ከዓለም አካባቢ
ቅዱሳን ጽሑፎች በ2,123 ቋንቋዎች
በአሁኑ ጊዜ ቅዱሳን ጽሑፎች ከ2,100 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ሊነበቡ እንደሚችሉ የጀርመን የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የኅትመት ኃላፊ በቅርቡ ማስታወቃቸውን ዌተራወር ዜይቱንግ የተባለ ጋዜጣ ዘግቧል። የሰው ልጅ 6,000 ቋንቋዎችን እንደሚናገር ይገመታል። ይህ ማለት ቢያንስ ቢያንስ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሰው ከሚናገራቸው ቋንቋዎች ውስጥ ከአንድ ሦስተኛ በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛሉ ማለት ነው። ቢበልሪፖርት በተባለው መጽሔት መሠረት ባሁኑ ጊዜ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በ349 ቋንቋዎች ይገኛል። “አዲስ ኪዳን” በሌሎች 841 ቋንቋዎች፣ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ደግሞ በ933 ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። በድምሩ መጽሐፍ ቅዱስ በ2,123 ቋንቋዎች ይገኛል። አብዛኞቹ የትርጉም ቡድኖች “አዲስ ኪዳንን” ለመተርጐም አራት ዓመት ያህል፣ “ብሉይ ኪዳንን” ለመተርጐም ደግሞ ስምንት ዓመት ያህል ያስፈልጋቸዋል። በአሁኑ ጊዜ በሌሎች 600 ቋንቋዎች አዲስ ትርጉም በመካሄድ ላይ ነው።
የተላላፊ በሽታዎች መቅሰፍት
አምና ከሞቱት 52 ሚልዮን ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚያህሉት የሞቱት በተላላፊ በሽታዎች ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) አስታውቋል። 17 ሚልዮን ይሆናሉ ተብለው ከተገመቱት ከእነዚህ ሟቾች ውስጥ አብዛኞቹ ሕፃናት ነበሩ። የዓለም ጤና ድርጅት ያሳተመው የዓለም ጤና ሪፖርት 1996 የተባለ መጽሔት ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ 30 አዳዲስ ተላላፊ በሽታዎች መገኘታቸውን አስታውቋል። ከእነዚህ ውስጥ የኢቦላ ቫይረስና ኤድስ ይገኙባቸዋል። እንደ ሳንባ ነቀርሳ፣ ኮሌራና ወባ የመሳሰሉ በሽታዎችን መከላከልና ማዳን የሚቻል ቢሆንም እንደገና እያንሰራሩ ከመሆናቸውም ሌላ መድኃኒትን የመቋቋም ኃይል አዳብረዋል። ከላይ የተጠቀሰው ሪፖርት ምክንያቱን ሲገልጽ “ሰዎች አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን አላስፈላጊና ያለ ምንም ቁጥጥር መውሰዳቸው ነው” በማለት ይናገራል። በዚህ ላይ ደግሞ ከአገር አገር የሚደረጉ ጉዞዎች፣ የወባ ትንኝ በሚበዛባቸው የሐሩር አካባቢዎች የሕዝብ ቁጥር ማደጉና የመሳሰሉ ምክንያቶች አሉ።
ምኗም አይጣልም
