የአካባቢ ባህሎችና ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች እርስ በርስ ይጣጣማሉን?
ስቲቨን የተባለ ከሰሜን አውሮፓ የመጣ አንድ የይሖዋ ምሥክር በአንዲት አፍሪካዊት አገር ሚስዮናዊ ሆኖ እንዲያገለግል ተመደበ። የዚያ አገር ተወላጅ ከሆነ አንድ ወንድም ጋር በከተማ መሃል እየሄዱ ሳለ ወንድም እጁን ሲይዘው በጣም ደነገጠ።
ከአንድ ሌላ ወንድ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በከተማ መካከል መሄድ ለስቲቨን የማይታሰብ ነገር ነው። በእርሱ አገር ሁለት ወንዶች እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ ከታየ ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች እንደሆኑ ተደርጎ ነው የሚታሰበው። (ሮሜ 1:27) ለአፍሪካዊው ወንድም ግን እጅ ለእጅ መያያዝ ንጹሕ የሆነ የወዳጅነት መግለጫ ነው። እጅ ለእጅ ለመያያዝ ፈቃደኛ አለመሆን ወዳጅነትን ለመቀበል አለመፈለግን የሚያሳይ ነው።
የአንዱ ባህል ከሌላው ባህል ጋር አለመጣጣም ይህን ያህል ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የይሖዋ ሕዝቦች “አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት” እንዲያደርጉ የተሰጣቸውን መለኮታዊ ተልእኮ የመፈጸም ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። (ማቴዎስ 28:19) አንዳንዶች ይህን ተልእኮ ከዳር ለማድረስ ሲሉ አገልጋዮች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ይሄዳሉ። በአዲሱ አካባቢ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያጋጥሟቸውን አዳዲስ ባህሎች ማወቅና ከእነርሱ ጋር መላመድ ይኖርባቸዋል። እንዲህ ካደረጉ ከመሰል ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ስምም ሆነው በአንድነት መሥራት ይችላሉ። ይህም ለሕዝብ የሚያደርጉትን አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ ያደርግላቸዋል።
ከዚህም በላይ ሁከት በሞላበት በዚህ ዓለም ብዙ ሰዎች በፖለቲካ ወይም በኢኮኖሚ አለመረጋጋት የተነሳ ከአገራቸው ተሰድደው በሌላ አገር ለመኖር ይገደዳሉ። ለእነዚህ ከሌላ አገር ለመጡ ሰዎች በምንሰብክበት ጊዜ አዲስ የሆኑ ወግና ልማዶች እንደሚያጋጥሙን የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 22:39) ከተለያዩ ሁኔታዎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስንገናኝ አዲሶቹን ወግና ልማዶች በሚመለከት ግራ የመጋባት ስሜት ሊሰማን ይችላል።
ምንም የማያሻሙ ጉዳዮች
ባህል ከሰብዓዊው ኅብረተሰብ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው። ስለዚህ “እጅግ ጻድቅ” በመሆን ጥቃቅን ልማዶች ሳይቀሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማሙ መሆን አለመሆናቸውን ለመወሰን ምርምር ውስጥ መግባት ምንኛ ከንቱ ድካም ነው!—መክብብ 7:16
