በሚያቆስሉ ቃላት ፈንታ የሚፈውሱ ቃላት መናገር
“ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው።”—ምሳሌ 18:21
መሳደብ ማለትም ሆን ብሎ ሌሎችን የሚያዋርድ ወይም የሚያቃልል ቃል መናገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ተከልክሏል። በሙሴ ሕግ ወላጆቹን የተሳደበ ሰው የሞት ቅጣት ይፈጸምበት ነበር። (ዘጸአት 21:17) ስለዚህ ይሖዋ አምላክ መሳደብን እንደ ቀላል ነገር አድርጎ አይመለከትም። መጽሐፍ ቅዱስ ተሳዳቢው አምላክን አገለግላለሁ እስካለ ድረስ ‘በገዛ ጓዳው የሚያደርገው ነገር እንደ ከባድ ነገር ሊቆጠር አይችልም’ በሚለው አስተሳሰብ አይስማማም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ “አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው” ይላል። (ያዕቆብ 1:26፤ መዝሙር 15:1, 3) ስለዚህ አንድ ሰው ሚስቱን የሚሳደብ ከሆነ የሚያደርጋቸው ክርስቲያናዊ ሥራዎች በሙሉ በአምላክ ዐይን ከንቱዎች ይሆኑበታል ማለት ነው።a— 1 ቆሮንቶስ 13:1-3
ከዚህም በላይ ተሳዳቢ የሆነ ክርስቲያን ከጉባኤ ሊወገድ ይችላል። የአምላክን መንግሥት በረከቶች እስከማጣትም ሊደርስ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 6:9, 10) በአንደበቱ ሰዎችን የሚያቆስል ሰው ከባድ ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርበት ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ለውጥ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
ችግሩን መግለጽ
ተሳዳቢ የሆነ ሰው ከባድ ችግር እንዳለበት በግልጽ ካልተረዳ ሊለወጥ አይችልም። የሚያሳዝነው ግን አንዲት አማካሪ እንዳሉት ተሳዳቢ የሆኑ ብዙ ወንዶች “ጠባያቸው መጥፎ እንደሆነ አይሰማቸውም። ለእነዚህ ወንዶች ይህ ጠባያቸው ምንም ስህተት የሌለው እንደሆነና በባልና ሚስት ግንኙነት የተለመደ እንደሆነ ያስባሉ።” ስለዚህ ብዙዎቹ ግልጽ ሆኖ ካልተነገራቸው ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው አይታያቸውም።
ብዙውን ጊዜ ሚስቲቱ ሁኔታዋን በጸሎት ከመረመረች በኋላ ለራስዋና ለልጆችዋ ደህንነት እንዲሁም ባልዋ በአምላክ ዘንድ ያለው አቋም እንዳይበላሽ ስትል ጉዳዩን ማንሳት እንደሚኖርባት ሊሰማት ይችላል። እርግጥ ጉዳዩን ማንሳትዋ ችግሩን ሊያባብስ፣ ከክህደት በስተቀር ምንም ዓይነት ውጤት ላያስገኝላት የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ጉዳዩን እንዴት እንደምታነሳበት በጥንቃቄ ካሰበች እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዳይፈጠር ማድረግ ትችል ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “በወቅቱ በትክክል የተነገረ ቃል፣ በብር ላይ እንደፈሰሰ የወርቅ ጌጥ፣ ውበት ይኖረዋል” ይላል። (ምሳሌ 25:11 የ1980 ትርጉም) ዘና በሚልበት ጊዜ ለዘብ ባለ አነጋገር በግልጽ ማነጋገር ልቡን ሊነካው ይችል ይሆናል።— ምሳሌ 15:1
