የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 2/8 ገጽ 13-15
  • በቆልት አብቅል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በቆልት አብቅል
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዝግጅት
  • በቆልት አብቅል
  • በቆልት የሚበላው እንዴት ነው?
  • ዘሩ እንዲያድግ ውኃ መጠጣት አለበት
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2011
  • የመንግሥቱን የእውነት ዘሮች መዝራት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ዓይነት—ለሕይወት የግድ አስፈላጊ ነው
    ንቁ!—2001
ንቁ!—1998
g98 2/8 ገጽ 13-15

በቆልት አብቅል

በሐዋይ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ገበያ ወጥተህ ትኩስ ወይም ያልጠወለገና ለጤና ጠቃሚ የሆነ አትክልት ለመግዛት ፈልገህ ያጣህበት ጊዜ አለ? ይህን ለማግኘት ርቀህ መሄድ አያስፈልግህም። በገዛ ቤትህ ውስጥ ብዙ ጊዜና ድካም ሳይጠይቅብህ አትክልት ማብቀል ትችላለህ። እንዴት? በቆልት በማብቀል ነዋ!

በቆልት ማብቀል ሕፃን ልጅ እንኳን ሊሠራው የሚችል ቀላል ሥራ ነው። ብዙ ቦታ፣ ቁፋሮ፣ አረም ማረም ወይም ከተለያዩ ኬሚካሎች ጋር ቀላቅሎ ማዘጋጀት አይፈልግም። ከሁሉ በላይ ደግሞ መብቀል በጀመረ አራትና አምስት ቀን ውስጥ ራስህ ያበቀልከውን በቆልት መብላት ትችላለህ! ይሁን እንጂ የበቆልት ጥቅም በቀላሉ መገኘት መቻሉ ብቻ አይደለም።

አንደኛ ነገር፣ የበቆልት ጥቅም በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ምግብነቱ ከተራ ጥራጥሬ ወይም አዝርዕት ይበልጣል። ዘ ቢንስፕራውት ቡክ የተባለው በጌይ ኩርተር የተጻፈ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ዘሮቹ መብቀል ሲጀምሩ በውስጣቸው ያለው የቪታሚን መጠን እየጨመረ ይሄዳል። በፔንስልቬንያ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው የአኩሪ አተር ዘር (በመቶ ግራም ውስጥ) ገና መብቀል ሲጀምር በውስጡ የሚገኘው የቪታሚን ሲ መጠን 108 ሚሊ ግራም ብቻ ነው። ከ72 ሰዓት በኋላ ግን በጣም ጨምሮ 706 ሚሊ ግራም ይደርሳል!”

ከዚህም በላይ በቆልት ማብቀል ብዙ ወጪ አይጠይቅም። እንዲያውም በቆልት ለማብቀል የሚያስፈልጉህ መሣሪያዎችና ዕቃዎች በሙሉ በቤትህ ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ።

ዝግጅት

በመጀመሪያ የሚያስፈልግህ ባዶ ዕቃ ነው። ተለቅ ያለ ከመስተዋት የተሠራ ዕቃ ወይም ጎድጓዳ የፕላስቲክ ሳህን አሊያም ደግሞ ብረትነት የሌለው ዕቃ፣ የሸክላ ድስት ወይም ማሰሮ ይበቃል። ሌላው ቀርቶ በጣም ጎድጓዳ ባልሆነ ሳህን መጠቀም እንኳ ይቻላል። ዘሮቹ እንዳይደርቁ ከላይና ከታች የረጠቡ የገበታ ወረቀቶች አንጥፎ በመካከሉ ዘሮቹን ማስቀመጥ ይቻላል። የሚያስፈልገው የምትጠቀምበት ዕቃ ዘሮቹን ለማብቀልና በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር የሚያስችል ስፋት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ነው። እንደ አተር ላሉት ጥራጥሬዎች የመስተዋት ዕቃ እንደሚሻል ተገንዝቤአለሁ። እንደ ባቄላ ላሉት ትላልቅ ጥራጥሬዎች ጎድጎዳ ሳህን ወይም ማሠሮ የተሻለ ነው። ይህም በቂ ስፋት ያለው ቦታ እንዲያገኙና በቆልቶቹ እንዳይበሰብሱ ወይም መራራ ጣዕም እንዳያመጡ ለማድረግ ያስችላቸዋል።

በተጨማሪም የምትጠቀምበትን ዕቃ አፍ የምትሸፍንበት ነገር ያስፈልግሃል። የፕላስቲክ መሸፈኛ፣ ወይም እንደ ደበላ ያለ ስስ ጨርቅ ለዚህ ሊያገለግል ይችላል። መሸፈኛውን ከዕቃው አፍ ጋር ለማሰር ደግሞ የብር ላስቲክ ወይም ክር መጠቀም ይቻላል። እርግጥ ዘሮቹ ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ መለቅለቅ ስለሚኖርባቸው ውኃና ማጥለያ ያስፈልግሃል።

በመጨረሻ የሚያስፈልጉህ ዘሮቹ ናቸው። ማንኛውም ለምግብነት የሚያገለግል ዘር በቆልት ሊሆን ይችላል። (ቢሆንም ኬሚካሎች የተረጩባቸውን ዘሮች እንዳልጠቀም ጥንቃቄ አደርጋለሁ።) ጀማሪ ለሆነ ሰው የሚሻለው ጥራጥሬ ባቄላ ወይም አልፋ አልፋ ነው። እነዚህ ዘሮች በቀላሉ የሚበቅሉ ሲሆኑ ጣዕማቸውም በጣም ጥሩ ነው። አሁን ዘዴውን እነግርሃለሁ።

