የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?
ዶክተር ሌኦናርድ ሃይፍሊክ “እርጅና የሚጀምረው በሕዋሶች ውስጥ መሆኑን ከማወቃችን በቀር ስለ እርጅና መሠረታዊ ምክንያት ያለን እውቀት ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ከነበረን እውቀት አልጨመረም” ብለዋል። እንዲያውም “እርጅና የሚመጣበትን ምንም በቂ ምክንያት ልናገኝ አልቻልንም” በማለት ተናግረዋል።
ከ30 ዓመታት በፊት በተደረገ አንድ ሙከራ ጤነኛ የሆኑ የሰው ሕዋሶች ከአንድ ሽል ተወስደው በጣም ተስማሚ በሆነ ሁኔታ እንዲኖሩ ሲደረግ 50 ያህል ጊዜ ከተባዙ በኋላ ሞተዋል። በጣም ካረጀ ሰው የተወሰዱ ሕዋሶች ግን ከሁለት እስከ አሥር ጊዜ ያህል ብቻ ከተባዙ በኋላ ሞተዋል። በዚህ ምክንያት ዚ ኢንክረድብል ማሽን የተባለው የናሽናል ጂኦግራፊ ማኅበር መጽሐፍ “እስካሁን ከሙከራ የተገኙት ማስረጃዎች የመሞት ባሕርይ ከልደታችን ጀምሮ አብሮን የሚወለድ መሆኑን ያረጋግጣሉ” ብሏል።
ይሁን እንጂ የሴሎች መራባት አንድ ደረጃ ላይ የግድ መቆም ያለበት ነገር ነውን? በፍጹም አይደለም። ፕሮፌሰር ሮበርት ኤም ሳፖልስኪ እና ፕሮፌሰር ካሌብ ኤ ፊንች የተባሉት ስለ እርጅና ብዙ ጥናት ያደረጉ ጠበብት “በምድር ላይ የሚኖሩ ሕያዋን ነገሮች ቀደምት ባሕርይ አለማርጀት የነበረ ይመስላል” ብለዋል። የሚያስገርመው ነገር አንዳንድ ጤናማ ያልሆኑ ማለትም ደንብ ወጥ የሆኑ ሰብዓዊ ሕዋሶች እንኳን ፈጽመው አያረጁም።
የመጀመሪያውን የሰውን ልብ ከአንዱ ወደ ሌላው የማዛወር ቀዶ ጥገና ያከናወኑት ዶክተር ክርስቲያን በርናርድ ባዘጋጁት ዘ ቦዲ ማሽን የተባለ መጽሐፍ “‘የማይሞቱ ሕዋሶች’ መገኘታቸው እነዚህ ሴሎች ደንብ ወጥ መሆናቸው እስኪታወቅ ድረስ ስለ እርጅና ለሚያጠኑ ባዮሎጂስቶች ራስ ምታት ሆኖባቸው ነበር” ብለዋል። አዎን፣ አንዳንድ የካንሰር ሕዋስ ዘሮች አመቺ በሆነ አካባቢ ሲኖሩ ፍጻሜ ለሌለው ዘመን እየተራቡ ይቀጥላሉ! ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ “ሳይንቲስቶች እንደነዚህ ያሉት ደንብ ወጥ ሕዋሶች ሳይሞቱ የሚኖሩበትን ምሥጢር ለማወቅ ቢችሉ ሕዋሶች የሚያረጁበትን ምክንያት ለማወቅ ይችሉ ነበር” ብሏል። ስለዚህ በዛሬው ጊዜ አንዳንድ የካንሰር ሴሎች በቤተ ሙከራ ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ሲችሉ ጤነኛ የሆኑ ሕዋሶች ግን አርጅተው ይሞታሉ።
ጉድለት ያለው ሂደት
የሰው ልጅ የሚያረጀውና የሚሞተው ዘ ቦዲ ማሽን የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “[ጤነኛ] ሕዋሶች የመባዛት ችሎታቸውን ሲያጡ” ነውን? እንዲህ ከሆነ “ይህን ማቆሚያ ያለውን የመራባት ችሎታ የሚቆጣጠረውን የአሠራር ሂደት ለይቶ ማወቅና በዚህም አማካኝነት የሰውን ልጅ ዕድሜ ለማራዘም መቻል በጣም አስፈላጊ ነው” ሲል መጽሐፉ ገልጿል።
ባለፈው ርዕስ ላይ ዶክተር ሃይፍሊክ “ከጽንሰት እስከ ልደት፣ ከዚያም እስከ ጉርምስናና ሙሉ ሰው ወደመሆን ስለሚያደርሰን ተአምር” እንደተናገሩ ታስታውሳለህ። ከዚያም ‘እነዚህ ታምራት ለዘላለም እንዲቀጥሉ ስለሚያስችል ይበልጥ ቀላል የሆነ የአሠራር ሂደት’ ተናግረዋል።
ሳይንቲስቶች ለበርካታ ዓመታት ሕይወት ለዘላለም እንዲቀጥል የሚያስችል ዘዴ ለማግኘት ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርጉም “እርጅና የሚመጣበት ምክንያት አሁንም ያልተፈታ ምሥጢር” እንደሆነ ዚ ኢንክረድብል ማሽን የተባለው መጽሐፍ አምኗል።
ይሁን እንጂ እንደ እውነቱ ከሆነ የእርጅናና የሞት ምክንያት ምሥጢር አይደለም። ምክንያቱን ለማወቅ እንችላለን።
ምክንያቱ ምንድን ነው?
