ለዘላለም እንዲኖር ሆኖ የተሠራ
የሰው አካል አፈጣጠር በጣም የሚያስደንቅ ነው። አስተዳደጉም ቢሆን ከተአምር የሚቆጠር ነው። አንድ የጥንት ጸሐፊ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ” በማለት አድናቆቱን ገልጿል። (መዝሙር 139:14) አንዳንድ ዘመናዊ የሳይንስ ሊቃውንት የሰውን አካል ድንቅ የሆነ አሠራር በሚገባ የተገነዘቡ በመሆናቸው የሰው ልጅ የሚያረጅበትና የሚሞትበት ምክንያት እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል። ለአንተስ?
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ስቲቨን ኦስታድ “እርጅና ሁልጊዜ ከፊታችን የሚደቀን ሲሆን ብዙ ሰዎች ዋነኛው ሥነ ሕይወታዊ ምሥጢር መሆኑን አለመገንዘባቸው ያስደንቀኛል” ሲሉ ጽፈዋል። ሁሉ ሰው የሚያረጅ መሆኑ “[እርጅና] ግራ የሚያጋባ እንቆቅልሽ ሆኖ እንዳይታይ አድርጓል” ሲሉ ኦስታድ በማከል ተናግረዋል። ያም ሆኖ ግን ነገሩን በጥሞና ብታስብበት እርጅናና ሞት ትርጉም ያላቸው ነገሮች ሆነው ታገኛቸዋለህን?
በ1994 ሌኦናርድ ሃይፍሊክ ሃው ኤንድ ኋይ ዊ ኤጅ (የምናረጀው እንዴትና ለምንድን ነው?) በተባለው መጽሐፋቸው የሰው ሕይወትና አስተዳደግ በጣም የሚያስደንቅ መሆኑን ከገለጹ በኋላ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “ተፈጥሮ ከጽንሰት እስከ ልደት፣ ከዚያም እስከ ጉርምስናና ሙሉ ሰው ወደመሆን የሚያደርሰንን ተአምር ከፈጸመች በኋላ ከዚህ በጣም ቀላል መስሎ የሚታየውን እነዚህን ተአምራት ለዘላለም እንዲቀጥሉ የማድረግ ዘዴ ላለመቀየስ የመረጠች ይመስላል። ይህ ነገር ለባዮጀሮንቶሎጂስቶች [የእርጅናን ባዮሎጂያዊ ሂደት ለሚያጠኑ ሳይንቲስቶች] ለብዙ አሥርተ ዓመታት ምላሽ የሌለው እንቆቅልሽ ሆኖባቸው ኖሯል።”
አንተስ ሰው የሚያረጅበትና የሚሞትበት ምክንያት እንቆቅልሽ ሆኖብሃልን? እነዚህ ነገሮች ዓላማቸው ምንድን ነው? ሃይፍሊክ እንዲህ ብለዋል:- “ከጽንሰት እስከ ጉርምስና ያሉት ባዮሎጂያዊ ክንውኖች በሙሉ ዓላማ ያላቸው ይመስላል። እርጅና ግን አንዳችም ዓላማ የለውም። እርጅና የሚመጣበት ምክንያት በግልጽ አይታወቅም። ስለ እርጅና ባዮሎጂያዊ ሂደት ብዙ ለማወቅ ብንችልም . . . አሁንም ሞትን ከሚያስከትለውና ዓላማ ቢስ ከሆነው እርጅና ለማምለጥ አልቻልንም።”
መጀመሪያውኑ የተፈጠርነው አርጅተን እንድንሞት ሳይሆን በምድር ላይ ለዘላለም እንድንኖር ሊሆን ይችላልን?
የመኖር ፍላጎት
ሁሉ ሰው ማርጀትና መሞት እንደማይፈልግ ሳትገነዘብ አልቀረህም። እንዲያውም ብዙዎች ሲያስቡት እንኳን ያስፈራቸዋል። የሕክምና ዶክተር የሆኑት ሸርዊን ቢ ኑላንድ ሃው ዊ ዳይ (የምንሞተው እንዴት ነው?) በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የማንኛችንም አእምሮ ሞተን የመቅረታችንን፣ ለዘላለም የማንሰማ፣ የማንለማ ሆነን የመቅረታችንን ሐሳብ ሊቀበል አይችልም።” ለማርጀት፣ ለመታመምና ለመሞት የሚፈልግ ሰው አይተህ ታውቃለህ?
