በሩዋንዳ በደረሰው ሰቆቃ ለተጎዱት ሰዎች እንክብካቤ ማድረግ
በአፍሪካ እምብርት የምትገኘው ሩዋንዳ “የአፍሪካ ስዊዘርላንድ” ተብላ ትጠራ ነበር። በዚህች አገር የአየር ክልል ላይ በአውሮፕላን የሚያልፉ ሰዎች ልምላሜዋን ለመመልከት ስለሚችሉ የዔደንን ገነት መስላ ትታያቸዋለች። ሩዋንዳ ገነት ነች ሲባል መቆየቱ አያስደንቅም።
በአንድ ወቅት ላይ አንድ ዛፍ ሲቆረጥ በምትኩ ሁለት ዛፍ ይተከል ነበር። በዓመቱ ውስጥ አንድ ሙሉ ቀን ለዛፍ ተከላ ይመደብ ነበር። በየአውራ ጎዳናዎች ዳርና ዳር የፍራፍሬ ዛፎች ተተክለዋል። በአገሪቱ በሙሉ በነጻነትና በቀላሉ መዘዋወር ይቻል ነበር። የተለያዩትን ክፍላተ ሀገራት ዋና ከተማ ከሆነችው ከኪጋሊ ጋር የሚያገናኙት ዋና ዋና ጎዳናዎች በአስፋልት የተነጠፉ ነበሩ። የዋና ከተማይቱ እድገት በጣም ፈጣን ነበር። አብዛኛው ሠርቶ አደር ከወር እስከ ወር የሚያደርሰው ገቢ ያገኝ ነበር።
በሩዋንዳ ይካሄድ የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴም ቢሆን ከፍተኛ እድገት በማሳየት ላይ ነበር። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከ2,600 የሚበልጡ ምሥክሮች በአብዛኛው ካቶሊኮች ለሆኑት ስምንት ሚልዮን የሚያክሉ የሩዋንዳ ሕዝቦች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ያደርሱ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) በመጋቢት ወር እነዚህ ምሥክሮች በሰዎች ቤት ውስጥ 10,000 የሚያክሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመሩ ነበር። በኪጋሊና በአካባቢዋ 15 ጉባኤዎች ነበሩ።
አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንደሚከተለው ብሏል:- “በኅዳር ወር 1992 አገለግላቸው የነበሩት ጉባኤዎች 18 ነበሩ። በመጋቢት ወር 1994 ግን የማገለግላቸው ጉባኤዎች 27 ደረሱ። የአቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች) ቁጥርም ቢሆን በየዓመቱ እድገት ያሳይ ነበር።” መጋቢት 26 ቀን 1994 ቅዳሜ ዕለት በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ 9,834 ሰዎች ተገኝተዋል።
ይሁን እንጂ በሩዋንዳ የነበረው ሁኔታ በአንድ ቀን ጀንበር በድንገት ተለዋወጠ።a
የነበረው የተረጋጋ ኑሮ በድንገት አከተመ
ሚያዝያ 6 ቀን 1994 ከምሽቱ 2 ሰዓት ገደማ ሲሆን ሁለቱም ሁቱዎች የነበሩት የሩዋንዳና የቡሩንዲ ፕሬዘዳንቶች በኪጋሌ በደረሰው የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ሞቱ። በዚያ ምሽት በዋና ከተማይቱ የፖሊስ ፊሽካ በየቦታው ይሰማ ነበር፤ መንገዶችም ተዘጉ። ከዚያም በዚያው ቀን ማለዳ ወታደሮችና ቆንጨራ የታጠቁ ሰዎች የቱትሲ ጎሣ አባላት የሆኑ ሰዎችን መግደል ጀመሩ። በመጀመሪያ ከተገደሉት ሰዎች መካከል የኪጋሊ ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች የከተማ የበላይ ተመልካች የሆነው ንታባና ኢውጂን፣ ባለቤቱ፣ ወንድ ልጁና ሴት ልጁ ይገኛሉ።
