ከዓለም አካባቢ
ለበሽተኞች በሚሰጥ ደም ላይ የተፈጸመ ቅሌት
ከማንኛውም አገር የበለጠ ደምና የደም ውጤቶች የሚወሰዱባት ጀርመን “በዓለም ከሚገኙ በጣም አስተማማኝ የሕክምና ተቋሞች አንዱ የሆነውን ድርጅት የትችት ዒላማ” ባደረገ ቅሌት ተናውጣለች ሲል ሱድዶቸ ሳይቱንግ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ቅሌቱ የተገኘው ለዓመታት መጠኑ በርካታ የሆነ ትክክለኛ ምርመራ ያልተደረገለት ደም ለሆስፒታሎች ሲሸጥ በቆየ የደምና የደም ውጤቶች አቀነባባሪ ኩባንያ ላይ ነው። በዚህም ምክንያት በእነዚህ የደም ውጤቶች የተጠቀሙ በሺህ የሚቆጠሩ የሆስፒታል ታካሚዎች ለኤች አይ ቪ ቫይረስ ተጋልጠዋል። የፌዴራሉ መንግሥት የጤና ሚኒስቴር የሆኑት ሆርስት ዚሆፈር “የቀዶ ጥገና ሕክምና በተደረገለት ጊዜ በተበከለ ደም ወይም በፕላዝማ ተዋጽኦ አማካኝነት በኤች አይ ቪ አለመለከፉን ለማረጋገጥ የሚፈልግ ማንም ሰው” ምርመራ እንዲያደርግ መክረዋል። ዲ ሳይት እንደዘገበው “ከጠቅላላው ሕዝብ 71 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ለሕክምና በሚሰጥ ደም አማካኝነት ኤድስ ይይዘኝ ይሆናል በሚል ስጋት ውስጥ ወድቆአል።”
ለቃጠሎ የተጋለጡ የሐሩር አካባቢ ጫካዎች
በኢንዶኔዥያ፣ በምሥራቅ ካሊሚንታን 3.5 ሚልዮን ሄክታር የሚያክል ስፋት ያለው ደን ከ1983 እስከ 1991 በነበሩት የድርቅ ዓመታት ወድሟል። ከዚህ ይበልጥ አስደንጋጭ የሆነው ግን በአማዞን በሚገኙ የእርጥብ ሐሩር ደኖች ላይ የሚደርሰው ቃጠሎ ነው። ለምን? በወትሮው የደኑ ቅርንጫፎችና ቅጠሎች ከሥር ያለውን እርጥብ አየር አምቀው ስለሚይዙ የአየሩ እርጥበት እሳት እንዳይቀጣጠል ያግድ ነበር። ባለፉት አምስት ዓመታት ግን ማንቸስተር ጋርዲያን ዊክሊ እንደዘገበው ዛፍ ቆራጮች ምርጥ የሆነውን ማሆገኒ የተባለ ዛፍ ፈልገው ለመቁረጥ ሲሉ በምሥራቅ አማዞን ደን ውስጥ በርካታ መንገዶችን በመሥራታቸው ምክንያት የአየሩ እርጥበት መሸሽ ጀምሯል። ዛፎቹ ከተቆረጡ በኋላ መሬት ላይ ተረብርበው የሚቀሩት ቅርንጫፎችና ቅጠሎች መቃጠላቸው ደኑን ለአደጋ የተጋለጠ እንዲሆን አድርጎታል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው 2 በመቶ የሚሆኑትን ዛፎች ብቻ መቁረጥ 56 በመቶ የሚሆነውን የደን ሽፋን ያወድማል። የብራዚል ገበሬዎች ከትላልቆቹ ዛፍ ግርጌ እስከ አምስት ኪሎ ሜትር የሚደርስ የእሳት ነበልባል እንደተመለከቱ ሪፖርት አድርገዋል።
የሚጥሚጣ ወዳጆች
