በሁከትና ብጥብጥ መሃል ክርስትና በተግባር ሲገለጽ
ጊዜው ሚያዝያ 1994 ነበር። ችግሩ የፈነዳው ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ ነው። አንድ አውሮፕላን ወድቆ በመከስከሱ የቡሩንዲና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንቶች ሞቱ። በሰዓታት ጊዜ ውስጥ እጅግ ዘግናኝ የሆነ ዓመፅ ሩዋንዳን አጥለቀለቃት። ከሦስት ወር እምብዛም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ከ500,000 በላይ የሚሆኑ ሩዋንዳውያን ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ለሕልፈተ ሕይወት ተዳረጉ። አንዳንድ ሰዎች ይህን ወቅት “የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ” ብለው ይጠሩታል።
የሩዋንዳ ነዋሪዎች 7.5 ሚልዮን ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ግማሽ የሚያክሉት ለመሸሽ ተገደዋል። ይህ በጎረቤት አገሮች የተጠለሉትን 2.4 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ይጨምራል። በቁጥርም ሆነ በፍጥነት በዘመናዊው የዓለም ታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው ፍልሰት ነበር። በዛየር (በአሁኗ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ)፣ በታንዛኒያና በቡሩንዲ የስደተኛ መጠለያዎች በፍጥነት ተቋቋሙ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በዓለም ውስጥ ከሚገኙት መጠለያዎች ሁሉ እጅግ የሚበልጡ ሲሆኑ 200,000 የሚሆኑ ሰዎችን አስጠልለው ነበር።
ከስደተኞቹ መካከል ሰላም ወዳድ ሕዝቦች የሆኑትና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ለመተርጎም የሚጥሩት የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል። በየትኛውም አገር ቢኖሩ ፍጹም ገለልተኛ አቋማቸውን ጠብቀው ከመመላለሳቸውም ሌላ በኢሳይያስ 2:4 ላይ የተጠቀሰውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ያደርጋሉ:- “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ቡድን በሩዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አለመሳተፉ በሰፊው ይታወቃል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆኑ’ ተናግሯል። ይሁን እንጂ በዓለም ውስጥ በመሆናቸው ምክንያት በብሔራት መካከል ከሚነሱ ብጥብጦች ሁልጊዜ ማምለጥ አይችሉም። (ዮሐንስ 17:11, 14) በሩዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ 400 የሚያክሉ ምሥክሮች ሕይወታቸውን አጥተዋል። እንዲሁም 2,000 የሚያክሉ ምሥክሮችና ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ተሰደዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች የዓለም ክፍል አይደሉም ማለት አደጋዎች ሲፈጠሩ ምንም ዓይነት እርምጃ አይወስዱም ማለት ነውን? አይደለም። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል:- “ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፣ ከእናንተ አንዱም:- በደኅና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።” (ያዕቆብ 2:15-17) ምሥክሮቹ ለጎረቤት ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው በእምነት ለማይዛመዷቸው ሰዎች ጭምር እርዳታ ያደርጋሉ።—ማቴዎስ 22:37-40