በሌላው በኩል ደግሞ ከመለኮታዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በግልጽ የሚጋጩ ልማዶችን ለይቶ ማወቁም አስፈላጊ ነው። “ነገሮችን ለማቅናት” የሚያስችለው የአምላክ ቃል ስላለ በእርግጥ ይህን ማድረግ አስቸጋሪ አይሆንም። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ለምሳሌ ያህል ብዙ ሚስቶችን ማግባት በአንዳንድ ባህሎች የተለመደ ነገር ቢሆንም እውነተኛ ክርስቲያኖች አንድ ወንድ በሕይወት ላለች አንዲት ሚስት ብቻ የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ደንብ ይከተላሉ።—ዘፍጥረት 2:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:2
በተመሳሳይም ርኩስ መንፈስን ከማራቅ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ወይም የማትሞት ነፍስ አለች በሚለው እምነት ላይ የተመሠረቱ የቀብር ልማዶች በእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። አንዳንድ ሰዎች ክፉ መንፈስን ለማራቅ በሚል በአስከሬን አጠገብ እጣን ያጨሳሉ ወይም ጸሎት ያቀርባሉ። ሌሎች ደግሞ ሟቹን ‘ለወዲያኛው ዓለም’ ሕይወት እንዲዘጋጅ ለማገዝ በሚል ሌሊቱን ሙሉ አስከሬኑ አጠገብ ያድራሉ ወይም ሁለተኛ የቀብር ሥነ ሥርዓት ይፈጽማሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ሲሞት ‘አንዳች ነገር እንደማያውቅና’ ከዚህም የተነሳ ማንንም ሰው ሊጠቅም ወይም ሊጎዳ እንደማይችል ያስተምራል።—መክብብ 9:5፤ መዝሙር 146:4
እርግጥ ነው፣ ከአምላክ ቃል ጋር የሚጣጣሙ ልማዶችም አሉ። በአሁኑ ጊዜም የእንግዳ ተቀባይነትን መንፈስ የሚያንጸባርቅ፣ ለአገሩ ባዳ ለሆነ ሰው ሞቅ ያለ አቀባበል ማድረግንና አልፎ ተርፎም ወደ ቤት ጋብዞ ማስተናገድን የሚያበረታታ ባህል ማግኘት እንዴት ደስ ይላል! እንዲህ ያለ አቀባበል ሲደረግልህ አንተም እንዲህ ያለውን ምሳሌ ለመከተል አትገፋፋም? የምትገፋፋ ከሆነ ክርስቲያናዊ ባሕርይህን እንደሚያሳድግልህ የተረጋገጠ ነው።—ዕብራውያን 13:1, 2
የቀጠረው ሰው ቀርቶበት ረጅም ሰዓት መጠበቅ የሚፈልግ ማን አለ? በአንዳንድ አገሮች ቀጠሮ አክባሪነት ከፍ ተደርጎ የሚታይ በመሆኑ ቀጠሮ ማፍረስ ብዙም አይታወቅም። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የሥርዓት አምላክ መሆኑን ይነግረናል። (1 ቆሮንቶስ 14:33 NW) በዚህም የተነሳ ክፉዎችን የሚያስወግድበት “ቀንና . . . ሰዓት” ቀጥሯል፤ እንዲሁም ጥፋቱ የሚፈጸምበት ወቅት ፈጽሞ ‘እንደማይዘገይ’ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:36፤ ዕንባቆም 2:3) በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ቀጠሮ አክባሪነትን የሚያበረታታ ባህል ሥርዓታማ እንድንሆንና ለሌሎች ሰዎችና ለጊዜያቸው ተገቢ አክብሮት እንድናሳይ ይረዳናል። ይህም ቅዱስ ጽሑፋዊ ከሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ነው።—1 ቆሮንቶስ 14:40፤ ፊልጵስዩስ 2:4
ጎጂ ስላልሆኑ ባህሎችስ ምን ለማለት ይቻላል?
