የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 7/8 ገጽ 21-22
  • መቻቻል ከአንዱ ጽንፍ ወደ ሌላው

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መቻቻል ከአንዱ ጽንፍ ወደ ሌላው
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከቻይነት ወደ ግትርነት
  • ከቻይነት ሥነ ምግባር የለሽ ወደ መሆን
  • ትክክለኛ ሚዛን መጠበቅ ለሕይወት ጣዕም ይጨምራል
    ንቁ!—1998
  • ሐሳበ ግትር ሳይሆኑ ለመለኮታዊ ደንቦች የጸና አቋም መያዝ
    ንቁ!—1998
  • መቻቻል
    ንቁ!—2015
  • መቻቻል—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 7/8 ገጽ 21-22

መቻቻል ከአንዱ ጽንፍ ወደ ሌላው

አንድ የ16ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋ የካሽሚር ሸለቆን የተፈጥሮ ውበት ከተመለከተ በኋላ በአድናቆት ተሞልቶ “ገነት አለ ከተባለ ከዚህ ሌላ ሊኖር አይችልም!” በማለት ተናግሯል። በአሁኑ ጊዜ በዚያ የዓለም ክፍል የሚታየው ሁኔታ እርሱ ይደርሳል ብሎ ከጠበቀው ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ ግልጽ ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በተገንጣዮችና በሕንድ ወታደሮች መካከል በተደረገው ጦርነት ቢያንስ 20,000 ሰዎች ተገድለዋል። ዙድዶቸ ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ አሁን ይህን አካባቢ “የእንባ ሸለቆ” ሲል ገልጾታል። የካሽሚር ሸለቆ ግልጽና ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ይሰጣል። አለመቻቻል ገነት የመሰለውን አካባቢ እንኳ ሊያበላሽ ይችላል።

ቻይ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ኮሊንስ ኮቢልድ ኢንግሊሽ ላንግዊጅ ዲክሽነሪ “ቻይ ሰው ከሆንክ ሰዎች የራሳቸውን ዝንባሌ ወይም እምነት ይዘው እንዲኖሩ፣ ወይም የማትስማማበት ወይም የማትደግፈው ቢሆንም እንኳን የተለየ ጠባይ እንዲያሳዩ ትፈቅዳለህ” ይላል። ልናዳብረው የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ባሕርይ ነው! ከራሳቸው የተለየ ቢሆንም እንኳን እምነቶቻችንንና ዝንባሌዎቻችንን ከሚያከብሩልን ሰዎች ጋር መሆን ያስደስተናል።

ከቻይነት ወደ ግትርነት

የመቻቻል ተቃራኒ አለመቻቻል ሲሆን ይህ ደግሞ የተለያየ መጠን አለው። አለመቻቻል ሌላው ሰው ያለውን ባሕርይ ወይም አንድ ነገር የሚሠራበትን መንገድ በጠባብ አመለካከት በመጥላት ወይም በመንቀፍ ሊጀመር ይችላል። ጠባብ አመለካከት የአንድን ሰው አእምሮ ለአዳዲስ ሐሳቦች ዝግ እንዲሆን በማድረግ ከሕይወት ሊገኝ የሚችለውን ደስታ ያሳጣል።

ለምሳሌ ያህል አንድ ወግ አጥባቂ የሆነ ሰው የሕፃን ልጅ ቡረቃ ላያስደስተው ይችላል። አንድ ወጣት ከእርሱ ሸምገል ያለ ሰው ባለው ዝግተኝነት ሊሰላች ይችላል። በጣም ጠንቃቃ የሆነ ሰው ማንኛውንም ነገር ከሚዳፈር ችኩል ሰው ጋር እንዲሠራ ቢጠየቅ ሁለቱም ሊበሳጩ ይችላሉ። መጥላትን፣ መሰልቸትንና መበሳጨትን ምን አመጣው? ሦስቱም አንዳቸው የሌላውን ዝንባሌና ጠባይ ለመቻል በመቸገራቸው ምክንያት ነው።