ታዲያ እርጅናና ሞት የተፈጥሮ ባሕርያችን ቢሆኑና ከመጀመሪያ የተፈጠርነው ለዚህ ቢሆን ኖሮ በደስታ አንቀበላቸውም ነበርን? ግን አንቀበላቸውም። ለምን? አፈጣጠራችን ለዚህ መልስ ይሰጠናል። መጽሐፍ ቅዱስ “[እግዚአብሔር] ዘላለምነትን [ለሰው] በልቡ ሰጠው” ይላል። (መክብብ 3:11) ሰዎች ይህን የመሰለ ለዘላለም የመኖር ፍላጎት ስላላቸው የወጣትነትን ምንጭ ለማወቅ ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ኖረዋል። ዘላለም ወጣት እንደሆኑ ለመኖር ይፈልጋሉ። ይህም ከአሁኑ የበለጠ ዕድሜ የማግኘት ችሎታ አለንን? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል።
ራሱን በራሱ እንዲያድስ ሆኖ የተሠራ
የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ኦስታድ ናቹራል ሂስትሪ በተባለው መጽሔት ላይ ሰዎች ስላላቸው የተለመደ አስተሳሰብ እንደሚከተለው በማለት ተናግረዋል:- “የራሳችንና የሌሎች እንስሳት አካል ከማንኛውም ማሽን ያልተለየ ሆኖ ይታየናል። ሁሉም ከጊዜ በኋላ ማርጀት የማይቀርላቸው እንደሆኑ አድርገን እናስባለን።” ይሁን እንጂ ይህ ትክክል አይደለም። ኦስታድ “ባዮሎጂያዊ ዘአካላት ከማሽኖች የሚለዩበት መሠረታዊ ምክንያት አለ። ራሳቸውን በራሳቸው የመጠገን ችሎታ አላቸው። ቁስሎች ይድናሉ፣ አጥንቶች ይጠግናሉ፣ በሽታዎች ያልፋሉ” ብለዋል።
ስለዚህ የምናረጀው ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ በእርግጥም ግራ የሚያጋባ ነው። ኦስታድ እንደጠየቁት “ታዲያ [ባዮሎጂያዊ ዘአካላት] ልክ እንደ ማሽኖች እርጅናና ድቀት የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?” አካላዊ ህብረ ሕዋሳት ራሳቸውን በራሳቸው የሚተኩ ከሆኑ ይህ ሂደት ለዘላለም የማይቀጥልበት ምክንያት ምንድን ነው?
የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪ የሆኑት ጃረድ ዳይመንድ ዲስከቨር በተባለው መጽሔት ላይ ሕያዋን ዘአካላት ያላቸውን ራሳቸውን በራሳቸው የማደስ አስደናቂ ችሎታ ሲገልጹ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ሰውነታችን ራሱን የሚጠግን ለመሆኑ ገሃድ ማስረጃ የሚሆነን ቆዳችን ሲቆስል ወዲያው የመዳኑ ባሕርይ ነው። ከእኛ ይበልጥ በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ ራሳቸውን ለመጠገን የሚችሉ በርካታ እንስሳት አሉ። የእንሽላሊቶች ጅራት፣ የኮከብ ዓሣና የሰርጣን እግሮች፣ የባሕር ኩከምበር አንጀት ከተቆረጠ በኋላ ተመልሶ ያድጋል።”
