የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
የምታምንበት ነገር ለውጥ ያመጣልን?
“ሰው ለማመን የሚፈልገው እውነት እንዲሆንለት የሚፈልገውን ነው”—ፍራንሲስ ቤከን፣ 1561-1626 እንግሊዛዊ ጸሐፊና መራሔ መንግሥት
በሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶች ረገድ አንድ ሰው ‘አንድ የበላይ አካል አለ’ ብሎ እስካመነና ሌሎች ሰዎችን እስከወደደ ድረስ በምንም ነገር ቢያምን ለውጥ አይኖረውም ብለው የሚያምኑ ሰዎች ብዙ ናቸው። አንዳንዶች የተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖች ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱላቸውን አምላክን፣ ዓላማውንና የአምላክን አምልኮ የሚመለከቱ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ አመለካከቶች ያዩና ልዩነቶቹ አንድ ሰው ከሚለብሳቸው የተለያዩ የልብስ ዓይነቶች የማይለዩ ውጪያዊ ልዩነቶቹ ብቻ ናቸው ብለው ይደመድማሉ። እንዲያውም አንዳንዶች እንደነዚህ ላሉት ልዩነቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች የእውነተኛውን ክርስትና መንፈስ የሳቱ እንደሆኑ ይሰማቸው ይሆናል።
ቅዱሳን ጽሑፎች ተገቢ ያልሆኑ በሃይማኖታዊ ትምህርቶች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች እንዳሉ ያመለክታሉ። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክቱ ላይ “የማያቋርጥ ክርክር [የ1980 ትርጉም]” ስለሚቆሰቁሱ ሰዎች ተናግሯል። ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች “ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ” እንደሚናፍቁ ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 6:4, 5) ጢሞቴዎስንም “ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ” ብሎታል። ጉባኤዎችንም ምንም የማይረባ ስለሆነ “በቃል እንዳይጣሉ” እንዲያሳስብ ነግሮታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:14, 23) በጊዜያችን ከሚደረጉ ሃይማኖታዊ ክርክሮች ብዙዎቹ ከዚህ መግለጫ ጋር የሚስማሙ ሆነው በመገኘታቸው ጊዜ ከማባከን ሌላ ምንም ፋይዳ የሌላቸው ሆነዋል።
ታዲያ እንዲህ ሲባል በሃይማኖታዊ እምነቶች ላይ የሚደረግ ውይይት በሙሉ ዋጋ የለውም ማለት ነውን? አንዳንድ ልብሶች የማይለበሱ ዓይነቶች ስለሆኑ ብቻ ማንኛውንም ዓይነት ልብስ አንለብስም እንደማንል የታወቀ ነው። እንላለን እንዴ? ታዲያ አንዳንድ መሠረተ ትምህርታዊ ጥያቄዎች ውይይት ሊደረግባቸው የማይገቡ በመሆናቸው ብቻ ማንኛውም ዓይነት በሃይማኖታዊ እምነቶች ላይ የሚደረግ ውይይት አስፈላጊ አይደለም ብለን የምንተወው ለምንድን ነው? ጳውሎስ የመሠረተ ትምህርቶችን ጉዳይ በጣም አክብዶ እንደተመለከተ ከላይ በተጠቀሱት የጳውሎስ ቃላት ዙሪያ ያለው ሐሳብ ያሳያል። የሐሰት ትምህርቶች አንድን ሰው ከእምነት ሊያወጡ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ካስጠነቀቀ በኋላ ጢሞቴዎስን “ማንም ልዩ ትምህርት እንዳያስተምር” እንዲያዝ አሳስቦታል። (1 ጢሞቴዎስ 1:3-7፤ 4:1፤ 6:3-5፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:14-18, 23-26፤ 4:3, 4) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የሚያምኑት ነገር ምንም ለውጥ የማያመጣ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ጠንከር አድርጎ እንደማይናገር የታወቀ ነው።
ታዲያ በመሠረተ ትምህርቶች ላይ ከሚነሱት ጥያቄዎች እንድንርቅ የመከረው ለምንድን ነው? በጳውሎስ ዘመን ‘አእምሮአቸው የጠፋባቸውና እውነትን የተቀሙ’ አንዳንድ ሰዎች የሌሎችን እምነት ለመገልበጥ ሲሉ ብቻ የመሠረተ ትምህርት ጥያቄዎችን ያነሱ ስለነበረ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:5) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ስለ ሃይማኖታዊ እምነቶች ከመነጋገር እንዲርቅ የመከረው እነዚህ ብልሹ ሰዎች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ረገድ ብቻ ነው።
እምነት በምግባር ላይ ተጽእኖ ያሳድራል?