አለመቻቻል በሚኖርበት ቦታ ሁሉ ጠባብ አመለካከት ወደ መሠረተ ቢስ ጥላቻ ይሸጋገርና አንድን የሰዎች ቡድን፣ ዘር ወይም ሃይማኖት በጅምላ ወደ መጥላት ሊያደርስ ይችላል። ግትርነት ከመሠረተ ቢስ ጥላቻ የሚያይል ሲሆን በኃይለኛ ጥላቻ ሊገለጽ ይችላል። በመጨረሻም መሪር ሐዘንና ደም መፋሰስ ይከተላል። አለመቻቻል በመስቀል ጦርነት ጊዜ ያስከተለውን አስብ! በአሁኑ ጊዜ እንኳን ሳይቀር በቦስኒያ፣ በሩዋንዳና በመካከለኛው ምሥራቅ ለተፈጠሩት ግጭቶች ዋነኛው መንስኤ አለመቻቻል ነው።

ቻይ መሆን ሚዛናዊ መሆንን ይጠይቃል። ትክክለኛውን ሚዛን መጠበቅ ደግሞ ቀላል ነገር አይደለም። ወዲያ ወዲህ እንደሚወዛወዝ የሰዓት መቁጠሪያ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ እንንጀዋጀዋለን። በአንድ ወቀት ቻይነት የሚጎድለን እንሆንና በሌላ ጊዜ ደግሞ በጣም ቻዮች እንሆናለን።

ከቻይነት ሥነ ምግባር የለሽ ወደ መሆን

ቻይ መሆን ከአግባብ ውጭ ሊሆን የሚችልበት ጊዜ ይኖራል? የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዳን ኮትስ በ1993 ባደረጉት ንግግር “መቻቻል ባለው ትርጉምና አፈጻጸም ላይ ስለሚደረግ ሙግት” ገልጸዋል። እንዲህ ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? የምክር ቤቱ አባል አንዳንዶች በመቻቻል ስም “የሥነ ምግባር እውነቶችን አሽቀንጥረው በመጣል በጥሩና በመጥፎ፣ በትክክልና በስህተት መካከል ልዩነት መኖሩን ክደዋል።” እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ማኅበረሰቡ መጥፎ ጠባይና ጥሩ ጠባይ ብሎ የመለየት መብት የለውም ብለው ያስባሉ።

የእንግሊዙ የፖለቲካ ሹም ሄይልሻም በ1990 “በጣም ኃይለኛ የሆነው የሥነ ምግባር ጠላት አምላክ የለሽ መሆን ወይም ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም የሚል አምነት መያዝ ወይም ፍቅረ ንዋይ ወይም ስግብግብነት ወይም ሰፊ ተቀባይነት ያገኙት ሌሎች ምክንያቶች አይደሉም። እውነተኛው የሥነ ምግባር ጠላት ኒሂሊዝም ማለትም በምንም ነገር አለማመን ነው” ብለዋል። በምንም ነገር የማናምን ከሆንን የትክክለኛ ጠባይ መስፈርት ስለማይኖረን ማንኛውንም ነገር እንቀበላለን ማለት ነው። ይሁን እንጂ ሁሉንም ዓይነት ጠባይ ችሎ መቀበሉ ተገቢ ነውን?

አንድ የዴንማርክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አይደለም በማለት ይመልሳሉ። በ1970ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ በጻፉት አንድ የጋዜጣ አምድ ላይ በእንስሳትና በሰዎች መካከል ሩካቤ ሥጋ ሲፈጸም የሚያሳይ ፊልም መውጣቱን የሚገልጽ ማስታወቂያ በጋዜጣ መታተሙን በምሬት ተቃውመዋል። እንደነዚህ ያሉ ማስታወቂያዎች ሊወጡ የቻሉት ዴንማርክ በምትከተለው “የመቻቻል” መርሕ ምክንያት ነው።

ባለመቻቻል ምክንያት ችግሮች እንደሚነሱ ሁሉ ከመጠን በላይ መቻቻልም ችግር መፍጠሩ የማይቀር ነው። ወደ ሁለቱም ጽንፍ ሳይሄዱ ትክክለኛውን ሚዛን መጠበቅ አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? እባክህ የሚቀጥለውን ርዕስ አንብብ።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች ሲያጠፉ ከልክ በላይ መቆጣት ጉዳት ሊያስከትልባቸው ይችላል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች የሚያደርጉትን ሁሉ ዝም ብሎ መመልከት በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው ኃላፊነቶች አያዘጋጃቸውም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