ጥርስ ከተነቀለ በኋላ ተመልሶ ስለመብቀሉ ዳይመንድ ሲናገሩ “ሰዎች ሁለት ጊዜ፣ ዝሆኖች ስድስት ጊዜ፣ ሻርኮች ቁጥሩ ላልተወሰነ በርካታ ጊዜ አዲስ ጥርስ ያበቅላሉ” ብለዋል። ከዚያም ሲያብራሩ “በማይክሮስኮፕ ብቻ ሊታዩ የሚችሉ ሕዋሳት ራሳቸውን በራሳቸው ይተካሉ። የአንጀታችን ግድግዳ ክፍል የሆኑት ሕዋሳት በየጥቂት ቀናት፣ የፊኛችን ግድግዳ ክፍል የሆኑት ሕዋሳት በየሁለት ወሩ፣ እንዲሁም ቀይ የደም ሕዋሶቻችን በየአራት ወሩ ይተካሉ” ብለዋል።
“በሞሊኪውል ደረጃ ደግሞ የፕሮቲን ሞሊኪውሎች እንደየፕሮቲኑ ዓይነት በተለያየ ፍጥነት ይተካሉ። በዚህ መንገድ ጉዳት የደረሰባቸው ሞሊኪውሎች ተጠራቅመው አይቆዩም። ስለዚህ የአንድ የምትወደውን ሰው መልክ ከወር በፊት ከነበረው መልክ ጋር ብታወዳድር ምንም ለውጥ የሌለው መስሎ ቢታይም የዚህ ገላ ክፍል የነበሩት በርካታ ሞሊኪውሎች ግን ተለውጠዋል። በምድር ያሉ ኃይላት በሙሉ የተሰበረ እንቁላል መልሰው ሊጠግኑ ባይችሉም ተፈጥሮ ግን በየቀኑ እየፈታታ መልሶ ይገጥመናል።”
አብዛኞቹ የሰውነት ሕዋሶች በየጊዜው በአዳዲስ ሕዋሶች ይተካሉ። እንደ አንጎል ሕዋሰ ነርቮች የመሰሉት ሕዋሶች ግን ፈጽሞ ላይተኩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሃይፍሊክ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “እያንዳንዱ የሕዋስ ክፍል ከተለወጠ የቀድሞው ሕዋስ ነው ሊባል አይችልም። ስትወለድ የነበሩህ ሕዋሰ ነርቮች ዛሬም ያልተለወጡ መስለው ይታዩ ይሆናል። ይሁን እንጂ የሕዋሰ ነርቮቹ ክፍል የሆኑት ሞሊኪውሎች በአብዛኛው . . . ተለውጠው በአዳዲስ ሞሊኪውሎች ተተክተው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በመባዛት ራሳቸውን በራሳቸው የማይተኩ ሕዋሶች ስትወለድ በነበሩበት ሁኔታ የቆዩ ላይሆኑ ይችላሉ።” ይህም የሆነው የሕዋሶቹ የተለያዩ ክፍሎች በአዳዲስ ክፍሎች ስለሚተኩ ነው። እንዲህ ከሆነ ሰውነታችን ያለው ራሱን በራሱ የማደስ ችሎታ ለዘላለም እንድንኖር ሊያስችለን ይገባ ነበር!
