በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
በቅርቡ አንድ የኒው ዮርክ ከተማ ጋዜጣ በመጀመሪያ ገጹ ላይ ያሰፈረው ርዕስ “ትምህርት ቤቶቻችን ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀዋል፣ አሁን ፖሊሶች ያስፈልጋሉ” ይላል። የኒው ዮርክ ከተማ የትምህርት ቦርድ 1,000 የሚያክሉትን የከተማው ትምህርት ቤቶች እየተዘዋወሩ የሚቆጣጠሩ 3,200 አባላት ያሉት የትምህርት ቤት ጸጥታ አስከባሪ ጓድ አለው። አሁን ግን መደበኛ ፖሊሶች ገብተው ጸጥታ እንዲያስከብሩ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። በእርግጥ ፖሊሶች ያስፈልጋሉን?
አንድ የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ “በኒው ዮርክ ከተማ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል 20 በመቶ የሚያክሉት የጦር መሣሪያ እንደሚይዙ አንድ ጥናት አረጋግጧል” ይላል። ከ1990 እስከ 1992 የኒው ዮርክ ከተማ ትምህርት ቤቶች ኃላፊ የነበሩት ጆሴፍ ፈርናንዴዝ “በአሁኑ ጊዜ በትላልቆቹ ከተሞቻችን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚታየውን የመሰለ ዓመፅ ፈጽሞ አይቼ አላውቅም። . . . የቻንስለርነቱን ቦታ በ1990 ስረከብ ይህን የመሰለ የከፋ ሁኔታ ያጋጥመኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ይሄ ጊዜ አመጣሽ ክስተት ሳይሆን እንደ ካንሰር የሚራባ ቁስል ነው” ብለዋል።
ምን ያህል የከፋ ነው?
ፈርናንዴዝ በሪፖርታቸው እንደሚከተለው ብለዋል:- “ቻንስለር በሆንኩባቸው የመጀመሪያዎቹ አሥር ወራት በሁለት ቀን ውስጥ በአማካይ አንድ ተማሪ ከምድር በታች ባሉ መጓጓዣ መንገዶች ላይ በጩቤ ይወጋል፣ በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢዎች ወይም በአውራ መንገድ ማዕዘናት ላይ በጥይት ይገደል ነበር። . . . አንዳንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በየኮሪደሮችና በየቅጥር ግቢው እየተዘዋወሩ የሚቆጣጠሩ አሥራ አምስት ወይም አሥራ ስድስት የሚደርሱ ጸጥታ አስከባሪዎች አሏቸው።” ሪፖርታቸውን በመቀጠል አንዲህ ብለዋል:- “በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚፈጸመው ዓመፅ ልክ እንደ ወረርሽኝ በሽታ እየተስፋፋ ነው፤ የግድ ከበድ ያለ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። በቺካጎ፣ በሎስ አንጀለስ፣ በዲትሮይት፣ በጠቅላላው በትላልቆቹ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሙሉ በምጽአት ቀን ብቻ ይሆናል ተብሎ የሚታሰብ አረመኔነት የሚካሄድባቸው ቦታዎች ሆነዋል።
“በዚህ ረገድ ሊሰማን የሚገባውን ኀፍረት ለመሸሸግ አንችልም። ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ፈጽሞ ተቀባይነት ማግኘት የማይኖርበትን ነገር ተቀብለናል። የአሜሪካ ትምህርት ቤቶች የውጊያ ቀጣናዎች ሆነዋል። የእውቀት መገብያ ቦታዎች መሆናቸው ቀርቶ የፍርሃትና የዛቻ ቤቶች ሆነዋል።”
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኙ 245 የትምህርት ቤት አስተዳደሮች ጸጥታ አስከባሪ ጓዶች ተመድበዋል። ከእነዚህ መካከል 102 በሚያክሉት አስተዳደሮች ጸጥታ አስከባሪዎች የጦር መሣሪያ ይታጠቃሉ። ነገር ግን የጦር መሣሪያ የሚታጠቁት ጸጥታ አስከባሪዎች ብቻ አይደሉም። የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት መሠረት በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ተማሪዎች ሌሎች የመግደያ መሣሪያዎች ሳይቆጠሩ በየቀኑ 270,000 የሚያክሉ ሽጉጦች ይዘው ወደየትምህርት ቤቶቻቸው ይሄዳሉ!