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አደጋ የተጋረጠባቸውን በሩዋንዳ የሚገኙ መሰል አማኞች ለመርዳት ይጓጉ የነበረ ቢሆንም እርዳታውን በምዕራብ አውሮፓ የሚገኙ ወንድሞች እንዲያስተባብሩ ተደረገ። በ1994 የበጋ ወቅት ከአውሮፓ የተውጣጡ ፈቃደኛ ምሥክሮችን የያዘ አንድ ቡድን በአፍሪካ የሚገኙ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለመርዳት በፍጥነት ወደዚያው ተጓዘ። ለሩዋንዳውያን ስደተኞች በደንብ የተደራጁ መጠለያዎችና የመስክ ሆስፒታሎች ተቋቋሙ። ከሌሎች ቦታዎች ደግሞ ብዛት ያላቸው ልብሶች፣ ብርድ ልብሶች፣ ምግብና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በአየርና በባሕር ተላከላቸው። በወቅቱ በሩዋንዳ ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው ማለትም ከ7,000 በላይ የሚሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የእርዳታው ተጠቃሚዎች ሆነዋል። በዚያው ዓመት በታኅሣሥ ወር በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ኑሯቸውን መልሰው ለማቋቋም ወደ ሩዋንዳ ተመልሰዋል።
በኮንጎ የተቀሰቀሰው ጦርነት
በ1996 በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ምሥራቃዊ ክፍለ ሃገር ጦርነት ተቀሰቀሰ። ይህ አካባቢ ኮንጎን ከሩዋንዳና ከቡሩንዲ ጋር የሚያዋስን ነበር። በዚህ አካባቢም ብዙዎች ተገደው ከመደፈራቸውም ሌላ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ሰዎች ከጥይት እሩምታውና በእሳት ከሚጋዩት መንደሮች መሃል ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሽሽቱን ተያያዙት። የይሖዋ ምሥክሮችም በብጥብጡ ወጥመድ በመያዛቸው 50 የሚያክሉት ሞተዋል። አንዳንዶቹ የሞቱት በተባራሪ ጥይቶች ተመትተው ነበር። ሌሎች የአንድ ጎሣ አባላት በመሆናቸው ወይም በስህተት ጠላቶች ተደርገው በመቆጠራቸው ተገድለዋል። 150 ምሥክሮች የሚኖሩበት አንድ መንደር በእሳት ጋይቷል። በሌሎች መንደሮች በደርዘን የሚቆጠሩ ቤቶችና ጥቂት የመንግሥት አዳራሾች በእሳት ተቃጥለው ወድመዋል። ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት ምሥክሮች ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሸሹ ሲሆን በዚያም የሚገኙ የአምልኮ አጋሮቻቸው ረድተዋቸዋል።
በጦርነት ጊዜ ሰብል ስለሚበላሽ፣ የምግብ ክምችቶች ስለሚዘረፉና የአቅርቦት መስመሮች ስለሚቋረጡ ረሃብ ተከትሎ ይመጣል። ያለውም ምግብ ቢሆን ውድ ነው። በግንቦት 1997 መግቢያ ላይ በኪሳንጋኒ የ1 ኪሎ ግራም ድንች ዋጋ ሦስት ዶላር የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ ከብዙዎቹ ሰዎች የገንዘብ አቅም በላይ ነበር። ብዙዎቹ ሊበሉ የሚችሉት በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነበር። የምግብ እጥረት በሽታን አስከትሎ እንደሚመጣ የተረጋገጠ ነው። የተመጣጠነ ምግብ እጦት ሰውነታችን እንደ ወባ፣ የተቅማጥ በሽታዎችና የጨጓራ መታወክ ያሉትን ሕመሞች ለመከላከል ያለውን ችሎታ ያዳክማል። በተለይ በተመጣጠነ ምግብ እጦት የሚጠቁትና የሚሞቱት ሕፃናት ናቸው።
