ረዥም ዕድሜ ለመኖር ያለን ተስፋ ምንድን ነው?
“ሥጋ ለባሽ ሰው ዕድሜው አጭር ነው፤ ያውም ቢሆን በመከራ የተሞላ ነው።”—ኢዮብ 14:1 ላይ ተመዝግበው የሚገኙ የኢዮብ ቃላት፣ “የ1980 ትርጉም”
የሕይወት አጭርነት በብዙ ሥነ ግጥሞች ተገልጿል። ልክ እንደ ኢዮብ አንድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ጸሐፊም “ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁ” ብሏል።—ያዕቆብ 4:14
አንተም ሕይወት በሚያሳዝን ሁኔታ አጭር መሆኑን ተገንዝበሃልን? ዊልያም ሼክስፒር 400 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት “ጥፊ፣ ጥፊ፣ አንቺ አጭር ጧፍ! ሕይወት እንደ ጥላ አላፊ ነው” ሲል ጽፏል። ባለፈው መቶ ዘመን ደግሞ አንድ የአሜሪካ ሕንዳውያን የጎሣ መሪ “ሕይወት ምንድን ናት?” ካሉ በኋላ “በማታ ታይታ ወዲያው እንደምትጠፋ የእሳት እራት ናት” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
የሰው ልጆች ዕድሜ እስከ ስንት ዓመት ሊደርስ ይችላል? ከ3,500 ዓመታት በፊት ነቢዩ ሙሴ በራሱ ዘመን የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ዕድሜያችን ሰባ ዓመት ነው፤ ቢበዛም ሰማኒያ ዓመት ነው፤ እርሱም በመከራና በሐዘን የተሞላ ነው፤ ዕድሜአችን በቶሎ ያልቃል፤ እኛም እናልፋለን።”—መዝሙር 90:10 የ1980 ትርጉም
ሰባ ዓመት 25,567 ቀን ብቻ ነው። ሰማንያ ዓመት ደግሞ 29,219 ቀን ይሆናል። በእርግጥም በጣም አጭር ጊዜ ነው! ታዲያ የሰው ልጆችን ዕድሜ ለማርዘም ይቻል ይሆን?
ከሕክምና ሳይንስ እርዳታ ሊገኝ ይችል ይሆን?
ሳይንስ መጽሔት “በ1900 የአንድ ሰው አማካይ በሕይወት የመቆያ ዘመን [በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ] 47 ዓመት የነበረ ሲሆን በ1988 ወደ 75 ዓመት ከፍ ሊል ችሏል” ብሏል። የጤና እንክብካቤና የአመጋገብ ሁኔታ በመሻሻሉ ምክንያት በሕፃንነታቸው የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በእጅጉ በመቀነሱ በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ሰዎች ሙሴ በገለጸው ዕድሜ ላይ ለመድረስ ችለዋል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሰዎች የሚኖሩበት የሕይወት ዘመን ከዚህ የበለጠ ከፍተኛ መሻሻል ያሳያል ብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላልን?
ስለ እርጅና በርካታ ምርምር ያደረጉት ሌኦናርድ ሃይፍሊክ ሃው ኤንድ ኋይ ዊ ኤጅ (የምናረጀው እንዴትና ለምንድን ነው?) በተባለው መጽሐፋቸው “በዚህ መቶ ዘመን በባዮሜዲካል መስክ በርካታ ምርምር በመደረጉና የተሻሻሉ የሕክምና ዘዴዎች ሥራ ላይ በመዋላቸው የሰው ልጆች አማካይ ዕድሜ ከፍ ሊል ችሏል። ይሁን እንጂ ይህ ጭማሪ የተገኘው ከቀድሞው የበለጡ ብዙ ሰዎች ለሰው ልጆች እስከተወሰነው ከፍተኛ የዕድሜ ጣሪያ እንዲደርሱ ለማድረግ በመቻሉ ብቻ ነው” ብለዋል። ስለዚህ “የሰው ልጆች ከዕድሜያቸው በፊት የመሞት አጋጣሚ ቀነሰ እንጂ ዕድሜያቸው አልጨመረም። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ወሳኝነት አለው።”
ታዲያ የሰው ልጆች “የተወሰነ ከፍተኛ የዕድሜ ጣሪያ” ምን ያህል ነው? አንዳንዶች በአሁኑ ዘመን ከ115 ዓመት በላይ የኖረ ሰው አለ ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም ይላሉ። ሳይንስ መጽሔት ግን “እስከ 1990 ድረስ በእርግጠኝነት የታወቀው የሰዎች የመጨረሻ ከፍተኛ ዕድሜ 120 ዓመት ነው” ብሏል። በ1995 መጀመሪያ ላይ የፈረንሣይ ጤና ሚኒስቴር ከበርካታ ጋዜጠኞችና ፎቶ ግራፍ አንሺዎች ጋር ሆነው በአርል፣ ፈረንሣይ በሚገኙት ዣን ካልማን 120ኛ የልደት በዓል ላይ ተገኝተዋል። ሙሴም የተለመደውን የሰዎች ዕድሜ አልፎ ለ120 ዓመት ኖሯል።— ዘዳግም 34:7
ታዲያ የሳይንስ ሊቃውንት ሰዎች ይህን ያህል ወይም ከዚህ የሚበልጥ ዕድሜ እንዲያገኙ ለማስቻል ተስፋ ይሰጣሉን? አብዛኞቹ አይሰጡም። በዲትሮይት ኒውስ ጋዜጣ ላይ የወጣ አምድ “ተመራማሪዎች የሰው ልጆች ከፍተኛ አማካይ ዕድሜ 85 ዓመት ሊሆን ይችላል” ብለዋል። በእርጅና ጉዳይ ላይ እውቅ ሊቅ የሆኑት ኤስ ጄይ ኦልሻንስኪ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ሰዎች የ85 ዓመት ዕድሜያቸውን ካለፉ በኋላ የተለያዩ ብልቶቻቸው ሥራቸውን ስለሚያቆሙ ይሞታሉ። መተንፈስ ያቆማሉ። በመሠረቱ የሚሞቱት በእርጅና ምክንያት ነው። ለዚህ ደግሞ መድኃኒት የለውም። የሰው ልጆች ሴሎች እንዳያረጁ ለማድረግ ካልተቻለ የሰው ልጆች ዕድሜ በፍጥነት ያድጋል ብሎ ተስፋ ማድረግ አይቻልም።”
ሳይንስ መጽሔት “የሰው ልጆች የዕድሜ ጣሪያ ላይ ሳንደርስ የቀረን አይመስልም። ከእንግዲህ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል ተብሎ አይታሰብም” ብሏል። ለሰዎች መሞት ምክንያት የሚሆኑትን ነገሮች በሙሉ ለማስወገድ ቢቻል እንኳን የሰዎች ዕድሜ ጣሪያ ከ20 ዓመት የበለጠ ከፍ እንደማይል ተነግሯል።
ስለዚህ ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት የሰውን የዕድሜ ርዝመት እንግዳ እንደሆነ ወይም ሊለወጥ እንደሚችል ነገር አድርገው አይመለከቱም። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ከዚህ ለበለጠ ዘመን መኖራቸው አይቀርም ብሎ ማመን ምክንያታዊ የሚሆነው ለምንድን ነው?