ሚስቲቱ እርሱን ከመወንጀል ይልቅ አቁሳይ የሆነው አንደበቱ እንዴት እንዲሰማት እንደሚያደርጋት ለመግለጽ መሞከር ይገባታል። “አንተ” ከማለት ይልቅ “እኔ” ተብለው የሚነገሩ ቃላት የተሻለ ውጤት ያስገኛሉ። ‘. . . ስትለኝ በጣም ይከፋኛል’ ወይም ‘. . . የሚለው አነጋገርህ በጣም ያሳዝነኛል’ እንደሚሉት ያሉ አነጋገሮች በተናጋሪው ላይ ሳይሆን በችግሩ ላይ የሚያነጣጥሩ ስለሆኑ ልቡን መንካታቸው አይቀርም።— ከዘፍጥረት 27:46— 28:1 ጋር አወዳድር።
ሚስቲቱ በዘዴና በቁርጠኝነት የምትናገረው ቃል ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። (ከመዝሙር 141:5 ጋር አወዳድር።) ስቲቨን ብለን የምንጠራው አንድ ሰው ይህ እውነት መሆኑን ተረድቷል። “ባለቤቴ ለእኔ ግልጽ ሆኖ ያልታየኝን የተሳዳቢነት ዝንባሌዬን ተገንዝባ ስለ ጉዳዩ እኔን ለማነጋገር ደፍራለች” ይላል።
እርዳታ ማግኘት
ይሁን እንጂ ባልዬው ችግሩን አምኖ ለመቀበል እምቢተኛ ከሆነ ሚስቲቱ ምን ልታደርግ ትችላለች? አንዳንድ ሚስቶች እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የውጭ እርዳታ ለማግኘት ይፈልጋሉ። የይሖዋ ምስክሮች እንዲህ ያለው አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የጉባኤያቸውን ሽማግሌዎች ለማነጋገር ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች የአምላክን መንፈሳዊ መንጎች ሲጠብቁ አፍቃሪዎችና ደጎች እንዲሆኑና የአምላክን ቃል ጤናማ ትምህርት ‘የሚቃወሙትን ግን እንዲገስጹ’ መጽሐፍ ቅዱስ አጥብቆ ይመክራቸዋል። (ቲቶ 1:9፤ 1 ጴጥሮስ 5:1-3) ሽማግሌዎች በባልና ሚስቶች የግል ጉዳይ ውስጥ መግባት ተገቢ እንዳልሆነ ቢገነዘቡም አንደኛው የትዳር ጓደኛ በሌላው ሻካራ ንግግር የሚሠቃይ ከሆነ ሁኔታው በጣም ያሳስባቸዋል። (ምሳሌ 21:13) እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ ስለሚከተሉ የስድብ ንግግሮችን እንደ ቀላል ነገር አይመለከቱም።b
ሽማግሌዎች ባልና ሚስቱ በጥሩ ሁኔታ እንዲወያዩ ሊረዷቸው ይችሉ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አንዲት ሴት ወደ አንድ ሽማግሌ ቀርባ የእምነት ባልደረባዋ የሆነ ባልዋ ለበርካታ ዓመታት በአንደበቱ ሲያቆስላት እንደኖረ ትነግረዋለች። ሽማግሌው ከሁለቱ ጋር የሚገናኝበትን ዝግጅት አደረገ። አንዳቸው ሲናገሩ ሌላው ጣልቃ ሳይገባ ዝም ብሎ እንዲያዳምጥ ጠየቃቸው። የሚስቲቱ ተራ ሲደርስ የባልዋን ግልፍተኝነትና ቁጣ ፈጽሞ መቋቋም እንዳቃታት ተናገረች። ለበርካታ ዓመታት ባልዋ ከውጭ ሲገባ ተቆጥቶ ይመጣ ይሆን እያለች ስለምታስብ በየምሽቱ ሆዷን ባር ባር እንደሚላት ገለጸች። በቁጣ ሲገነፍል ቤተሰቦችዋን፣ ወዳጆችዋንና እሷነቷን የሚያዋርድ ነገር ይናገር ነበር።