አውሮፓውያን የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች ቱትሲዎች ከሆኑ በርካታ ጎረቤቶቻቸው ጋር መጽሐፍ ቅዱስ አጥንተው ነበር። ከእነዚህ ጎረቤቶቻቸው መካከል ዘጠኝ የሚሆኑት ገዳዮቹ በእብደት ከቤት ወደ ቤት እየተዘዋወሩ ሰዎችን ሲጨፈጭፉ ተመልክተው በእነዚህ አውሮፓውያን ቤት ተጠልለው ነበር። ብዙም ሳይቆይ 40 የሚያክሉ ዘራፊዎች መጥተው በቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ በሙሉ ሰባበሩ። ቱትሲዎቹ ጎረቤቶችም በአሳዛኝ ሁኔታ ተገደሉ። ሌሎቹ ግን የወዳጆቻቸውን ነፍስ ለማዳን ያደረጉት ጥረት ባይሳካም ከነሕይወታቸው እንዲሸሹ ተፈቅዶላቸዋል።
ጭፍጨፋው ለበርካታ ሳምንታት ቀጠለ። በጠቅላላው 500,000 የሚያክሉ ወይም ከዚያ የሚበልጡ ሩዋንዳውያን ተገደሉ። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በተለይ ቱትሲዎች ነፍሳቸውን ለማዳን ሸሽተው ተሰደዱ። በዛየር የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በፈረንሳይ ለሚገኙ ወንድሞች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አሳወቀ። “በአንድ ኮንቴይነር አሮጌ ልብስ እንዲልኩ ጠየቅናቸው” ይላል የዛየር ቅርንጫፍ ቢሮ። “የፈረንሳይ ወንድሞች ግን አምስት ኮንቴይነር የሚሞሉ በአብዛኛው አዳዲስ ልብሶችና ጫማዎች ላኩልን።” ሰኔ 11 ቀን 650 ኩንታል የሚያክል ልብስ ተላከ። በተጨማሪም የኬንያ ቅርንጫፍ ለስደተኞቹ ልብስና መድኃኒት፣ እንዲሁም በራሳቸው ቋንቋ የተዘጋጁ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች ላከ።
በሐምሌ ወር የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር የሚባለው ቱትሲዎች የሚበዙበት ሠራዊት ሁቱዎች የሚበዙበትን የመንግሥት ጦር ድል አደረገ። ከዚህ በኋላ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሁቱዎች መሰደድ ጀመሩ። ሁለት ሚልዮን የሚያክሉ ወይም ከዚያ የሚበልጡ ሩዋንዳውያን በጎረቤት አገሮች እንደ ነገሩ በችኮላ በተቋቋሙ ሠፈሮች ለመጠለል በሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ትርምስ ተፈጠረ።
እርስ በርስ ለመረዳዳት ሞከሩ
በኪጋሊ የይሖዋ ምሥክሮች የትርጉም ቢሮ ይሠሩ ከነበሩት ስድስት ሰዎች መካከል ሁለቱ ማለትም አናኒ ምባንዳ እና ሙካጊሳጋራ ዴኒስ የተባሉት ቱትሲዎች ነበሩ። ሁቱ ወንዶሞች ከሞት ሊያድኗቸው ያደረጉት ሙከራ ለጥቂት ሳምንታት ሰምሮላቸው ነበር። ይሁን እንጂ በግንቦት ወር 1994 መጨረሻ አካባቢ እነዚህ ቱትሲ ምሥክሮች ተገድለዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች የገዛ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው፣ እንዲያውም መሥዋዕት አድርገው የሌላ ጎሣ አባላት የሆኑትን ክርስቲያኖች ከጉዳት ለማዳን ሞክረዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 15:13) ለምሳሌ ሙካባሊሳ ሻንታል ቱትሲ ነች። የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር አባላት ትኖርበት በነበረው ስታዲየም ሁቱዎችን በሚያስሱበት ጊዜ ሁቱዎች ባልንጀሮችዋን እንዳይጎዱባት ተማጸነቻቸው። አማጺዎቹ በልመናዋ ቢናደዱም ከመካከላቸው አንዱ “እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች በጣም የጠነከረ ወንድማማችነት አላችሁ። ከሁሉ የሚሻለው ሃይማኖት የእናንተ ነው!” ብሏታል።
ከጎሣ ጥላቻ መራቅ