ላም ታርዳ 250 ኪሎ ግራም የሚያህል ሥጋ ለመብል ከተወሰደ በኋላ የቀረው ነገር ምን ይሆናል? አንዳንዱ የውስጥ አካሏ ለምሳሌ የታይሮይድ ዕጢ፣ ቆሽት፣ ሳንባ፣ ጣፊያ፣ አድሬናል ዕጢ፣ የዕንቁላል ማምረቻ ክፍል (ኦቫሪ)፣ ፒቱታሪ ዕጢ፣ በሐሞት ከረጢትና በጉበት ውስጥ ያለው ሐሞት ለመድኃኒት መሥሪያነት ያገለግላሉ። ከአጥንት፣ ከሰኮናና ከቆዳ የሚወጣው ኮላጅን የተባለ ንጥረ ነገር የፀጉርና የፊት ቅባት ይሠራበታል። አንጆውና ስቡ ለፀጉርና ለቁንጅና ቅባቶች መሥሪያነት በሚያገለግሉ ብዩቲል ስቴይሬት፣ PEG-150 ዳይስቴይሬት፣ ግላይኮል ስቴይሬት በተባሉ ዝግጅቶች ውስጥ ይጨመራሉ። አብዛኞቹ የሳሙና ዓይነቶች የሚሠሩት ከከብት ስብ ነው። አጥንቱና ሰኮናው ተፈጭቶ እንደ አይስክሬም፣ ከረሜላ፣ እና በርካታ “ቅባት አልባ” ምግቦች ለመሥራት በሚያገለግለው ጀላቲን ውስጥ ይጨመራል። ሌሎች የሰውነት ክፍሎች እንደ ባለ ቀለም እርሳሶች፣ ክብሪት፣ ሰም፣ ፕላስቲክ የወለል ምንጣፍ፣ የበረዶ ቅዝቃዜ መከላከያ፣ ሲሚንቶ፣ የአረም መድኃኒቶች፣ የልብስ መጠቅለያ ፕላስቲክ፣ የፎቶግራፍ ወረቀት፣ የስፖርት ዕቃዎች፣ የመኪና ወንበር ሽፋን፣ ልብስ እና ሌሎች ብዙ ነገሮችን ለመሥራት ያገለግላሉ። ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣው የሐሞት ጠጠሩ ሲሆን 28 ግራም በ600 የአሜሪካ ዶላር ይሸጣል! የሩቅ ምሥራቅ ነጋዴዎችም የጾታ ስሜት ይቀሰቅሳሉ ብለው በማሰብ ይገዟቸዋል።
በወሊድ የሚሞቱት ብዛት
በያመቱ 585,000 ሴቶች በእርግዝና ወይም በወሊድ ወቅት እንደሚሞቱ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ያካሄደው መጠነ ሰፊ አዲስ ጥናት ያሳያል። በ1996 የልዩ ልዩ አገሮች ዕድገት በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የጽሑፍ ሪፖርት መሠረት በወሊድ ጠንቅ የሚመጣውን አብዛኛውን የሞት አደጋ ማስቀረት ይቻል ነበር። ሪፖርቱ እንዲህ ይላል:- “አብዛኞቹ ሴቶች የሞቱት ታማሚ ስለሆኑ፣ በጣም ስላረጁ ወይም በጣም ልጅ ስለሆኑ አይደለም። በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ጤናማ ሴቶች ናቸው።” በያመቱ 75,000 የሚያክሉ ሴቶች ለማስወረድ ሲሞክሩ፤ 40,000 የሚያህሉ ሴቶች በማኅፀን መጥበብ ምክንያት ምጥ ሲበረታባቸው፤ 100,000 ደማቸው ስለሚመረዝ፤ 75,000 በኢክላምፕሲያ (በእርግዝና ወቅት የሚከሰት እንቅጥቅጥና ከፍተኛ የደም ግፊት ብዛት በሚያስከትለው የአንጎልና የኩላሊት ጉዳት)፤ 140,000 በደም መፍሰስ ሳቢያ ይሞታሉ። ለዚህ ዋናው ምክንያት በአያሌ አገሮች ነፍሰ ጡሮችንና ወላዶችን የሚረዱ ሐኪሞች እጥረት ስላለ ነው። የዩኒሴፍ ባለ ሥልጣኖች እንደገለጹት በደቡብ እስያ ውስጥ ከ35 ሴቶች አንዷ፣ ከሳሃራ በታች ባሉት የአፍሪካ አገሮች ከ13 ሴቶች አንዷ ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ሳቢያ ሲሞቱ በካናዳ ግን ከ7,300 ሴቶች አንዷ፣ በዩናይትድ ስቴተስ ከ3,300 ሴቶች አንዷ፣ በአውሮፓ ከ3,200 ሴቶች አንዷ ብቻ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ይሞታሉ። ከዚህ በፊት በወሊድ ጠንቅ የሚሞቱት ሴቶች ቁጥር 500,000 እንደሚሆን ተገምቶ ስለነበረ የአሁኑ አኃዝ 20 በመቶ ከፍ ያለ ነው።
በውጥረት ብዛት ኃይል እንዳይሟጠጥ!