በቆልት አብቅል

አንደኛ ቀን:- በመጀመሪያ ዘሮቹን በጥንቃቄ አለቅልቅ። ከዚያ በኋላ ጥራጥሬዎቹን ወይም ባቄላውን አምስት ሴንቲ ሜትር ያህል ከፍ ብሎ ሊሸፍን የሚችል ውኃ ዕቃህ ውስጥ ጨምር። ቢያንስ ለስምንት ወይም ለአሥር ሰዓት ተነክሮ ይቆይ። ማታ ከመተኛትህ በፊት ነክረህ ልታሳድር ትችላለህ። ከስምንት እስከ አሥር ሰዓት ከሚደርስ ጊዜ በኋላ ዘሮቹ ያብጣሉ፣ ቆዳቸውም መሰንጠቅ ይጀምራል። ለመብቀል ተዘጋጅተዋል ማለት ነው።

ሁለተኛ ቀን:- ጠዋት ክዳኑን ግለጥና ውኃውን ከዕቃው ውስጥ አፍስስ። (ይህ ውኃ ቪታሚኖች ስለሚኖሩት ብዙውን ጊዜ አትክልቶቼን ለማጠጣት እጠቀምበታለሁ።) አሁን እንደገና ውኃ ጨምርበት። ለጥቂት ጊዜያት ነቅነቅ፣ ነቅነቅ ካደረግህ በኋላ ገልብጠህ ትርፍ የሆነው ውኃ ተጠንፍፎ እንዲፈስስ አድርግ። ሦስት ጊዜ ያህል ውኃ ጨምረህ ካለቀለቅህ በኋላ ውኃውን አጠንፍፈህ ድፋ። ተዘፍዝፈው የቆዩትን ዘሮች በጣም ጎድጓዳ ወዳልሆነ ሣህን የምታዛውር ከሆነ ወረቀቶቹ ላይ በቀስታ ውኃ ከጨመርክ በኋላ ሣህኑን ዘንበል አድርገህ ውኃውን አፍስስ። ዘሮቹ በቀን ሁለት ጊዜ መለቅለቅ ስለሚኖርባቸው ቆየት ብለህ ቀደም ሲል እንደተገለጸው አለቅልቅ።

ሦስተኛ ቀን:- በዚህ ጊዜ ዘሮችህ መብቀል መጀመራቸውን ማየት መቻል ይኖርብሃል። በቀን ሁለት ጊዜ ማለቅለቅህን አታቋርጥ።

አራተኛ ቀን:- በቆልትህን መብላት መጀመር ትችላለህ! ያበቀልከው ባቄላ ከሆነ ለጥቂት ቀናት ቢያድግ ምሬት አያመጣም። በቀን ሁለት ጊዜ ማለቅለቅህን ግን አትርሳ። በተጨማሪም በቆልቶችህን ለአንድ ሰዓት ያህል ፀሐይ ካሞቅህ በኋላ ማቀዝቀዣ ውስጥ ልትጨምር ትችላለህ። ትናንሾቹ ቅጠሎች አረንጓዴ ቀለም ማምጣት ስለሚጀምሩ ለመብላት ያጓጓሉ!

አሁን የመጀመሪያ ሙከራህ ስለተሳካ ሌሎቹን ጥራጥሬዎችና አዝርዕቶች መሞከር ትፈልግ ይሆናል። እያንዳንዱ ዘር በጣዕሙና ለመብቀል በሚወስድበት ጊዜ ከሌላው ይለያል። ለምሳሌ ያህል ሱፍ ለማብቀል ትሞክር ይሆናል። የሱፍ በቆልቶች ቁመታቸው ከሁለት ሴንቲ ሜትር ሳይበልጥ በበቀሉ በሁለት ቀን ውስጥ መበላት አለባቸው። ከዚህ ይበልጥ ካደጉ መራራ የሆነ ጣዕም ያመጣሉ።

በቆልት የሚበላው እንዴት ነው?

አብዛኞቹ በቆልቶች በጥሬነታችው በሰላጣ፣ በሳንድዊች ወይም ባቄላና ሌሎች ጥራጥሬዎች በሚገቡባቸው ምግቦች ሁሉ ተጨምረው ሊበሉ ይችላሉ። የባቄላ በቆልት ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ለሚደርስ ጊዜ በእንፋሎት ብቻ ተቀቅሎም ሊበላ ይችላል። አለበለዚያም ከነጭ ሽንኩርትና ከጨው ጋር በትንሽ ዘይት ጠብሶ መብላት ይቻላል። ይህ በተለይ በጣም ጣፋጭ የሆነ ምግብ ነው። የስንዴ በቆልት ጣፋጭ በመሆኑ በዳቦ ወይም በፓስታ ላይ ተጨምሮ ሊበላ ይችላል።

ስለዚህ የጥራጥሬዎችንና የአዝርዕትን በቆልት ማብቀል ጤናማና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ የትርፍ ጊዜ ሥራ ነው። በጣም የሚያስደስትና ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ሥራ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። እንዲያውም የተሳካ ውጤት የማግኘት ዕድልህ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ግሩም የሆነ ምግብ ለመብላት ያስችልሃል!

[ምንጭ]

Japanese Stencil Designs

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንደኛ ቀን:- ዘሮቹን ከስምንት እስከ አሥር ሰዓት ያህል በውኃ ውስጥ ዘፍዝፋቸው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁለተኛና ሦስተኛ ቀን:- ዘሮቹን በቀን ሁለት ጊዜ በደንብ አለቅልቃቸው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አራተኛ ቀን:- ለመበላት የደረሰ በቆልት! (ስስ ጨርቅ በተነጠፈበት ዕቃ ውስጥ ሆኖ ከጎን ሲታይ)

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