ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ሁሉም ሲያገባ እኔ ብቻ የቀረሁት ለምንድን ነው?
“ባገባ በጣም ደስ ይለኝ ነበር። አለዚያ ግን ደስተኛ ልሆን አልችልም።”—ሼሪልa
ለማግባት መፈለግ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ነው። አምላክ ወንድንና ሴትን በመካከላቸው ተፈጥሯዊ የሆነ መሳሳብ እንዲኖር አድርጎ ፈጥሯቸዋል። እንዲሁም በወንድና በሴት መካከል የሚኖር ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን በማሰብ ጋብቻን መሠረተ።—ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:21-24
ስለዚህ እስካሁን ካላገባህና በተለይም ብዙ እኩዮችህ ትዳር መሥርተው ከሆነ ተስፋ ልትቆርጥ ወይም ማንም እንደማይፈልግህ ሆኖ ሊሰማህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ጓደኞችህ በቅን ልቦና ተነሳስተው የሚናገሩት ነገር ጭንቀትህን ሊያባብስብህ ይችላል። ቲና እንዲህ ብላለች:- “24 ዓመት ቢሆነኝም ነጠላ ነኝ፣ በአሁኑ ጊዜ ለትዳር ያሰብኩት ጓደኛ የለኝም። የእኔ አለማግባት ሰውን ሁሉ የሚያስገርመው ስለሚመስለኝ ይህ ሁኔታ በጣም ጭንቀት እየፈጠረብኝ ነው። ቆሜ እንደቀረሁ ወይም የሆነ ችግር እንዳለብኝ ሆኖ እንዲሰማኝ ያደርጉኛል።”
ለአንዳንድ ሰዎች ነጠላነትን ደስታ እንዳያገኙ የሚያግድ ሊወጡት የማይችሉት ትልቅ ግንብ መስሎ ሊታይ ይችላል። እያንዳንዱ ዓመት ባለፈ ቁጥር የግንቡ ቁመት ከፍ እንዲል የሚያደርጉ ጡቦች የሚጨመሩ ሊመስል ይችላል። አንድ/ዲት ወጣት እሱ ወይም እሷ ማራኪ እንዳልሆነ/ነች ወይም የሚፈልገው/ጋት እንደሌለ ሆኖ ይሰማው/ት ይሆናል። በኢጣልያ የምትኖር ሮዛና የተባለች አንዲት ወጣት “ብዙ ጊዜ የብቸኝነትና የከንቱነት ስሜት ይሰማኛል፣ የማግባት አጋጣሚዬ ያከተመ ይመስለኛል” ብላለች። ወጣት ወንዶችም ተመሳሳይ የሆነ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል ፍራንክ ሁሉም ጓደኞቹ ካገቡ በኋላ ይበልጥ ተወዳጅና አዋቂ ሰው እንደሆኑ አድርጎ ተመልክቷቸው ነበር። እኔም ትዳር ብመሠርት ምናልባት እንዲህ ዓይነት ሰው ልሆን እችላለሁ በማለት አሰበ።
አንተም አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ብለህ ታስባለህን? ነጠላ ከሆንክ አንዳንድ ጊዜ ችግር እንዳለብህ ወይም ለዘላለሙ የነጠላነት ሕይወት እንድትገፋ እንደተፈረደብህ ሆኖ ይሰማሃል?
