ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚደረገው ጥረት ሊሳካ የሚችለው እንዴት ነው?
አንዳንዶች በአዲሱ ሺህ ዓመት የሰው ልጅ ዕድሜን ለማራዘም በሚያደርገው ጥረት አንድ ዓይነት እመርታ ላይ ይደርሳል የሚል ትልቅ ተስፋ አላቸው። እንዲህ ዓይነት ተስፋ ካላቸው ሰዎች መካከል ዶክተር ሮናልድ ክላትዝ ይገኙበታል። ሰብዓዊ ሕይወትን ለማራዘም ምርምር የሚያደርጉ ሐኪሞችንና ሳይንቲስቶችን ያቀፈው አሜሪካን አካዳሚ ኦቭ አንታይ-ኤጂንግ ሜዲሲን የተባለው ድርጅት ፕሬዚዳንት ናቸው። እሳቸውም ሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው ረጅም ዕድሜ የመኖር ዕቅድ አላቸው። “ቢያንስ ቢያንስ” ይላሉ ዶክተር ክላትዝ “130 ዓመት ለመኖር አስባለሁ። እርጅና ሊቀር የሚችል ነገር እንደሆነ እናምናለን። በአሁኑ ጊዜ ተፈጥሯዊ እንደሆነ ተደርጎ የሚታየውን አካል ቀስ በቀስ እየተዳከመ እንዲሄድ የሚያደርገውን በሽታ ማለትም እርጅናን ለማዘግየት፣ ለማስቆም አልፎ ተርፎም አካልን ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ አለ።” ዶክተር ክላትዝ ራሳቸው ዕድሜን ለማስረዘም በሚያደርጉት ፍልሚያ በቀን ወደ 60 የሚጠጉ የመድኃኒት እንክብሎችን ይወስዳሉ።
የሆርሞን ሕክምናና ጀነቲክስ —ተስፋ ሰጪ ናቸውን?
ተስፋ ሰጪ ሆኖ የተገኘው አንዱ መስክ የሆርሞን ሕክምና ነው። ዲ ኤች ኢ ኤ በመባል በሚታወቀው ሆርሞን አማካኝነት በቤተ ሙከራ እንስሳት ላይ የተደረጉ ሙከራዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ የእርጅናን ሂደት ማዘግየት የሚቻል ይመስላል።
አፍቶንብላደት የተባለው የስዊድን ዕለታዊ ጋዜጣ በዴንማርክ በኦርሁስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሱረሽ ሮቶን ኪንቲን የተባለውን የእፅዋት ሆርሞን በተመለከተ እንደሚከተለው ሲሉ መናገራቸውን ጠቅሶ ነበር:- “ኪንቲን በተባለው የእፅዋት ሆርሞን የዳበሩ የሰው ቆዳ ሕዋሶች በዕድሜ መግፋት ምክንያት ምንም ለውጥ እንደማይታይባቸው በቤተ ሙከራችን የተካሄዱ ሙከራዎች ያሳያሉ። ምንጊዜም ወጣት እንደሆኑ ይኖራሉ።” በዚህ ሆርሞን ሙከራ የተደረገባቸው ነፍሳት ከ30 እስከ 45 በመቶ ከተለመደው ዕድሜያቸው በላይ እንደሚኖሩ ይነገራል።
ሜላቶኒን በተባለው ሆርሞን የተደረገው ሙከራ ደግሞ የአይጥን ዕድሜ 25 በመቶ ማራዘም ችሏል። እንዲያውም አይጧ ይበልጥ ወጣት፣ ጤናማና ንቁ ሆና ታይታለች።