የተለያየ መንስዔ ያለው የውጥረት ስሜት እየጨመረ መጥቷል። ኤለን ማክግራት የተባሉ የሥነ ልቦና ምሁር በአሜሪካ እየታተመ በሚወጣው ጤና (Health) የተባለ መጽሔት ላይ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የኃይል መሟጠጥ ደርሶበት ለበሽታ ከመጋለጡ በፊት ሊወስዳቸው የሚገቡትን እርምጃዎች ጠቁመዋል።
◼ እያረፍክ ሥራ:- የቱንም ያህል ትንሽ ቢሆን ዕረፍት ያስፈልግሃል። ለአሥር ደቂቃ ያህል በእግር ሂድ ወይም ለአምስት ደቂቃ ያህል ፀጥ ባለ ቦታ አየር በኃይል በመሳብ ተንፍስ። በእያንዳንዱ ቀን መጀመሪያና መደምደሚያ ላይ ለ15 ደቂቃ ያህል አንብብ ወይም አሰላስል።
◼ ተረጋግተህ ሥራ:- እንደ ፎቶግራፍ፣ አበቦች፣ የማስታወሻ ዕቃዎች የመሳሰሉ ሳቅ እንድትል የሚያደርጉ ነገሮች አጠገብህ አድርግ። የሥራ ፕሮግራሞችህን ኃላፊነት ባለው መንገድ ፈጽም፤ መቅረት የማይችሉ ነገሮችን ውጥረት በማይበዛበት ሰዓት አከናውን።
◼ በደንብ ተመገብ:- የቱንም ያህል ሥራ ቢበዛብህ በጣም እስኪርብህ ድረስ አትቆይ። በማይረባ ጣፋጭ ምግብ ሆድህን አትደልለው። ፍራፍሬዎችና ቅጠላ ቅጠል የሚበዛባቸውን ምግቦች በተወሰነ ሰዓት ቶሎ ቶሎ መመገብ ድካም ያስቀርልሃል።
◼ ተንቀሳቀስ:- ብዙ እንቅስቃሴ ውጥረትን ይቀንሳል፣ የእርካታ ስሜትን ይጨምራል፣ ነገሮች ከቁጥጥርህ ውጭ እንዳልሆኑ እንዲሰማህ ያደርጋል። ነገሩን እንደ መዝናኛ አድርገህ ተመልከተው።
ወንጀል የሚያስከትለው ከፍተኛ ኪሣራ
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በየቀኑ 94,000 የወንጀል ድርጊቶች እንደሚፈጸሙ የፍትሕ ዘርፉ ይገምታል። ኤድ ሩበንስታይን የተባሉ ኢኮኖሚስት በተናገሩት መሠረት እንደ መኪና፣ ገንዘብ፣ ጌጣጌጦች የመሳሰሉ ነገሮችን በመዘረፍ በቀጥታ የሚደርሰው ኪሣራ በዓመት 20 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል። በዚህ ላይ እንደ ፍርድ ቤት፣ ወኅኒ፣ እና ጥበቃ ለመሳሰሉ ሕግ አስከባሪ አካላት የሚመደበው ወጪ ቢደመር ጠቅላላው ኪሣራ ወደ 100 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ይሆናል። ከዚህም ሌላ የወንጀል ሰለባ የሆኑ ብዙ ሰዎች ድንጋጤ፣ ፍርሃትና ጭንቀት ስለሚሰማቸው እነዚህን አፍራሽ ስሜቶች ለመቋቋም ከሥራ ቀርተው እቤት ይውላሉ። ስለዚህ ምርታማነት እንደሚቀንስ ሲታሰብ ወንጀል የሚያስከትለው ጠቅላላ ኪሳራ በያመቱ “ከ250 እስከ 500 ቢልዩን ዶላር ይደርሳል” በማለት ሩበንስታይን ይናገራሉ።
የዕቃ መወልወያ ጨርቅ በሽታ ሊያስተላልፍ ይችላል
ሳይንቲስቶች የተሠራባቸው የዕቃ መወልወያ ጨርቆችና የወጥ ቤት ስፖንጅ ብዙ ጐጂ ባክቴሪያዎች ያለባቸው ሆነው አግኝተዋቸዋል። ዩሲ በርክለይ ዌልነስ ሌተር በተባለ ጽሑፍ ላይ የሰፈረ በቅርብ የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው “ምርመራ ከተካሄደባቸው 500 እርጥብ ጨርቆችና ስፖንጆች ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት በሽታ ሊያመጡ በሚችሉ ባክቴሪያዎች ተበክለው ተገኝተዋል።” አንድ አራተኛ የሚሆኑት ጨርቆች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ “ምግብ ወለድ በሽታዎችን በማምጣት በኩል ዋነኛ የሆኑት ሳልሞኔላ እና ስታፊሎኮከስ የተባሉ ሁለት የባክቴሪያ ዓይነቶች ተገኝተውባቸዋል።” ስፖንጅ ቶሎ ቶሎ መቀየር እንዳለበት፣ የዕቃ ማድረቂያ ጨርቅም ቶሎ ቶሎ መታጠብ እንዳለበት ባለሞያዎቹ አሳስበዋል። ዌልነስ ሌተር የተባለው ጽሑፍ “የዕቃ መወልወያ ጨርቆችንና ስፖንጆችን ከሚታጠቡት ዕቃዎች ጋር ጨምሮ ማጠቢያ ማሽን ውስጥ መክተት ይቻላል” ብሏል። ጥሬ ሥጋ የነኩ ዕቃዎችን በታጠቡ ጨርቆች ወይም በስፖንጅ ከማድረቅ ይልቅ በአፍ መጥረጊያ ወረቀት ማጽዳት ይቻላል።
ፍጥነታችሁን ጠብቁ!