ጋብቻን በተመለከተ ብዙዎች ያላቸው አመለካከት ከሐቁ ጋር ሲነፃፀር
በመጀመሪያ ደረጃ ትዳር ለደስታ በር ከፋች ነው የሚለውን የብዙዎች አመለካከት እስቲ እንመርምር። ብዙውን ጊዜ ትዳር ለአንድ ሰው ደስታ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እሙን ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ስላገባ ብቻ ደስተኛ ይሆናል ማለት አይደለም። ሌላው ቀርቶ የተሳካ ትዳር እንኳ በተወሰነ ደረጃ ‘በሥጋ ላይ መከራ’ ያመጣል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ከትዳር ደስታ የሚገኘው ዘወትር የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግና በጥረት ብቻ ነው። በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ታላቅ የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነጠላ ነበረ። ኢየሱስ ደስተኛ አልነበረም ብሎ ለመናገር የሚደፍር ሰው ይኖራልን? በፍጹም! ደስታን ያገኘው የይሖዋን ፈቃድ ከማድረግ ነበር።—ዮሐንስ 4:34
ሌላው የተሳሳተ አመለካከት ደግሞ ትዳር ለብቸኝነት ፍቱን መድኃኒት ተደርጎ መወሰዱ ነው። ግን አይደለም። አንድ ያገባ ክርስቲያን ወንድ “ሚስቴ በፍጹም ምሥጢሯን አካፍላኝ ወይም ከእኔ ጋር ትርጉም ያለው ጭውውት አድርጋ አታውቅም!” ሲል በምሬት ተናግሯል። አንዳንድ ክርስቲያን ሚስቶች ባሎቻቸው ከእነሱ ጋር የሐሳብ ግንኙነት እንደማያደርጉ ወይም ከእነሱ ይልቅ ለሥራቸው ወይም ለጓደኞቻቸው ይበልጥ ትኩረት እንደሚሰጡ በምሬት ይናገራሉ። የሚያሳዝነው ያገቡ ቢሆንም ብቸኝነት የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች አሉ።
ሌሎች ሰዎች ደግሞ ትዳርን ከቤተሰብ ችግር መገላገያ አድርገው ይመለከቱታል። አንዲት ወጣት ባለትዳር እንዲህ ብላለች:- “እኔ እንደሚሰማኝ ወላጆቼ እኔን ሁልጊዜ እንደ ልጅ ሊያዩኝ አይገባም ነበር። እነሱ ግን የወንድ ጓደኛ እንዲኖረኝም ሆነ ከጓደኞቼ ጋር እንድዝናና ፈቅደውልኝ አያውቁም። . . . ወላጆቼ አጋጣሚውን ሰጥተውኝ ቢሆን ኖሮ በ16 ዓመቴ አላገባም ነበር ብዬ አስባለሁ። እኔ ግን ይህን ያደረግሁት ልጅ አለመሆኔን ላሳያቸው ፈልጌ ነበር።”
ከቤተሰብ ጋር አብሮ መኖር እንደ እስር ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ይሁን እንጂ ትዳር የአንድን ሰው የግል ነፃነት የሚገድቡ ኃላፊነቶችን ያመጣል። መተዳደሪያ ለማግኘት ሲሉ መሥራት፣ የመብራት፣ የውኃና የመሳሰሉትን ወጪዎች መክፈል፣ ቤትንና መኪናን መጠገን፣ ምግብ ማብሰል፣ ማጽዳት፣ ልብስ ማጠብና ምናልባትም ልጆችን ማሳደግ የሚያስከትለውን ነገር አስብ። (ምሳሌ 31:10-31፤ ኤፌሶን 6:4፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) ብዙ ወጣቶች አዋቂዎች ሊሸከሟቸው ከሚችሏቸው ከእነዚህ ኃላፊነቶች ጋር መጋፈጣቸው ጭንቀት ላይ ጥሏቸዋል።
አንዳንዶች ትዳር መያዝ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን የሚረዳ ቁልፍ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ትዳር ስለመሠረትህ ብቻ ሌሎች የአንተ ወይም የትዳር ጓደኛህ ወዳጅ ለመሆን ይፈልጋሉ ብሎ በእርግጠኝነት ለመናገር አይቻልም። አንድ ሰው አገባም አላገባም ደግ፣ ለጋስና ለሰው አሳቢ ከሆነ ሰዎች ይወዱታል። (ምሳሌ 11:25) ምንም እንኳ ባለ ትዳር መሆን ከሌሎች ባለ ትዳሮች ጋር መወዳጀትን በተወሰነ ደረጃ ቀላል ሊያደርገው የሚችል ቢሆንም አንድ ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” መሆናቸውን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ዘፍጥረት 2:24) እነሱን ሊያሳስባቸው የሚገባው ዋነኛው ነገር ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ሳይሆን እርስ በርሳቸው እንዴት ተስማምተው ሊኖሩ እንደሚችሉ መሆን አለበት።
ለማግባት ዝግጁ ነህ?