የሰውነትን እድገት የሚቆጣጠረው (hGH) የተባለው ሆርሞን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የሚያምኑ ሰዎች ይህ ሆርሞን ቆዳን በማለምለም፣ ጡንቻን በማዳበር፣ የጾታ ስሜትን ከፍ በማድረግ፣ የደስታ ስሜት በመፍጠር፣ አእምሮን ንቁ ለማድረግና አፍላ የወጣትነት ስሜት እንዲመለስ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይናገራሉ።
ብዙዎች ደግሞ ፊታቸውን ወደ ጀነቲክስ ያዞራሉ። ሳይንቲስቶች ጂኖችን በመጠቀም የወስፋትን ወይም የድቡልቡል ትልን ዕድሜ መቆጣጠር ይቻላል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። እንዲያውም የአንዳንዶቹን ትሎች ዕድሜ ስድስት ጊዜ እጥፍ ማራዘም ችለዋል። ይህም በሰዎች አካል ውስጥ ተመሳሳይ ጂኖችን ፈልጎ በማግኘት ተመሳሳይ ውጤት ላይ መድረስ ይቻላል የሚል ተስፋ ፈንጥቋል። ታይም መጽሔት በሚግል ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ዶክተር ሲግፍሬድ ሄክሚ “የሰዎችን ዕድሜ የሚቆጥሩትን ሁሉንም ጂኖች ማግኘት ብንችል ወደኋላ ትንሽ በማዘግየት ዕድሜን ማራዘም እንችላለን” ሲሉ መናገራቸውን ጠቅሶ ነበር።
አንድ ሕዋስ በተባዛ ቁጥር በሃብለበራሂ (chromo-somes) ጫፍ ላይ የሚገኘው ቴሎሜር የተባለው ክፍል እያጠረ እንደሚሄድ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ከረጅም ጊዜ በፊት ደርሰውበታል። ቴሎሜር ከቁመቱ 20 በመቶ ገደማ ካጠረ የሕዋስ የመባዛት ችሎታ ይቋረጥና በመጨረሻ ሕዋሱ ይሞታል። ቴሎሜሬዝ የተባለው ኤንዛይም ቴሎሜር ሙሉ ቁመቱን መልሶ እንዲያገኝ በማድረግ ሕዋሱ መባዛቱን እንዲቀጥል ያስችለዋል። ይህ ኤንዛይም በአብዛኞቹ ሕዋሶች ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም ምንም ሥራ አያከናውንም። ሆኖም ገቢር ቴሎሜሬዝ (active telomerase) የተባለውን ኤንዛይም በአንዳንድ ሕዋሶች ውስጥ በተሳካ ሁኔታ መክተት የተቻለ ሲሆን ይህም ሕዋሶቹ እንዲያድጉና ከወትሮው በበለጠ መጠን እንዲባዙ አድርጓቸዋል።
ይህም ከእርጅና ጋር በተያያዘ የሚመጡ በሽታዎችን ለመዋጋት ትልቅ በር እንደሚከፍት ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በሰው አካል ውስጥ የሚገኙትን የሰውነት ኅብረሕዋስ ራሱን ማደስ እንዲችል የሚያደርጉት ሕዋሶች በገቢር ቴሎሜሬዝ አማካኝነት “ለዘላለም መባዛታቸውን እንዲቀጥሉ” በተደረጉ ሕዋሳት ስለመተካትስ ምን ሊባል ይችላል? ዶክተር ዊልያም ኤ ሃሰልቲን “በሚቀጥሉት 50 ዓመታት ቀስ በቀስ ለሰዎች ለማስተዋወቅ የሚሞከረውን ሰብዓዊ ያለመሞት ባሕርይ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ
ኔኖቴክኖሎጂ እና ክራዮኒክስ መፍትሄ ያስገኙ ይሆን?
