የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 4/8 ገጽ 16-17
  • ዳንስ ለክርስቲያኖች ተገቢ ነውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዳንስ ለክርስቲያኖች ተገቢ ነውን?
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሐሳብና የስሜት መግለጫ ነው
  • ተገቢ የሆነና ተገቢ ያልሆነ ዳንስ
  • ተገቢ መሆኑን ወይም አለመሆኑን እንዴት ማወቅ ይቻላል?
  • የምትመርጠው ሙዚቃና ውዝዋዜ
    ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
  • ምን ዓይነት መዝናኛ ብመርጥ ይሻላል?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • የአካባቢ ባህሎችና ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች እርስ በርስ ይጣጣማሉን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • የተሻለ ነገር አግኝተናል
    ንቁ!—2005
ንቁ!—1997
g97 4/8 ገጽ 16-17

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ዳንስ ለክርስቲያኖች ተገቢ ነውን?

በቀዝቃዛው የምሽት አየር ለመንሸራሸር ከመቀመጫው እየተነሳ “እንዲህ ያለውን ነገር ፈጽሞ ማየት አልችልም። መውጣት አለብኝ” ሲል አንድ ወጣት ለሚስቱ በሽክሹክታ ተናገረ። የተመለከተው ነገር ረብሾት ነበር።

ይህ ሰውና ሚስቱ ወዳጆቻቸው ቤት ተጋብዘው ነበር። ጋባዦቹ የሦስት ሴቶችን ዳንስ የሚጨምር የመድረክ ትዕይንት ለማሳየት ወስነው ነበር። ሌሎቹ ተመልካቾች ግን በነገሩ የተረበሹ አይመስሉም። ታዲያ ይህ ሰው ከሚገባው በላይ ጥብቅ ሆኖ ነውን? ዳንሰኞቹ ውስጣዊ ስሜታቸውን መግለጻቸውና ባላቸው የመደነስ ነጻነት መደሰታቸው አይደለምን? ዳንስን ከክርስቲያናዊ አመለካከት አንጻር ለመረዳት እንሞክር።

የሐሳብና የስሜት መግለጫ ነው

ሰዎች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን ከሚገልጡባቸው መንገዶች አንዱ አካላዊ እንቅስቃሴ ነው። ለምሳሌ ያህል ብዙ አገር ጎብኚዎች ነውርነት የላቸውም የሚሏቸው አካላዊ መግለጫዎች እንግዳ በሆኑባቸው አገሮች የተለየ ትርጉም እንዲያውም በጥሩ ስሜት የማይታዩ መሆናቸውን ሲገነዘቡ በጣም ተደንቀዋል። በሰሎሞን ደሴቶች፣ በማሌዥያና በፓፑዋ ኒው ጊኒ ተመድቦ የነበረ አንድ ሚስዮናዊ እንዲህ ብሏል:- “በአንዳንድ አካባቢዎች አንዳንድ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ከሩካቤ ሥጋ ጋር ግንኙነት ያለው ትርጉም አላቸው። ለምሳሌ ያህል አንዲት ሴት እግሯን ዘርግታ ብትቀመጥና አንድ ሰው በእግሮቿ ላይ ተራምዶ ቢያልፍ እንደ ነውር ይቆጠራል። በተመሳሳይም አንዲት ሴት መሬት ላይ በተቀመጠ ሰው ፊት ብታልፍ እንደ ግዴለሽነት ይቆጠራል። ለሁለቱም ሁኔታዎች የሩካቤ ሥጋ አንድምታ ያለው ትርጉም ይሰጣል።” ልብ አልነውም አላልን አካላዊ እንቅስቃሴያችን የራሱ ቋንቋ አለው። ስለዚህ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ዳንስ የሐሳብና የስሜት መግለጫ ሆኖ ማገልገሉ ሊያስደንቅ አይገባም።

በዳንስ አማካኝነት በክብረ በዓል ወቅት ከሚታየው የደስታና የፈንጠዝያ ስሜት አንስቶ እስከ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የተለያዩ ስሜቶች ሊገለጹ ይችላሉ። (2 ሳሙኤል 6:14-17፤ መዝሙር 149:1, 3) ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ዳንሰኛው በሁለት የተለያዩ መንገዶች፣ ማለትም በአካሉና በፊቱ ስሜቱን በመግለጽ ወይም አስመስሎ በመደነስና በምልክት በመጠቀም መልእክቱን ለተመልካቾች ያስተላልፋል።” በአንዳንድ ዳንሶች የሚተላለፈው መልእክት ግልጽና ጉልህ ሆኖ ይታያል። በሌሎች የዳንስ ዓይነቶች ደግሞ የዳንሱን መልእክት ሊረዱ የሚችሉት በቂ እውቀት ያላቸው ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በክላሲካል ባሌት ዳንስ እጅ ልብ ላይ ሲያርፍ ፍቅርን ሲያመለክት አራተኛውን የግራ ጣት ማመልከት ጋብቻን ያመለክታል። በቻይናውያን ኦፔራ ዙሪያን መዞር ጉዞን ሲያመለክት ቀጥ ያለ አለንጋ ይዞ መድረኩን መዞር ፈረስ መጋለብን ያመለክታል። በተጨማሪም ጥቁር ባንዲራ እያወዛወዙ ማለፍ ማዕበልን ሲያመለክት ባንዲራው ደብዘዝ ያለ ሰማያዊ ከሆነ ቀለል ያለ ነፋስን ያመለክታል። ስለዚህ ሰውነት በዳንስ እንቅስቃሴዎችና መግለጫዎች አማካኝነት መልእክት ያስተላልፋል። ይሁን እንጂ የሚተላለፈው መልእክት ሁልጊዜ ተገቢ ይሆናልን?