ሚጥሚጣ የሚበሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ሚጥሚጣ መብላት የማይወዱ ብዙ ሰዎች ሚጥሚጣ የምግቦችን የተፈጥሮ ጣዕም ያሳጣል ብለው ያምናሉ። የሚጥሚጣ ወዳጆች ግን ከዚህ የባሰ ውሸት ሊኖር አይችልም ይላሉ። ሪደርስ ዳይጀስት መጽሔት እንዳለው በቅርቡ ስለ ሚጥሚጣ የተጻፈ አንድ መጽሐፍ ሚጥሚጣ ከአፍ የቅምሻ ሴሎች ጋር ተዋሕዶ የሴሎቹን ጣዕም የመለየት ችሎታ የሚጨምር ሽታ አልባ ኬሚካል እንዳለው ገልጿል። ሚጥሚጣ ለጤንነት ይጠቅማል የሚሉም አሉ። አንድ ያልበሰለ ሚጥሚጣ ከአንድ ብርቱካን የበለጠ ቪታሚን ሲ አለው። እስካሁን ከታወቁት የሚጥሚጣ ዝርያዎች ሁሉ በጣም የሚያቃጥለው በዩካታን ሜክሲኮ የሚገኘው ሃባኔሮስ የተባለው ዝርያ ነው። ሃባኔሮስ የበላ ሰው ጭንቅላቱ ከሌላው የሰውነቱ ክፍል የተለያየ ይመስለዋል ይባላል። ይሁን እንጂ ምንም ቢያደርጋቸው መብላታቸውን የማይተው ሰዎች አሉ።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለአንዲት የይሖዋ ምሥክር ፈረደላት
ከአራት ዓመት በፊት አንዲት በፍሎሪዳ ዩ ኤስ ኤ የምትኖር የይሖዋ ምሥክር ሐኪሞች በቀዶ ጥገና ሊያዋልዷት ሲሞክሩ በርካታ ደም ፈስሷት ነበር። ሐኪሞችዋ ሕይወትዋን ለማትረፍ ደም መስጠት እንደሚያስፈልግ ተሰማቸው። ታካሚዋ ግን በሃይማኖታዊ እምነትዋና በሕሊናዋ ምክንያት ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ አልሆነችም። የአካባቢው ፍርድ ቤት ባስቻለው አስቸኳይ ችሎት የሚያክሟት ሐኪሞች አስፈላጊ መስሎ ከታያቸው ከታካሚዋ ፈቃድ ውጭ ደም ሊሰጧት እንደሚቻል በየነ። ዋናው የክርክር ነጥብ ታካሚዋ ብትሞት ልጆችዋ አላሳዳጊና ተንከባካቢ ይቀራሉ የሚል ነበር። የፍሎሪዳ አውራጃ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም ይህን ብይን አጽድቆታል። በመጨረሻም ጉዳዩ ለፍሎሪዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበ። ይህ ፍርድ ቤት በጊዜው ደርሶ ያልተፈለገውን ደም የመስጠት ሕክምና ለማስቆም ባይችልም የሁለቱን የበታች ፍርድ ቤቶች ብይን ሽሮ የምሥክርዋን አቋም የሚደግፍ ብይን አስተላልፏል። የፍሎሪዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወላጅነት “በራሱና ብቻውን አንድ ሰው በሚያምንበት እምነት መሠረት እንዳይኖር ሊከለክለው አይችልም” ብሏል። ፍርድ ቤቱ በዚህ ብያኔው የታካሚዋን የሃይማኖት ነፃነትና በአካልዋ ላይ ስለሚደረጉ ነገሮች የመወሰን መብትዋን አረጋግጦላታል።
የጭንቀት ስሜት ጨምሯል
“በጠቅላላው 43,000 ለሚያክሉና በዘጠኝ አገሮች ለሚኖሩ ሰዎች ቃለ መጠይቅ ተደርጎ የተገኘ የአሥራ ሁለት ነፃ ጥናቶች ውጤት በ20ኛው መቶ ዘመን ውስጥ በብዙዎቹ የዓለም ክፍሎች ከባድ የሆነ የጭንቀት ስሜት እየጨመረ መጥቷል ከሚል መደምደሚያ ላይ የደረሰውን ቀደም ያለ የአሜሪካ ጥናት ውጤት እውነተኝነት አረጋግጧል” በማለት ዘ ሃርቫርድ ሜንታል ኸልዝ ሌተር ዘግቧል። ይህ “ከ1905 እስከ 1955 የተወለዱትን ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች በየተወለዱበት አሥር ዓመት ከፋፍሎ በመመደብ” የተደረገ ጥናት “በቅርብ ዓመታት የተወለዱ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በአንድ ወቅት በጭንቀት ስሜት የመዋጣቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ሆኖ እንደተገኘ አሳይቷል።” በዚህ መቶ ዘመን የከባድ ጭንቀት ስሜት በጣም የጨመረ መሆኑን ብዙ ጥናቶች አረጋግጠዋል።