ይሁን እንጂ አንዳንዶች ሃይማኖታዊ እምነቶቻችን በማንነታችን ላይ፣ ማለትም በግል ባሕርያችንና ምግባራችን ላይ ብዙ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ ወይ ብለው ይጠይቃሉ። ምግባርና እምነት ሁለት የተለያዩና ምንም ዓይነት ዝምድና የሌላቸው፣ እንደየለባሹ ምርጫ ተነጣጥሎ ወይም በአንድነት ሊለበስ እንደሚችል ኮትና ሱሪ ሆነው ሊታዩአቸው ይችላሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እምነትና ምግባር በአንድነት ብቻ እንጂ ተነጣጥሎ ሊለበስ እንደማይችል ኮትና ሱሪ ሆኖ ተገልጿል።
መጽሐፍ ቅዱስ በምናምነው እምነትና በማንነታችን መካከል ቀጥተኛ የሆነ ተዛምዶ እንዳለ ያመለክታል። አቅጣጫውን የሳተ እምነት ምግባርን ሊነካ እንደሚችል በኢየሱስ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ራሳቸውን ያመጻድቁ የነበሩ ፈሪሳውያን ማስረጃ ሊሆኑ ይችላሉ። (ማቴዎስ 23:1-33፤ ሉቃስ 18:9-14) በአንጻሩ ቆላስይስ 3:10 (NW) “የፈጠረውን መልክ እንዲመስል በትክክለኛ እውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ስብዕና ልበሱ” ሲል አጥብቆ ያሳስባል። አምላካዊ አኗኗር የመምራት ችሎታ ስለ አምላክ ትክክለኛ የሆነ እውቀት ከማግኘት ጋር እንደተዛመደ ልብ በሉ።
በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 20 ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኘውና “ትክክለኛ እውቀት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል የተስተካከለ፣ የተሟላና ፍጹም የሆነን እውቀት ያመለክታል ብለዋል። የግሪክኛ ምሁር የሆኑት ናትናኤል ከልቨርዌል “ከዚህ በፊት አውቀው ከነበረ ነገር ጋር በይበልጥ መተዋወቅን፣ ከዚህ በፊት ከሩቅ ያየሁትን ነገር ይበልጥ ትክክል በሆነ መንገድ ማየትን” ያመለክታል። ስለዚህ አንድ የጌጣ ጌጥ ሠሪ የአንድን የከበረ ዕንቁ ዋጋና ጥራት ለመተመን በጥንቃቄና በቅርብ እንደሚመረምር ሁሉ አንድም ክርስቲያን የሚያገለግለውን አምላክ አጣርቶ፣ በትክክልና በተሟላ መንገድ ለማወቅ የአምላክን ቃል መመርመር ይኖርበታል። ይህም የአምላክን ባሕርይ፣ ዓላማ፣ የሥነ ምግባር ደረጃዎችና ‘የጤናማ ቃላት ሥርዓት’ ክፍል የሆኑትን ትምህርቶች በሙሉ ጠንቅቆ ማወቅን ይጨምራል። ይህ እንዲሁ ‘አንድ የበላይ አካል አለ’ ብሎ ከማመን ፈጽሞ የተለየ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 1:13
አንድ ሰው አምላክን ከሩቅ ብቻ በሚያውቅበት ጊዜ የሚያፈራቸው ፍሬዎች በመንፈስ አነሳሽነት ለሮሜ ሰዎች በተጻፈው መልእክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ተገልጸዋል። ይህ ጥቅስ የሚናገረው “እግዚአብሔርን እያወቁ ስላልወደዱ” ሰዎች ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የተሳሳቱ እምነቶቻቸው ያስከተሉባቸውን ውጤቶች እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዓመፃ ሁሉ፣ ግፍ፣ መመኘት፣ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፣ ነፍስ መግደልን፣ ክርክርን፣ ተንኰልን፣ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፣ ሐሜተኞች፣ አምላክን የሚጠሉ፣ የሚያንገላቱ፣ ትዕቢተኞች፣ ትምክህተኞች፣ ክፋትን የሚፈላለጉ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያስተውሉ፣ ውል የሚያፈርሱ፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ምሕረት ያጡ ናቸው።”—ሮሜ 1:21, 28-31
እነዚህ ሰዎች የነበሯቸው እምነቶች ክርስቲያናዊ አኗኗር ለመምራት ባላቸው ችሎታ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አሳድረው እንደነበረ አያጠያይቅም። ዛሬም በተመሳሳይ እምነትና ምግባር በስፌት ሳይሆን በአንድ ድር ተጋጥሞ እንደተሠራ ልብስ የማይለያዩ ሆነዋል። ስለዚህ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ሃይማኖታዊ እምነቶቻቸው በጠራ እውነትና በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ” የአምላክ ፈቃድ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:4
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፈሪሳዊው ያሳየው ራስን የማመጻደቅ ባሕርይ እምነቱን በቀጥታ የሚያንጸባርቅ ነው