ሐሳበ ግትር ሳይሆኑ ለመለኮታዊ ደንቦች የጸና አቋም መያዝ
አንድ የቻይናውያን ምሳሌ “ደደብ ሰው ቻይ ሆኖ አያውቅም፣ ቻይ ሰው ደግሞ ደደብ ሆኖ አያውቅም” ይላል። ይህ ምሳሌ እውነትነት አለው። ምክንያቱም ቻይ መሆን ትክክለኛ ለሆኑ የሥነ ምግባር ደንቦች ቆራጥ አቋም መያዝን የሚጠይቅ በመሆኑ ተፈታታኝ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ራሳችንን ማስገዛት የሚገባን በየትኛው የሥነ ምግባር ደንብ ነው? የሰው ልጆች ፈጣሪ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሰፈረው ደንብ መሠረት መመራቱ ምክንያታዊ አይሆንም? አምላክ ራሱ ያወጣቸውን ደንቦች በማክበር ረገድ ከሁሉ የተሻለ ምሳሌ ይሆነናል።
ፈጣሪ ከሁሉ የበለጠ ምሳሌያችን ነው
ሁሉን የሚችለው አምላክ ይሖዋ፣ ቻይነትን በተመለከተ ከመጠን የማያልፍ፣ ወይም የማያንስ ሲሆን ፍጹም በሆነ መንገድ ሚዛኑን የሚጠብቅ ነው። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ስሙን የሚነቅፉትንና ምድርን የሚያበላሹትን ምግባረ ብልሹ የሰው ልጆች ታግሷል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 9:22 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ‘ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ችሏል’ በማለት ጽፏል። አምላክ ይህን ለሚያክል ዘመን ችሎ የኖረው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ዓላማ ስላለው ነው።
አምላክ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ” የሰው ልጆችን ይታገሳል። (2 ጴጥሮስ 3:9) ፈጣሪ ለሰው ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን ከመስጠቱም በላይ አገልጋዮቹ የሥነ ምግባር ደንቦቹን በመላው ዓለም እንዲያሳውቁ አዟል። እውነተኛ ክርስቲያኖች እነዚህን ደንቦች የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው። ታዲያ ይህ ማለት የአምላክ አገልጋዮች በሁሉም ነገር ሐሳበ ግትሮች መሆን አለባቸው ማለት ነውን?
ጥብቅ ግን ግትር ያልሆኑ
ኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ‘በጠባቡ በር እንዲገቡ’ መክሯል። ይሁን እንጂ በጠባቡ በር መግባት ማለት ጠባብ አመለካከት መያዝ ማለት አይደለም። ከሌሎች ጋር ስንሆን ሐሳበ ግትር ወይም እኔ ያልኩት ካልሆነ የምንል ከሆነ በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ይበልጥ ደስተኞች እንዲሆኑ ይህን ዝንባሌያችንን መለወጥ ይኖርብናል። ግን እንዴት መለወጥ ይቻላል?—ማቴዎስ 7:13፤ 1 ጴጥሮስ 4:15
ቲዎፋኖ የተባለ ግሪካዊ ተማሪ የተለየ አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ይበልጥ ስለ እነርሱ ማወቅ እንደሚያስችል ገልጾ “እነርሱ እንደ እኛ እንዲያስቡ ለማስገደድ ከመሞከር ይልቅ እኛ የእነርሱን አስተሳሰብ ለመቅዳት መሞከራችን በጣም አስፈላጊ ነው” ብሏል። ስለዚህ አንድን ሰው ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ የምግብ ምርጫው ወይም አነጋገሩ እንዳሰብነው በጣም እንግዳ እንዳልሆነ ልንገነዘብ እንችላለን። ሁልጊዜ ብዙ መናገር አለብኝ ወይም እኔ የተናገርኩት ሁሉ ተቀባይነት ማግኘት አለበት ከማለት ይልቅ የእርሱን አመለካከት በማዳመጥ በርካታ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን መማር ይቻላል። በእርግጥም ሰፋ ያለ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ከሕይወት የበለጠ ደስታ ያገኛሉ።
የግል ምርጫዎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ረገድ ሐሳበ ግትሮች ባለመሆን ሌሎች የራሳቸውን ምርጫ እንዲከተሉ መፍቀድ ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ለፈጣሪያችን ታዛዥ መሆንን የሚመለከት ከሆነ ጥብቅ መሆን ይገባናል። ሁሉን የሚችለው አምላክ ሁሉንም ዓይነት ጠባይ አይፈቅድም። ይህንንም ጥንት ከነበሩ ሕዝቦቹ ላይ ባደረጋቸው ነገሮች አሳይቷል።
ከመጠን በላይ ቻይ መሆን የሚያስከትለው ወጥመድ
የጥንቱ እስራኤል ሊቀ ካህናት የነበረው ኤሊ ከመጠን በላይ ቻይ መሆን በሚያመጣው ወጥመድ ውስጥ የወደቀ የአምላክ አገልጋይ ነበር። እስራኤላውያን የአምላክን ሕግጋት ለመጠበቅ የተስማሙና ከአምላክ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና የመሠረቱ ሕዝቦች ነበሩ። ይሁን እንጂ ሆፍኒና ፊንሐስ የተባሉት የኤሊ ወንድ ልጆች በጣም ስግብግቦችና ባለጌዎች በመሆን ሁሉን የሚችለውን አምላክ በጣም ተዳፈሩ። ኤሊ የአምላክን ሕግ ጠንቅቆ ያውቅ የነበረ ቢሆንም በጣም የለዘበ ተግሳጽ ከመስጠት አላለፈም፤ እንዲሁም ጠንከር ያለ የቅጣት እርምጃ አልወሰደም። አምላክ የክፋት ድርጊቶችን በቸልታ የሚያልፍ መስሎት ነበር። ፈጣሪ ድካምንና ክፋትን በአንድ ዓይን አይመለከትም። የኤሊ ክፉ ልጆች የአምላክን ሕግ ሆን ብለው በመጣሳቸው የሚገባቸውን ከባድ ቅጣት ተቀብለዋል።—1 ሳሙኤል 2:12-17, 22-25፤ 3:11-14፤ 4:17
