ዛሬ ነገ ማለት የጊዜ ሌባ ነው
“ዛሬ ነገ ማለት የጊዜ ሌባ ነው።”— ኤድዋርድ ያንግ፣ በ1742 ገደማ
ቆይ! ይህን ጽሑፍ ማንበብህን አታቁም! ብታቆም ምን ሊሆን እንደሚችል ታውቃለህ። መጽሔቱን ቁጭ ታደርግና “በጣም ጥሩ ርዕስ ነው፤ ግን አሁን የማነብበት ጊዜ የለኝም። በኋላ እመለስበታለሁ” ትላለህ። ያ በኋላ የተባለው ጊዜ ግን ፈጽሞ ሳይመጣ ይቀራል።
ዛሬ ነገ ስለ ማለት የተጻፈውን ይህን ጽሑፍ ለማንበብ ዛሬ ነገ አትበል! ጽሑፉን ለማንበብ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድብህ ገምት። በአምስት ደቂቃ ውስጥ አንብበህ ሳትጨርስ አትቀርም። ለአምስት ደቂቃ ያህል ካነበብክ የዚህን መጽሔት 10 በመቶ ጨርሰሃል ማለት ነው! እስቲ አሁን ሰዓት ያዝና ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድብህ ተመልከት። (እስከ አሁን ባለው ጊዜ ውስጥ እንኳን ሳይታወቅህ 5 በመቶ የሚሆነውን አንብበሃል!)
ዛሬ ነገ ማለት ነውን?
አሁኑኑ ማድረግ የምትችለውን ወይም የሚኖርብህን ነገር ለሌላ ጊዜ ካስተላለፍህ ዛሬ ነገ እያልክ የማመንታት ችግር አለብህ ማለት ነው። በሌላ አባባል አሁን ወይም ዛሬ ማድረግ የምትችለውን ነገር ለነገ ታስተላልፋለህ። ዛሬ ነገ እያለ የሚያመነታ ሰው ቶሎ መደረግ የሚኖርበት አንድን ነገር ለሌላ ጊዜ ያስተላልፋል ማለት ነው።
አንድ አለቃ በበታቹ ያለውን ሠራተኛ ሪፖርት እንዲያቀርብለት ይጠይቃል። ወላጆች ልጃቸው የራሱን ክፍል እንዲያጸዳ ይጠይቃሉ። ሚስት ባልዋን የውኃውን ቧንቧ እንዲጠግን ትጠይቃለች። ሰዎች ሥራውን ለመሥራት ያደረጉት ምንም ጥረት ሳይኖር “በጣም ሥራ በዝቶብኝ ነበር” ወይም “ረሳሁት” ወይም “ጊዜ አልነበረኝም” በማለት የተለያዩ ሰበቦችን ይፈጥራሉ። እውነተኛው ምክንያት ብዙዎቻችን ይበልጥ የሚያስደስቱ ሌሎች ሥራዎች በሚኖሩበት ጊዜ ሪፖርት መጻፍ ወይም ቤት ማጽዳት ወይም ደግሞ ቧንቧ መጠገን ደስ የማይለን ስለሆነ ነው። በዚህም ምክንያት ሥራውን ለሌላ ጊዜ እናስተላል ፋለን።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ሥራዎችን ለሌላ ጊዜ የምናስተላልፈው ዛሬ ነገ እያልን ለመቆየት ፈልገን ላይሆን የሚችልበት ጊዜ እንዳለ ታውቃለህ? አንዲት የንግድ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ መልስ ለመስጠት የሚያስቸግራት ጥያቄ ሲመጣባት ደብዳቤውን ጠረጴዛዋ ላይ “መልስ የሚያስፈልጋቸው” በሚል ፋይል ውስጥ ታስቀምጣለች። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በዚህ ፋይል ውስጥ ያስቀመጠቻቸውን ደብዳቤዎች እንደገና ትመለከታለች። በዚህ ጊዜ ከግማሽ የሚበልጡት ምንም ዓይነት ምላሽ ወይም እርምጃ የማይጠይቁ እንደሆኑ ትገነዘባለች። አንድም በራሳቸው መፍትሔ አግኝተዋል፣ አለበለዚያም ምንም ዓይነት መፍትሔ የማያስፈልጋቸው ሆነዋል። አንድን ነገር ከማዘግየትና ወዲያው ከማድረግ የትኛው እንደሚሻል እርግጠኛ ካልሆንክ ለሌላ ጊዜ የምታስተላልፈውን ነገር ፈጽሞ ሳታደርገው ብትቀር ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ሞክር። ብታደርገው ውጤቱ የተሻለ ይሆናል ወይስ የባሰ?