ሁኔታው ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ ሄዷል። በርካታ ትምህርት ቤቶች በጦር መሣሪያ መፈተሻ መሣሪያዎች ቢጠቀሙም መሣሪያዎች ወደ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢዎች እንዳይገቡ ለማገድ አልቻሉም። በ1994 የበልግ ወራት በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሪፖርት የተደረጉ የኃይል ድርጊቶች ባለፈው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሪፖርት ከተደረገው ጋር ሲወዳደር 28 በመቶ እድገት አሳይቷል። ፋይ ዴልታ ካፓን በዩናይትድ ስቴትስ ስለተደረገ የሕዝብ አስተያየት ጥናት ሲገልጽ “ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከተጋረጡባቸው ችግሮች መካከል የአንደኛነቱን ደረጃ የያዘው ‘የዲስፕሊን መጥፋትን’ ጨምሮ ‘መደባደብ፣ ዓመፅና ተደራጅቶ ወንጀል መፈጸም’ ሆኗል” ብሏል።
በትምህርት ቤቶች የሚፈጸም ዓመፅ በብዙ አገሮች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ችግር ሆኗል። በካናዳ የቶሮንቶው ግሎብ ኤንድ ሜይል ጋዜጣ “ትምህርት ቤቶች ወደ ጦርነት ቀጣናነት እየተለወጡ ነው” የሚል ርዕስ አውጥቷል። በሜልቦርን፣ አውስትራሊያ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ከሚከታተሉ ልጆች መካከል 60 በመቶ የሚያክሉት በመንገድ ላይ ጥቃት ይደርስባቸዋል ወይም ይጠለፋሉ ብለው በመፍራት ወላጆቻቸው ራሳቸው ወደ ትምህርት ቤት ያመላልሷቸዋል።
ይሁን እንጂ በትምህርት ቤት አካባቢዎች የሚፈጸም ዓመፅ የችግሩ አንድ ክፍል ብቻ ነው። እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች ነገሮችም በትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ እየተፈጸሙ ነው።
ሥነ ምግባርን በተመለከተ
መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙት፣ ማለትም ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ የጾታ ግንኙነት ስህተት እንደሆነ ቢገልጽም በዛሬው ጊዜ ትምህርት ቤቶች ለዚህ ጠንካራ የሆነ የሥነ ምግባር ትምህርት በቂ ድጋፍ አይሰጡም። (ኤፌሶን 5:5፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3-5፤ ራእይ 22:15) ይህም ፈርናንዴዝ “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ከሚገኙት ወጣቶቻችን መካከል 80 በመቶ የሚያክሉት የጾታ ብልግና በመፈጸም ላይ የሚገኙ ናቸው” በማለት ለገለጹት ሁኔታ አስተዋጽኦ እንዳደረገ አያጠራጥርም። በቺካጎ በሚገኝ በአንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሴት ተማሪዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት አርግዘው ተገኝተዋል!
አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎቻቸውን ልጆች የሚያሳድጉባቸው አጸደ ሕፃናት አሏቸው። በተጨማሪም እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ የሄደውን ኤድስና ዲቃላ መውለድ ለመግታት ሲሉ በየጊዜው ኮንዶም የሚያድሉ ትምህርት ቤቶች አሉ። ኮንዶም ማደል ተማሪዎች ዝሙት እንዲፈጽሙ ያበረታታቸዋል ባይባልም እንኳ ዝሙት መፈጸማቸውን መቀበል ማለት እንደሚሆን መካድ አይቻልም። ተማሪዎቹ ስለ ሥነ ምግባር ምን ሊያስቡ ይችላሉ?
