የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g96 10/8 ገጽ 5-6
  • ጥሩ ትምህርት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥሩ ትምህርት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት
  • ንቁ!—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መፍትሔ መፈለግ
  • የተለያዩ ውጤቶች
  • ጥሩ ትምህርት አስፈላጊ ነው
  • በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
    ንቁ!—1996
  • ጥሩ ትምህርት ለማግኘት የሚያስችሉ ቁልፎች
    ንቁ!—1996
  • ወላጆች—ልጆቻችሁ ወደፊት ምን እንዲሆኑ ትፈልጋላችሁ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ልጄን ትምህርት ቤት ማስገባት ይኖርብኛል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1996
g96 10/8 ገጽ 5-6

ጥሩ ትምህርት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት

ጥሩ ትምህርት ልጆችን በዛሬው ኅብረተሰብ ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው የኑሮ ችግሮች ያዘጋጃል። አጣርቶ ማንበብና መጻፍን እንዲሁም መደበኛ ስሌቶችን ጨምሮ ሌሎች ሙያዎችን እንዲቀስሙ ያስችላል። ከዚህም በላይ ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ ተጽእኖ ከማሳደሩም በላይ ጤናማ በሆኑ የሥነ ምግባር ሕግጋት እንዲታነጹ ያደርጋል።

ይሁን እንጂ የምንኖርበት ዘመን አስጨናቂ በመሆኑ ምክንያት እንዲህ ያለውን ትምህርት መስጠት አስቸጋሪ ሆኗል። ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉ አንድ አውስትራሊያዊ እንደሚከተለው በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል:- “በክፍል ውስጥ የሚገኙት ልጆች የኃይል ድርጊት መፈጸምና መሳደብ የሚቀናቸው፣ ለረዥም ሰዓት ቴሌቪዥን በመመልከት የተነሳ እንቅልፍ የሚያንገላጅጃቸው፣ ገንቢ ምግብ የማይመገቡ ወይም የተራቡ እንዲሁም መረን ተለቅቀው ያደጉ ናቸው።” መምህራን እንደሚናገሩት ደግሞ “ሥርዓት የማይጠብቁ ልጆችን ማስተማር ፈጽሞ አይቻልም።”

የአሜሪካ መምህራን ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት የሆኑት አልበርት ሻንከር መምህራን ያጋጠማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚከተለው በማለት ገልጸዋል:- “ስለ አልኮል፣ ስለ አደንዛዥ ዕፆች፣ ስለ ጾታ፣ . . . ለማስተማር ይገደዳሉ። በተጨማሪም ተማሪዎች ስለ ራሳቸው ያላቸውን ግምት መገምገም፣ የወንጀለኞች ቡድን አባላት እንዳይሆኑ መቆጣጠርና . . . ሌሎች በርካታ ተግባራትን ማከናወን ይኖርባቸዋል። በጠቅላላው ከማስተማር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌለው ብዙ ነገር ያደርጋሉ። . . . የማኅበራዊ ኑሮ ሠራተኞች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ሐኪሞች፣ ፖሊሶች፣ የሥነ ምግብ አማካሪዎች፣ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ሠራተኞች፣ የሕክምና ቴክኒሽያኖች እንዲሆኑ ይጠየቃሉ።”

ይህ ሁሉ ተግባር ከመምህራን የሚጠየቀው ለምንድን ነው? በሰሜናዊ ምሥራቅ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ ትልቅ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ባሉ ክፍሎች ላይ የተደረገ ጥናት የዚህን መልስ ያመለክተናል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ አንድ ሊቅ 23 ተማሪዎች ስለሚገኙበት አንድ አማካይ ክፍል የሰጡትን መግለጫ አውጥቷል። “ከ8 እስከ 15 የሚሆኑት በድህነት የሚኖሩ፣ 3ቱ ዕፅ ከሚወስዱ እናቶች የተወለዱ፣ 15ቱ ከነጠላ ወላጆች ጋር የሚኖሩ ናቸው” ብለዋል።

የቤተሰብ ተቋም በመፈራረስ ላይ እንዳለ ግልጽ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ከሦስት ሕፃናት አንዱ የሚወለደው ከጋብቻ ውጭ ነው። ከሁለት ትዳሮች መካከል ደግሞ አንዱ በፍቺ ያከትማል። በዴንማርክ፣ በፈረንሳይ፣ በታላቋ ብሪታንያና በስዊድን አገሮች ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከፍተኛ ነው። ይህ ሁኔታ በትምህርት ቤቶች ላይ የሚፈጥረውን ችግር ለመቋቋም ምን ጥረት እየተደረገ ነው?

