የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች ማሟላት በጣም አስቸጋሪ ነውን?
“አምላክ ሰዎችን በኢንች አይለካም።”—የስኮትላንዳውያን ጥንታዊ ምሳሌ።
የትምህርት ቤት ፈተና፣ ሥራ ለመግባት የሚደረግ ቃለ መጠይቅና የሕክምና ምርመራ በሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ከሚያስከትሉ አንድ ሰው የሚለካባቸው ሁኔታዎች ጥቂቶቹ ናቸው። ሆኖም ብዙ ሰዎች አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች በየዕለቱ እያሟሉ መኖር እንደማይችሉ ሆኖ ይሰማቸዋል። የአንተም እምነት እንደዚህ ነውን? አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች ማሟላት ትችላለህን?
ለመልሱ ይረዳን ዘንድ አስቀድመን አምላክ እርሱን ለሚያመልኩ ሰዎች ያወጣቸውን ብቃቶች እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን በግልጽ አስፍሯል። (መዝሙር 119:105) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዙንም ጠብቅ፤ ምክንያቱም ይህ የሰው ዋና ተግባሩ ነው” በማለት ደምድሟል። (መክብብ 12:13 የ1980 ትርጉም) ነቢዩ ሚክያስ “እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” ብሏል።—ሚክያስ 6:8
የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ” እና “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ከሚሉት ትእዛዛት የሚበልጥ ትእዛዝ እንደሌለ ተናግሯል። (ማርቆስ 12:30, 31) በተጨማሪም ትእዛዛቱን ሁሉ ስንጠብቅ አምላክን እንደምንወደው እናሳያለን።—1 ዮሐንስ 5:3
በቀላል አነጋገር ሰዎች አምላክን መውደድና ማክበር፣ ትእዛዛቱን መጠበቅ፣ ሰዎችን እኩል ማየት፣ ለሁሉም ሰው ደግ መሆንና ኩራትን ማስወገድ አለባቸው። እነዚህን ብቃቶች ማሟላት የማይቻል ነገር ነውን?
አምላክ ድካማችንን ይረዳልናል
አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች ሰዎች እንዲያሟሉ መጠበቁ ተገቢ ነው። ሆኖም ሐቁን ለመናገር፣ እነዚህን ብቃቶች ሙሉ በሙሉ የሚያሟላ ሰው ይኖራልን? ከአባታችን ከአዳም አለፍጽምና ስለወረስን እነዚህን ብቃቶች ሙሉ በሙሉ የሚያሟላ ሰው እንደሌለ የታወቀ ነው። (ሮሜ 5:12) በዚህ የተነሳ ስሕተት መሥራት ይቀናናል። ሆኖም ይህ ሁኔታ አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ከማገልገል አያግደንም።
ለምሳሌ ያህል መኪና መማር ያለውን ውጣ ውረድ ተመልከት። ፈተናውን ለማለፍ የሚያበቃ ችሎታ ለማግኘት ትምህርቱን ሳያቋርጡ በንቃት መከታተልና ጊዜን መሥዋዕት ማድረግ ይጠይቃል። መንጃ ፈቃድ ካገኘን በኋላ እንኳ የማሽከርከር ችሎታችንን ማሻሻል ይኖርብናል። ልምድ እያገኘን ስንሄድ ጥሩ ችሎታ ይኖረናል። ይሁን እንጂ ፍጹም የሆኑ አሽከርካሪዎች የሉም!