አንዳንድ ባህሎች ከክርስቲያናዊ የአኗኗር መንገድ ጋር የሚጣጣሙ ቢሆኑም አንዳንዶች ግን እንደዚያ አይደሉም። ይሁን እንጂ በጥሩ ወይም በመጥፎ ልንፈርጃቸው ስለማንችላቸው ባህሎችስ ምን ለማለት ይቻላል? የማያስከፉ ወይም ጎጂ ያልሆኑ በርካታ ባህሎች ያሉ ሲሆን ለእነርሱ የሚኖረን አመለካከትም መንፈሳዊ ሚዛናችንን ለማሳየት ያስችለናል።
ለምሳሌ ያህል ብዙ ዓይነት የሰላምታ አሰጣጥ አለ። እጅ ለእጅ መጨባበጥ፣ እጅ መንሳት፣ መሳሳም ወይም መተቃቀፍ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም የገበታ ሥርዓትን በተመለከተ የተለያዩ ባህሎች አሉ። በአንዳንድ አገሮች ሰዎች በአንድ ትሪ ወይም በአንድ እቃ አቅርበው ይመገባሉ። በአንዳንድ አገሮች ማግሳት ተቀባይነት ያለው እንዲያውም እንደ አድናቆት መግለጫ ስለሚታይ የሚፈለግ ነገር ሲሆን በአንዳንድ አገሮች ግን ይህ ድርጊት በጣም ነውር እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።
ከእነዚህ ጎጂ ያልሆኑ ባህሎች ውስጥ ይኼኛውን እወደዋለሁ ይኼኛውን ደግሞ እጠላዋለሁ ብለህ ከመወሰን ይልቅ ለእነዚህ ባህሎች ትክክለኛ የሆነ አመለካከት ለመያዝ ጥረት አድርግ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጊዜ የማይሽረው ምክር ‘ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት ምንም ነገር እንዳናደርግ’ ሐሳብ ይሰጣል። (ፊልጵስዩስ 2:3) በተመሳሳይም ኢልነር ቦይኪን ዚስ ዌይ፣ ፕሊስ—ኤ ቡክ ኦፍ ማነርስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “የሚያስፈልግህ ዋናው ነገር ደግ ልብ ነው” ብለዋል።
እንዲህ ዓይነቱ ትህትና የተሞላበት አመለካከት የሌሎችን ባህል ከማንቋሸሽ እንድንርቅ ይረዳናል። እኛ ከምናውቀው ለየት ያለ የሆነውን ሁሉ ከመራቅ ወይም በጥርጣሬ ዓይን ከመመልከት ይልቅ የሌሎች ሰዎችን አኗኗር ለማወቅ፣ የባህላቸው ተካፋይ ለመሆንና ምግባቸውን ለመቅመስ ፈቃደኝነታችንን ማሳየት ይኖርብናል። አእምሯችንን ክፍት ማድረጋችንና አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር ፈቃደኛ መሆናችን የጋባዦቻችንን ወይም የባዕድ አገር ጎረቤቶቻችንን አክብሮት እንድናተርፍ ይረዳናል። በተጨማሪም ልባችንንም ሆነ የአመለካከት አድማሳችንን ‘በማስፋታችን’ ራሳችንን እንጠቅማለን።—2 ቆሮንቶስ 6:13
ባህሉ መንፈሳዊ እድገትን የሚገታ ከሆነ
ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር በቀጥታ የማይጋጩ ሆኖም በመንፈሳዊ እድገት እንዳናደርግ ማነቆ የሚሆኑ ልማዶች ቢያጋጥሙን ምን እናደርጋለን? ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ አገሮች ያሉ ሰዎች ዛሬ ነገ የማለት ልማድ የተጠናወታቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ የግዴለሽነት አኗኗር ጭንቀትን ሊቀንስ ይችላል፤ ይሁን እንጂ አገልግሎታችንን ‘ሙሉ በሙሉ’ እንዳንፈጽም እንቅፋት እንደሚሆንብን እሙን ነው።—2 ጢሞቴዎስ 4:5
ሌሎች ሰዎች አንገብጋቢ ጉዳዮችን “በይደር” ከማስቀመጥ እንዲቆጠቡ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? “የሚያስፈልግህ ዋናው ነገር ደግ ልብ መሆኑን” አትዘንጋ። በፍቅር ተገፋፍተን ምሳሌ ልንተውላቸውና ዛሬ ሊሠራ የሚገባውን ነገር በይደር ለነገ አለማስተላለፉ ያለውን ጠቀሜታ በደግነት ልንገልጽላቸው እንችላለን። (መክብብ 11:4) ይህንንም ስናደርግ እርስ በርስ ያዳበርነውን የመተማመን መንፈስ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ስንል ብቻ መሥዋዕት እንዳናደርግ መጠንቀቅ አለብን። ያቀረብነው ሐሳብ በሌሎች ዘንድ ወዲያው ተቀባይነት ባያገኝ የግድ እንዲቀበሉት ልናስገድዳቸው ወይም ልንቆጣቸው አይገባም። ምንጊዜም ቢሆን ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚገባው ከሥራ ቅልጥፍና ይልቅ ፍቅር መሆን ይኖርበታል።—1 ጴጥሮስ 4:8፤ 5:3
