የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 4/8 ገጽ 5-7
  • የስድብን ምንጭ ለይቶ ማወቅ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የስድብን ምንጭ ለይቶ ማወቅ
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ምንጩ ምንድን ነው?
  • የጨቋኞች ኃይል
  • በሚያቆስሉ ቃላት ፈንታ የሚፈውሱ ቃላት መናገር
    ንቁ!—1997
  • ጎጂ ንግግርን ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2013
  • ባሎች፣ ሚስቶቻችሁን አክብሯቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ‘ሌሎችን የሚያንጽ መልካም ቃል’ ተናገር
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1997
g97 4/8 ገጽ 5-7

የስድብን ምንጭ ለይቶ ማወቅ

“በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራል።”—ማቴዎስ 12:34

ኢየሱስ ወደ ሁለት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ከላይ የተጠቀሱትን ቃላት ተናግሯል። አዎን፣ ብዙውን ጊዜ የአንድ ሰው ቃላት የሚያንጸባርቁት በውስጡ ያለውን ስሜትና ዝንባሌ ነው። ስሜቱና ዝንባሌው ሊመሰገን የሚገባው ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 16:23) በአንጻሩ ደግሞ ተንኮለኛ ሊሆን ይችላል።— ማቴዎስ 15:19

አንዲት ሴት ስለ ትዳር ጓደኛዋ እንዲህ ብላለች:- “ማንም ሳይነካው በባዶ ሜዳ የሚቆጣ ይመስለኛል። ከእርሱ ጋር መኖር ፈንጂ በተቀበረበት አካባቢ እንደመሄድ ነው። ምን ነገር እንደሚያስቆጣው ማወቅ አይቻልም።” ሪቻርድ ደግሞ ሚስቱ ይህን የሚመስል ባሕርይ እንዳላት ይናገራል። “ሊድያ ምን ጊዜም ለጥል የተዘጋጀች ናት። ስትናገር እንዲሁ አትናገርም። ሕፃን የሆንኩ ይመስል ጣቷን እየቀሰረች በኃይለ ቃል ትናገረኛለች።”

እርግጥ ነው፣ በጣም ጥሩ ነው በሚባል ትዳር ውስጥ እንኳን ጭቅጭቅ መነሳቱ አይቀርም። ሁሉም ባሎች ወይም ሚስቶች በኋላ የሚጸጸቱበትን ነገር ይናገራሉ። (ያዕቆብ 3:2) የትዳር ጓደኛን መስደብ ግን ከዚህ የተለየ ነው። የትዳር ጓደኛን ለመጫን ወይም ለመቆጣጠር ተብሎ የሚነገር የነቀፌታ ወይም የንቀት ቃል ነው። ጎጂ ንግግር በለዘበ አነጋገር ተቀባብቶ የሚቀርብበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል መዝሙራዊው ዳዊት በንግግሩ ለስላሳ ሆኖ ተንኮል ስለሚሸርብ ሰው ተናግሯል። “አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ፣ በልቡ ግን ሰልፍ ነበረ፤ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ፣ እነርሱ ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው” ብሏል። (መዝሙር 55:21፤ ምሳሌ 26:24, 25) ሻካራ ንግግር በልዝብ አንደበት የተሸፋፈነም ሆነ በግልጽ የተነገረ፣ አንድን ትዳር ሊያፈርስ ይችላል።

ምንጩ ምንድን ነው?

አንድ ሰው የስድብ ቃል እንዲናገር የሚያደርገው ምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው አነጋገር የሚመነጨው ከሚታዩትና ከሚሰሙት ነገሮች ነው። በበርካታ አገሮች ሽሙጥ፣ ስድብና ሌሎችን ማዋረድ ተቀባይነት ያላቸው፣ እንዲያውም እንደ ቀልድ የሚቆጠሩ ድርጊቶች ናቸው።a በተለይ የባሎች ጠባይ “ወንድነት” ጉልበተኛ በመሆንና ሴቶችን በመጫን እንደሚታይ አድርገው በሚያቀርቡ መገናኛ ብዙሐን ሊለወጥ ይችላል።