ሆኖም አምላክ ድካማችንን የሚረዳልን መሆኑ ያስደስታል። ምክንያታዊ ነው፤ የማንችለውን ነገር አይጠይቅብንም ወይም ስሕተቶቻችንን አይለቅምም። ድካማችንንና ጉድለታችንን ይረዳልናል። ከባድ ኃጢአት የፈጸመው ንጉሥ ዳዊት “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም” በማለት አስታውቋል። እንደዚህ የሚያደርገው ለምንድን ነው? ‘ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ ስላጠነከረ’ ነው። ይሖዋ ኃጢአት እንደምንሠራ ቢያውቅም “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ” መተላለፋችንን ከእኛ ለማራቅ ዝግጁ ነው።—መዝሙር 103:10-14
ተስፋ አትቁረጥ
አምላክን በቅንዓት የሚያመልክ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል:- “አንዳንዴ ሐዘን ሲሰማኝ አምላክ የሚጠይቃቸውን ብቃቶች ማሟላት አልችልም ብዬ እደመድማለሁ። ሆኖም ከሌላው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ብሩህ አመለካከት በምይዝበት ጊዜ አምላክ በሚፈልግብኝ መንገድ መኖር እንደምችል ይሰማኛል። ነገር ግን እንዲህ ማድረጉ ቀላል አይደለም!” እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። እንዲህ ያለው ስሜት የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም።
ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና . . . በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ። እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ!” ሆኖም አምላክ የሚጠይቀው ነገር በጣም አስቸጋሪ ነው ብሎ አልደመደመም። ምክንያቱም በመቀጠል እንደዚህ ብሏል:- “ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ፣ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ እገዛለሁ።” (ሮሜ 7:21-25) ስለዚህ ኃጢአተኛ ቢሆንም አምላክን ማስደሰት እንደሚችል ተሰምቶታል።
አፍቃሪ ፈጣሪያችን ይሖዋ ውድ ልጁ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛዊ መሥዋዕት ባስገኛቸው ጥቅሞች አማካኝነት በደላችንንና ድካማችንን ይቅር ይለናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተሰሪያ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ከአምላክ ጋር ወዳጆች ለመሆን የሚያስችለንን ብቃት እንዳናሟላ ኃጢአት የፈጠረው እንቅፋት የክርስቶስ መሥዋዕት ባለው ኃይል ተወግዷል። በዚህ መሠረት ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችል አጋጣሚ እንደገና ተከፍቷል።
አምላክ “የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር” ስለሚቀመጥ ይህን ፍቅራዊ ዝግጅት በትሕትና መቀበል የኃጢአት ይቅርታ ያስገኛል። (ኢሳይያስ 57:15) መንፈሳችንን እንዲያነቃቃልን በእርሱ ላይ መታመን እንችላለን። ‘ችግረኛን ከመሬት እንደሚያነሳ’ ቃል ገብቷል። አምላክን ሙሉ በሙሉ መታዘዝ ሲያቅተን ዝም ብለን በጭንቀት መዋጥ የለብንም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የሚጠይቃቸውን ብቃቶች አሟልተን ለመኖር ያደረግነውን ጥረት ፈጽሞ እንደማይረሳ ልንተማመን እንችላለን።—መዝሙር 113:7፤ ዕብራውያን 6:10-12
ምንም እንኳ ትግል የሚጠይቅ ቢሆንም አምላክን የሚያስደስት ነገር በማድረግህ ደስተኛ ትሆናለህ። ለአምላክ ያደሩ መሆን አንተም ሆንክ አብረውህ የሚኖሩ ሰዎች በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ይበልጥ መቋቋም እንድትችሉ ይረዳችኋል። ስለወደፊቱም ጊዜ አስብ። በአሁኑ ጊዜ አምላክ የሚጠይቃቸውን ብቃቶች አሟልቶ ለመኖር ጥረት ማድረግ በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል።—ኢሳይያስ 48:17፤ ሮሜ 6:23፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:8
ልምድ ያላቸው ተራራ ወጪዎች ተራራው ጫፍ ላይ ሲደርሱ ጉዟቸውን ማጋመሳቸው እንደሆነ ይገነዘባሉ። ገና ተራራውን በሰላም መውረድ ይኖርባቸዋል። በተመሳሳይም አምላክን የሚፈሩ ሰዎች አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች ማሟላትና ዘወትር ከእነርሱ ጋር ተስማምተው መኖር አለባቸው።—ሉቃስ 21:19፤ ያዕቆብ 1:4
አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች ማሟላት በጣም አስቸጋሪ እንዳልሆነ በማወቅህ ተጽናና። አንዳንድ ጊዜ ብቃቶቹን ሙሉ በሙሉ ሳታሟላ ስትቀር ይቅርታ ጠይቀው። የሚሰጥህን ፍቅራዊ ድጋፍ ተጠቀምበት። (መዝሙር 86:5) ስለዚህ በይሖዋና በልጁ እርዳታ አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች ማሟላትና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ትችላለህ።—ምሳሌ 12:2