አሁኑኑ እርምጃ የሚጠይቅ ነገር ቢያጋጥመን እርምጃውን መውሰድ እየቻልን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፋችን ተጨማሪ ችግር የሚፈጥር ከሆነ ዛሬ ነገ እያልን ነው ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል የተበላባቸውን ሳህኖች አዘግይቶ ማጠብ ሥራውን ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል። መኪናን በጊዜው አለመጠገን ቆየት ብሎ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ብልሽት ሊያስከትል ይችላል። የመብራት ወይም የውኃ ሂሳብ በጊዜው አለመክፈል መቀጮ ሊያስከትል አለዚያም እናገኝ የነበረውን አገልግሎት ሊያሳጣን ይችላል። አንዲት ሴት የትራፊክ ቅጣቶችን በጊዜው አለመክፈልዋና፣ የተዋሰቻቸውን የቪዲዮ ክሮችና መጻሕፍት በጊዜው አለመመለስዋ በአንድ ወር ብቻ 300 ብር የሚያህል ተጨማሪ ወጪ አስከትሎባታል!
ሌባውን መያዝ
መሥራት ያለብህን ሥራ ዛሬ ነገ እያልክ የምታዘገየው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ሞክር። የሚከተሉትን ምክንያቶች ተመልከትና በአሁኑ ጊዜ ያልጀመርከውን ወይም ጀምረህ ያልጨረስከውን አንድ ሥራ እስካሁን ያዘገየህበትን ምክንያት ለማወቅ ሞክር:-
ልማድ:-
ሥራውን ሳልሠራ እስከመጨረሻው ጊዜ ብቆይ ለመጨረስ ተጨማሪ ግፊት አገኛለሁ።
በመጨረሻው ሰዓት ላይ ሠርቼ ለመጨረስ የማደርገው ጥድፊያ ያስደስተኛል።
አለቃዬ አንድ ሁለት ጊዜ እስኪያስታውሰኝ እቆያለሁ። ደጋግሞ ካስታወሰኝ በእርግጥም እንዲሠራ የሚፈልገው ሥራ እንደሆነ አውቃለሁ።
በጣም ሥራ ስለሚበዛብኝ ትኩረት የምሰጠው በጣም አሳሳቢ ለሆኑ ነገሮች ብቻ ነው።
ዝንባሌ:-
ሥራውን ለመሥራት ፍላጎቱ ወይም ግፊቱ የለኝም።
አንድ ነገር የምሠራው ሲመስለኝ ወይም ደስ ሲለኝ ብቻ ነው።
ማድረግ የምፈልገው ሌላ ነገር አለ።
ራሴን ተቆጣጥሬ ማሠራት አልችልም።
ፍርሃት:-
ልሠራው የምችል አይመስለኝም።
ሥራውን ለመሥራት በቂ ጊዜ የለኝም።
በጣም ከባድ ሥራ ስለሆነ ረዳት ያስፈልገኛል።
ባይሳካልኝስ? ወይም ሳልጨርሰው ብቀርስ?