ዶክተር ሃይፍሊክ “ከጽንሰት እስከ ልደት ስለሚያደርሰን ተአምር” ተናግረው እንደነበረ ትዝ ይበልህ። ከእነዚህ ተአምራት አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እነዚህን ተአምራት በአጭሩ በምንመለከትበት ጊዜ “ይበልጥ ቀላል የሆነው እነዚህን ተአምራት ለዘላለም እንዲቀጥሉ የማድረግ ሂደት” አስቸጋሪ መሆን እንደሌለበት አስብ።
ሕዋስ
በአንድ ሙሉ ሰው ውስጥ እያንዳንዳቸው ልንገምት ከምንችለው በላይ ውስብስብ የሆኑ 100 ትሪልዮን ሕዋሶች አሉ። ኒውስዊክ መጽሔት አንድ ሕዋስ ምን ያህል የተወሳሰበ እንደሆነ ለማስረዳት ሕዋስን በግንብ በታጠረ ከተማ መስሏል። መጽሔቱ እንዳለው “የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ለሕዋሱ የሚያስፈልገውን ኃይል ያመነጫሉ። ፋብሪካዎች የኬሚካል ንግድ መሠረት የሆኑትን ፕሮቲኖች ያመነጫሉ። በጣም ውስብስብ የሆኑ የመጓጓዣ አውታሮች የተለያዩ ኬሚካሎችን በሕዋሱ ውስጥና ከሕዋሱ ውጭ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ ያጓጉዛሉ። በየኬላው የቆሙ በረኞች ገቢና ወጪ ንግዶችን ይቆጣጠራሉ፣ ከውጭው ዓለም የሚመጡ የአደጋ ምልክቶችንም ይከታተላሉ። በደንብ የሰለጠኑ ሥነ ሕይወታዊ ሠራዊቶች ወራሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በተጠንቀቅ ቆመው ይጠባበቃሉ። ማዕከላዊ የሆነ የጂኖች መስተዳድር ሥርዓት ያስከብራል።”
አንተ፣ ማለትም 100 ትሪልዮን የሚያክሉት ሕዋሶችህ እንዴት ሊገኙ እንደቻሉ አስብ። የአባትህ ወንዴ ዘርና የእናትህ እንቁላል በተጣመሩ ጊዜ አንድ ሕዋስ ነበርክ። ይህ ጥምረት ሲከናወን በዚህ አዲስ በተፈጠረው ሕዋስ ውስጥ በሚገኘው ዲ ኤን ኤ (ዲኦክሲራይቦኒኩሊክ አሲድ በአጭሩ ሲጻፍ) ውስጥ ፈጽሞ አዲስ የሆንከውን አንተን ለማስገኘት የሚያስፈልጉት ንድፎች በሙሉ ሠፍረዋል። በዲ ኤን ኤ ውስጥ የሚገኘው መመሪያ “ወጥቶ ቢጻፍ እያንዳንዳቸው 600 ገጽ ያሏቸው አንድ ሺህ መጻሕፍት ይሞላ ነበር” ይባላል።
ይህ የመጀመሪያ ሕዋስ ሁለት፣ አራት፣ ስምንት እየሆነ ራሱን ማባዛት ይጀምራል። በመጨረሻም ከ270 ቀናት በኋላ በእናትህ ማኅፀን ውስጥ የተለያየ ዓይነት ያላቸው በሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሕዋሶች አድገው ሙሉ ሕፃን ከሆንክ በኋላ ተወለድክ። ይህ የመጀመሪያ ሕዋስ አንተን ለማስገኘት የሚያስፈልገው ዝርዝር መመሪያ በሙሉ የሠፈረባቸው በርካታ መጻሕፍት እንደተከማቹበት ግዙፍ ክፍል ነበር። እነዚህ እጅግ የተወሳሰቡ መረጃዎች ከአንዱ ሕዋስ ወደ ሌላው የሚተላለፉበት መንገድም ቢሆን ከዚህ ባላነሰ መጠን የሚያስደንቅ ነው። አዎን፣ በሰውነትህ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሕዋስ የመጀመሪያው ጽንስ ሕዋስ የነበረው መረጃ በሙሉ አለው!