ኔኖቴክኖሎጂ ማለትም በኔኖሜትር (የአንድ ሜትር አንድ ቢልዮንኛ) መጠን የሚካሄደው የምሕንድስና ሳይንስም ተስፋ ሰጪ መስሎ እየታየ ነው። በዚህ መስክ ወደፊት ከፍተኛ ውጤት ይገኛል የሚል ሕልም ያላቸው ሰዎች የሚያረጁ ሕዋሶችን፣ ኅብረሕዋሳትን እና አባላአካላትን የሚጠግኑና የሚያድሱ በሞሊኪውል ደረጃ ቀዶ ሕክምና የሚያከናውኑ ከሕዋስ በጣም ያነሱ በኮምፒዩተር የሚመሩ መሣሪያዎች እንደሚሠሩ ይናገራሉ። በአንድ ፀረ-እርጅና ጉባኤ ላይ አንድ ተመራማሪ የ21ኛው መቶ ዘመን ሐኪሞች ኔኖቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሰው ልጅ ያለመሞትን ባሕርይ መስጠት ሳይችሉ አይቀርም ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
ክራዮኒክስ፣ ወደፊት ሳይንስ የሞቱ ሕዋሶች እንደገና እንዲያንሰራሩና በሕይወት እንዲኖሩ ያደርጋል በሚል ተስፋ የሰውን አስከሬን አቀዝቅዞ የማቆየት ሂደት ነው። መላውን አካል ወይም ደግሞ አንጎሉን ብቻ አቀዝቅዞ ማቆየት ይቻላል። እንዲያውም አንድ ሰው አንሶላ አቀዝቅዞ አስቀምጧል። ደግሞ አንሶላን አቀዝቅዞ ማስቀመጥ ለምን አስፈለገ? ይህ አንሶላ ጠፍቶ የቀረ ጓደኛው ይተኛበት የነበረ ሲሆን የተወሰኑ የቆዳ ሕዋሶችና ፀጉሮች አሉበት። ሰውየው የጓደኛውን ሕዋሳት ቀዝቅዘው እንዲቆዩ ያደረገው ወደፊት ሳይንስ በጥቂት ሕዋሳት አልፎ ተርፎም በአንዲት ሕዋስ ብቻ ሰዎችን እንደገና መገጣጠም የሚችልበት ደረጃ ላይ በሚደርስበት ጊዜ ጓደኛው እንደገና በሕይወት መኖር እንዲችል ለማድረግ ነው።
እምነት መጣል የሚኖርብን በየትኛው ላይ ነው?
ሰው በተፈጥሮው በሕይወት መኖር እንጂ መሞት አይፈልግም። ስለሆነም በዚህ መስክ የሚደረግ ማንኛውም ሳይንሳዊ እድገት ወዲያው መወደስና በከፍተኛ ተስፋ ሰጪነት መታየት ይጀምራል። ይሁን እንጂ ዲ ኤች ኢ ኤ፣ ኪኔቲን፣ ሜላቶኒን፣ ኤች ጂ ኤች የተባሉት ሆርሞኖች ወይም ሌላ ንጥረ ነገር በእርግጥ እርጅናን ማዘግየት እንደሚችል የሚያሳይ እስከ አሁን ምንም ዓይነት የተጨበጠ ማስረጃ የለም። እንዲያውም አንዳንዶች ቴሎሜሬዝ የተባለውን ኢንዛይም በዚህ መንገድ በሕዋስ ላይ መጠቀም የካንሰር ሕዋሳትን ከመፍጠር ባሻገር የሚፈይደው ነገር የለም የሚል ስጋት አላቸው። ኔኖቴክኖሎጂ እና ክራዮኒክስም ቢሆኑ ከሳይንስ ልብ ወለድነት የሚያልፉ ነገሮች አይደሉም።
ሳይንስ አንዳንዶች የተሻለ ጤና አግኝተው ረዘም ያለ ዕድሜ እንዲኖሩ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ አሁንም በማድረግ ላይ ነው። ሆኖም ማንንም ለዘላለም እንዲኖር ማድረግ አይችልም። ለምንድን ነው የማይችለው? በአጭር አነጋገር የእርጅናና የሞት መሠረታዊ አመጣጥ ከሰብዓዊ ሳይንስ ውጭ ስለሆነ ነው።
የእርጅናና የሞት አመጣጥ
እርጅናና ሞት በሆነ መንገድ በስነ ባሕርያችን ውስጥ የሰረጹ ነገሮች መሆናቸውን አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች ይስማሙበታል። ጥያቄው ግን በሰው ልጅ ጄኔቲክ ኮድ ውስጥ የሰረጹት መቼ፣ እንዴትና ለምን የሚለው ነው።
ምንም እንኳ ከጄኔቲክስ ወይም ከዲ ኤን ኤ አንፃር ባያብራራውም መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ቀላል የሆነ መልስ ይሰጠናል። ሮሜ 5:12 እንደሚከተለው ይነበባል:- “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።”
የመጀመሪያው ሰው አዳም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ከፊቱ ተዘርግቶለት ነበር። አካሉ ለዘላለም ለመኖርና ለመደሰት በሚያስችለው መንገድ የተሠራ ነበር። ሆኖም የዘላለም ሕይወት በአንድ ሁኔታ ላይ የተመካ ነበር። አዳም ምንጊዜም በሕይወት እንዲቀጥል ከፈለገ የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከፈጣሪው ጋር መተባበርና ለእርሱ ታዛዥ መሆን ነበረበት።—ዘፍጥረት 1:31፤ 2:15-17