እነዚህ ነጥቦች ምክንያታዊ መሆናቸውን ብትገነዘብም አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ልትቆርጥ እንደምትችል የተረጋገጠ ነው። አንድ የጥንት ምሳሌ “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” ይላል። (ምሳሌ 13:12) ለምሳሌ ወጣቱ ቶኒ ነጠላ በመሆኑ ምክንያት ተስፋ ወደ መቁረጥ ደረጃ ደርሶ ነበር። ከዚህም የተነሳ ማንም ትሁን ማን ለማግባት ወስኖ ነበር። በተመሳሳይም ሳንድራ የተባለች አንዲት ወጣት ልጃገረድ ስለ አዳዲስ ፍቅረኞች ስትሰማ ተስፋ በመቁረጥ እኔስ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ የማገኘው መቼ ይሆን በማለት ራሷን ትጠይቃለች።
በሐዘንና በብስጭት ከመዋጥህ በፊት ‘ለማግባት በእርግጥ ዝግጁ ነኝን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በግልጽ ለመናገር በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ከሆነ መልሱ ዝግጁ አይደለህም ነው! በዩናይትድ ስቴትስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የሚፈጽሟቸው አብዛኛዎቹ ጋብቻዎች በአምስት ዓመታት ውስጥ ይፈርሳሉ።b በእርግጥ ጥቂት ወጣቶች ከዕድሜያቸው በላይ የበሰሉ በመሆናቸው ትዳራቸውን የተሳካ ለማድረግ ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት አንተ የግድ ማግባት አለብህ ማለት አይደለም። ትዳር የሚያመጣቸውን ኃላፊነቶች ለመቀበል ዝግጁ ስለመሆንህ በሐቀኝነት አስበህበታል?
በሐቀኝነት ራስን መመርመር ብዙ ነገሮችን ግልጽ ሊያደርግ ይችል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል የጎለመስህና ኃላፊነት መሸከም የምትችል ሰው ነህ? ገንዘብ ትቆጥባለህ ወይስ ታባክናለህ? የመብራት፣ የውኃና ሌሎች ወጪዎችህን በወቅቱ ትከፍላለህ? ቋሚ ሥራ ማግኘት ወይም ቤተሰብ ማስተዳደር ትችላለህ? ከሌሎች ጋር ማለትም ከሥራ ባልደረቦችህና ከወላጆችህ ጋር ትስማማለህ ወይስ ዘወትር ትጋጫለህ? ይህ ከሆነ ከትዳር ጓደኛህ ጋር በስምምነት ለመቀጠል በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ታገኘዋለህ።
ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኙ ከሆነ ጥሩ ባል ወይም ጥሩ ሚስት ለመሆን የሚያበቃችሁ ጉልምስናና ጥንካሬ እንዲኖራችሁ ተጨማሪ ተሞክሮ ለማግኘት ጥቂት ዓመታት መቆየት እንደሚያስፈልጋችሁ ልትገነዘቡ ትችላላችሁ። ይህን እውነታ መቀበልህ አስተሳሰብህን እንድታስተካክልና ትዳርን ወደፊት ሊሆን የሚችል ነገር አድርገህ እንድትመለከተው ሊረዳህ ይችላል። ይህ ለጊዜውም ቢሆን በነጠላነት ለመኖር ‘ልብህ እንዲጸና’ ያደርገው ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 7:37
ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ
ይሁን እንጂ ‘ከአፍላ የጉርምስና ዕድሜ’ እንዳለፋችሁና ለማግባት ዝግጁ እንደሆናችሁ የሚሰማችሁ ከሆነስ? የትዳር ጓደኛ ሊሆኗችሁ የሚችሉ ሰዎች ጥቂት መሆናቸው ወይም ለጋብቻ የምታቀርቡት ጥያቄ ሁልጊዜ ተቀባይነት የሚያጣ ከሆነ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህ ተፈላጊ አይደላችሁም ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። ንጉሥ ሰሎሞን በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጥ ሀብትና ጥበብ የነበረው ቢሆንም ያፈቀራትን አንዲት ወጣት ልጃገረድ ለማግባባት ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም! ችግሩ ምን ነበር? የልጃገረዲቱ ልብ ለእሱ ምንም የፍቅር ስሜት አልነበረውም። (መኃልየ መኃልይ 2:7) በተመሳሳይም እናንተ ለትዳር የሚሆናችሁ ዓይነት ሰው አላገኛችሁ ይሆናል።
