ለምን ያህል ጊዜ መኖር ትችላለህ?
አብዛኞቻችን በሕይወት ጎዳና ላይ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ለመቀበል አናመነታም። ያም ሆኖ ግን በሕይወት መኖራችን ያስደስተናል። በልጅነት ጊዜያችን ብቻ ወይም አጭር ጊዜ በመኖር አንረካም። ለብዙ ዓመታት መኖር እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ ሞት ሊቀር የማይችል ነገር ይመስላል። አይቀርም እንዴ?
የምንሞትበትን ቀን ማዘግየት ይቻላልን? ሕይወታችን ሊራዘም ይችላልን?
የተራዘመ ሕይወት?
በ1990 አንድ የዜና ዘገባ የሰውን ሕይወት ወደ “አንድ መቶ አሥር ዓመት” ማራዘም የሚቻልበት መንገድ መገኘቱን አስታውቆ ነበር። ይህ አባባል የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱሱን መዝሙራዊ የሙሴን አነጋገር በተዘዋዋሪ መንገድ መጥቀሱ ነበር:- “የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፣ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፣ እኛም እንገሠጻለንና።” (መዝሙር 90:10) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው አማካይ ዕድሜ 70 ወይም 80 ዓመት ነው ይላል። ነገር ግን በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው እኖራለሁ ብሎ ሊጠብቅ የሚችለው ስንት ዓመት ነው?
በዓለም ጤና ድርጅት የታተመ አንድ ዘገባ በ1992 ዓለም አቀፉን አማካይ ዕድሜ 65 ዓመት ላይ አድርሶት ነበር። እንደ ጤና ድርጅቱ አባባል አማካዩ ዕድሜ “የሕፃናት መቀጨት እየቀነሰ ስለሚሄድ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ በአራት ወር እያደገ ይሄዳል።” የሕክምና ተአምር ተፈጥሮ ከ50 ዓመት ዕድሜ በፊት ማንም ሰው እንዳይሞት ቢደረግ እንኳ ታይም መጽሔት በአሜሪካን አገር “በሰው ሕይወት ላይ የሚጨመረው አማካይ ዕድሜ 3 ዓመት ተኩል ብቻ ይሆን ነበር” ይላል።
ሕይወት ለምን አጭር ሆነ?
በኔዘርላንድ በሚገኘው የኤክስፐሪመንታል ጄሮንቶሎጂ ኢንስቲትዩት ውስጥ የሞሊኪውላር ባዮሎጂ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ያን ፈክ አንዳንድ በሽታዎች ከሰብአዊው የአካል ሴሎች ጉድለት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሁሉ የእርጅና ሁኔታም ከዘር በተወረሱ ነገሮች የሚነካ ይመስላል በማለት ይከራከራሉ። አንዳንድ ተመራማሪዎች እያረጀን ስንሄድ “ጥቂት ዋና ዋና ጂኖች” መተካት ቢችሉ ኖሮ ረዘም ያለ ጊዜ መኖር እንችል ነበር ብለው ያምናሉ። ሌሎች እንደዚህ የመሰለውን ሐሳብ “ችግርን አቃልሎ መመልከት ነው” ብለውታል።
ያም ሆነ ይህ ታይም መጽሔት እንደዘገበው ሳይንቲስቶች “በሰብአዊ አካል ውስጥ ያሉ ሴሎች ከዚህ አትለፍ የሚል በተፈጥሮ የተቀመጠ የተወሰነ ፕሮግራም ያላቸው ይመስላል” ብለው አምነዋል። “ለሁልጊዜው መኖር እንደምንችል ሆነን ነው የተሠራነው” ብለው የሚያምኑ ሰዎች እንኳ “አንድ የተሳሳተ ነገር አለ” ብለው ለማመን ተገደዋል። ለ65፣ ለ70፣ ወይም ለ80 ወይም ከዚያ ትንሽ በለጥ ለሚል ጊዜም ብንኖር መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ሕይወታችን በሞት “ይቀጫል”።
ይሁን እንጂ ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ በአንደኛው መቶ ዘመን በልበ ሙሉነት እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል:- “የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው።” (1 ቆሮንቶስ 15:26) ሞት የሚጠፋው እንዴት ነው? ሞት የሚጠፋም ቢሆን እንኳ በአሁኑ ጊዜ አንድ የምታፈቅረው ሰው ቢሞት ኀዘንህን እንዴት ልትቋቋመው ትችላለህ?