እንዲህ ሲባል ግን የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ የአፍሪካ ክፍል በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሰፍኖ በኖረው የጎሣ ጥላቻ አይነኩም ማለት አይደለም። አንድ ለእርዳታ ሥራ ከፈረንሳይ አገር የመጣ ምሥክር እንደሚከተለው ብሏል:- “ክርስቲያን ወንድሞቻችን እንኳን በቃላት ለመግለጽ አዳጋች ለሆነው ለዚህ እልቂት መንስዔ በሆነው የጎሣ ጥላቻ እንዳይበከሉ ከፍተኛ ጥረት ለማድረግ ተገደዋል።
“ዓይናቸው እያየ ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ወንድሞች አግኝተናል። ለምሳሌ ያህል አንዲት ክርስቲያን እህት ባልዋ የተገደለው ካገባችው ከሁለት ቀን በኋላ ነበር። አንዳንድ ምሥክሮች ልጆቻቸውና ወላጆቻቸው ሲገደሉ ተመልክተዋል። በአሁኑ ጊዜ በኡጋንዳ የምትኖር አንዲት እህት መላ ቤተሰብዋ፣ ባልዋ ጭምር ታርደው ሲገደሉ ተመልክታለች። ይህ የሚያሳየው በእያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ላይ ምን ዓይነት የስሜትና የአካል ጉዳት እንደ ደረሰ ነው።”
በጠቅላላው 400 የሚያክሉ ምሥክሮች በዚህ በጎሣ ጥላቻ ምክንያት በተነሳው ግጭት ተገድለዋል። ሆኖም ከእነዚህ መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ በእምነት ወንድሞቻቸው በይሖዋ ምሥክሮች እጅ አልተገደሉም። ቱትሲም ሆኑ ሁቱ የሮማ ካቶሊክና የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ተካታዮች ግን በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል። በሚገባ እንደሚታወቀው በመላው የምድር ክፍሎች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነቶች፣ በአብዮቶችና እነዚህን በሚመስሉ ማናቸውም የዚህ ዓለም ግጭቶች በምንም ዓይነት መንገድ አይካፈሉም። — ዮሐንስ 17:14, 16፤ 18:36፤ ራእይ 12:9
በቃላት ሊገለጽ የማይችል መከራ
በዚህ ባለፈው የክረምት ወራት በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ሊታመን የማይችል የሰብዓዊ ፍጡር ሰቆቃን የሚያሳዩ ሥዕሎች ተመልክተዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሩዋንዳውያን ስደተኞች ወደ ጎረቤት አገሮች ሲጎርፉና ከፍተኛ የጽዳት ጉድለት ባለበት ሁኔታ ሲኖሩ ታይተዋል። አንድ ከፈረንሳይ አገር ለእርዳታ ሥራ የመጣ የይሖዋ ምሥክር እርሱና የሥራ ባልደረቦቹ ሐምሌ 30 የተመለከቱትን ሁኔታ እንደሚከተለው በማለት ገልጿል:-
“የተመለከትነው ሁሉ በጣም የሚዘገንን ነበር። በረዥም ጎዳናዎች ግራና ቀኝ አስከሬኖች ተጥለዋል። የመቃብር ጉድጓዶች በሺህ በሚቆጠሩ ሬሣዎች ጢም ብለዋል። በሚተራመሱት ሰዎች መካከል ስናልፍ የሚሸተንን መጥፎ ሽታ መቋቋም አልቻልንም። ሕፃናት ሬሣዎች አጠገብ ተቀምጠው ይጫወታሉ። ገና በሕይወት ያሉ ልጆች የወላጆቻቸውን ሬሣዎች የሙጥኝ ብለው ይዘው ይታዩ ነበር። እንደነዚህ ያሉትን ሁኔታዎች ደጋግሞ ማየት በአእምሮ ውስጥ ሊፋቅ የማይችል አሻራ ትቶ ያልፋል። ማንም ሰው ምንም ለማድረግ የማይችል ደካማ መሆኑ ይሰማዋል። በዚህ አሠቃቂና ዘግናኝ ሁኔታ የማይነካ ሰው ሊኖር አይችልም።”
በሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ዛየር በሚጎርፉበት ጊዜ በዛየር የሚኖሩ ምሥክሮች ወደ አገሪቱ ድንበር ሄደው ክርስቲያን ወንድሞቻቸውና መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ለይተው እንዲያውቋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎቻቸውን ይዘው በጎዳናዎች ላይ ቆመው ነበር። ከዚያም ከሩዋንዳ የተሰደዱት ምሥክሮች አንድ ላይ ተሰብስበው እንክብካቤ ወደሚደረግላቸው በጎማ የሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ተወሰዱ። በቂ መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያ ለማግኘት ባይቻልም የሕክምና ልምድ ያላቸው ምሥክሮች የታመሙትን ስደተኞች ሥቃይ ለማስታገስ የተቻላቸውን ሁሉ አደረጉ።
ሥቃይ የደረሰባቸውን ለመርዳት አፋጣኝ ምላሽ ተገኘ
ሐምሌ 22 ቀን ዐርብ ዕለት በፈረንሳይ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከአፍሪካ የፋክስ መልእክት ደረሳቸው። ከሩዋንዳ የተሰደዱት ክርስቲያን ወንድሞቻቸው የወደቁበትን አስቸጋሪ ሁኔታ የሚገልጽ መልእክት ነበር። ወንድሞች መልእክቱ በደረሳቸው ከአምስት እስከ አሥር ደቂቃ ውስጥ አስቸኳይ እርዳታ በዕቃ ማመላለሻ አውሮፕላን ለመላክ ወሰኑ። ለዚህም ቅዳሜና እሁድ ከፍተኛ ዝግጅት አደረጉ። እንዲህ ባለ አጭር ጊዜ ውስጥ ይህን የሚያክል አስቸኳይ እርዳታ አሰባስበውና ልከው ስለማያውቁ የተከናወነው ሥራ በጣም የሚያስደንቅ ነበር።
ለነፍስ አድን እርዳታ የተሰጠው ምላሽ በጣም የሚያስደንቅ ነበር። በቤልጅየም፣ በፈረንሳይና በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ወንድሞች ብቻ ከ1, 600, 000 ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ አዋጡ። ምግብ፣ መድኃኒትና ሌሎች ለነፍስ ማቆያ የሚያገለግሉ ዕቃዎች ተሰባስበው በፈረንሳይ አገር በሉቭዬ እና በቤልጅየም አገር በብራሰልስ በሚገኙት የማኅበሩ መሥሪያ ቤቶች በሣጥን ታሽገው የጽሑፍ ምልክት ተደረገባቸው። ጭነቱን የቤልጅየም ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ኦስቴንድ ለማድረስ ምሥክሮቹ ቀንና ሌሊት መሥራት ነበረባቸው። ረቡዕ ዕለት ሐምሌ 27 ቀን ከ350 ኩንታል የሚበልጥ ጭነት በአውሮፕላን ማረፊያው ደርሶ በዕቃ ማመላለሻ አውሮፕላን ተጫነ። በማግስቱ ደግሞ በአብዛኛው መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ የሚገኝበት አነስ ያለ ጭነት ተላከ። ከሁለት ቀን በኋላ ደግሞ ቅዳሜ ዕለት ሌላ አውሮፕላን ለጉዳተኞቹ የሚደርስ የሕክምና መገልገያ ጭኖ ተጓዘ።
ከጭነቱ በፊት ከፈረንሳይ አገር አንድ የሕክምና ዶክተርና ሌሎች ምሥክሮች ወደ ጎማ ሄደው ነበር። ሰኞ ዕለት ሐምሌ 25 ዶክተር ሄንሪ ታለት ጎማ ሲደርስ 20 ምሥክሮች በኮሌራ በሽታ የሞቱ ሲሆን በየቀኑ የሚሞቱም ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ጭነቱ የሚጓጓዘው 240 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በቡሩንዲ ዋና ከተማ በቡጁምቡራ በኩል ስለነበረ ከሐምሌ 29 ቀን ዐርብ ጠዋት በፊት ጎማ ሊደርስ አልቻለም።
የተነሳውን በሽታ መቋቋም
በዚህ ጊዜ በጎማ የሚገኘው አነስተኛ የመንግሥት አዳራሽ በሚገኝበት ቦታ 1,600 የሚያክሉት ምሥክሮችና ወዳጆቻቸው ተጨናንቀው ሰፍረው ነበር። ለእነዚህ ሰዎች በሙሉ የሚያገለግል አንድ መጸዳጃ ቤት ብቻ ሲኖር ምንም ውኃ አልነበረም። የነበራቸው ምግብም በጣም ጥቂት ነበር። በኮሌራ በሽታ የተበከሉት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ታጭቀዋል። በየቀኑ የሚሞቱት ቁጥር በጣም እየጨመረ ሄዶ ነበር።
ኮሌራ በአንድ ሰው አካል ውስጥ ያለውን ፈሳሽ በሙሉ አሟጦ የሚያደርቅ በሽታ ነው። ዓይን እንደ ብርጭቆ ከነጣ በኋላ ወደ ላይ ይገለበጣል። ያጣውን ፈሳሽ እንዲያገኝ ከተደረገ ግን በሁለት ቀን ውስጥ በእግሮቹ ለመቆም ይችላል። ስለዚህም በበሽታው የተለከፉት ወንድሞች ያጡትን ፈሳሽ በቦታው በተገኙ መድኃኒቶች ለመተካት አፋጣኝ ጥረት መደረግ ተጀመረ።
በተጨማሪም በበሽታው የተለከፉት ወደ ጤነኞቹ እንዳያስተላልፉ ለማድረግ ወንድሞች ሕሙማኑን ለይተው ለብቻቸው እንዲሆኑ አደረጉ። ስደተኞቹን በጎማ ከሚገኘው አስከፊ ሁኔታ ወደ ሌላ ሥፍራ ለማዛወር ፈለጉ። በኪቩ ሐይቅ አጠገብ ከአቧራና አየሩን ከሞላው የአስከሬን ሽታ የራቀ ተስማሚ ቦታ ተገኘ።
የመጸዳጃ ጉድጓዶች ተቆፈሩ፣ ሁሉም ጥብቅ የሆኑ የኃይጂን ሕጎችን እንዲጠብቁ ተደረገ። ይህም ሽንት ቤት ከሄዱ በኋላ ቆሻሻ የሚያጠራ መድኃኒትና ውኃ ባለበት ሣህን ውስጥ እጅ መታጠብን ይጨምር ነበር። ይህን ማድረግ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ከተገለጸላቸው በኋላ ስደተኞቹ የሚፈለግባቸውን ሁሉ ማድረግ ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ በሽታው ያደርስ የነበረው ቅስፈት ጋብ አለ።
የተጫነው አስቸኳይ እርዳታ ዐርብ ዕለት ሐምሌ 29 ቀን ሲደርስ በጎማ በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ አነስተኛ ሆስፒታል ተቋቋመ። 60 የሚያክሉ የመንገድ አልጋዎች ተዘረጉ፣ የውኃ ማጣሪያ መሣሪያም ተተከለ። በተጨማሪም በኪቩ ሐይቅ ዳርቻ ላይ እንዲሠፍሩ ለተደረጉት ስደተኞች ድንኳኖች ተላኩ። በአጭር ጊዜ ውስጥ 50 ድንኳኖች ሥርዓት ባለው መንገድ በመስመር በመስመር ተስተካክለው ተተከሉ።
እስከ 150 የሚደርሱ ምሥክሮችና ወዳጆቻቸው የታመሙበት ጊዜ ነበር። በመጀመሪያው የነሐሴ ሳምንት ከ40 የሚበልጡ ምሥክሮች በጎማ ሞተው ነበር። የሕክምና መገልገያዎችና እርዳታዎች በጊዜው በመድረሳቸው ግን ብዙ ሕይወት ለማዳንና ብዙ ሥቃይ ለማስቀረት ተችሏል።
አመስጋኝ የሆኑ መንፈሳዊ ሰዎች
ስደተኞቹ ምሥክሮች ለተደረገላቸው ሁሉ ጥልቅ የሆነ የአመስጋኝነት መንፈስ አሳይተዋል። በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ባሳዩአቸው ፍቅርና ዓለም አቀፋዊ የሆነ የወንድማማቾች ማኅበር አባሎች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ግልጽ ማስረጃ በማየታቸው ልባቸው በጣም ተነክቷል።
ስደተኞቹ ብዙ መከራ ቢደርስባቸውም መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀዋል። እንዲያውም አንድ ታዛቢ “ምንም ነገር ያልነበራቸው ቢሆኑም ሥጋዊ እርዳታ ከመቀበል ይልቅ መንፈሳዊ ምግብ ለመቀበል ይጓጉ ነበር” ብሏል። በቀረበው ጥያቄ መሠረት በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለው የሩዋንዳውያን ቋንቋ በሆነው በኪንያሩዋንዳ የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መጽሐፍb 5,000 የሚያክሉ ቅጂዎች ወደ ተለያዩት የስደተኛ ካምፖች ተልከዋል።
ስደተኞቹ በየቀኑ በአንድ ጥቅስ ላይ ውይይት ያደርጋሉ። የጉባኤ ስብሰባዎችም አደራጅተዋል። በተጨማሪም ለሕፃናቱ ትምህርት ቤት የሚያገኙበት ዝግጅት ተደረገ። መምህራኑ በእነዚህ የትምህርት ክፍሎች በመጠቀም የኃይጂን ሕጎችን እና እነዚህን ሕጎች መጠበቅ በሕይወት ለመቆየት አስፈላጊ መሆኑን ለማስገንዘብ ችለዋል።
ተከታታይ እርዳታ መስጠት አስፈላጊ ሆኗል
ከጎማ በተጨማሪ እንደ ሩትሹሩ ባሉት ሌሎች ቦታዎች ስደተኛ ምሥክሮች ሰፍረዋል። ለነዚህም ወንድሞች ተመሳሳይ እርዳታ ቀርቦላቸዋል። ሐምሌ 31 ቀን አንድ ሰባት ምሥክሮች የሚገኙበት የምሥክሮች ቡድን 450 ስደተኛ ምሥክሮች ወደሚገኙበት ከጎማ በስተ ደቡብ ወደሚገኘው ወደ ቡካቩ ተጓዘ። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል ከቡሩንዲ የተሰደዱም ይገኙ ነበር። በዚህ ሥፍራም የኮሌራ ወረርሽኝ ተነስቶ ስለነበረ ከወንድሞች መካከል ማንም እንዳይሞት ጥረት ተደርጓል።
በማግስቱ ደግሞ ይህ ቡድን ከሩዋንዳና ከቡሩንዲ የተሰደዱ 1,600 የሚያክሉ ምሥክሮች በተለያየ ቦታ ሠፍረው በሚገኙበት የ140 ኪሎ ሜትር መንገድ በመኪና ተጉዞ ኡቪራ፣ ዛየር ደረሰ። እነዚህ ስደተኞች ራሳቸውን እንዴት ከበሽታ ሊከላከሉ እንደሚችሉ ትምህርት ተሰጥቷል። ይህ ቡድን የተመለከተውን መሠረት በማድረግ ያቀረበው ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “እስከ አሁን የተደረገው ሁሉ የሥራው መጀመሪያ ነው። በአሁኑ ጊዜ እርዳታችንን በማግኘት ላይ የሚገኙት 4,700 የሚያክሉ ሰዎች ለሚመጡት በርካታ ወራት ተጨማሪ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።”
በመቶ የሚቆጠሩ ምሥክሮች እስከ ነሐሴ ወር ድረስ ወደ ሩዋንዳ እንደተመለሱ ሪፖርት ተደርጓል። ቢሆንም ቤታቸውና ንብረታቸው ፈጽሞ ወድሟል። ስለዚህ የመኖሪያ ቤቶችንና የመንግሥት አዳራሾችን የመሥራት ችግር ተደቅኖባቸዋል።
የአምላክ አገልጋዮች በሩዋንዳ ከፍተኛ መከራ ስለ ተቀበሉት ወንድሞቻቸው መጸለያቸውን አያቋርጡም። የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረበ ሲሄድ ዓመፅ እንደሚበዛ እናውቃለን። በመላው ዓለም የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ግን ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን በመጠበቅና ልባዊ ርህራሄ በማሳየት ይቀጥላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በታኅሣሥ 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ “በሩዋንዳ ውስጥ ለደረሰው ሰቆቃ ተጠያቂው ማን ነው?” በሚል ርዕስ የወጣውን ጽሑፍ ተመልከት።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዛየር
ሩትሹሩ
ጎማ
ኡጋንዳ
ሩዋንዳ
ኪጋሊ
ብሩንዲ
ቡጁምቡራ
ኪቩ ሐይቅ
ኡቪራ
ቡካቩ
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስተግራ:- ንታባና ኢውጂን እና ቤተሰቡ ተገድለዋል። በስተቀኝ:- የቱትሲ ጎሣ አባል የሆነችው ሙካጊሳጋራ ዴኒስ ሁቱ ወንድሞች ሊያድኗት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ተገድላለች
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ:- በጎማ የመንግሥት አዳራሽ በሽተኞችን ማስታመም። ከታች በስተግራ:- ምሥክሮች ያሰባሰቡት ከ350 ኩንታል የሚበልጥ አስቸኳይ እርዳታ በጄት አውሮፕላን ተጭኖ ሲላክ። ከግርጌ:- ምሥክሮች በተዛወሩበት በኪቩ ሐይቅ አጠገብ። ከታች በስተቀኝ:- የሩዋንዳ ስደተኞች በዛየር በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