በአካባቢው ተቀባይነት ያለውን ግምት ውስጥ ማስገባት
የምንሰነዝረው ማንኛውም አስተያየት ተገቢ መሆኑንና የራሳችንን ምርጫ በሌሎች ላይ ለመጫን ብለን አለመሆኑን እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል አለባበስ ከቦታ ወደ ቦታ ይለያያል። በብዙ ቦታዎች አንድ የምሥራቹ ሰባኪ ክራቫት እንዲያስር የሚጠበቅበት ሲሆን በአንዳንድ ሞቃታማ አገሮች ግን ክራቫት ማሰር አጉል ወግ አጥባቂነት እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ተቀባይነት ያለው የፕሮቶኮል አለባበስ የቱ እንደሆነ ለመወሰን የአካባቢውን ምርጫ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ሌሎችን በቀላሉ ቅር ሊያሰኝ የሚችለውን ልብስን አስመልክቶ በምንነጋገርበት ጊዜ “ጤናማ አእምሮ” መጠቀም በእጅጉ አስፈላጊ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10
አንድ ባህል ደስ የሚለን ባይሆንስ? ወዲያው ልንጠላው ይገባልን? የግድ እንደዚያ ማድረግ የለብንም። ከላይ እንደተገለጸው ወንድ ለወንድ እጅ ተያይዞ የመሄድ ልማድ በዚያ የአፍሪካ ማኅበረሰብ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለው ነው። ሚስዮናዊው ወንድም ሌሎች ወንዶችም እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ ሲያይ ዘና እያለ ሄደ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ረዥሙን ሚስዮናዊ ጉዞውን በሚያደርግበት ጊዜ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች አባል የሆኑባቸውን ጉባኤዎች ጎብኝቷል። በተለያዩ ልማዶች መካከል ግጭት እንደሚፈጠር የተረጋገጠ ነው። በዚህም የተነሳ ጳውሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጹትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሳይጥስ ከሁሉም ልማዶች ጋር ተስማምቶ ኖሯል። “በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ” በማለት ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 9:22, 23፤ ሥራ 16:3
አዲስ ለሆኑ ባህሎች ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት ለመወሰን እንዲረዳን አንዳንድ አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎች መጠየቃችን ሊጠቅመን ይችላል። አንድን ባህል በመቀበላችን ወይም ባለመቀበላችን በሌሎች ታዛቢዎች ላይ የምናሳድረው ስሜት ምንድን ነው? በባህላቸው እነርሱን መስለን ለመኖር የምናደርገውን ጥረት ሲመለከቱ ወደ መንግሥቱ መልእክት ይሳባሉ? በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢያችን ያለውን ልማድ ብንከተል ‘አገልግሎታችንን ያስነቅፍብን’ ይሆን?—2 ቆሮንቶስ 6:3
“ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ” የመሆን ምኞት ካለን ተገቢ የሆኑና ተገቢ ያልሆኑ ጉዳዮችን በሚመለከት አንዳንድ ሥር የሰደዱ አመለካከቶቻችንን መለወጥ ሊኖርብን ይችላል። ብዙውን ጊዜ አንድን ነገር የምናከናውንበት መንገድ “ትክክል” ወይም “ስህተት” መሆኑ የተመካው በምንኖርበት አካባቢ ነው። ስለዚህም ወንድ ለወንድ እጅ ለእጅ ተያይዞ መሄድ በአንዳንድ አገሮች የወዳጅነት መግለጫ ሲሆን በአንዳንድ አገሮች ደግሞ እንዲህ ያለው ድርጊት ከመንግሥቱ መልእክት የሚያርቅ ይሆናል።
ይሁን እንጂ በተለያዩ ቦታዎች ተቀባይነት ያላቸውና ክርስቲያኖችም ሊያደርጓቸው የሚገቡ ሆኖም ጥንቃቄ የሚጠይቁ ባህሎች አሉ።
ድንበር እንዳታልፉ ተጠንቀቁ!