ይህን ምሥጢር የሚፈታልን “ከጽንሰት እስከ ልደት የሚያደርሱንን ተአምራት” የፈጠረውና ሁሉን የሚያውቀው ፈጣሪ ማለትም ይሖዋ አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ አምላክ ሲናገር “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነው፤” “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደሆነ እወቁ፣ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም” ይላል።—መዝሙር 36:9፤ 100:3
ይሖዋ አምላክ በማኅፀን ውስጥ የምታደርገውን እድገት እንዴት ባለ አስደናቂ መንገድ እንደነደፈና ከማንም የተለየህ ሰው ሆነህ እንድታድግ ያስቻለህን መመሪያ ጽፎ እንዳስቀመጠ አስብ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙራዊ “አቤቱ፣ አንተ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና፣ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል” ሲል ጽፏል። “እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ . . . አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ . . . አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍ ተጻፉ።” (መዝሙር 139:13, 15, 16 ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) በጣም አስደናቂ አሠራር ያለው ሰብዓዊ አካላችን በድንገተኛ አጋጣሚ የተገኘ አለመሆኑ ግልጽ ነው!
ታዲያ ይሖዋ አምላክ ፍጹምና ለዘላለም የምንኖር አድርጎ ከፈጠረን አርጅተን የምንሞተው ለምንድን ነው? የዚህን መልስ የምናገኘው አምላክ በምድር ላይ በጣም በተዋበ ሥፍራ ባኖረው በመጀመሪያው ሰው አዳም ላይ ከጣለው እገዳ ነው። አምላክ “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፣ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፣ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቶት ነበር።—ዘፍጥረት 2:16, 17 ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
ታዲያ ምን ሆነ? አዳም የሰማይ አባቱን ትእዛዝ ከመጠበቅ ይልቅ ከሚስቱ ከሔዋን ጋር ተባብሮ ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ በላ። በራስ ወዳድነትና በስስት ዓመፀኛው መልአክ የሰጣቸውን የውሸት ተስፋ ለመጨበጥ ጎመጁ። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ራእይ 12:9) በዚህ ምክንያት አምላክ አስቀድሞ እንዳስጠነቀቀው ሞቱ። አዳምና ሔዋን ለዘላለም እንዲኖሩ ሆነው የተፈጠሩ ቢሆኑም ይህ ለዘላለም የመኖር ችሎታቸው አምላክን በመታዘዝ ላይ የተመካ ነበር። ትእዛዙን በመጣሳቸው ኃጢአት ሠሩ። ኃጢአተኛ በመሆናቸውም ለዘሮቻቸው በሙሉ ለሞት ምክንያት የሆነውን ጉድለት አስተላለፉ። በዚህም ምክንያት “ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።”—ሮሜ 5:12፤ ኢዮብ 14:4
ይሁን እንጂ እንዲህ ስለተባለ እርጅናንና ሞትን ድል ለመንሳት የሚቻልበት ምንም ተስፋ የለም ማለት አይደለም። አንዳች የማይሳነው ፈጣሪያችን በውስጣችን ያለውን ማንኛውንም የጂን ቀውስ ሊፈውስና ሕይወታችን ለዘላለም እንዲቀጥል የሚያስችለውን ኃይል ሊሰጥ ይችላል ብሎ ማመን አዳጋች አይሆንም። ይሁን እንጂ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? እርሱ የሰጠውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለማግኘትስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?