ሥራውን ከመጀመሬ በፊት ለሥራው የሚያስፈልጉትን ዕቃዎች በሙሉ ማግኘት አለብኝ።
ሰዎች ሊተቹኝ ወይም የሚያሳፍር ነገር ሊናገሩኝ ይችላሉ።
የተለያዩ ሰዎች መሥራት የሚኖርባቸውን ሥራ ዛሬ ነገ እያሉ የሚያስተላልፉባቸው ሁኔታዎች ይለያያሉ። አንዳንዶች የሚሠሩትን ሥራ በጣም አክብደው ስለሚመለከቱ ዛሬ ነገ እያሉ የሚያመነቱት ሥራውን ከመጀመራቸው በፊት ነው። ሌሎች ሥራውን ይጀምሩና ሲያጋምሱት ለሥራው ያላቸው ስሜት ቀዝቅዞ ሳይጨርሱት ይቀራሉ። ሌሎች ደግሞ ሥራውን ሊጨርሱ ከተቃረቡ በኋላ ሳይጨርሱት ወደ ሌላ ሥራ ይሄዳሉ። (በነገራችን ላይ ጥሩ እየገፋህ ነው። ይህን ርዕስ አጋምሰኸዋል።)
አንድን ሥራ የማትጀምረው ወይም የማትጨርሰው በሦስቱም ምክንያቶች ሊሆን ይችላል። ኔል ፊዮሬ ዘ ናው ሃቢት በተባለው መጽሐፋቸው “አንድን ሥራ በአብዛኛው ዛሬ ነገ እያልክ የምታስተላልፈው በሦስት ዐበይት ምክንያቶች የተነሣ ነው። በደል እንደተፈጸመብህ ሲሰማህ፣ ግራ ስትጋባ ወይም ላይሳካልኝ ይችላል የሚል ስጋት ሲያድርብህ ነው” ብለዋል። ምክንያትህ የትኛውም ቢሆን የችግሩን መነሻ ለማወቅ ከቻልክ ወደ መፍትሔው ተቃርበሃል ማለት ነው።
ሥራዎችን ዛሬ ነገ እያልክ የምታስተላልፍበት ምክንያት ግልጽ ካልሆነልህ ለአንድ ሳምንት ያህል የምትሠራቸውን ሥራዎች በየግማሽ ሰዓቱ መዝግብ። ጊዜህን እንዴት እንደምታሳልፍ እወቅ። አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን በምናከናውንባቸው ጊዜያት መካከል ያሉትን በርካታ ጊዜያት በጣም አስፈላጊ ላልሆኑ ጉዳዮች እንደምናባክን ማወቃችን የችግራችንን መንስዔ ሊጠቁመን ይችላል። ከዚያስ በኋላ?
ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች አስብ
አንድ ሥራ ያለምንም ጥረት ሊሠራ ይችላል ብሎ መጠበቅ መጥፎ ስሜት ሊያሳድር ይችላል። ሥራው ተሠርቶ ማለቅ ወደሚኖርበት ቀን እየተቃረብህ ስትሄድ ውጥረትና ጭንቀት ይሰማሃል። ይህ ዓይነቱ ስሜት እየጨመረ ሲሄድ የፈጠራ ችሎታህ እክል ያጋጥመዋል። በጣም የሚያሳስብህ ነገር ሥራውን መጨረስህ ነው እንጂ በምን መንገድ ባከናውነው ይሻላል የሚለው ጉዳይ አይደለም።
ለምሳሌ ያህል አንድ ንግግር እንድትሰጥ ተመድበሃል እንበል። ንግግሩን ነገ ልትሰጥ ዛሬ ማታ ቁጭ ብለህ ጥቂት ቃሎችን ወረቀት ላይ ታሰፍራለህ። ስለምትናገርበት ርዕሰ ጉዳይ በቂ ጥናትና ምርምር ስላላደረግህ ለጊዜው ትዝ ያለህንና የመጣልህን ነገር ብቻ ትናገራለህ። ምናልባት መጠነኛ ጥረት ብታደርግ ተሞክሮዎችን፣ ድጋፍ ሰጪ ሐሳቦችን ወይም አድማጮችህ ርዕሰ ጉዳዩን እንዲገነዘቡ የሚረዷቸውን ሥዕሎች ለመጨመር ትችል ነበር።
አንድን ሥራ ስናዘገይ የሚከተለው ሌላ ውጤት ነጻ ጊዜ በሚኖረን ወቅት እንኳን ለመዝናናት አለመቻላችን ነው። ያልሠራኸው ሥራ አለ እያለ የሚጎተጉተን ስሜት ወይም ሰው ይኖራል።
ምን ላደርግ እችላለሁ?