ሌሎች ሰዎችን የሚማርክ መልክ እንደሌላችሁ ሆኖ ይሰማችኋልን? እርግጥ ጥሩ መልክ የራሱ ጥቅሞች ቢኖሩትም ብቸኛው ተፈላጊ ነገር ግን አይደለም። ስለምታውቋቸው ባልና ሚስት ስታስቡ የተለያየ ቁመት፣ ቅርጽና የውበት ደረጃ ያላቸው መሆኑን አላስተዋላችሁም? ከዚህም በላይ በእርግጥ አምላካዊ ፍርሃት ያለው ሰው ይበልጥ ትኩረት የሚሰጠው ‘ለተሰወረው የልብ ሰው’ እንጂ ለውጫዊ መልክ አይደለም።—1 ጴጥሮስ 3:4
እርግጥ ለሰውነት አያያዛችሁ በፍጹም ቸልተኞች መሆን የለባችሁም፤ በተቻለ መጠን ያላችሁን ውበት ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ ይኖርባችኋል። የተዝረከረከ አለባበስና አበጣጠር ሌሎች ስለ እናንተ መጥፎ ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጋል።c በተጨማሪም መጥፎ አነጋገር ወይም በባህርያችሁ ላይ ጉድለት ካለባችሁ ሌሎች እንዳይቀርቧችሁ ሊያደርጋቸው ይችላል። አንድ የጎለመሰ ጓደኛችሁ ወይም አንድ ወላጅ በዚህ ረገድ የት ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልጋችሁ ሊነግራችሁ ይችላል። ሐቁን መቀበል ሊከብዳችሁ ቢችልም አምኖ መቀበሉ ግን ማስተካከያ እንድታደርጉና በሌሎች ፊት ይበልጥ ተቀባይነት እንድታገኙ ሊረዳችሁ ይችላል።—ምሳሌ 27:6
በመጨረሻም በግለሰብ ደረጃ ያለህ ተፈላጊነት ወይም ጥቅም በማግባትህ ወይም ባለማግባትህ ላይ የተመካ አይደለም። አሳሳቢው ነገር አምላክ እንዴት ይመለከትሃል የሚለው ነው፤ ምክንያቱም እሱ “ልብን ያያል።” (1 ሳሙኤል 16:7) ሊያሳስብህና ትኩረት ልትሰጠው የሚገባው ነገር በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትህ እንጂ ማግባትህ ሊሆን አይገባም። ትዳር ሐሳብህንና ንግግርህን እንዲቆጣጠር አትፍቀድለት። ጓደኞችህን፣ የምታዳምጠውን ሙዚቃና መዝናኛህን በጥንቃቄ ምረጥ።
እርግጥ ትዳር ለመመሥረት ያለህ ፍላጎት አይጠፋ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ አትጨነቅ። ታገሥ። (መክብብ 7:8) ነጠላነትህን እንደ እርግማን አድርገህ ከመቁጠር ይልቅ ነጠላነት የሚያስገኘውን ነፃነት፣ ሐሳብህ ሳይከፋፈል አምላክን ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ አድርገህ ሙሉ በሙሉ ተጠቀምበት። (1 ቆሮንቶስ 7:33-35, 38) ትዳር ጊዜውን ጠብቆ ይመጣ ይሆናል። ምናልባትም አንተ ከጠበቅኸው በላይ ቅርብ ሊሆን ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b በሚያዝያ 22, 1995 የእንግሊዝኛ ንቁ! እትማችን ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . በልጅነታችን ብናገባ ትዳራችን ይሰምር ይሆን?” የሚለውን ርዕሰ ትምህርት ተመልከት።
c በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 እና 11 ተመልከት።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ሰው የዕድሜ እኩዮቹ ሲያገቡ ሲያይ እሱ ብቻ እንደቀረ ሆኖ ሊሰማው ይችላል