መኪናን በፍጥነት ማሽከርከር በእንግሊዝ አገር በያመቱ 1,000 ሰዎችን ለሞት፣ 77,000 ሰዎችን ደግሞ ለከባድ ጉዳት እንደሚዳርጋቸው ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ የተባለ የለንደን ጋዜጣ አስታውቋል። ሌላው ቀርቶ በተፈቀደው ፍጥነት ማሽከርከርም በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ከአደጋ አያድንም። በፍጥነት ማሽከርከር በሚፈቀድባቸው መንገዶች ላይ ከሚደርሱት አደጋዎች ውስጥ 10 በመቶ የሚሆኑት ከፊት ለፊት ወዳለው ተሽከርካሪ በጣም በመጠጋት የሚፈጠሩ ናቸው። የብሪታንያ የአውራ ጐዳና ደንብ ከፊት ለፊት ካለው ተሽከርካሪ የሁለት ሴኮንድ ርቀት ቢኖር ጥሩ እንደሆነ ይጠቁማል፤ ሆኖም መንገዱ በውኃ ከተሸፈነ፣ የሚያዳልጥ ከሆነ ወይም እይታን የሚከለክል ነገር ካለ ይህ ርቀት እጥፍ መሆን ይኖርበታል። በጣም ተጠግቶ መንዳት ለአደጋ የሚያጋልጥ ከመሆኑም አልፎ አድካሚና የስሜት ውጥረት የሚፈጥር ነው። አሽርካሪዎች ለአደጋ የማያጋልጥ ክፍተት ከተውን ሌላ መኪና ጥልቅ ብሎ ይገባል በማለት ብዙ ጊዜ ያማርራሉ። ቢሆንም አሁንም ከአደጋ ለመዳን ያለው ብቸኛው መንገድ ፍጥነትን ቀንሶ ክፍተቱን እንደገና ማስፋት ነው። በድንገት ፍሬን መያዝ ግጭት ሊያስከትል ስለሚችል አደጋ የሚያመጡ ነገሮችን ለመከታተል ፊት ፊት እያየህ አሽከርክር። መኪና መንዳት የሚያስረምሩት ፖል ሪፕለይ “ለማንኛውም ሁኔታ ተስማሚ የሆነው ከአደጋ የሚያድነው ፍጥነት አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ከሚገምቱት በታች ነው” ብለዋል።
የሳንባ ነቀርሳ መስፋፋት
“አንድ ሦስተኛው የዓለም ሕዝብ በሳንባ ነቀርሳ እንደተለከፈና” ይህ በሽታ በያዝነው አሥርተ ዓመት ውስጥ 30 ሚልዮን ሰዎች ይገድላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለንደን የሚታተመው ዘ ታይምስ የተባለ ጋዜጣ ዘግቧል። የዓለም ጤና ድርጅት አዲስ መቅሰፍት ብሎ የጠራው ይህ በሽታ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከኤድስ በከፋ ሁኔታ ተዛማችና ደምሳሽ እንደሚሆን፣ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታትም 300 ሚልዮን ሰዎች በበሽታው እንደሚያዙ ድርጅቱ አበክሮ ገልጿል። የሳንባ ነቀርሳ የሚያመጡ ባሲላይ የተባሉት ባክተሪያዎች አየር ወለድ ስለሆኑ በሽታው በጣም ተዛማች ነው ማለት ነው። በሩስያ አንዳንድ አካባቢዎች አሁንም እንኳ የሳንባ ነቀርሳ በወረርሽኝ ደረጃ ተስፋፍቷል። ብዙ የሳንባ ነቀርሳ ሕሙማን የሚታዘዙላቸውን አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ስድስት ወር አሟልተው ስላልወሰዱ መድኃኒቱን የሚቋቋሙ የባሲለስ ባክቴሪያዎች ተፈጥረዋል በማለት የእንግሊዝ የሕክምና ተራድኦ ድርጅት አስታውቋል። በዚህ ምክንያት ባሲላይ የሚባሉት ባክቴሪያዎች መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ አዳብረው በሕይወት ለመቀጠል ችለዋል።