የምትሠራቸውን ሥራዎች ዝርዝር ጻፍ። ይህን የምታደርገው ሥራው ከሚሠራበት ቀን በፊት ባለው ምሽት ነው። በሚቀጥለው ቀን ልታከናውን የምትፈልጋቸውን ነገሮች ወረቀት ላይ አስፍር። እንዲህ ስታደርግ የምትዘነጋው ሥራ አይኖርም። በተጨማሪም በሠራሃቸው ነገሮች ላይ ምልክት እያደረግህ ምን ያህል ሥራ እንዳከናወንክ ለማወቅ ትችላለህ። በወረቀት ላይ በዝርዝር ካሰፈርከው ከእያንዳንዱ ሥራ በስተቀኝ ሥራው ሊፈጅ የሚችለውን ጊዜ በግምት ጻፍ። በወረቀት ላይ የምታሰፍረው በቀኑ ውስጥ መሠራት የሚኖርባቸውን ሥራዎች ከሆነ ጊዜውን በደቂቃ ጻፍ። ሰፋ ያለ እቅድ ከሆነ ደግሞ የሚፈጀውን ጊዜ በሰዓት ጻፍ። ይህን ዝርዝር የምታዘጋጀው ሥራው ከሚሠራበት ቀን በፊት ባለው ምሽት ነው። ጥቂት ደቂቃዎች ወስደህ በሚቀጥለው ቀን ልትሠራ የምትፈልጋቸውን ሥራዎች ዝርዝር አዘጋጅ። የቀን መቁጠሪያ ከአጠገብህ አይለይ። ቀጠሮና የሥራ ትእዛዝ ስትቀበል በቀን መቁጠሪያው ላይ ጻፍ።
በማግስቱ ማከናወን የሚኖርብህን ሥራዎች ስታስብ የቀን መቁጠሪያህን አይተህ ሥራዎችህን በአስፈላጊነታቸው መጠን ሀ፣ ለ፣ ሐ እያልክ በቅደም ተከተል አስቀምጥ። አንዳንድ ሰዎች አንድን ሥራ በተሻለ ሁኔታ መሥራት የሚችሉት ጠዋት ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከሰዓት በኋላ ወይም ማታ ነው። ተለቅ ያለውን ሥራ በተሻለ ሁኔታ መሥራት በምትችልበት የቀኑ ክፍል ለማከናወን ፕሮግራም አድርግ። እምብዛም የማትወዳቸውን ሥራዎች ከምትወዳቸው አስቀድም።
የሚፈጅብህን ጊዜ እወቅ። ሁልጊዜ የምትዘገይና የምትጣደፍ ከሆንክ የምትሠራው ሥራ የሚፈጅብህን ጊዜ ለማወቅ ሞክር። አንድን ሥራ ለማከናወን ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅብህ በትክክል ለመገመት መሞከር አለብህ ማለት ነው። የሚያዘገይህ ያልተጠበቀ ችግር ሊያጋጥምህ ስለሚችል ጥቂት ተጨማሪ ደቂቃዎች ጨምር። ከአንዱ ቀጠሮ ወደ ሌላው ቀጠሮ ለመሄድ የሚያስችልህ በቂ ጊዜ መመደብህን አትርሳ። በጉዞ ላይ የምታሳልፈውን ጊዜ መጨመር ያስፈልግሃል። ቦታው ምንም ያህል ቢቀራረብ አንዱን ስብሰባ በ4:00 ሰዓት ጨርሰህ ሌላው ስብሰባ ላይ በ4:00 ሰዓት መድረስ አትችልም። በመካከሉ በቂ ጊዜ እንዲኖር አድርግ።