አዳም ፈጣሪን ላለመታዘዝ መረጠ። አዳም ይህን ሲያደርግ ሰው ከአምላክ ተነጥሎ ራሱን በራሱ ቢገዛ የተሻለ ነው ማለቱ ነው። በዚህ መንገድ ኃጢአት ሠራ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአዳም ጄኔቲክ ኮድ የተዛባ ያክል ሆነ። አዳም ለዘሮቹ የዘላለም ሕይወት ከማውረስ ይልቅ ኃጢአትንና ሞትን ማስተላለፍ ጀመረ።—ዘፍጥረት 3:6, 19፤ ሮሜ 6:23
እውነተኛው ተስፋ
ሆኖም ይህ ሁኔታ ለዘለቄታው የሚቀጥል አይደለም። ሮሜ 8:20 “ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፣ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም” ይላል። የሰው ልጅ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ሰዎች በእሱ ላይ ኃጢአት ስለሠሩ ለሞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ያም ሆኖ ግን ተስፋ ሰጪ የሆነ ዝግጅትም አድርጓል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ሲመጣ ይህ ዝግጅት ምን እንደሆነ በግልጽ ታወቀ። ዮሐንስ 3:16 እንዲህ ይላል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ይሁን እንጂ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ከሞት ሊያድነን የሚችለው እንዴት ነው?
ሞትን ያመጣው ኃጢአት ከሆነ ሞት ከመወገዱ በፊት ኃጢአት መወገድ ይኖርበታል። ክርስቶስ በመሆን ኢየሱስ ገና አገልግሎቱን ሲጀምር መጥምቁ ዮሐንስ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ሲል ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 1:29) ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ነፃ ስለነበረ የኃጢአት ደሞዝ ለሆነው ሞት ተገዢ አልነበረም። ቢሆንም ሌሎች እንዲገድሉት ፈቃደኛ ሆነ። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ በማድረጉ የኃጢአትን ዋጋ ለመክፈል ሲል ነው።—ማቴዎስ 20:28፤ 1 ጴጥሮስ 3:18
ይህ ዋጋ በመከፈሉ በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ ሞትን ሳይቀምሱ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ሊከፈትላቸው ችሏል። ሳይንስ ዕድሜያችንን ውስን ለሆነ ጊዜ ሊያራዝምልን ይችል ይሆናል፤ ሆኖም የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻለው በኢየሱስ በማመን ብቻ ነው። ኢየሱስ በሰማይ ይህን ዓይነት ሕይወት አግኝቷል፤ ታማኝ ሐዋርያቱና የተወሰኑ ሌሎችም ተመሳሳይ ሕይወት አግኝተዋል። ሆኖም በኢየሱስ የምናምን አብዛኞቻችን የዘላለም ሕይወት የምናገኘው በዚሁ ምድር ላይ ይሖዋ አምላክ መልሶ በሚያቋቁመው ምድራዊ ገነት ውስጥ ነው።—ኢሳይያስ 25:8፤ 1 ቆሮንቶስ 15:48, 49፤ 2 ቆሮንቶስ 5:1
ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት
አንድ ሰው “ለመሆኑ ሞትን ሳይቀምሱ ለዘላለም መኖር የሚጓጉ ስንቶቹ ናቸው?” ሲሉ ጠይቀው ነበር። ሳይሞቱ ለዘላለም መኖር አሰልቺ ነውን? የሚሰለች ነገር እንደማይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ዋስትና ይሰጠናል። “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው።” (መክብብ 3:11) የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች እጅግ ብዙና ውስብስብ ከመሆናቸው የተነሳ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ሌላው ቀርቶ ለዘላለም የማወቅ ፍላጎት የሚያሳድሩብን፣ አእምሮአችንን የሚያመራምሩንና ደስታ የሚሰጡን ይሆናሉ።
ሳይቤሪያን ጄይ በመባል ስለሚታወቀው ወፍ ያጠኑ ሰው ስለ ወፉ ያደረጉትን ጥናት “እጅግ አስደናቂና አስደሳች ትውውቅ ነበር” ሲሉ ከጠሩት በኋላ ስለዚህ ወፍ ምርምር ማድረግ በሕይወታቸው ውስጥ ካሳለፉት ገጠመኝ ሁሉ እጅግ የሚያስደስት እንደሆነ ተናግረዋል። ስለዚህ ወፍ ይበልጥ ባጠኑ ቁጥር ይበልጥ አመራማሪ ሆኖ አግኝተውታል። 18 ዓመት ሙሉ ጥናት ካደረጉም በኋላ እንኳ ጥናታቸው ገና ምንም እንዳልተነካ ተናግረዋል። አንድ የወፍ ዝርያ አንድ ምሁር 18 ዓመት ሙሉ የፈጀ ጥልቅ ምርምርና ጥናት እንዲያደርግና እንዲደሰት ካደረገ ስለ መላው የምድር ፍጥረት ማጥናት ምን ያህል አስደሳችና አርኪ ሊሆን እንደሚችል አስበው።
ሕይወቱ በጊዜ ለማይገደብበት ሰው የሚከፈቱትን አስደሳች የሳይንስ ምርምር መስኮች በዓይነ ኅሊናህ ተመልከት። ተዘዋውረህ ልትጎበኛቸው የምትችላቸውን አስገራሚ የሆኑ ቦታዎች ብዛትና በዚያ የምትተዋወቃቸውን የተለያየ ዓይነት ሰዎች አስብ። አዳዲስ ሐሳብ በማፍለቅ፣ ንድፍ በማውጣትና የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ረገድ የሚኖረውን ሰፊ አጋጣሚ በዓይነ ኅሊናህ ለመሳል ሞክር። የፈጠራ ችሎታችንን እንዳናዳብርና እንዳንጠቀም የሚያግዱን ምንም ዓይነት ሁኔታዎች አይኖሩም። ቁጥር ስፍር ስለሌላቸው የፍጥረት ሥራዎች ስናስብ ሕይወት የምትለግሰውን ማንኛውንም አጋጣሚ ሙሉ በሙሉ መጠቀም የሚቻለው ለዘላለም መኖር ሲቻል ብቻ መሆኑን እንገነዘባለን።
መጽሐፍ ቅዱስ በትንሣኤ አማካኝነት የሞቱ ሰዎች ተነስተው ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንደሚዘረጋላቸው ይገልጻል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ሁኔታው በቀጥታ የደረሰባቸው ሰዎች እያንዳንዱን ዝርዝር ሁኔታ ሲነግሩንና ጥያቄዎቻችንን ሲመልሱልን አሁን ምስጢር የሆኑብን አብዛኞቹ ታሪካዊ ክንውኖች ግልጽ ሊሆኑልን ይችላሉ። በትንሣኤ የሚነሱ ሰዎች በተለያዩ የታሪክ ዘመናት ስለተፈጸሙ ሁኔታዎች ሊነግሩን የሚችሉትን ነገር አስበው።—ሥራ 24:15
ስለዚያ ጊዜ በምታሰላስልበት ወቅት ኢዮብ በትንሣኤ ሲነሳ በኢዮብ 14:1 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንደገና አሻሽሎ መናገር እንደሚፈልግ ልትገምት ትችላለህ። ምናልባትም ‘ከሴት የተወለደ ሰው አሁን የሕይወት ዘመኑ ለዘላለም ነው፣ እርካታም ይሞላዋል’ ብሎ ይናገር ይሆናል።
በይሖዋ ላይ ትምክህታቸውን ለሚጥሉና በኢየሱስ ለሚያምኑ ሰዎች ዕድሜያቸውን ለዘላለም ማራዘም እንዲያው የሕልም እንጀራ አይደለም። ይህ ተስፋ በቅርቡ እውን ይሆናል። እርጅና እና ሞት ይጠፋሉ። ይህም “ከሞት የሚታደገን አምላክ፣ ከእግዚአብሔር ነው” ከሚለው ከመዝሙር 68:20 [የ1980 ትርጉም] ጋር ይስማማል።—ራእይ 21:3, 4
[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በሳይንስ ረገድ የተደረገው እድገት ዕድሜን ማራዘም የሚቻልበት አጋጣሚ ይኖር ይሆናል የሚል ጉጉት አሳድሯል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕይወት የምትለግሰውን ማንኛውንም አጋጣሚ ሙሉ በሙሉ መጠቀም የሚቻለው ለዘላለም መኖር ሲቻል ነው