የሚከተለውን ደግሞ ተመልከት። እያንዳንዱ ሕዋስ ሁሉንም ዓይነት ሕዋሶች ለማስገኘት የሚያስችል መረጃ እያለው፣ እንበልና፣ የልብ ሕዋሶችን ለማስገኘት በሚያስፈልግበት ጊዜ የቀሩትን ሌሎች ሕዋሶች ለማስገኘት የሚያስፈልጉት መረጃዎች ሥራ ላይ እንዳይውሉ የሚታገዱት እንዴት ነው? ሕዋስ አንድን ሕፃን ለመሥራት የሚያስችሉ ንድፎች ሣጥኑ ውስጥ ሞልቶ እንደያዘ ሥራ ተቋራጭ የልብ ሕዋሶችን ብቻ ለመሥራት የሚያስችለውን ንድፍ አውጥቶ ይሠራል። ሌላው ሕዋስ ደግሞ የነርቭ ሕዋሶችን ለመሥራት የሚያስችለውን ሌላ ንድፍ ያወጣል። አሁንም ሌላው ሕዋስ የጉበት ሕዋሶችን ለመሥራት የሚያስፈልገውን ንድፍ ያወጣል። በእርግጥም ይህ እስከ አሁን ድረስ በቂ ማብራሪያ ያልተገኘለት የሕዋሶች አንድን የተወሰነ የሕዋስ ዓይነት መርጦ የመሥራትና ሌሎቹን መመሪያዎች በሙሉ የማገድ ችሎታ ‘ከጽንሰት እስከ ልደት ከሚያደርሱን በርካታ ተአምራት’ አንዱ ነው።
ሆኖም በዚህ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ለምሳሌ ያህል የልብ ሕዋሶች በአንድ የተወሰነ ሥርዓት ጭብጥ ዘርጋ እንዲሉ የሚቀሰቅሳቸው ነገር መኖር አለበት። በዚህ ምክንያት ልባችን ሰውነታችን የተያያዘውን ተግባር እንዲፈጽም በሚያስችለው መጠን እንዲመታ የሚያደርግ የኤሌክትሪክ ንዝረት የሚያመነጭ ውስብስብ የሆነ ክፍል በልብ ውስጥ ተሠርቷል። በእርግጥም ተአምራዊ የሆነ አስደናቂ ንድፍ ነው! ዶክተሮች ስለ ልብ ሲናገሩ “የሰው ልጅ እስከ ዛሬ ከሠራቸው ማሽኖች በሙሉ የበለጠ ቅልጥፍና ያለው ማሽን ነው” ማለታቸው የሚያስደንቅ አይደለም።
አንጎል
የአንጎል አፈጣጠር ደግሞ ከዚህ ይበልጥ በጣም የሚያስደንቅና ምሥጢራዊ ነው። ከጽንሰት በኋላ ሦስት ሳምንት ቆይቶ የአንጎል ሕዋሶች መፈጠር ይጀምራሉ። ከጊዜ በኋላ ኒውሮን ተብለው የሚጠሩ 100 ቢልዮን የሚያክሉ የነርቭ ሕዋሶች በአንጎል ውስጥ ይታጨቃሉ። በፍኖተ ሐሊብ ውስጥ ያሉትን ከዋክብት የሚያክሉ ሕዋሶች ማለት ነው።
ታይም መጽሔት እንደዘገበው “እያንዳንዱ ሕዋሰ ነርቭ 10,000 ከሚያክሉ ሌሎች ሕዋሰ ነርቮች መልእክት የሚቀበል ሲሆን አንድ ሺህ ለሚያክሉ ሌሎች ሕዋሰ ነርቮች ደግሞ መልእክት ያስተላልፋል።” የነርቭ ሳይንቲስት የሆኑት ጀራልድ ኤደልማን ይህ የእርስ በርስ ግንኙነት ምን ያህል የተወሳሰበ እንደሆነ ሲያስረዱ “የክብሪት አናት የሚያክል መጠን ያለው የአንጎል ክፍል አንድ ቢልዮን የሚያክሉ መገናኛዎች ሲኖሩት እነኚህ መገናኛዎች እርስ በርስ የሚጣመሩበትን መንገድ በአሃዝ ለማስቀመጥ ያስቸግራል። አሥር ቁጥርን ጽፎ ሚልዮን ዜሮዎችን ከጎኑ መደርደር ይጠይቃል።”
በዚህ ምክንያት አእምሮ ምን ዓይነት ቅምጥ ችሎታ ሊኖረው ችሏል? ካርል ሳጋን የተባሉት የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የሰው አንጎል “ሃያ ሚልዮን የሚያክሉ ባለ ትልቅ ጥራዝ መጻሕፍት፣ በትላልቆቹ የዓለም ቤተ መጻሕፍት የሚገኙ መጻሕፍት በሙሉ ማለት ይቻላል፣ የሚይዙትን” መረጃ በሙሉ ለመያዝ ይችላል ብለዋል። እንዲያውም ጆርጅ ሊዎናርድ የተባሉት ደራሲ “በአሁኑ ጊዜ ሊታመን የማይችል ንድፈ ሐሳብ ልናቀርብ ሳንችል አንቀርም። የአንጎል የፈጠራ ችሎታ መጨረሻም ሆነ ገደብ የሌለው ነው” ብለዋል።