ለረዥም ዘመናት የዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩ አንድ ሰው “ትክክል ወይም ስህተት የሆነ ነገር የለም፣ የሥነ ምግባር ምርጫዎች በእያንዳንዱ ግለሰብ ስሜት ላይ የሚመኩ ናቸው ብለው የሚያስቡ በርካታ ወጣቶች አሉ” ብለዋል። ወጣቶች እንዲህ የሚያስቡት ለምንድን ነው? እኚሁ መምህር “ምናልባት ስለ ትክክለኛ ሥነ ምግባር እርግጠኞች ሊሆኑ ያልቻሉት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባጋጠማቸው ተሞክሮ ምክንያት ይሆናል” ብለዋል። እንዲህ ያለው ስለ ትክክለኛ ሥነ ምግባር እርግጠኛ አለመሆን ምን ዓይነት ውጤት ያስከትላል?
አንድ በቅርቡ የወጣ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ “ለማንኛውም ነገር በኃላፊነት የሚጠየቅ ማንም ሰው ያለ አይመስልም” ሲል አማሯል። አዎን፣ መልእክቱ ስህተት የሆነ ምንም ነገር የለም የሚል ነው። ይህ ዝንባሌ በተማሪዎች ላይ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚያስከትል ለማየት አንድ ምሳሌ እንመልከት። በአንድ የዩኒቨርሲቲ ክፍል አንድ መምህር ስለ ሁለተኛው የዓለም ጦርነትና ስለ ናዚዝም አነሳስ ሲያስተምሩ ከተማሪዎቻቸው መካከል አብዛኞቹ በአይሁዳውያን ላይ ለደረሰው እልቂት ማንም ሊወቀስ አይገባም ብለው እንደሚያምኑ ተገንዝበዋል! መምህሩ እንዳሉት “በተማሪዎቹ አስተሳሰብ መሠረት ሆሎኮስት የተባለው በአይሁዳውያን ላይ የደረሰ እልቂት እንደ ማንኛውም የተፈጥሮ አደጋ ሊወገድና ሊቀር የማይችል ነገር ነው።”
ታዲያ ተማሪዎች ስህተቱን ከትክክሉ መለየት ሲያቅታቸው ጥፋቱ የማን ነው?
በአስጨናቂ ዘመን ውስጥ
መምህር የነበሩ አንድ ሰው ስህተቱ የትምህርት ቤቶች አለመሆኑን ሲገልጹ “ችግሩ የመነጨው ከማኅበረሰቡ ነው፤ ትምህርት ቤቶች ያንጸባረቁት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር ነው” ብለዋል። በእርግጥም የኅብረተሰቡ መሪዎች ተግባር ላይ ማዋል ያቃታቸውን ነገር በትምህርት ቤት ፈጽሙ ብሎ ማስተማር ያስቸግራል።
የአሜሪካ መንግሥት ባለ ሥልጣናት የሥነ ምግባር ብልግና ርዕሰ ዜና ሆኖ በወጣበት ወቅት አንዲት የታወቁ ጋዜጠኛ ይህን በምሳሌ ለማስረዳት እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “በዚህ ነገሮችን ሁሉ በመጥፎ በሚመለከት ትውልድ ውስጥ አስተማሪዎች ግብረ ገብነትን እንዴት ማስተማር እንደሚችሉ አላውቅም። . . . ወጣት ልጆች ‘እስቲ ዋሽንግተንን ተመልከቱ!’ ብለው ተቃውሟቸውን ያሰማሉ። በታሪክ ዘመናት በሙሉ ከተፈጸሙት የአጭበርባሪነት ድርጊቶች በሙሉ የከፋ ማጭበርበር በዋይት ሐውስ ጣሪያ ሥር እንደሚከናወን ያውቃሉ።”
መጽሐፍ ቅዱስ ‘በመጨረሻው ቀን አስጨናቂ ዘመን እንደሚሆን’ ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በእርግጥም የምንኖረው በአስጨናቂ ዘመን ውስጥ ነው! ታዲያ ትምህርት ቤቶች ያጋጠሟቸውን ከባድ ችግሮች ለመቋቋምና ተማሪዎች ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ ለመርዳት ምን እየተደረገ ነው? ወላጆችና ተማሪዎችስ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? የሚቀጥሉት ርዕሶች ይህን ጉዳይ ያብራራሉ።