ምንም እንኳ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ከዓለም ወጥተው መኖር እንደማይችሉ የተናገረ ቢሆንም ‘ከዓለም ርቀው’ መኖር ግን ነበረባቸው። (ዮሐንስ 17:15, 16) ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የሰይጣን ዓለም ክፍል የሆነውንና እንዲሁ ባህል የሆነውን መለየት ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ያህል ዘፈንና ጭፈራ በሁሉም ባህል ለማለት ይቻላል የተፈቀደ ሲሆን እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች ናቸው።
በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ሳይሆን በአስተዳደጋችን ላይ ብቻ ተመርኩዘን ፍርድ ልንሰጥ እንችላለን። አሌክስ የተባለ አንድ ጀርመናዊ ወንድም ስፔይን ሄዶ እንዲያገለግል ተመደበ። ቀደም ሲል ይኖርበት በነበረው አካባቢ ጭፈራ በሰፊው የታወቀ አልነበረም። ይሁን እንጂ በስፔይን ጭፈራ የባህሉ አንዱ ክፍል ነው። አንድ ወንድምና አንዲት እህት አንድ ላይ ሲጨፍሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለከት ደነገጠ። ጭፈራው ስህተት ወይም ደግሞ ዓለማዊ ስለሆነ ነውን? በዚህ ባህል መሠረት እሱም ቢጨፍር ክርስቲያናዊ አቋሙን ማላላት ይሆንበታልን? አሌክስ ምንም እንኳን ዘፈኑና ጭፈራው ከአገሩ የተለየ ቢሆንም በስፔይን ያሉት ወንድሞችና እህቶች ለክርስቲያኖች የተሰጡትን መስፈርቶች እየጣሱ ነው ብሎ ማሰብ እንደሌለበት ተገነዘበ። ግራ እንዲጋባ ያደረገው የባህል ልዩነት ነው።
የስፓኝ ባህላዊ ጭፈራ የሚያስደስተው ኤሚልዮ የተባለ አንድ ወንድም ጭፈራው አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ተገንዝቧል። “ብዙውን ጊዜ ወንዶቹና ሴቶቹ የሚጨፍሩት በጣም ተጠጋግተው እንደሆነ ተመልክቻለሁ” በማለት ይገልጻል። “ነጠላ እንደመሆኔ መጠን በዚህ መንገድ ተጠጋግቶ መጨፈሩ የአንደኛውን ወገን ስሜት ሊነካ እንደሚችል እገነዘባለሁ። አንዳንድ ጊዜ አብሮ መጨፈር ማለት ለማረከህ ሰው ፍቅርህን ለመግለጥ የምትጠቀምበት መንገድ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ጤናማ ሙዚቃ መጠቀሙና አካላዊ መነካካት እንዳይኖር ማድረጉ ጥበቃ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። የሆነ ሆኖ ነጠላ የሆኑ ወጣት ወንድሞችና እህቶች በቡድን ሆነው በሚጨፍሩበት ጊዜ ቲኦክራሲያዊ ሥርዓት የሰፈነበት ማድረግ በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን ማመን አለብኝ።”
እርግጥ ነው፣ ባህላችን ዓለማዊ በሆኑ ጠባዮች እንድንዘፈቅ እንዲያደርገን መፍቀድ አይኖርብንም። በእስራኤላውያን ባህል ዘፈንና ጭፈራ ቦታ ነበራቸው። እስራኤላውያን ቀይ ባህርን አቋርጠው ከግብጽ ነፃ በወጡበት ጊዜ ደስታቸውን በዘፈንና በጭፈራ ጭምር ገልጸዋል። (ዘጸአት 15:1, 20) ይሁን እንጂ ዘፈናቸውና ጭፈራቸው አካባቢያቸው ከነበረው አረማዊ ዓለም ፈጽሞ የተለየ ነበር።