በተመሳሳይ የስድብ ቃል የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ተቆጪ፣ አኩራፊና ጯሂ ወላጅ ባለበት ቤት ያደጉ ናቸው። ከትንሽነት ዕድሜያቸው ጀምሮ እንዲህ ካለው ጠባይ ጋር ተላምደው ያድጋሉ ማለት ነው።

እንዲህ ባለው አካባቢ ያደገ ልጅ የሚያዳምጠውን የአነጋገር ስልት ከመኮረጁም በላይ ስለራሱና ስለ ሌሎች ሰዎች ያለው አመለካከት የተጣመመ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ሁልጊዜ ቁጣ የሚወርድበት ልጅ ከሆነ ሲያድግ ለምንም ነገር የማይረባ እንደሆነ ይሰማዋል። ግልፍተኛም ይሆናል። አባቱ እናቱን በአንደበቱ ሲያቆስል ያዳምጥ ከነበረስ? ልጁ በዕድሜ አነስተኛ ቢሆንም አባቱ ለሴቶች ያለውን ንቀት ማስተዋል ይችላል። ከአባቱ ጠባይ ወንድ ሴትን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንደሚገባውና ሊቆጣጠር የሚችለው ደግሞ በማስፈራራትና በመጉዳት እንደሆነ ይማራል።

ቁጡ የሆነ ወላጅ እንደርሱ ቁጡ የሆነ ልጅ ሊያሳድግ ይችላል። ልጁ ደግሞ ሲያድግ “ብዙ በደል የሚፈጽም” “ግልፍተኛ” ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 29:22 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ግርጌ ማስታወሻ) በዚህ መንገድ ጎጂ የሆነ የአነጋገር ልማድ ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፍ ይችላል። ጳውሎስ አባቶችን “ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው” ሲል የመከረው አለበቂ ምክንያት አይደለም። (ቆላስይስ 3:21) ቲኦሎጂካል ሌክስከን ኦቭ ዘ ኒው ተስታመንት በሚለው መሠረት “ማበሳጨት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ለጠብ መዘጋጀትንና ጠብ ማነሳሳትን” ሊያመለክት ይችላል።

የወላጆች ተጽእኖ ሌሎችን በቃላትም ሆነ በሌላ መንገድ ለመጉዳት በቂ ምክንያት ይሆናል ባይባልም ሻካራ ንግግር የመናገር ዝንባሌ በአንድ ሰው ባሕርይ ውስጥ ሥር ሊሰድ የሚችልበትን አንድ ምክንያት እንድንገነዘብ ያስችለናል። አንድ ወጣት ባል ሚስቱን አይደበድባት ይሆናል። ግን በአንደበቱና በጠባዩ ያቆስላታልን? ራሱን ቢመረምር አባቱ ለሴቶች ያለውን ንቀት እንደወረሰ ሊገነዘብ ይችል ይሆናል።

ከላይ የገለጽናቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች በሴቶችም ላይ ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው ግልጽ ነው። አንዲት እናት ባልዋን የምትሳደብና የምታዋርድ ከሆነች ልጅዋም አድጋ ትዳር ስትይዝ ባልዋን እንደ እናትዋ መሳደብና ማዋረድ ትጀምር ይሆናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ከጠበኛና ከቁጡ ሴት ጋር ከመቀመጥ በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል” ይላል። (ምሳሌ 21:19) ቢሆንም በዚህ ረገድ ወንዶች ይበልጥ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። ለምን?