ተገቢ የሆነና ተገቢ ያልሆነ ዳንስ

ዳንስ የሚያስደስት መዝናኛና ጥሩ ስፖርት ሊሆን ይችላል። በሕይወት መኖር የሚያስገኘውን ልባዊ ደስታ ወይም የይሖዋን ጥሩነት ለመግለጽ የሚደረግ ንጹሕና ስውር መልእክት የሌለው ሊሆን ይችላል። (ዘጸአት 15:20፤ መሳፍንት 11:34) አንዳንድ በቡድን የሚደረጉ ዳንሶችና ባሕላዊ ዳንሶች የሚያስደስቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ኢየሱስ እንኳን ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ወቅቱን አስደሳች ለማድረግ የተቀጠሩ ዳንሰኞች ተገኝተው እንደነበረ አመልክቷል። (ሉቃስ 15:25) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ዳንስን እንደማያወግዝ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ መጥፎ አሳቦችንና ፍላጎቶችን መቀስቀስን ያወግዛል። አንዳንድ ዳንሶች ተገቢ የማይሆኑትና እንዲያውም በመንፈሳዊነት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉት በዚህ ምክንያት ነው። (ቆላስይስ 3:5) ከጥንት ዘመናት ጀምሮ ዳንስ የሩካቤ ሥጋ ስሜት ለመቀስቀስና ጎጂ ለሆኑ ዓላማዎች የዋለባቸው ጊዜያት አሉ።— ከማቴዎስ 14:3-11 ጋር አወዳድር።

ጠላታችን ሰይጣን ዲያብሎስ የዳንስ እንቅስቃሴ ንጹሕ ካልሆኑ ሐሳቦች ጋር ሲጣመር ዓላማውን ለማስፈጸም የሚያስችል ኃይለኛ ጠንካራ መሣሪያ እንደሚሆን ያውቃል። (ከያዕቆብ 1:14, 15 ጋር አወዳድር።) ስሜት የሚማርክ የሰውነት እንቅስቃሴ የሩካቤ ስሜት እንደሚቀሰቅስ አሳምሮ ያውቃል። ሰይጣን እኛን አሳስቶ ‘አሳባችን ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና’ እንድንርቅ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 11:3) ከሥርዓት ውጭ የሆነ ዳንስ በማየታችን ወይም በመደነሳችን ምክንያት አእምሮአችን ተጠልፎ ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ አስተሳሰብ ብንወድቅ ዲያብሎስ ምን ያህል ደስ እንደሚሰኝ አስብ። በፍላጎታችን ወይም በምኞታችን ላይ ልጓም ሳናበጅ ቀርተን በብልግና ድርጊቶች አሽክላ ብንዋጥ ደግሞ ይበልጥ ይፈነጥዛል። በቀደሙት ዘመናት የሰውነት እንቅስቃሴዎችንና ዳንስን ለዚህ ዓላማ ተጠቅሟል።— ከዘጸአት 32:6, 17-19 ጋር አወዳደር።

ተገቢ መሆኑን ወይም አለመሆኑን እንዴት ማወቅ ይቻላል?

ዳንሱ በቡድን ወይም በሁለት ሰዎች መካከል አለበለዚያም በተናጠል የሚደረግ ቢሆን ንጹሕ ያልሆኑ ስሜቶችን የሚቀሰቅስብህ ከሆነ ሌሎችን የማይጎዳ እንኳን ቢሆን ለአንተ ጎጂ ነው።

በአንዳንድ ዘመናዊ ዳንሶች የዳንሱ ተጓዳኞች እርስ በርሳቸው እንኳን እንደማይነካኩ የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ዋናው ጉዳይ አለመነካካቱ ነውን? ብሪታኒካ “ተጓዳኞቹ ቢተቃቀፉ ወይም እንዲሁ ብቻ ቢተያዩ የሩካቤ ሥጋ ስሜታቸው ከተቀሰቀሰና በዚህም የደስታ ስሜት ከተሰማቸው የመጨረሻው ውጤት አንድ ነው” የሚል መደምደሚያ ይሰጣል። በጋብቻ ላልተሳሰሩት የዳንስ ጓደኛ የሩካቤ ሥጋ ስሜት እንዲቀሰቀስ ማድረግ ጥበብ ነውን? ኢየሱስ “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” ሲል በተናገረው መሠረት ጥበብ አይደለም።— ማቴዎስ 5:28

መደነስ ወይም አለመደነስ የግልህ ምርጫ ነው። ይሁን እንጂ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ በሚገባ ማሰላሰል ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ለማድረግ ያስችልሃል። የዚህ ዳንስ ዓላማ ምንድን ነው? ምን ዓይነት ዝና ያተረፈ ዳንስ ነው? የዳንሱ እንቅስቃሴዎች በምን ነገሮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው? በውስጤ ምን ዓይነት አሳብና ስሜት ይቀሰቅሱብኛል? በዳንስ ጓደኛዬ ወይም በሚመለከቱ ሰዎች ላይ ምን ዓይነት ስሜት ይቀሰቅሳሉ? በእርግጥ ሌሎች ምንም አደረጉ ምን በመግቢያችን ላይ እንደተገለጸው ወጣት ባል ሕሊናችንን መታዘዝ ተገቢ ነው።

ፈጣሪያችን በውበት፣ ለዛና ቅንጅት ባለው እንቅስቃሴ እንድንደሰት እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። አዎን፣ በእነዚህ ነገሮች ተደሰት። ግን በምትደንስበት ጊዜ አካልህ መልእክት እንደሚያስተላልፍ መዘንጋት የለብህም። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 4:8 ላይ የሰጠውን መመሪያ አትዘንጋ:- “እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን እነዚህን አስቡ።”

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

Picture Fund/Courtesy, Museum of Fine Arts, Boston

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