ሽማግሌው ሚስቲቱን ባልዋ እንዲህ ያለውን ነገር ሲናገር እንዴት እንደሚሰማት ጠየቃት። “ማንም ሰው ሊወደኝ የማይችል መናኛ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል” ስትል መለሰች። “እናቴን ‘እማዬ፣ ማንም ሰው አብሮኝ ሊኖር የማይችል አስቸጋሪ ሰው ነኝ? ልወደድ የማልችል ሰው ነኝ?’ ብዬ የምጠይቅበት ጊዜ አለ።” ባልዋ የሚናገረው ነገር የሚያሳድርባትን ስሜት መግለጽዋን ስትቀጥል ባልዋ ማልቀስ ጀመረ። ሚስቱን በአንደበቱ እንዴት ሲያቆስላት እንደኖረ ለመጀመሪያ ጊዜ መገንዘብ ቻለ።
ለውጥ ልታደርግ ትችላለህ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የስድብ ቃላት የመናገር ችግር ነበረባቸው። እነዚህን ሰዎች ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ቁጣንና ንዴትን፣ ክፋትንም፣ ከአፋቸውም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር’ እንዲያስወግዱ መክሯቸዋል። (ቆላስይስ 3:8) ይሁን እንጂ ሻካራ ንግግር የመናገር ችግር የሚከሰተው በምላስ ሳይሆን በልብ ምክንያት ነው። (ሉቃስ 6:45) ጳውሎስ በማከል ‘አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ግፈፉት . . . አዲሱን ሰው ልበሱ’ ያለው በዚህ ምክንያት ነው። (ቆላስይስ 3:9, 10) ስለዚህ ለውጡ የአነጋገር ለውጥ ብቻ ሳይሆን የስሜት ለውጥ ማድረግን ጭምር የሚጠይቅ ነው።
ጎጂ የሆኑ ቃላት የመናገር ልማድ ያለበት ባል ከጠባዩ በስተጀርባ ያለው ዝንባሌ ምን እንደሆነ እንዲገነዘብ እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልገው ይችላል።c “አቤቱ፣ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፈትነኝ መንገዴንም እወቅ። በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ” እንዳለው መዝሙራዊ ያለ ዝንባሌ እንዲኖረው መፈለግ ይኖርበታል። (መዝሙር 139:23, 24) ለምሳሌ ያህል፣ ሚስቱን ጨቁኖ ለመግዛት ወይም ለመቆጣጠር የሚፈልገው ለምንድን ነው? የስድብ ቃላት እንዲናገር የሚያነሳሳው ነገር ምንድን ነው? ኃይለ ቃል የሚናገረው በውስጡ አምቆ የያዘው ቅሬታ ስላለው ነውን? (ምሳሌ 15:18) በልጅነቱ ብዙ የሚያዋርደው የቁጣ ንግግር ሲሰማ ስላደገ ከንቱ ሰው እንደሆነ ይሰማው ይሆንን? አንድ ሰው እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች መጠየቁ የባሕርዩ ምንጭ ምን እንደሆነ እንዲገነዘብ ሊረዳው ይችላል።
የተሳዳቢነት ልማድ በተለይ ሻካራ አንደበት ካላቸው ወላጆች ወይም አምባገነንነትን ከሚያደፋፍር ባሕል የተወረሰ ከሆነ ከሥሩ ነቅሎ መጣል አስቸጋሪ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የተለመደ ማንኛውም ልማድ በቂ ጊዜ ከተሰጠውና ጥረት ከተደረገበት ሊወገድ ይችላል። በዚህ ረገድ ትልቁን እርዳታ የምናገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሥር የሰደዱ ባሕርያትን እንኳን እንድናስወግድ ሊረዳን ይችላል። (ከ2 ቆሮንቶስ 10:4, 5 ጋር አወዳድር።) እንዴት?