መፍትሔ መፈለግ

የተለያዩ የሙከራ ወይም አማራጭ ትምህርት ቤቶች ተቋቁመዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች አብዛኛውን ጊዜ አነስተኞች በመሆናቸው የቅርብ ክትትል ለማድረግ የሚቻልባቸው ናቸው። ብዙዎቹም የልጆቹን ፍላጎት በተሻለ ሁኔታ ለማሟላት እንዲችሉ የየራሳቸውን ሥርዓተ ትምህርት ያዘጋጃሉ። በኒው ዮርክ ከተማ ከ1993 ጀምሮ እንደነዚህ ያሉ 48 ትናንሽ ትምህርት ቤቶች የተቋቋሙ ሲሆን 50 የሚያክሉ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ለማቋቋም ታስቧል። “ይህ ሙከራ እንዲደረግ ምክንያት የሆነው [በትምህርት ቤቶች] የተስፋፋው ዓመፅና የኃይል ድርጊት ነው” በማለት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ገልጿል። በ1992 በሩሲያ 500 የሚያክሉ አማራጭ ትምህርት ቤቶች የተቋቋሙ ሲሆን በእነዚህ ትምህርት ቤቶች 333,000 ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይከታተላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ “በሺህ የሚቆጠሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ግል ትምህርት ቤቶች በመላክ ላይ ናቸው” በማለት ዘ ቶሮንቶ ስታር ሪፖርት አድርጓል። የካናዳ ክፍለ ሐገር በሆነችው በኦንታርዮ ብቻ 75,000 የሚያክሉ ልጆች በግል ትምህርት ቤቶች ይማራሉ። የግል ትምህርት ቤቶች በአሁኑ ጊዜ በመላይቱ ሩሲያ የሚገኙ ሲሆን ቻይና ቱዴይ የተባለው መጽሔት እንዳለው በቻይና አገር “ከጸደይ ዝናብ በኋላ እንደሚያቆጠቁጥ የቀርከሃ ቀንበጥ በብዛት ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።” በዩናይትድ ስቴትስ ዘ ሃንድቡክ ኦቭ ፕራይቬት ስኩልስ የተባለ መጽሐፍ 1,700 የሚያክሉ የግል ትምህርት ቤቶችን ዝርዝር ያወጣ ሲሆን እነዚህ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ዓመት እስከ 120,000 ብር ወይም ከዚያ በላይ ያስከፍላሉ።

ሌሎች ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን እዚያው እቤታቸው እንዲማሩ ማድረግ መርጠዋል። በ1970 በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በየቤታቸው የሚማሩ ልጆች ቁጥር 15,000 የነበረ ሲሆን በ1995 ግን አንድ ሚልዮን ደርሷል።

የተለያዩ ውጤቶች

በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ የትምህርት ቤት አስተዳደሮች መካከል ጥሩ ውጤት እያገኙ ያሉት አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው። ሻንከር በሐምሌ ወር 1993 በዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኙ የትምህርት ባለሞያዎች በተናገሩት ቃል “ሌሎች አገሮች ባሏቸው ትምህርት ቤቶች ከእኛ የተሻለ ውጤት በማግኘት ላይ ናቸው” ብለዋል። አባባላቸውን በምሳሌ ሲያስረዱ ከሩስያ መጥተው በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ባልና ሚስት አግኝተው እንደነበረ ከገለጹ በኋላ እንዲህ ብለዋል:- “ልጃቸውን በጣም ጥሩ ነው በሚባል የግል ትምህርት ቤት ያስገቡ ቢሆንም የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ልጃቸው በአሁኑ ጊዜ የምትማረው አገሯ ሳለች በሦስተኛ ክፍል የተማረችውን ነው” ብለዋል።

የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት ዜጎቿ በሙሉ ማንበብና መጻፍ እንዲማሩ ያስቻለ ሥርዓተ ትምህርት ዘርግታ ነበር። በአንጻሩ ግን የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የትምህርት መምሪያ በሰጠው ግምት መሠረት 27 ሚልዮን የሚያክሉ አሜሪካውያን በመንገድ ላይ የተተከለ ምልክት ወይም የአውቶቡስ ቁጥር ማንበብ አይችሉም። የአውስትራሊያው ካንቤራ ታይምስ እንደዘገበው ደግሞ “ከአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል 25 በመቶ የሚያክሉት ማንበብና መጻፍ ሳይችሉ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገባሉ።”

በአሁኑ ጊዜ መጠኑ ይነስ ይብዛ እንጂ ትምህርት ቤቶች ችግር ላይ ያልወደቁበት አገር አይገኝም። በ1994 የወጣው ኤጁኬሽን ኤንድ ሶሳይቲ ኢን ዘ ኒው ራሽያ የተባለ መጽሐፍ “ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው የሶቪዬት መምህራን መካከል 72.6 በመቶ የሚሆኑት የመማር ማስተማር ሂደቱ ከፍተኛ ችግር የገጠመው መሆኑን አምነዋል።” ታንያ የሚባሉ በመምህርነት ለበርካታ ዓመታት የሠሩ አንዲት የሞስኮ ነዋሪ እንደተናገሩት የችግሩ ዋነኛ ምክንያት “ወላጆችም ሆኑ ተማሪዎች ለትምህርት አነስተኛ ግምት መስጠታቸው ነው።” ምሳሌ ሲጠቅሱ “የአንድ መምህር ደመወዝ አንድ የአውቶቡስ ሾፌር የሚያገኘውን ግማሽ ወይም ከዚያ ያነሰ ነው” ብለዋል።

ጥሩ ትምህርት አስፈላጊ ነው

የምንኖርበት ማኅበረሰብ ይበልጥ ውስብስብ እየሆነ በሄደ መጠን የጥሩ ትምህርት አስፈላጊነት እየጨመረ ይሄዳል። በብዙ አገሮች አንድ ወጣት ራሱንም ሆነ ወደፊት የሚመሰርተውን ቤተሰብ ለማስተዳደር የሚያስችል ሥራ ለማግኘት የሚያስፈልገው የትምህርት ደረጃ ከፍ ብሏል። በመሆኑም መሠረታዊ የሆኑ ችሎታዎችን ያዳበሩ ወጣቶች የተሻለ ሥራ የማግኘት አጋጣሚ ይኖራቸዋል። ቀጣሪዎች ከፍተኛ ግምት የሚሰጡት አመልካቹ የሚሰጠውን ሥራ ለመሥራት ምን ያህል ችሎታ አለው ለሚለው ጥያቄ ነው።

አንድ የሥራና ሠራተኞች አገናኝ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ስለሚወጡ ብዙ ወጣቶች ሲናገሩ “ሥራ ለመሥራት የሚያስችላቸው ትምህርት ፈጽሞ አላገኙም” ብለዋል። በመቀጠልም “ብዙ አሠሪዎች በወጣት ሠራተኞቻቸው ረገድ ስላጋጠማቸው ችግር ሲነግሩኝ አጣርተው ማንበብና መጻፍ እንኳን አይችሉም ይሉኛል። የሥራ ማመልከቻ ቅጽ እንኳን መሙላት አይችሉም።”

ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ እንደሚፈልጉ የተረጋገጠ ነው። ወጣቶችም ቢሆኑ ጥሩ ትምህርት ለማግኘት ቢፈልጉ ይበጃቸዋል። ይሁን እንጂ ይህን ለማግኘት አስፈላጊ በሆኑት ቁልፎች መጠቀም ይኖርባቸዋል። እነዚህ ቁልፎች ምንድን ናቸው? እንዴት ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሩስያ “የአንድ መምህር ደመወዝ አንድ የአውቶቡስ ሾፌር የሚያገኘውን ግማሽ ነው”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