ምን እንደሚያስፈልግ መገምገም
በአውሮፓ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማቅረብ እንደገና አፋጣኝ ምላሽ ሰጡ። በሚያዝያ 1997 ሁለት የሕክምና ዶክተሮችን ያካተተ የምሥክሮች የእርዳታ ቡድን መድኃኒትና ገንዘብ ይዞ በአውሮፕላን ሄደ። በጎማ የሚገኙ የአካባቢው ምሥክሮች የሚያስፈልገውን ነገር ለማወቅና እርዳታው ወዲያው እንዲከፋፈል ለማድረግ ሲሉ የእርዳታ ኮሚቴዎችን አቋቁመው ነበር። ቡድኑ ከተማውንና በዙሪያው ያሉትን አካባቢዎች በሙሉ እየተዘዋወረ ጥናት አደረገ። በጣም ሩቅ በሆኑ አካባቢዎች ስላለው ሁኔታ መረጃ ለማግኘት መልእክተኞች ተላኩ። በተጨማሪም ከጎማ በስተ ምዕራብ በ1,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ከኪሳንጋኒ መረጃዎች ለማሰባሰብ ተችሎ ነበር። በአካባቢው የሚገኙ ወንድሞች 700 የሚሆኑ ምሥክሮች በነበሩበት በጎማ እርዳታ በማስተባበር እገዛ አድርገዋል።
በጎማ ከሚገኙት ክርስቲያን ሽማግሌዎች መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል:- “ወንድሞቻችን እኛን ለመርዳት ሲሉ ያን ሁሉ ርቀት አቋርጠው መምጣታቸውን ስናይ በጣም ተነካን። እነርሱ ከመምጣታቸው በፊትም እርስ በርሳችን እንረዳዳ ነበር። ወንድሞች ከገጠር አካባቢዎች ወደ ጎማ መሸሽ አስፈልጓቸው ነበር። አንዳንዶች ቤታቸውን አጥተዋል፤ እንዲሁም ማሳቸውን ትተው መጥተዋል። ወደ ቤታችን በመውሰድ ያሉንን ልብሶችና ጥቂት ምግብ አካፈልናቸው። እኛ ልናደርግላቸው የምንችለው ነገር አነስተኛ ነበር። አንዳንዶቻችን የተመጣጠነ ምግብ በማጣት እየተሰቃየን ነበር።
“በጊዜው ምግብ እንደልብ የማይገኝና ውድ የነበረ ቢሆንም ከአውሮፓ የመጡት ወንድሞች የሰጡን ገንዘብ ምግብ ለመግዛት አስችሎናል። ብዙዎች በቤታቸው የሚቀመስ ነገር ስላልነበራቸው ምግቡ የመጣው ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ነበር። ምግቡን የይሖዋ ምሥክሮች ለሆኑትም ላልሆኑትም አከፋፈልን። እርዳታው ትንሽ ዘግይቶ ቢደርስ ኖሮ ብዙዎች በተለይም ሕፃናት ያልቁ ነበር። ይሖዋ ሕዝቡን አድኗል። ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች በጣም ተነክተዋል። ብዙዎቹ ስላለን አንድነትና ፍቅር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አንዳንዶች የያዝነው ሃይማኖት እውነተኛ መሆኑን አምነዋል።”
ምግብ ከአካባቢው ለመግዛትና መድኃኒት ለማሰራጨት የተቻለ ቢሆንም ገና የሚያስፈልግ ተጨማሪ ነገር ነበር። ልብሶችና ብርድ ልብሶች በተጨማሪም ብዛት ያለው የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት ያስፈልግ ነበር። የፈራረሱ ቤቶችንም መልሶ ለመገንባት እርዳታ ያስፈልግ ነበር።
በልግስና ሰጥተዋል
በአውሮፓ የሚገኙ ወንድሞች እርዳታ ለመለገስ ዝግጁ ነበሩ። በሉቪዬ ፈረንሳይ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በሮን ሸለቆና በኖርማንዲ ለሚገኙ ጉባኤዎች እንዲሁም በፓሪስ አካባቢ ለሚገኙ አንዳንድ ጉባኤዎች ስለ ሁኔታው አሳወቀ። በዚህ ጊዜ ሌላ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ሆኗል:- “በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፣ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል። እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።”—2 ቆሮንቶስ 9:6, 7
በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በደስታ ሰጥተዋል። ልብሶችን፣ ጫማዎችንና ሌሎች ቁሳ ቁሶችን የያዙ ካርቶኖችና ከረጢቶች ወደ መንግሥት አዳራሾች ጎረፉ፤ ከዚያም በፈረንሳይ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተወሰዱ። በዚያም 400 የሚያክሉ ፈቃደኛ ሰዎች “ዛየርን መርዳት” ዓላማው ባደረገው በዚህ ፕሮጀክት ቀጣይ እርምጃ ለመሳተፍ ዝግጁ ሆነው ይጠባበቁ ነበር። የእርዳታ እቃዎቹ ሲደርሱ እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ልብሶቹን ከለዩ፣ ካጠፉና በካርቶኖች ውስጥ ከከተቱ በኋላ እያንዳንዳቸው 30 ካርቶኖችን በሚይዙ ሣጥኖች ውስጥ አሸጓቸው። ልጆችም ቢሆኑ በአፍሪካ የሚገኙ ወጣት ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በማስታወስ የሚያብረቀርቁ መጫወቻ መኪናዎችን፣ እሽክርክሪቶችን፣ አሻንጉሊቶችንና መጫወቻ ድቦችን ልከውላቸዋል። እነዚህ እቃዎች ለሕይወት አስፈላጊ ከሆኑት ሌሎች ቁሳ ቁሶች ጋር በአንድነት ተልከዋል። በአጠቃላይ እቃዎቹ እያንዳንዳቸው 12 ሜትር ርዝመት ባላቸው ዘጠኝ ትላልቅ የዕቃ መላኪያ የብረት ሣጥኖች ተሞልተው ወደ ኮንጎ በመርከብ ተላኩ።
በቤልጂየም፣ በፈረንሳይና በስዊዘርላንድ በሚገኙ በሺህ በሚቆጠሩ ወንድሞች እርዳታ ወደ መካከለኛው አፍሪካ ምን ያህል እርዳታ ተልኮ ይሆን? እስከ ሰኔ 1997 ድረስ በአጠቃላይ 500 ኪሎ ግራም መድኃኒት፣ 10 ቶን የሚመዝኑ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያላቸው ብስኩቶች፣ 20 ቶን ሌሎች ምግቦች፣ 90 ቶን ልብሶች፣ 18,500 ጥንድ ጫማዎችና 1,000 ብርድ ልብሶች ተልከዋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችም እንዲሁ ተልከዋል። ይህ ሁሉ በእጅጉ የሚደነቅ፣ ስደተኞቹን የሚያጽናና እንዲሁም ያለባቸውን ችግር እንዲቋቋሙ የሚረዳ ነበር። የተላኩት ቁሳ ቁሶች ጠቅላላ ዋጋ በገንዘብ ሲተመን ወደ 1,000,000 የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ነበር። እንደዚህ ያሉት መዋጮዎች ይሖዋን በሚያገለግሉት ሕዝቦች መካከል ያለው ወንድማማችነትና ፍቅር ማረጋገጫዎች ናቸው።
በኮንጎ የተካሄደው የማከፋፈል ሥራ
እቃዎቹ ኮንጎ መድረስ እንደጀመሩ በከተማው ከሚገኙ የእርዳታ ኮሚቴዎች ጋር በሕብረት ለመሥራት ሁለት ወንድሞችና አንዲት እህት ከፈረንሳይ መጡ። በኮንጎ የሚገኙ ምሥክሮች ያሳዩትን አመስጋኝነት አስመልክታ ጆስሊን እንዲህ ብላለች:- “በርካታ የምስጋና ደብዳቤዎች ደርሰውናል። አንዲት ድሃ እህት ከመዳብ የተሠራ ጌጥ ሰጠችኝ። ሌሎች ፎቶ ግራፎቻቸውን ሰጥተውናል። ቦታውን ለቀን ስንሄድ እህቶች ይስሙኝ፣ ያቅፉኝና ያለቅሱ ነበር። እኔም አለቀስሁ። ብዙዎች ‘ይሖዋ ጥሩ ነው። ይሖዋ ያስብልናል’ እንደሚሉ ያሉ አስተያየቶችን ይሰነዝሩ ነበር። ስለዚህ ለዚህ ሁሉ ስጦታ ሊመሰገን የሚገባው አምላክ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። ምግብ በምናድልበት ጊዜ ወንድሞችና እህቶች በመንግሥቱ መዝሙሮች ይሖዋን ያወድሱ ነበር። ሁኔታው ልብ የሚነካ ነበር።”