የጨቋኞች ኃይል

በትዳር ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ትልቅ ኃይል ወይም ሥልጣን የሚኖረው ከሚስቲቱ ይልቅ ባልዬው ነው። አብዛኛውን ጊዜ የበለጠ ጉልበት የሚኖረው እርሱ ስለሚሆን የሚሰነዝርባት ዛቻ ይበልጥ አስፈሪ ይሆናል።b በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ የበለጠ የሥራ ችሎታ፣ ኑሮውን የማሸነፍ ብቃትና የተሻለ ገንዘብ የሚኖረው ወንዱ ነው። በዚህ ምክንያት በአንደበት የቆሰለችው ሴት መሄጃ እንደሌላትና ብቸኛ እንደሆነች ሊሰማት ይችላል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፣ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፣ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም” ሲል ከተናገረው ቃል ጋር ትስማማ ይሆናል።— መክብብ 4:1

አንዲት ሚስት ባልዋ አንድ ጊዜ በጣም ጨዋና አፍቃሪ፣ ወዲያው ደግሞ ተለውጦ ተቺ ከሆነ ግራ ልትጋባ ትችላለች። (ከያዕቆብ 3:10 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ ባልዋ ለቤቱ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልቶ የሚያቀርብ ከሆነ ሁልጊዜ በሻካራ ቃላት የምትቆስለዋ ሴት ትዳርዋ አንድ ጉድለት እንዳለው ማሰቧ አግባብ እንዳልሆነ ስለሚሰማት የበደለኛነት ስሜት ያድርባታል። እንዲያውም ለባልዋ መጥፎ ባሕርይ ምክንያት የሆነችው እርስዋ እንደሆነች ሊሰማት ይችላል። አንዲት ሴት “አካላዊ ድብደባ የደረሰባት ሚስት ጥፋቱ የኔ ነው ብላ እንደምታስብ ሁሉ እኔም እንደዚያ ይሰማኝ ነበር” ብላለች። ሌላዋ ሴት ደግሞ “ስሜቱን ለመረዳት የበለጠ ጥረት ባደርግና ‘ብታገሠው’ ኖሮ ሰላም አገኝ ነበር ብዬ ወደ ማመን አዘንብዬ ነበር” ብላለች። የሚያሳዝነው ግን የሚፈጸመው ግፍ አብዛኛውን ጊዜ ማቆሚያ አይኖረውም።

ብዙ ባሎች ሊወዷትና ሊንከባከቧት የማሉላትን ሴት በኃይል በመግዛት ያላቸውን ሥልጣን አለአግባብ መጠቀማቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። (ዘፍጥረት 3:16) ይሁን እንጂ እንዲህ ስላለው ሁኔታ ምን ማድረግ ይቻላል? አንዲት ሴት “ትቼው ለመሄድ አልፈልግም። የምፈልገው እኔን መስደቡን እንዲተው ብቻ ነው” ብላለች። አንድ ባል በትዳር ዘጠኝ ዓመት ካሳለፈ በኋላ “ኑሯችን ስድብ የሞላበት እንደሆነና ተሳዳቢውም እኔ እንደሆንኩ እገነዘባለሁ። ጠባዬን መለወጥ እንጂ ከሚስቴ መለየት አልፈልግም” ብሏል።

የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያመለክተው ትዳራቸው በጎጂ አንደበት የተቃወሰባቸው ሰዎች እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር። ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሺነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት “ግሪኮች መሳደብን ወይም ስድብን ችሎ ማለፍን እንደ ትልቅ ችሎታ አድርገው ይመለከቱት ነበር” ይላል።

b አፍ እላፊ ወደ ጠብ ሊሸጋገር ይችላል። (ከዘጸአት 21:18 ጋር አወዳድር።) በደል ለተፈጸመባቸው ሴቶች ምክር የሚሰጡ አንዲት ሴት “ተደብድባ ወይም ተወግታ ወይም ታንቃ እንዳትገደል የሕግ ጥበቃ እንዲደረግላት ለመጠየቅ የምትመጣ ሴት ሁሉ ረዘም ላለ ጊዜ ሥነ ልቦናዊ በደል ሲፈጸምባት የቆየች ናት።”

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ብዙ ባሎች ሊወዷትና ሊንከባከቧት የማሉላትን ሴት በኃይል በመግዛት ያላቸውን ሥልጣን አለአግባብ መጠቀማቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአንድ ልጅ ባሕርይ ወላጆቹ አንዳቸው ለሌላው በሚያሳዩት ጠባይ ይነካል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