ሥራህን ለሌሎች አካፍል። ብዙውን ጊዜ አስፈላጊ በማይሆንበት ጊዜም እንኳ ሁሉንም ነገር ራሳችን ለማድረግ እንሞክራለን። ወደ ፖስታ ቤት የሚሄድ ሰው እንዳለ ካወቅን የእኛንም ደብዳቤ አብሮ ሊወስድልን ይችል ይሆናል።
ሥራህን ከፋፍለው። አንዳንድ ጊዜ አንድን ሥራ የማንጀምረው ሥራው እጅግ ግዙፍ ሆኖ ስለሚታየን ይሆናል። ትልቁን ሥራ አነስ አነስ አድርገህ ከፋፍለው። አነስ ያሉትን ሥራዎች ስንጨርስ ምን ያህል ሥራ እንዳከናወንን ለማየት ስለምንችል የሥራውን ሌላ ክፍል ለመጨረስ እንበረታታለን።
በሥራህ ላይ ጣልቃ ሊገቡ ለሚችሉ ነገሮች የቅድሚያ ዝግጅት አድርግ። የስልክ ጥሪ፣ ሊጠይቁን የሚመጡ ሰዎች፣ ደብዳቤዎች፣ ድንገተኛ ችግሮችና እነዚህን የመሳሰሉ በሥራችን ጣልቃ የሚገቡ ነገሮች ያጋጥማሉ። ሥራችንን በቅልጥፍና ለማጠናቀቅ እንፈልጋለን። አንዳንድ ጊዜ ግን አንደኛው ሥራቸውን በጊዜው ማጠናቀቅ ከሚኖርባቸው ሰዎች ጋር ለመሥራት እንገደዳለን። የምንጨነቀው ስለ ሥራችን ቅልጥፍና ብቻ ከሆነ ሌሎች በሥራችን ጣልቃ ሲገቡ እንበሳጫለን። ስለዚህ በሥራህ ላይ ጣልቃ ለሚገቡ ሁኔታዎች በቂ ዝግጅት አድርግ። ሳይታሰቡ ለሚያጋጥሙ ሁኔታዎች በየዕለቱ በቂ ጊዜ መድብ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ ትርፍ ጊዜ እንደሚኖርህ ስለምታውቅ ሳትጨነቅ ሁኔታውን እንዳመጣጡ ልትመልስ ትችላለህ።
ለራስህ ወሮታ የሚሆን ነገር አድርግ። ፕሮግራም በምታወጣበት ጊዜ 90 ደቂቃ ለሚያክል ጊዜ አለፋታ ወይም በትኩረት ለመሥራት እቅድ ማውጣት ይኖርብሃል። ለሥራው ዝግጅት የምታደርግበት ተጨማሪ ጊዜ መመደብህን አትርሳ። ሥራውን ከጀመርክና አንድ ሰዓት ተኩል ለሚያክል ጊዜ ስትሠራ ከቆየህ በኋላ አጭር እረፍት መውሰድ ሊያስፈልግህ ይችላል። የምትሠራው ቢሮ ውስጥ ከሆነ ለጥቂት ጊዜ ሥራውን ቆም አድርገህ ተንጠራራ ወይም አስብ። የምትሠራው በውጭ ከሆነ ጥቂት የሚበላ ወይም የሚጠጣ ነገር ውሰድ። ላከናወንከው ሥራ ወሮታ የሚሆን ነገር አድርግ።— መክብብ 3:13
ይህን ርዕስ አንብበህ እስክትጨርስ የወሰደብህ ጊዜ አምስት ደቂቃ ያህል ነው። በዚህ አያያዝህ ከቀጠልክ እያሻሻልክ ነው ማለት ነው!