እኛም ለቤተሰባችን አባላት ከመጠን በላይ ልል ብንሆንና ልጆቻችን በተደጋጋሚ የሚፈጽሟቸውን መጥፎ ድርጊቶች አይተን እንዳላየ ሆነን ብናልፍ በጣም አሳዛኝ ይሆናል! ከዚህ ይልቅ “በጌታ ተግሣጽና ምክር” ብናሳድጋቸው ምንኛ የተሻለ ይሆናል! እኛ ራሳችን መለኮታዊ የሥነ ምግባር ደንቦችን አጥብቀን መከተልና በልጆቻችንም አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጹ ማድረግ ይኖርብናል ማለት ነው።—ኤፌሶን 6:4
በተመሳሳይም የክርስቲያን ጉባኤ ክፋት ሲፈጸም ዝም ብሎ አይመለከትም። አንድ የጉባኤ አባል ከባድ በደል ቢፈጽምና ንስሐ ለመግባት እምቢተኛ ቢሆን መወገድ ይኖርበታል። (1 ቆሮንቶስ 5:9-13) ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከራሳቸው ቤተሰብና ከጉባኤያቸው ክልል ውጭ ያለውን ኅብረተሰብ በሙሉ ለመለወጥ አይሞክሩም።
ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና መመሥረት
ሥጋትና ጭንቀት ሲኖር ያለመቻቻል ባሕርይ ይስፋፋል። ይሁን እንጂ ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ከኖረን ሚዛናችንን እንዳንስት የሚረዳ የመረጋጋት መንፈስ ይኖረናል። ምሳሌ 18:10 ላይ “የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው፣ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል” የሚል ቃል እናነባለን። ፈጣሪ በቀጠረው ጊዜ ሊያስወግድ የማይችለው ጉዳት በእኛም ሆነ በምንወዳቸው ሰዎች ላይ ሊደርስ እንደማይችል የተረጋገጠ ነው።
ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና በመመሥረት ከፍተኛ ጥቅም ካገኙ ሰዎች መካከል አንዱ ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። ሳውል በተባለው አይሁዳዊ ስሙ ይታወቅ የነበረው ይህ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስን ተከታዮች ያሳድድ ስለነበረ ንጹሕ ደም እንዲፈስ ያደረገ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ሳውል ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ በሙሉ ጊዜ የወንጌላዊነት ሥራ ተካፍሏል። ጳውሎስ “ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም” ሰዎች ለመስበክ ሰፊ አመለካከት ይዟል።—ሮሜ 1:14, 15፤ ሥራ 8:1-3
ይህን የመሰለ ለውጥ ሊያደርግ የቻለው እንዴት ነው? የቅዱሳን ጽሑፎችን ትክክለኛ እውቀት በማግኘትና ለማያዳለው ፈጣሪ ያለውን ፍቅር በማሳደግ ነው። አምላክ እያንዳንዱን ግለሰብ የሚዳኘው በግለሰቡ ማንነትና በግል ባደረጋቸው ነገሮች እንጂ በዘሩ ወይም በባሕሉ ባለመሆኑ በፍርድ የማያዳላ አምላክ መሆኑን ጳውሎስ ተገንዝቦ ነበር። አዎን፣ ተግባር በአምላክ ፊት ትልቅ ቦታ አለው። ጴጥሮስ ይህን ሲያረጋግጥ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” ብሏል። (ሥራ 10:34, 35) ሁሉን የሚችለው አምላክ በጭፍን አይጠላም። የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ሲሉ ሆን ብለው ያለመቻቻል መንፈስ ከሚያራግቡ አንዳንድ የዓለም መሪዎች ፈጽሞ የተለየ ነው።
ለውጥ እየታየ ነው
በእንግሊዝ አገር የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ጆን ግሬይ እንዳሉት መቻቻል “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተመናመነ የመጣ ባሕርይ ነው።” ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ይለወጣል። በመለኮታዊ ጥበብ የተስተካከለ ሚዛናዊ መቻቻል ያሸንፋል።
በቅርቡ በሚመጣው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ አለመቻቻል ፈጽሞ አይኖርም። ካለመቻቻል የሚመነጩት መሠረተ ቢስ ጥላቻና ግትርነት ዘመን ያለፈባቸው ነገሮች ይሆናሉ። በአመለካከት ጠባብነት ምክንያት ከሕይወት ልናገኝ የሚገባንን ደስታ አናጣም። በዚያን ጊዜ በካሽሚር ሸለቆ ከነበረው ገነት እጅግ በጣም የሚበልጥ ገነት በመላው ምድር ላይ ይሰፍናል።—ኢሳይያስ 65:17, 21-25
በዚህ አዲስ ዓለም ለመኖር ትናፍቃለህ? በዚያ መኖር እንዴት ያለ ታላቅና አስደሳች መብት ይሆናል!
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያው ጳውሎስ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ስለነበረው ትክክለኛ ሚዛን ለማሳየት ችሏል