የሕፃናትን ጤንነት መጠበቅ
“በታዳጊው ዓለም የሚኖሩ 230 ሚልዩን የሚያክሉ ለትምህርት ዕድሜ ያልደረሱ ሕፃናት ወይም 43 በመቶ የሚያክሉ ሕፃናት በቂ ምግብ ባለማግኘት ወይም በበሽታ ምክንያት በደረሰባቸው የአመጋገብ ጉድለት የተነሣ እድገታቸው ቀጭጯል” ይላል አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዜና መግለጫ። በ1993 አራት ሚልዮን የሚያክሉ ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ወይም የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘታቸው ለከፋ በሽታ ስላጋለጣቸው እንደ ሞቱ ይገመታል። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? የዓለም የጤና ድርጅት የሚከተለውን ምክር ይሰጣል። “ሁሉም ሕፃናት ከአራት እስከ ስድስት ወር ዕድሜያቸው ጡት ብቻ ይጥቡ። ከዚያም በኋላ ቢሆን ከሁለት ዓመት በላይ እስኪሆናቸው ድረስ ተስማሚና በቂ የሆነ ተጨማሪ ምግብ እየተሰጣቸው ጡት መጥባት ይኖርባቸዋል።” እናቶችና የጤና አጠባበቅ ሠራተኞች ጡት የሚጠቡ ሕፃናት እድገት እንደ ዘገየ በመገመት ቸኩለው ከጡት የተለየ ሌላ ምግብ መስጠት እንዳይጀምሩ ይመከራሉ። ይህን ማድረግ ለሕፃኑ አደገኛ ነው። በተለይ የሚሰጠው ምግብ በተሐዋስያን የተበከለና በምግብነቱ ዝቅተኛ ከሆነ ሕፃኑን ለተመጣጠነ ምግብ ጉድለትና ለበሽታ ይዳርገዋል።
ጉንዳኖች መንገዳቸውን የሚያውቁት እንዴት ነው?
ጉንዳኖች መንገዳቸውን የሚያውቁት እንዴት ነው? ብዙዎቹ በመጡበት መንገድ ላይ የኬሚካል አሻራ እየተው ያልፉና ሲመለሱ ያንኑ አሻራ ተከትለው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ። ይሁን እንጂ በስዊዘርላንድ የዙሪክ ዩንቨርስቲ ዙዎሎጂስት የሆኑት ዶክተር ሩዲገር ቨህነር በሰሃራ በረሃ የሚኖሩ ጉንዳኖች እንዴት መንገዳቸውን እንደሚያገኙ ተደንቀዋል። ምክንያቱም በሰሃራ በረሃ ያለው የፀሐይ ትኩሳት ጉንዳኖቹ የሚተውትን የኬሚካል አሻራ በደቂቃ ውስጥ አትንኖ ያደርቀዋል። ዶክተር ቨህነር በቴክሳስ ዩኒቨርስቲ ባደረጉት ንግግር የምድረ በዳ ጉንዳኖች በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት አንዳንድ አውሮፕላኖች እንደተጠቀሙበት በመሰለ የበረራ ዘዴ እንዴት እንደሚጠቀሙ አስረድተዋል። ጉንዳኖቹ ወደ ሰማይ ያንጋጥጡና በሰው ዓይን ሊታዩ የማይችሉና የሚርገበገቡ የብርሃን ጨረሮችን ቅርጽ ይመለከታሉ። ራሳቸውን ከጨረሩ ቅርጽ ጋር ለማላመድ ከተሽከረከሩ በኋላ በቀጥታ ወደ ቤታቸው ተመልሰው መጓዝ ይጀምራሉ። ዘ ዳላስ ሞርኒንግ ኒውስ “በሰሜናዊው የሰሃራ በረሃ በጠራራ ፀሐይ መንገድ ቢጠፋብህ አቅጣጫህን እንድታመላክትህ ጉንዳንን ጠይቅ” በማለት ቀልዷል።