አምላክ ለሰጠው ቦታ ተገቢ አመለካከት መያዝ
አብዛኛውን ጊዜ ጎጂ ቃላት የሚናገሩ ሰዎች አምላክ ለባልና ሚስት የሰጠውን ቦታና የሥራ ድርሻ በተመለከተ የተጣመመ አመለካከት አላቸው። ለምሳሌ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ ሚስቶች ‘ለባሎቻቸው እንዲገዙ’ እና “ባል የሚስት ራስ” እንደሆነ ተናግሯል። (ኤፌሶን 5:22, 23) አንድ ባል የራስነት ቦታው በሚስቱ ላይ የፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣን እንደሚሰጠው ሊሰማው ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ትክክል አይደለም። ሚስቱ ለእርሱ የምትገዛ ብትሆንም ባሪያው አይደለችም። ‘ረዳቱ’ ወይም ‘ማሟያው’ ነች። (ዘፍጥረት 2:18) በዚህም ምክንያት ጳውሎስ በማከል “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፣ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለ ሆንን፣ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፣ ይመግበዋል ይከባከበውማል” ብሏል።— ኤፌሶን 5:28, 29
የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘ደግሞ መቼ ይሆን ተቆጥቶ የሚጮህብን’ ብለው እስኪጨነቁ ድረስ የቁጣ ወይም የወቀሳ ውርጅብኝ አውርዶባቸው አያውቅም። ከዚህ ይልቅ በደግነትና በርህራሄ በመያዝ ክብራቸውን ይጠብቅ ነበር። ‘እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ስለሆንኩ አሳርፋችኋለሁ’ ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 11:28, 29) አንድ ባል ኢየሱስ የራስነት ሥልጣኑን እንዴት እንደተጠቀመበት በጸሎት ቢያሰላስል የራስነት ቦታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዲመለከት ሊረዳው ይችላል።
ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ
የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማወቅ ቀላል ቢሆንም አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ማዋል ከባድ ነው። አንድ ባል አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙት ጊዜ ሻካራ ንግግር ወደ መናገር ልማዱ እንዳይመለስ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?
አንድ ባል በሚቆጣበት ጊዜ ኃይለ ቃል መናገሩ የወንድነት ምልክት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፣ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስድ ይበልጣል” ይላል። (ምሳሌ 16:32) እውነተኛ የወንድነት ስብዕና የተላበሰ ሰው መንፈሱን ይቆጣጠራል። ‘የምናገረው ቃል ሚስቴ ምን እንዲሰማት ያደርጋል? እኔ በእርሷ ቦታ ብሆን እንዴት ይሰማኛል?’ ብሎ በማመዛዘን ራሱን በሚስቱ ቦታ አስቀምጦ ያያል።— ከማቴዎስ 7:12 ጋር አወዳድር።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ሁኔታዎች ሊያስቆጡ እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። መዝሙራዊው እንደነዚህ ስላሉት ሁኔታዎች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ተቆጡ፣ ነገር ግን ኃጢአትን አታድርጉ። በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፤ ዝም በሉ።” (መዝሙር 4:4) በተጨማሪም እንዲህ ተብሏል:- “መቆጣት ምንም ስህተት የለውም፤ የተቆጡበትን ሰው በማዋረድ፣ በማሽሟጠጥ ወይም በማቃለል በአንደበት ማቁሰል ግን ስህተት ነው።”