ከቡድኑ አባላት መካከል አንዱ የሕክምና ዶክተር የሆነው ሎይክ ነበር። በርካታ ሰዎች የእርሱን እርዳታ ለማግኘት በመንግሥት አዳራሹ ተሰብስበው ተራቸው እስኪደርስ ድረስ በትዕግሥት ይጠባበቁ ነበር። አንዲት የኮንጎ እህት የበኩሏን ለማድረግ በማሰብ 40 የሚያህሉ ፓስቲዎችን ጠብሳ አመጣች። ሐኪሙ ጋ ለመግባት ይጠባበቁ የነበሩት 80 የሚያክሉ ሰዎች ስለነበሩ እያንዳንዳቸው ግማሽ ግማሽ ፓስቲ ደርሷቸዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች ላልሆኑ ሰዎች የተደረገ እርዳታ
ይህ ሰብዓዊ እርዳታ የተደረገው ለይሖዋ ምሥክሮች ብቻ አልነበረም። ብዙዎች በ1994 በተሰጠው እርዳታ እንደተጠቀሙ ሁሉ በዚህ ጊዜም ሌሎችም ተጠቃሚ ሆነዋል። ይህ በገላትያ 6:10 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው:- “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።”
ምሥክሮቹ ለበርካታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በጎማ አቅራቢያ ለሚገኝ የጓለማውታ ተቋም መድኃኒትና ልብስ አድለዋል። ይህ ጓለማውታ 85 ልጆችን የያዘ ነበር። የእርዳታው ቡድን ስለ ሁኔታው ለማጥናት ሲል ይህን የጓለማውታ ተቋም ጎብኝቶ የነበረ ሲሆን 50 ካርቶን ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያላቸው ብስኩቶች፣ በርካታ ካርቶን ልብሶች፣ 100 ብርድ ልብሶች፣ መድኃኒትና መጫዎቻዎች ለማሳደጊያ ተቋሙ ለመስጠት ቡድኑ ቃል ገብቶ ነበር። ልጆቹ በግቢው ውስጥ በሰልፍ በመቆም ለጎብኚዎቹ ዘመሩ። ቀጥሎም አንድ ልዩ ጥያቄ አቀረቡ። እግር ኳስ እንድንጫወት አንድ ኳስ ማግኘት እንችላለን?
ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ የእርዳታ ቡድኑ እቃዎቹን በማምጣት የገባውን ቃል ፈጸመ። የጓለማውታው ዲሬክተር የተደረገውን ልግስና ማየቱና የተበረከተለትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ማንበቡ ስለነካው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግሯል። ልጆቹስ የጠየቁትን ኳስ አግኝተው ይሆን? ከፈረንሳይ የመጣው የእርዳታ ቡድን አስተባባሪ የነበረው ክሎድ “ከአንድም ሁለት ኳሶች ሰጥተናቸዋል” በማለት መልሷል።
የስደተኛ መጠለያዎች
እርዳታው በኮንጎ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ከጦርነቱ ቀጠና በመሸሽ ሦስት የስደተኛ መጠለያዎች በፍጥነት ወደ ተቋቋሙበት በአቅራቢያው ወደሚገኝ አገር ሄደው ነበር። ምሥክሮቹ ወደዚያ ጭምር በመሄድ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመልክተዋል። ይህ ሪፖርት በሚዘጋጅበት ጊዜ በአብዛኛው ከኮንጎ የመጡ 211,000 ስደተኞች በመጠለያዎቹ ውስጥ ተጠግተው ነበር። ከእነዚህ ውስጥ 800 የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮችና ልጆቻቸው እንዲሁም ለመንግሥቱ ምሥራች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ነበሩ። በመጠለያዎቹ ውስጥ የነበረው አንገብጋቢ ችግር የምግብ እጥረት ነበር። በአንድ መጠለያ ውስጥ የነበረው ምግብ ለሦስት ቀናት ብቻ የሚበቃ ነበር። ይኸውም ሦስት ዓመት ያለፈበት ባቄላ ተጨምሮ ነው።
ያም ሆኖ ግን ምሥክሮቹ ጥሩ መንፈስ ነበራቸው። ያሏቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ጥቂት ቢሆኑም ራሳቸውን በመንፈሳዊ ለመገንባት በገላጣ ሥፍራዎች ስብሰባዎችን ያደርጉ ነበር። በመጠለያዎቹ ውስጥ ለሚገኙ ሌሎች ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራም ተጠምደው ነበር።—ማቴዎስ 24:14፤ ዕብራውያን 10:24, 25
የምሥክሮቹ አጥኚ ቡድን አንድ የሕክምና ዶክተር ይገኝበት ነበር። ባለ ሥልጣናቱ በእያንዳንዱ መጠለያ ውስጥ እንዲቆዩ የፈቀዱላቸው ለጥቂት ቀናት ብቻ ቢሆንም የሕክምና ምክሮችን ይሰጡ ነበር። ለክርስቲያን ሽማግሌዎች መድኃኒትና ገንዘብ ትተው ሄዱ። በዚህ መንገድ ወንድሞች ሕይወታቸውን ማቆየት ችለዋል። ቡድኑ በመጠለያዎች ውስጥ የሚገኙት ምሥክሮች በቅርቡ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ተስፋ ያደርጋል።
ስለ ወደፊቱ ጊዜስ ምን ለማለት ይቻላል? ኢየሱስ ክርስቶስ ያለንበት ጊዜ በጦርነቶችና በምግብ እጥረት የሚታመስ ሁከትና ብጥብጥ የነገሠበት ጊዜ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7) የይሖዋ ምሥክሮች ዛሬ በምድራችን ላይ የሚገኘውን ሥቃይ ወደ ፍጻሜው የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን ያውቃሉ። በአምላክ መንግሥት ግዛት ምድራዊ መኖሪያችን ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ሰላም የሰፈነባት፣ ሁሉም ነገር የተትረፈረፈባትና ማብቂያ የሌለው ደስታ የሚኖርባት ገነት ትሆናለች። (መዝሙር 72:1, 3, 16) እስከዚያ ድረስ ግን ምሥክሮቹ ስለ ሰማያዊው መንግሥት ምሥራች ማወጃቸውንና በችግር ጊዜም መሰል አምላኪዎችንና ሌሎች ሰዎችን መርዳታቸውን ይቀጥላሉ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ከ1994 ወዲህ በአውሮፓ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ በአፍሪካ ለሚገኙ የታላላቅ ሐይቆች አገራት ከ190 ቶን የሚበልጡ ምግቦች፣ መድኃኒትና ሌሎች የእርዳታ ቁሳቁሶች ልከዋል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ክርስቲያናዊ ፍቅር ተግባራዊ ሲሆን
በፈረንሳይ በተካሄደው “ዛየርን መርዳት” በተሰኘው ፕሮጀክት በቅንዓት ከተካፈሉት መካከል ሩት ዳኔ ትገኝበታለች። በክርስቲያናዊ እምነቷ ምክንያት በልጅነቷ በናዚ የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታስራ ነበር። እንዲህ ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች:- “በአፍሪካ ለሚገኙት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አንድ ነገር ልናደርግላቸው በመቻላችን በጣም ተደስተናል! ይሁን እንጂ ደስታዬን እጥፍ ድርብ ያደረገ ሌላም ነገር ነበር። በ1945 ከጀርመን ወደ ቤታችን ስንመለስ ምንም ነገር አልነበረንም። ሌላው ቀርቶ የለበስነው ልብስ እንኳ በውሰት ያገኘነው ነበር። ይሁንና ወዲያውኑ በአሜሪካ ከሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ቁሳዊ እርዳታ አገኘን። ስለዚህ ይህ የእርዳታ ዝግጅት ከረዥም ጊዜ በፊት ሌሎች ለእኛ ያሳዩትን ደግነት ለመመለስ አስችሎኛል። ክርስቲያናዊ ፍቅርን በተግባር የሚያሳዩ ወንድማማቾች ያሉበት የዚህ ትልቅ ቤተሰብ ክፍል መሆን እንዴት ያለ መብት ነው!”—ዮሐንስ 13:34, 35
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅርቡ የተትረፈረፉ ነገሮች የሞሉባት ምድራዊ ገነት ትመጣለች