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት
አንድ በቅርቡ የተደረገ ጥናት 16 ዓመትና ከዚያም በላይ ከሆናቸው ካናዳውያን ሴቶች መካከል 51 በመቶ የሚያክሉት ቢያንስ በሕይወታቸው ውስጥ አንድ ጊዜ ከወንዶች ጥቃት እንደ ደረሰባቸው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል ገልጿል። ይህም ከአምስት ሚልዮን የሚበልጡ ሴቶች ማለት ነው። ይህ የካናዳ ጋዜጣ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ሴቶች መካከል ግማሽ የሚያህሉት ጥቃት የደረሰባቸው “ከወንድ ጓደኞቻቸው፣ ከባሎቻቸው፣ ከወዳጆቻቸው፣ ከቤተሰባቸው አባሎችና ከሌሎች በቅርብ የሚያውቋቸው ወንዶች” እንደሆነ ዘግቧል። ጥናት ከተደረገባቸው ሴቶች መካከል አሥር በመቶ የሚያክሉት ጥቃት የደረሰባቸው ባለፈው ዓመት ነው። ከአምስት ጥቃቶች አንዱ አካላዊ ጉዳት እስከ ማድረስ የከፋ ነበር። ብዙ ሴቶች በባሎቻቸው ወይም በኑሯቸው ባጋጠሙአቸው ሌሎች ወንዶች እንደ ተገፈተሩ፣ እንደ ተጎተቱ፣ እንደ ተመናጨቁ፣ በጥፊ እንደ ተመቱ፣ እንደ ተረገጡ፣ እንደ ተነከሱና እንደ ተደበደቡ ሪፖርት አድርገዋል።
በዓመፅ አንደኛ የሆነች አገር
“ከመላው ዓለም በዓመፅ አንደኛ የሆነችው አገር ዩናይትድ ስቴትስ ነች” በማለት ጋዜጠኛው አን ላንደርስ ጽፈዋል። “በ1990 በሽጉጥ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በአውስትራልያ 10፣ በታላቋ ብሪታንያ 22፣ በካናዳ 68 ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ግን 10,567 ነበር።” በጦር መሣሪያ ብዛትም ቢሆን የአንደኛነቱን ቦታ ይዛለች። የዚህች አገር ሕዝቦች ያላቸው 200 ሚልዮን የሚያክል ጠመንጃ ሲሆን 255 ሚልዮን ለሚያክለው የአሜሪካ ሕዝብ ለእያንዳንዱ አንድ ጠመንጃ ሊደርሰው ምንም ያህል አይቀርም። በዓመፁ ትምህርት ቤቶችም ሳይነኩ አላለፉም። ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል 20 በመቶ የሚያክሉት አንድ ዓይነት መሣሪያ ይይዛሉ። በየዓመቱ በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ ወይም አጠገብ ሦስት ሚልዮን የሚያክሉ ወንጀሎች ይፈጸማሉ። በየቀኑ 40 የሚያክሉ አስተማሪዎች ሲደበደቡ 900 መቶ የሚያክሉት የዱላ ዛቻ ይደርስባቸዋል። ብሔራዊ የትምህርት ማኅበር እንዳለው 100,000 የሚያክሉ ተማሪዎች በየቀኑ ሽጉጥ ይዘው ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ። በየቀኑ በአማካይ 