የሚያሳዝነው ደግሞ እስራኤላውያን ሙሴ ከሲና ተራራ እስኪመለስ ድረስ እየጠበቁት ሳለ ትዕግሥታቸው በመሟጠጡ የወርቅ ጥጃ ሠሩ፤ እንዲሁም ከበሉና ከጠጡ በኋላ “ሊዘፍኑ ተነሱ።” (ዘጸአት 32:1–6) ሙሴና ኢያሱ ዘፈናቸውን ሲሰሙ ወዲያው ተረበሹ። (ዘጸአት 32:17, 18) እስራኤላውያን ያንን “ድንበር” አልፈው ስለነበር አሁን እያደረጉ ያሉት ዘፈንና ጭፈራ በአካባቢያቸው ያለውን አረማዊ ዓለም የሚያንጸባርቅ ሆኖ ተገኘ።
በተመሳሳይም ዛሬ ዘፈንና ጭፈራ በአካባቢያችን ተቀባይነት ያለው እንዲሁም የሌሎችን ሕሊና የማይረብሽ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ መብራቱ እንዲደበዝዝ ቢደረግ፣ ብልጭ ድርግም የሚል መብራት ቢበራ ወይም የተለየ ዓይነት ምት ያለው ዘፈን ቢከፈት ቀደም ሲል ተቀባይነት የነበረው ዘፈን ወይም ጭፈራ አሁን የዓለምን መንፈስ የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይችላል። “ይህ ባህላችን ነው” ብለን እንከራከር ይሆናል። አሮን አረማዊ መልክ ያለው መዝናኛና አምልኮ እያከናወነ “የእግዚአብሔር በዓል” እየተደረገ እንዳለ በመግለጽ ተመሳሳይ የሆነ ሰበብ አቅርቦ ነበር። እንዲህ ያለው ደካማ ሰበብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። እንዲያውም የፈጸሙት ድርጊት “በጠላቶቻቸው ፊት አቅላቸውን አጥተው እንዲነቀፉ” አድርጓቸው ነበር።—ዘጸአት 32:5, 25 የ1980 ትርጉም
ባህል የራሱ ቦታ አለው
ከዚህ ቀደም የማናውቀውን ባህል ለመጀመሪያ ጊዜ ስናይ ሊያስደነግጠን ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁሉም ዓይነት ባህል ተቀባይነት የለውም ለማለት አይቻልም። “የሰለጠነ የማመዛዘን ችሎታችንን” በመጠቀም ከክርስቲያን መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጣጣሙትንና የሚጋጩትን ባህሎች ለመለየት እንችላለን። (ዕብራውያን 5:14 NW) ፍቅር የተሞላ ደግ ልብ ለእምነት ወንድሞቻችን በምናሳይበት ጊዜ ጎጂ ያልሆኑ ባህሎች ካጋጠሙን በጥሩ ሁኔታ እንቀበላቸዋለን።
በአካባቢያችን ለሚኖሩ ሰዎች ወይም በውጭ አገር ለሚኖሩ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች በምንሰብክላቸው ጊዜ ለተለያዩ ዓይነት ባህሎች ሚዛናዊ አመለካከት መያዛችን ‘ለሁሉም ዓይነት ሰዎች’ እንደ እነርሱ ለመሆን ያስችለናል። እንዲሁም የተለያዩ ባህሎችን በተቀበልን መጠን ትርጉም ያለው፣ አስደሳችና ማራኪ የሆነ ሕይወት እንድንመራ አስተዋጽኦ የሚያበረክትልን ሆኖ እንደምናገኘው የተረጋገጠ ነው።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያናዊ ሰላምታ ተገቢ በሆነ መንገድ በተለያየ መልክ ሊገለጽ ይችላል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለተለያዩ ባህሎች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ አስደሳችና ማራኪ ሕይወት ለመምራት ይረዳል