ስለዚህ የሚከተለው መግለጫ ሊያስደንቀን አይገባም:- ሞሊኪውላር ባዮሎጂስት የሆኑትና የዲ ኤን ኤን ቅርጽ ከሌላ ባልደረባቸው ጋር ያገኙት ጀምስ ዋትሰን “እስከ ዛሬ ድረስ የአንጎልን ያህል የተወሳሰበ ነገር በመላው ጽንፈ ዓለም ውስጥ አላገኘንም” ብለዋል። አንጎልን ከኮምፒዩተር ጋር ማነጻጸር ተገቢ አይደለም የሚሉት ኒውሮሎጂስቱ ሪቻርድ ሬስታክ ደግሞ “አንጎል በትንሹ እንኳን የሚመስለው ነገር እስካሁን በታወቀው ጽንፈ ዓለም ስለማይገኝ በዓይነቱ ልዩ ነው” ብለዋል።
በዚህ በአሁኑ ዕድሜያችን የምንጠቀመው ከአንጎላችን አቅም አንድ አሥር ሺህኛውን ወይም የአንድ መቶኛውን አንድ መቶኛ ብቻ እንደሆነ የነርቭ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። እስቲ ቆም ብለህ አስብ። ይህን የመሰለ ተአምራዊ ችሎታ ያለው አንጎል ተሰጥቶን ልንጠቀምበት አለመቻላችን ምክንያታዊ ነውን? ገደብና ዳርቻ የሌለው የመማር ችሎታ ያለው የሰው ልጅ የተፈጠረው ለዘላለም እንዲኖር ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለምን?
ይህ እውነት ከሆነ፣ ታዲያ የምናረጀው ለምንድን ነው? ምን የተጓደለ ነገር ቢኖር ነው? አካላችን ለዘላለም እንዲኖር የተፈጠረ ሆኖ ሳለ ከ70 እና ከ80 ዓመት በኋላ የምንሞተው ለምንድን ነው?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ተአምራዊ አወቃቀር ያለው ሕዋስ
የሕዋስ ክርታስ
ወደ ሕዋስ ውስጣዊ ክፍል የሚገባውንና የሚወጣውን የሚቆጣጠረው ሽፋን
ኑክለስ
በድርብ ሽፋን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የሕዋሱን መላ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ማዕከል ነው
መካነ ፕሮቲን (ራይቦዞም)
አሚኖ አሲዶች ወደ ፕሮቲን የሚለወጡበት ክፍል
ክሮሞሶም
የሕዋሶች ጂን ዋነኛ ንድፍ የሆነው ዲ ኤን ኤ የሚገኝበት ክፍል
ኑክሎለስ
ራይቦዞሞች የሚገጣጠሙበት ክፍል
ሕዋስ ሰናስልት (ኤንዶፕላዝሚክ ሬቲኩለም)
በላያቸው የተጣበቁት ራይቦዞሞች የሚሠሩትን (አንዳንድ ራይቦዞሞች በሕዋሱ ውስጥ ያለምንም ችግር የሚንቀሳቀሱ ናቸው) ፕሮቲን የሚያጓጉዙ ወይም የሚያከማቹ ክፍሎች
ኃይለ ሕዋስ (ማይቶኮንድርያ)
ሕዋሱ የሚያስፈልገውን ኃይል የሚያቀርቡት ኤ ቲ ፒ የተባሉ ሞሊኪውሎች የሚመረቱበት ማዕከል
የጎልጂ ዕቃ (ጎልጂ ቦዲ)
ሕዋሱ የሚያመርታቸውን ፕሮቲኖች አሽገው የሚያከፋፍሉ ጠፍጣፋ ብራና መሰል ከረጢቶች
ማእከሊት (ሴንትርዮል)
በኑክለስ አቅራቢያ የሚገኙ ሲሆን በሕዋሶቹ መባዛት ረገድ አስፈላጊ የሆነ ሚና ይጫወታሉ