40 የሚሆኑ ልጆች በጦር መሣሪያ ይገደላሉ ወይም ይጎዳሉ። የአእምሮ ጤና ብሔራዊ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ጆን ኢ ሪችተርስ “ለዓመፅ ያለን ቸልተኝነት በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው። ትምህርት ቤቶችም የዚህ ቸልተኝነት ነጸብራቆች ናቸው” ብለዋል። አንድ የእንግሊዝኛ መምህር የ12ኛ ክፍል ተማሪዎቹ ድርሰት እንዲጽፉ አዝዞ ትእዛዙን የፈጸሙት 10 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ብቻ ሲሆኑ “በጣም የምወደው የጦር መሣሪያ” በሚል ርዕስ እንዲጽፉ በጠየቃቸው ጊዜ ግን ሁሉም ተማሪዎች ጽፈውለታል።
ራስን በራስ የመግደል መመሪያ መጽሐፍ
ዘ ኮምፕሊት ማንዋል ኦቭ ሱሳይድ (የተሟላ ራስን በራስ የመግደል መመሪያ መጽሐፍ) የተባለው መጽሐፍ በጃፓን አገር ከፍተኛ ሽያጭ ያገኘ መጽሐፍ ሆኗል። ለብዙ ሰዎች መሞትም ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። መጽሐፉ ከፉጂ ተራራ ግርጌ የሚገኘው 2,500 ሄክታር ስፋት ያለው የአኦኪጋርሃ ጫካ ራስን ለመግደል በጣም አመቺ ቦታ እንደሆነ ይናገራል። ይህ መጽሐፍ ታትሞ በወጣ የሦስት ወር ጊዜ ውስጥ በአኦኪጋርሃ ጫካ ሁለት አስከሬኖች ተገኝተዋል። በሁለቱም እጅ መጽሐፉ ተገኝቷል። ሌላ ራሱን ለመግደል ያሰበ ሰው ደግሞ መጽሐፉን ይዞ በዚሁ ጫካ ውስጥ ሲባዝን ተይዟል። እስከ ጥቅምት ወር 1993 ድረስ በአኦኪጋርሃ ራሳቸውን የገደሉ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት በ50 በመቶ ጨምሯል። ይሁን እንጂ የመጽሐፉ ደራሲ በተፈጸሙት ራስን የመግደል ወንጀሎችና በመጽሐፉ መካከል ምንም ዓይነት ዝምድና መኖሩን ክደዋል። “በዚህ መጽሐፍ ራስን መግደልን እንደ አንድ ምርጫ አድርጌ በማቅረብ ሕይወት ይበልጥ ቀላል እንዲሆን ሞክሬአለሁ” ብለዋል።
በማንበብ መደሰት
ዘ ቶሮንቶ ስታር በቅርቡ 2.9 ሚልዮን የሚያክሉ ጎልማሳ ካናዳውያን “በዕለታዊ ኑሮአቸው የሚያጋጥሟቸውን ጽሑፎች” ለማንበብ የማይችሉ መሆናቸውን ጥናቶች እንዳመለከቱ ዘግቧል። መሐይምነትን ለመዋጋት ሲባል “የማንበብን ፍቅርና አስደሳችነት” የሚያበረታታ የካናዳ ሕፃናት መጻሕፍት ሳምንት ተከብሯል። በዚህ ሙዚቃ፣ ቴሌቪዥንና ቪድዮ በተስፋፋበት ዘመን ልጆችን ማንበብ እንዲወዱ ማስተማር ቀላል ሆኖ አልተገኘም። ቁልፉ ልጆች ገና ሕፃናት ሳሉ ጀምሮ ማስተማርና ትኩረታቸውን የሚከፋፍሉባቸውን ነገሮች ማስወገድ ነው። ጋዜጣው ወላጆቿ ቴሌቪዥናቸውን ያስወገዱ አንዲት የአሥር ዓመት ልጅ “ማንበብ በጣም የሚያስደስት ከመሆኑም በላይ አዳዲስ ነገሮችን እንድማር ያስችለኛል” ስትል እንደተናገረች ጠቅሷል። አንድ የአሥር ዓመት ልጅ ደግሞ “የፈለግኩትን ሁሉ ለማየት እንደሚያስችለኝ መስኮት ስለሆነ ማንበብ በጣም እወዳለሁ” ብሏል።