች ቁጥር በአማካይ ከአሥር አንድ ብቻ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከአሥር ልጆች መካከል ሦስቱ ይነወራሉ። በ1980 የጥቃቱ ሰለባ የነበሩት ልጆች አማካይ ዕድሜ ከ12 እስከ 14 ዓመት ነበር። አሁን ግን ይበልጡን ተጠቂ የሆኑት ከሦስት ዓመት በታች የሆኑት ናቸው። እንዲህ ያለውን ሰቅጣጭ ወንጀል በዋነኛነት የሚፈጽሙት እነማን ናቸው? ልጆች በሚማሩበት ትምህርት ቤት አካባቢ ልጆችን በከረሜላ አታልሎ ለመውሰድ አድፍጠው የሚጠብቁ ማንነታቸው የማይታወቅ ሰዎች ናቸው የሚለው ሐሳብ ፈጽሞ እውነትነት የለውም። ኤል ዩኒቨርሳል ሲያብራራ 70 በመቶ የሚሆኑት ዘመዶች ወይም የቤተሰብ ወዳጆች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የእንጀራ ወላጆች ሲሆኑ የቀሩት ደግሞ እንደ ታላቅ ወንድም፣ የአጎት ወይም የአክስት ልጅ ወይም አስተማሪ ያሉ በጥቅሉ ሲታይ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች ናቸው።

“የባቤል ግንብ”

የአውሮፓ ሕብረት (EU) 11 ይፋዊ ቋንቋዎች ሲኖሩት ወደፊት ደግሞ ሌሎች 10 ቋንቋዎች ይጨመሩ ይሆናል በማለት ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቡን የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ዘግቧል። የአውሮፓ ሕብረት ሥራ አስፈጻሚ አካል የሆነው የአውሮፓ ኮሚሽን የተባበሩት መንግሥታት ዋና መሥሪያ ቤት ካሉት አራት እጅ የሚበልጡ የጽሑፍና የቃል ተርጓሚዎች ቀጥሯል። የተባበሩት መንግሥታት ዋና መሥሪያ ቤት የሚጠቀምባቸው ይፋዊ ቋንቋዎች አምስት ብቻ ናቸው። አውሮፓን አንድ ለማድረግና የአውሮፓ ሕብረት የሚያስፈጽማቸውን ጉዳዮች ለማቅለል ጥረት በመደረግ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት ቋንቋን በተመለከተ ከዚህ ተቃራኒ የሆኑ ሁኔታዎች በመከሰት ላይ ናቸው። እያንዳንዱ አባል አገር የራሱን ቋንቋ ለማስከበር ይሯሯጣል። “የባቤል ግንብ በማንሰራራት ላይ ነው” በማለት ጋዜጣው አስተያየቱን ሰጥቷል። በተጨማሪም ኮሚሽኑ “ዩሮስፒክ” በሚባለው በውስጡ በሚነገረው እንግዳና ለመረዳት አዳጋች በሆነ ቋንቋ ሳቢያ ችግር ገጥሞታል። አንድ ተርጓሚ እንደተናገረው የፖለቲካ ሰዎች “ብዙውን ጊዜ ዋነኛ ዓላማቸው አሻሚና አደናጋሪ በሆነ መንገድ መናገር ስለሆነ” ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲናገሩ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው።

ፈገግታ ማሳየትን መማር

ደንበኞችን በጥሩ ሁኔታ የማስተናገድ ባሕል አላት በምትባለው በጃፓን ኩባንያዎች “ይበልጥ ወዳጃዊ መንፈስ ማሳየት የሚቻልበትን መንገድ መማር ይችሉ ዘንድ ወደ ትምህርት ቤቶች የሚልኳቸው ሠራተኞች” ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ አሳሂ ኢቭኒንግ ኒውስ ዘግቧል። “ኩባንያዎች ፈገግታ፣ ሳቅና ጨዋታ የቀዘቀዘውን ገበያ ሞቅ ለማድረግ የሚያስችል ብዙ ወጪ የማይጠይቅና ውጤታማ የሆነ ዘዴ ነው የሚል እምነት አላቸው።” በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች መስታወት ፊት ተቀምጠው “ይበልጥ ማራኪ በሆነ መንገድ ፈገግታ ማሳየት የሚቻልበትን መንገድ ለመማር” ልምምድ ያደርጋሉ። በጣም ስለሚወዱት ሰው እንዲያስቡ ምክር ይሰጣቸዋል። አስተማሪዎቹ፣ ተማሪዎቹ ዘና እንዲሉና ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ፈገግ እንዲሉ ለመርዳት ይጥራሉ። አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ በተጨማሪ ዘወትር ፈገግታ ማሳየትን በሚገባ የሠለጠኑ ሠራተኞች ወደሚሠሩባቸው ቀለል ያሉ ምግቦች ወደሚዘጋጁባቸው ምግብ ቤቶች ሄደው የደንበኞችን ትእዛዝ እንዲቀበሉ ያደርጋሉ። ፈገግታ ማሳየት ገበያን ሞቅ ያደርጋል? ጋዜጣው እንዳለው ከሆነ ከ3,000 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞቹ ፈገግታ ማሳየትን መለማመድ የሚችሉባቸውን ኮርሶች እንዲወስዱ ያደረገ አንድ የውበት መጠበቂያ ቅባቶች ኩባንያ የምርት ሽያጩ በዚያው ዓመት 20 በመቶ እድገት አሳይቷል። አንዲት ሠራተኛ ኮርሱ በቢሮዋ ውስጥ ያለውን ሁኔታም እንደለወጠው ገልጻለች። “ፈገግታ ከሚነበብባቸው ጥሩ አለቆች ጋር መሥራት ያስደስታል” ብላለች።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