አንድ ባል አንደበቱን መቆጣጠር እያቃተው እንደሆነ ከተሰማው ንግግሩን የት ላይ ማቆም እንዳለበት መማር ያስፈልገዋል። ምናልባት ክፍሉን ጥሎ ቢወጣ፣ ጥቂት ወዲያ ወዲህ ብሎ ቢመለስ ወይም መንፈሱን የሚያረጋጋበት ጸጥ ያለ ሥፍራ ቢፈልግ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ምሳሌ 17:14 “ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው” ይላል። የሁለቱም ስሜት ረጋ በሚልበት ጊዜ ወደ ውይይቱ መመለስ ይቻላል።
እርግጥ ማንም ሰው ፍጹም አይደለም። ኃይለ ቃል የመናገር ልማድ የነበረበት ባል ይህ ልማዱ በየጊዜው ሊያገረሽበት ይችላል። በዚህ ጊዜ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል። ‘አዲሱን ሰው መልበስ’ በአንድ ጊዜ የማይከናወን ቀጣይነት ያለው ሂደት ቢሆንም ብዙ ዋጋ ያስገኛል።— ቆላስይስ 3:10
ፈዋሽ የሆኑ ቃላት
አዎን፣ “ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው።” (ምሳሌ 18:21) የሚያቆስሉ ቃላት አንድን ትዳር ሊያጠናክሩና ሊገነቡ በሚችሉ ቃላት መተካት ይኖርባቸዋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፣ ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው” ይላል።— ምሳሌ 16:24
ከጥቂት ዓመታት በፊት ቤተሰቦች በጥሩ ሁኔታ አብረው እንዲኖሩ ባስቻሉ ነገሮች ላይ አንድ ጥናት ተደርጎ ነበር። “የእነዚህ ቤተሰቦች አባሎች እርስበርሳቸው እንደሚዋደዱና የሚዋደዱ መሆናቸውንም አንዳቸው ለሌላው በየጊዜው እንደሚገልጹ ይህ ጥናት አረጋግጧል” ሲሉ ጋብቻ ነክ ስለሆኑ ጉዳዮች በርካታ ጥናት ያደረጉት ዴቪድ አር ሜስ ሪፖርት አድርገዋል። “አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅርና ድጋፍ ይገልጻሉ፣ አንዳቸው ሌላውን ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው እንዲሰማቸው ያደርጋሉ፣ ፍቅራቸውን በቃልና በድርጊት ሊገልጹ በሚያስችሏቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ይጠቀማሉ። በዚህም ምክንያት አብረው መኖራቸው ያስደስታቸዋል። በመካከላቸው ያለው ዝምድናም የተጠናከረና ከፍተኛ እርካታ የሚያስገኝላቸው ይሆናል።”
ማንም ፈሪሐ አምላክ ያለው ባል ሆን ብሎ ሚስቱን በአንደበቱ እያቆሰለ ሚስቴን እወዳለሁ ሊል አይችልም። (ቆላስይስ 3:19) ሚስትም ብትሆን ባልዋን በአንደበቷ የምትጋረፍ ከሆነች ባሌን እወዳለሁ ለማለት አትችልም። ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የጻፈውን ምክር መከተል ግዴታቸው እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” ብሏል።— ኤፌሶን 4:29
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጥፋተኛው በተባዕታይ ጾታ ቢጠቀስም እዚህ የሰፈሩት መሠረታዊ ሥርዓቶች ለሴቶችም እኩል የሚሠሩ ናቸው።
b አንድ ሰው ሽማግሌ ለመሆን ብቁ እንዲሆንና በዚህ ኃላፊነቱ ለመቀጠል ማሟላት ከሚኖርባቸው ብቃቶች አንዱ የማይማታ መሆን ነው። ሌሎችን የሚደበድብ ወይም በመርዘኛ ቃላት የሚማታ መሆን የለበትም። ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ቤተሰባቸውን በሚገባ የሚያስተዳድሩ መሆን አለባቸው። አንድ ሰው በውጭ ምንም ዓይነት የደግነት ባሕርይ ቢያሳይ በቤቱ አምባገነን ከሆነ በእነዚህ የኃላፊነት ቦታዎች ለማገልገል ብቃት አይኖረውም።— 1 ጢሞቴዎስ 3:2-4, 12
c አንድ ክርስቲያን የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ቢፈልግ ይህ በግሉ የሚያደርገው ውሳኔ ነው። ይሁን እንጂ የሚሰጠው ማንኛውም ዓይነት ሕክምና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የማይጥስ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ባልና ሚስት እንዲግባቡ ሊረዳቸው ይችል ይሆናል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሎችና ሚስቶች አንዳቸው የሌላውን ስሜት ለመረዳት ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል