የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 2/8 ገጽ 4-9
  • ድልና አሳዛኝ ሽንፈት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ድልና አሳዛኝ ሽንፈት
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በመጨረሻ መፈወሻ መድኃኒት ተገኘ!
  • ቀሳፊው በሽታ ዳግመኛ አገረሸ
  • እንደገና ያገረሸው ለምንድን ነው?
  • ኤች አይ ቪ እና ሳንባ ነቀርሳ—ጣምራ ችግሮች
  • ብዙ መድኃኒቶችን ሊቋቋም የሚችል ሳንባ ነቀርሳ
  • መከላከያና ፈውስ
  • ከሳንባ ነቀርሳ ጋር ለሚደረገው ፍልሚያ የተቀየሰ አዲስ ስልት
    ንቁ!—1999
  • ከጦርነት ጋር የሚመጣጠን እልቂት
    ንቁ!—1998
  • የሳንባ ነቀርሳ አገርሽቷል!
    ንቁ!—1996
  • ምድር አቀፍ መፍትሔ ሊገኝ ይችል ይሆን?
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 2/8 ገጽ 4-9

ድልና አሳዛኝ ሽንፈት

“ያለፈው የሰላሳ ዓመት የሳንባ ነቀርሳ ታሪክ፣ ድልና አሳዛኝ ሽንፈት የተመዘገበበት ወቅት ነው። በሽታውን ለመቆጣጠርና ብሎም ፈጽሞ ለማጥፋት የሚያስችለውን ዘዴ ላገኙት ሳይንቲስቶች ትልቅ ድል ሲሆን የእነዚህን ሳይንቲስቶች ግኝት ሥራ ላይ ማዋል ላቃታቸው ሰዎች ግን አሳዛኝ ሽንፈት ሆኗል።”—ጄ አር ቢግናል፣ 1982

ሳንባ ነቀርሳ (TB) የሰው ልጆችን መግደል ከጀመረ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። አውሮፓውያን የደቡብ አሜሪካን ምድር ከመርገጣቸው በፊት በፔሩ ይኖሩ የነበሩትን ኢንካዎች ይገድል ነበር። ፈርዖኖች በታላቅ ግርማ ይገዙ በነበረበት ዘመን ግብጻውያን በዚህ በሽታ ይጠቁ ነበር። በጥንቷ ባቢሎን፣ በግሪክና በቻይና ሳንባ ነቀርሳ ሀብታምና ድሃ ሳይለይ ብዙ ሰዎችን ይቀስፍ እንደነበረ የጥንት ጽሑፎች ያመለክታሉ።

ከአሥራ ስምንተኛው እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ባለው ጊዜ በምዕራቡ ዓለም ዋነኛው የመሞቻ ምክንያት ሳንባ ነቀርሳ ነበር። በ1882 ሮበርት ኮኽ የተባለ ጀርመናዊ ዶክተር የዚህ በሽታ መንስዔ የሆነውን ባሲለስ ለይቶ ማወቁን አስታወቀ። ከአሥራ ሦስት ዓመት በኋላ ቪልኸልም ሮንትገን ኤክስ ሬይ የተባሉ ጨረሮችን በማግኘቱ በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሳንባ በመመርመር የበሽታው ምልክት ያለባቸውና የሌለባቸው መሆኑን ማወቅ ተቻለ። ከዚያ ቀጥሎ በ1921 የፈረንሳይ ሳይንቲስቶች ከሳንባ ነቀርሳ የሚከላከል ክትባት ሠሩ። በፈልሳፊዎቹ ሳይንቲስቶች ስም ቢ ሲ ጂ (ባሲለስ ካልመት-ገሪ) እየተባለ የሚጠራው ይህ ክትባት ብቸኛው የሳንባ ነቀርሳ መከላከያ ሆኖ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ሳንባ ነቀርሳ ብዙ ሰዎችን መፍጀቱን አላቆመም።

በመጨረሻ መፈወሻ መድኃኒት ተገኘ!

ሐኪሞች የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞችን ወደ ማገገሚያ ጣቢያዎች ይልኩ ነበር። እነዚህ ሆስፒታሎች አብዛኛውን ጊዜ የሚሠሩት በሽተኞች ጥሩ እረፍትና ንጹህ አየር ሊያገኙ በሚችሉባቸው ተራራማ አካባቢዎች ነበር። በ1944 ግን በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ዶክተሮች የሳንባ ነቀርሳ በሽታን ለማዳን የመጀመሪያ የሆነውን ስትሬፕቶማይሲን የተባለ አንቲባዮቲክ አገኙ። ወዲያው ሌሎች ፀረ ሳንባ ነቀርሳ የሆኑ መድኃኒቶች በተከታታይ ተፈለሰፉ። በመጨረሻ የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞችን ከገዛ ቤታቸው መውጣት ሳያስፈልጋቸው ማዳን ተቻለ።

በበሽታው የሚለከፉ ሰዎች ቁጥር በጣም እየቀነሰ በመሄዱ የወደፊቱ ጊዜ ብሩሕ ሆኖ መታየት ጀመረ። የሳንባ ነቀርሳ ማገገሚያ ጣቢያዎች ተዘጉ። በሳንባ ነቀርሳ ላይ ምርምርና ጥናት ለሚያደርጉ ተመራማሪዎች ይመደብ የነበረው ባጀት በጣም ቀነሰ። የመከላከያ ፕሮግራሞች ከመቋረጣቸውም በተጨማሪ ሳይንቲስቶችና ዶክተሮች በአዳዲስ የሕክምና ችግሮች ላይ ምርምር ማድረግ ጀመሩ።

ባልበለጸጉ አገሮች በሳንባ ነቀርሳ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ገና ያልቀነሰ ቢሆንም ሁኔታው መሻሻሉ እንደማይቀር ታመነ። ሳንባ ነቀርሳ ታሪክ ብቻ ሆኖ ይቀራል ተብሎ ታሰበ። ግን ተሳስተው ነበር።

ቀሳፊው በሽታ ዳግመኛ አገረሸ

በ1980ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ሳንባ ነቀርሳ በሚያስደነግጥ ሁኔታ አገርሽቶ የብዙ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፍ ጀመረ። በሚያዝያ ወር 1993 የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ሳንባ ነቀርሳ “አስቸኳይ መፍትሔ የሚሻ ዓለም አቀፍ አደጋ” መሆኑን ከመግለጹም በተጨማሪ “የበሽታውን ስርጭት ለመግታት አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት 30 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ይሞታሉ” ሲል አስታወቀ። የዓለም ጤና ድርጅት በታሪኩ ውስጥ እንዲህ ያለ መግለጫ ሲያወጣ የመጀመሪያው ነበር።

ከዚያ ጊዜ ወዲህ በሽታውን ለመግታት የተወሰደ “አፋጣኝ እርምጃ” የለም። እንዲያውም ሁኔታው ተባብሷል። የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ሪፖርት እንዳደረገው በ1995 በሳንባ ነቀርሳ ምክንያት የሞቱት ሰዎች በማንኛውም ዓመት ከሞቱት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል። በተጨማሪም የዓለም ጤና ድርጅት በሚቀጥሉት 50 ዓመታት ውስጥ እስከ ግማሽ ቢልዮን የሚደርሱ ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ እንደሚታመሙ አስጠንቅቋል። ብዙ መድኃኒቶችን ሊቋቋም በሚችልና ፈውስ በሌለው ዓይነት ሳንባ ነቀርሳ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያደር እየጨመረ መጥቷል።

እንደገና ያገረሸው ለምንድን ነው?

አንደኛው ምክንያት ባለፉት 20 ዓመታት የሳንባ ነቀርሳ መቆጣጠሪያ ፕሮግራሞች በብዙ የዓለም ክፍሎች መዳከማቸውና እንዲያውም ጨርሶ እስከ መቆም መድረሳቸው ነው። በዚህ ምክንያት በሽታው መኖሩን ቶሎ ብሎ ለማወቅና አፋጣኝ ሕክምና ለመስጠት ሳይቻል ቆይቷል። ይህ ደግሞ የበሽታው ስርጭትና በበሽታው ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል።

ሳንባ ነቀርሳ እንደገና እንዲያገረሽ ያደረገው ሌላው ምክንያት በተለይ ባልበለጸጉ አገሮች በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩና በቂ ምግብ የማያገኙ ድሆች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ነው። የሳንባ ነቀርሳ በሽታ የሚይዘው ድሆችን ብቻ ባይሆንም (ማንም ሰው በዚህ በሽታ ሊለከፍ ይችላል) የአካባቢ ንጽሕና መጓደልና በጣም በተፋፈገ ሁኔታ መኖር የበሽታውን ስርጭት ያፋጥናል። በተጨማሪም እነዚህ ሁኔታዎች የሰዎችን በሽታ የመቋቋም አቅም በጣም ያደክማሉ።

ኤች አይ ቪ እና ሳንባ ነቀርሳ—ጣምራ ችግሮች

ዋነኛው ችግር ሳንባ ነቀርሳ የኤድስ መንስዔ ከሆነው የኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር ግንባር መፍጠሩ ነው። በ1995 ከኤድስ ጋር ተዛምዶ ባላቸው ምክንያቶች ከሞቱት አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የሞቱት በሳንባ ነቀርሳ እንደሆነ ይገመታል። ይህ የሆነው ኤች አይ ቪ ሰውነት ሳንባ ነቀርሳን ለመከላከል ያለውን አቅም ስለሚያዳክም ነው።

አብዛኛውን ጊዜ በሳንባ ነቀርሳ የተለከፈ ሰው የበሽታው ታማሚ ወደ መሆን ደረጃ አይደርስም። ለምን? ምክንያቱም የሳንባ ነቀርሳ ባሲለሶች ማክሮፌጅ በሚባሉ ሴሎች ውስጥ እስረኛ ሆነው ስለሚኖሩ ነው። በእነዚህ ሴሎች ውስጥ በሰውዬው የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት፣ በተለይም ቲ ሊምፎሳይት ወይም ቲ በሚባሉት ሕዋሳት ተጠምደው ይቀራሉ።

የሳንባ ነቀርሳ ባሲለሶች ጥሩ ግጣም ባለው ቅርጫት ውስጥ ተዘግቶባቸው እንደተቀመጡ መርዛማ እባቦች ናቸው። ቅርጫቱ ማክሮፌጆች ሲሆኑ የቅርጫቱ ክዳን ደግሞ ቲ ሕዋሳት ናቸው። የኤድስ ቫይረሶች በሚመጡበት ጊዜ ግን የቅርጫቱን ክዳን ይከፍታሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ባሲለሶቹ ከቅርጫቱ ውስጥ አፈትልከው ይወጡና ያገኙትን የሰውነት ክፍል ማጥቃት ይጀምራሉ።

ስለዚህ የኤድስ በሽተኞች በሳንባ ነቀርሳ የመያዛቸው አጋጣሚ ጤነኛ የሆነ የበሽታ መከላከያ ካላቸው ሰዎች በጣም የበለጠ ይሆናል። በስኮትላንድ የሚኖሩ አንድ የሳንባ ነቀርሳ ተመራማሪ “ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ለሳንባ ነቀርሳ የተጋለጡ ናቸው” ብለዋል። “አንድ ክሊኒክ ውስጥ ሁለት የኤች አይ ቪ ሕመምተኞች መተላለፊያ ላይ ተቀምጠው ሳለ አንድ የሳንባ ነቀርሳ ሕመምተኛ በሚገፋ አልጋ ላይ ሆኖ ሲያልፍ በሽታው ተጋብቶባቸዋል።”

ስለዚህ ኤድስ ለሳንባ ነቀርሳ ወረርሽኝ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። በአንድ ግምት መሠረት በ2000 ዓመት 1.4 ሚልዮን የሚያክሉ በሌላ ምክንያት ሊያዙ የማይችሉ ሰዎች በኤድስ ወረርሽኝ ምክንያት የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች ይሆናሉ። ለሳንባ ነቀርሳ ወረርሽኝ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት የሆነው የኤድስ በሽተኞች በሳንባ ነቀርሳ የመያዝ ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በሽታውን ለሌሎች ሰዎች ሌላው ቀርቶ ኤድስ ለሌለባቸው ጭምር ለማስተላለፍ የሚችሉ መሆናቸው ነው።

ብዙ መድኃኒቶችን ሊቋቋም የሚችል ሳንባ ነቀርሳ

ከሳንባ ነቀርሳ ጋር የሚደረገውን ውጊያ በጣም አስቸጋሪ ካደረጉት ምክንያቶች የመጨረሻው፣ መድኃኒቶችን መቋቋም የሚችሉ የሳንባ ነቀርሳ ዓይነቶች እየተስፋፉ መሄዳቸው ነው። እነዚህ የሳንባ ነቀርሳ ዓይነቶች አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ከመፈልሰፋቸው በፊት እንደነበረው ዘመን በሽታውን ፈውስ የለሽ ወደማድረግ እየተቃረቡ ነው።

በጣም የሚያሳዝነው መድኃኒቶችን የሚቋቋሙ የሳንባ ነቀርሳ ዓይነቶች የተፈጠሩት በፀረ ሳንባ ነቀርሳ መድኃኒቶች ተገቢ ያልሆነ የአወሳሰድ ልማድ ሳቢያ ነው። የሳንባ ነቀርሳ ሕክምና ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ አራት ዓይነት መድኃኒቶች በተከታታይና አለማሰለስ ቢያንስ ለስድስት ወራት መውሰድ ያስፈልጋል። በሽተኛው በየቀኑ ከደርዘን የማያንሱ እንክብሎችን መውሰድ ሊኖርበት ይችላል። በሽተኞች መድኃኒቶቹን አዘውትረው ካልወሰዱ ወይም ሙሉውን ሕክምና ካልጨረሱ ለማዳን አስቸጋሪ የሆኑ ወይም ፈጽመው ሊድኑ የማይችሉ የሳንባ ነቀርሳ ዓይነቶች ይፈጠራሉ። አንዳንዶቹ የባሲለስ ዓይነቶች እስከ ሰባት የሚደርሱ የተለመዱትን ፀረ ሳንባ ነቀርሳ መድኃኒቶች የመቋቋም አቅም ያላቸው ናቸው።

በርካታ መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ያለውን የሳንባ ነቀርሳ ዓይነት ማከም አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው። ሌሎች የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞችን ለማከም ከሚጠይቀው ወጪ ከመቶ እጥፍ በላይ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ አንድን በሽተኛ ለማከም ከ250,000 ዶላር በላይ ወጪ ሊጠይቅ ይችላል!

ወደፊት በመላው ዓለም 100 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች መድኃኒቶችን የመቋቋም አቅም ባላቸው የሳንባ ነቀርሳ ዓይነቶች ሊያዙ እንደሚችሉና ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በማንኛውም ዓይነት ፀረ ሳንባ ነቀርሳ መድኃኒት ሊታከሙ የማይችሉ እንደሚሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት ገምቷል። እነዚህ ቀሳፊ የሳንባ ነቀርሳ ዓይነቶች ወደ ሌላ ሰው የመጋባት ችሎታቸው ከተራዎቹ ዓይነቶች አይተናነስም።

መከላከያና ፈውስ

ይህን ምድር አቀፍ አደጋ ለመግታት ምን እየተደረገ ነው? ከሁሉ የሚሻለው የመግቻ ዘዴ በሽታው ገና ሥር ሳይሰድ መርምሮ ማግኘትና አክሞ ማዳን ነው። እንዲህ ማድረግ ሕመምተኞቹን ከመርዳቱም በላይ በሽታው ወደ ሌሎች እንዳይዛመት ይከላከላል።

ሳንባ ነቀርሳ ሳይታከም በሚቆይበት ጊዜ በበሽታው ከተያዙት መካከል ከግማሽ የሚበልጡትን ይገድላል። ተገቢው ሕክምና ከተሰጠ ግን መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ያለው ዓይነት እስካልሆነ ድረስ ሁሉም ይድናል ማለት ይቻላል።

ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ሕክምናው ውጤታማ የሚሆነው በሽተኛው ሙሉውን የሕክምና ሂደት ሲጨርስ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ግን በሽተኞች ሙሉውን ሕክምና ተከታትለው አይጨርሱም። ለምን? አብዛኛውን ጊዜ ሳሉ፣ ትኩሳቱና ሌሎቹ የበሽታው ምልክቶች ሕክምናው በተጀመረ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይቆማሉ። በዚህ ምክንያት ብዙ በሽተኞች ድኛለሁ ይሉና መድኃኒቶቹን መውሰድ ያቆማሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ይህንን ችግር ለመቋቋም ሲል ዲ ኦ ቲ ኤስ (ዳይሬክትሊ ኦብዘርቭድ ትሪትመንት፣ ሾርት ኮርስ) የሚባል ፕሮግራም ያካሂዳል። ይህ ፕሮግራም ስሙ እንደሚያመለክተው የጤና ባለሞያዎች ቢያንስ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት በሽተኞቻቸው እያንዳንዱን መድኃኒት በተወሰነው ጊዜ መውሰዳቸውን የሚያረጋግጡበት ነው። ይሁን እንጂ ይህን ማካሄድ ቀላል አልሆነም። ምክንያቱም ብዙ የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች የሚኖሩት ራቅ ባሉ አካባቢዎች ነው። በተጨማሪም አብዛኛውን ጊዜ ሕይወታቸው በችግርና በጭንቀት የተሞላ ስለሆነ (እንዲያውም አንዳንዶቹ የራሳቸው ቤት የሌላቸው ናቸው) በየቀኑ መድኃኒታቸውን መውሰዳቸውን ማረጋገጥ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።

ታዲያ ይህ በሰው ልጆች ላይ የደረሰ መቅሰፍት ድል የሚደረግበት ተስፋ ይኖር ይሆን?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሳንባ ነቀርሳን የሚመለከቱ አንዳንድ መረጃዎች

መግለጫ:- ሳንባ ነቀርሳ አብዛኛውን ጊዜ ሳንባን የሚያጠቃና የሚጎዳ በሽታ ነው። ይሁን እንጂ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊዛመትና በተለይ በአንጎል፣ በኩላሊትና በአጥንቶች ላይ ጉዳይ ሊያደርስ ይችላል።

የበሽታው ምልክቶች:- ሳንባ ነቀርሳ ሳል፣ የክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ሌሊት ሌሊት በጣም ማላብ፣ ድካም፣ የትንፋሽ ማጠርና የደረት ሕመም ሊያስከትል ይችላል።

በሽታው በምርመራ የሚታወቀው እንዴት ነው? አንድ ሰው የበሽታው መንስዔ ከሆኑት ባሲለሶች ጋር ንክኪ የነበረው መሆኑ በቆዳ ላይ ተወግቶ በሚታይ ምርመራ ሊታወቅ ይችላል። ደረትን ራጂ መነሣት በሳንባ ላይ የደረሰ ጉዳት መኖሩን ስለሚያመለክት የሳንባ ነቀርሳ ልክፈት መኖሩን ሊያረጋግጥ ይችላል። የሳንባ ነቀርሳ ባሲለሶች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ከሁሉ የሚሻለው ዘዴ ግን የአክታ ምርመራ ማድረግ ነው።

መመርመር የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው? የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ምልክቶች የሚታዩባቸው ወይም ከሳንባ ነቀርሳ በሽተኛ ጋር ብዙ ጊዜ አብረው የቆዩ፣ በተለይ በቂ አየር በሌለበት ክፍል ውስጥ ብዙ ጊዜ ከበሽተኛው ጋር አብረው የኖሩ ሰዎች መመርመር ያስፈልጋቸዋል።

ክትባት:- እስከ ዛሬ ድረስ ያለው አንድ ክትባት ብቻ ሲሆን ቢ ሲ ጂ ተብሎ ይጠራል። ልጆች በሳንባ ነቀርሳ በሽታ እንዳይያዙ የሚከላከል ሲሆን በጉርምስና ዕድሜ ላሉና ለትላልቅ ሰዎች ግን ምንም ፋይዳ የለውም። ክትባቱ ከበሽታው የሚከላከለው ለ15 ዓመት ያህል ብቻ ነው። ቢ ሲ ጂ በመከላከያነት የሚያገለግለው ገና በበሽታው ላልተለከፉ ሰዎች ሲሆን በሽታው ለያዛቸው ግን ምንም ጥቅም የለውም።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሳንባ ነቀርሳና ፋሽን

ነገሩ እንግዳ ቢመስልም በ19ኛው መቶ ዘመን የበሽታው ምልክቶች ማስተዋልና የሥነ ጥበብ ችሎታ ይቀሰቅሳሉ ተብሎ ይታመን ስለነበረ ሳንባ ነቀርሳ ተወዳጅ ሆኖ ነበር።

አሌክሳንድር ዱማስ የተባለው ፈረንሳዊ ፀሐፌ ተውኔትና ደራሲ ስለ ግሉ ትውስታዎች በጻፈው መጽሐፍ ላይ ስለ 1820ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት እንደሚከተለው ብሏል:- “በደረት ሕመም መሰቃየት እንደ ቄንጥ ይቆጠር ነበር። ሰው ሁሉ፣ በተለይም ባለቅኔዎች ሳንባ ነቀርሳ ይዟቸው ነበር፤ ከሠላሳ ዓመት ዕድሜ በፊት መሞት እንደ ጥሩ ነገር ይታይ ነበር።”

ሎርድ ባይረን የተባሉት እንግሊዛዊ ባለቅኔ እንደሚከተለው እንዳሉ ተዘግቧል:- “በሳንባ ነቀርሳ ብሞት ደስ ይለኛል። . . . ምክንያቱም ወይዛዝርት በሙሉ ‘አይ ምስኪኑ ባይረን፣ ሲሞት እንኳን እንዴት ያምር እንደነበረ ተመልከቱ’ ይሉኛል!”

ሄንሪ ዴቪድ ቶሮ የተባለው አሜሪካዊ ደራሲ የሞተው በሳንባ ነቀርሳ እንደሆነ ሲታመን “መበስበስና ሞት . . . እንደ አጣዳፊው የሳንባ ነቀርሳ ትኩሳት ያማረ ነው” ሲል ጽፏል።

ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ሰዎች ለሳንባ ነቀርሳ ስለነበራቸው ፍቅር እንደሚከተለው ሲል ገልጿል:- “ሰዎች ለዚህ በሽታ የነበራቸው ያልተለመደ ፍቅር በጊዜው በነበረው ፋሽን ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድሮ ነበር። ወይዛዝርት የገረጡና የከሱ ሆነው ለመታየት ይጣጣሩ ነበር። ፊታቸውን የሚያገረጣ ቅባት ይቀቡ፣ ከጥጥ የተሠሩ ስስ ልብሶችን ይመርጡ ነበር። በዘመናችን ያሉትን ከሲታ የፋሽን ሞዴሎች መስለው ለመታየት ይፈልጉ ነበር።”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሳንባ ነቀርሳ በሽታ በቀላሉ ይይዛልን?

የዓለም ጤና ድርጅት የሳንባ ነቀርሳ ፕሮግራም ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር አራታ ኮቺ “ከሳንባ ነቀርሳ ባክቴሪያ ተደብቆ ማምለጥ ፈጽሞ አይቻልም” በማለት ያስጠነቅቃሉ። “ማንም ሰው በሳል ወይም በማስነጠስ አማካኝነት በአየር ውስጥ የተበተነ የሳንባ ነቀርሳ ባክቴሪያ ተንፍሶ ወደ ሰውነቱ ሊያስገባና በበሽታው ሊለከፍ ይችላል። እነዚህ ጀርሞች በአየሩ ውስጥ ለበርካታ ሰዓታት እንዲያውም ለዓመታት ሊቆዩ ይችላሉ። ሁላችንም ለአደጋው የተጋለጥን ነን።”

ይሁን እንጂ ማንም ሰው በሳንባ ነቀርሳ ከመታመሙ በፊት ሁለት ነገሮች መኖር አለባቸው። በመጀመሪያ እርሱ ወይም እርሷ በሳንባ ነቀርሳ ባክቴሪያ መለከፍ ይኖርባቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢንፌክሽኑ ተባብሶ ወደ በሽታነት ደረጃ መድረስ አለበት።

በሽታውን በከፍተኛ ሁኔታ ከሚያስተላልፍ ሰው ጋር ለአጭር ጊዜ ብቻ በመቀራረብ በሽታው ሊጋባ የሚችል ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ በሽታው የሚተላለፈው በበሽታው ከተለከፈ ሰው ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ በመቀራረብ ነው፤ ይህም በተፋፈገ ሁኔታ በሚኖር ቤተሰብ ውስጥ ሊከሰት እንደሚችለው ማለት ነው።

አንድ ሰው በትንፋሽ አማካኝነት በገቡ ባሲለሶች ቢበከል በደረቱ ውስጥ ይራባሉ። ይሁን እንጂ ከአሥር ሰዎች መካከል ዘጠኙ በሰውነታቸው የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ኢንፌክሽኑ ስለሚገታ በባክቴሪያው የተለከፉ ቢሆንም አይታመሙም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ሰውነት በሽታ የመከላከል አቅሙ በኤች አይ ቪ፣ በስኳር በሽታ፣ ለካንሰር በሚወሰዱ መድኃኒቶች ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሲዳከም አንቀላፍተው የቆዩት ባሲለሶች ይቀሰቀሳሉ።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኒው ጀርሲ ሕክምና ትምህርት ቤት—ብሔራዊ የሳንባ ነቀርሳ ማዕከል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኤድስ ቫይረሶች ቀስቅሰው የሚያስነሷቸው የሳንባ ነቀርሳ ባሲለሶች ከተዘጉበት ቅርጫት ውስጥ እንደሚወጡ መርዛማ እባቦች ናቸው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