አምላክ አጋጣሚዎችን ይጠቀማል ወይስ ይፈጥራል?
“ብዙ ሳይንቲስቶች መንፈሳዊ ስለሆነ ነገር ምንም ማስረጃ ሊገኝለት አይችልም የሚለውን አባባል ይቅርና ስለ መለኮታዊ ኃይል የሚቀርበውን ማንኛውንም ዓይነት ሐሳብ አይቀበሉም። አምላክ ወይም ሌላ ስብዕና የሌለው የፍጥረት ምንጭ ሊኖር ይችላል በሚለው ፅንሰ ሐሳብ ያፌዛሉ። . . . እኔ በግሌ በዚህ ዓይነቱ ፌዝ አልስማማም።” በሳውዝ አውስትራሊያ አደሌይድ ዩኒቨርሲቲ የማትማቲካዊ ፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ዴቪስ ይህንን ያሉት ዘ ማይንድ ኦቭ ጎድ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ነው።
ዴቪስ አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “ጥልቀት ያለው ጥናት ስናደርግ የአጽናፈ ዓለሙ ሕግ በጣም ውስብስብ የሆኑና ብዙ ዓይነት ያላቸውን ሕያዋን ነገሮች ለማስገኘት በሚችል አስገራሚ መንገድ የተቀመጠ መሆኑን መረዳት እንችላለን። ሕያዋን ዘአካሎች ሕልውና ያገኙት እንደ ዕድል ሆኖ በተደጋጋሚ አጋጣሚዎቹ ስለተሰካኩላቸው ይመስላል። በመሆኑም አንዳንድ ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች እነዚህ በጣም አስገራሚ አጋጣሚዎች ናቸው ሲሉ አወድሰዋቸዋል።”
ዴቪስ በመቀጠል እንዲህ ብለዋል:- “ሳይንሳዊው ፍለጋ ወደማይታወቅ አገር የሚደረግ ጉዞ ነው። . . . ይሁን እንጂ ምክንያታዊነትና ሥርዓት ምን ጊዜም ከዚህ ፍለጋ ጋር አብረው የሚጓዙ ነገሮች ናቸው። ይህ የአጽናፈ ዓለም ሥርዓት የቆመው ረቂቅና አንድነት ያለው ኅብረት ለመፍጠር እርስ በርሳቸው በተጣመሩ የሒሳብ ሕጎች ላይ ነው። እነዚህ ሕጎች ግልጽና ግራ የማያጋቡ ናቸው።”
ዴቪስ እንዲህ በማለት ደምድመዋል:- “የአጽናፈ ዓለሙን ሁኔታ የመረዳት ችሎታ ያለው ሆሞ ሳፒየን መሆኑ ጥልቅ ምሥጢር ነው። . . . እጅግ ሰፊ በሆነው በዚህ አጽናፈ ዓለም ድራማ ውስጥ የተገኘነው እንዲሁ በዕድል፣ በጊዜ ሂደት በተፈጠረ አጋጣሚና በድንገተኛ ሁኔታ ነው ብዬ ማመን ይከብደኛል። ከአጽናፈ ዓለሙ ጋር ያለን ትስስር በጣም የጠበቀ ነው። . . . በእርግጥም እኛ የተሠራነው በዚህ አጽናፈ ዓለም እንድንኖር ነው።” ነገር ግን ዴቪስ አንድ ፈጣሪ አለ የሚል መደምደሚያ ላይ አልደረሱም። ይሁን እንጂ የአንተ መደምደሚያ ምንድን ነው? የሰው ልጅ እዚህ ምድር ላይ እንዲኖር ታስቦ ነበርን? ከሆነ ይህን ያደረገው ማን ነው?
‘የምሥጢሩ’ ቁልፍ
ዴቪስ “ጥልቅ ምሥጢር” ያሉትን ነገር ለመረዳት የሚያስችል ፍንጭ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መዝግቦ እናገኛለን። ጳውሎስ አምላክ ራሱን እንዴት እንደገለጠ ሲናገር:- “እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፣ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ [“እውነትን በሚሰውሩ ሰዎች”] ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ . . . የሚያመካኙት አጡ።” (ሮሜ 1:18-20)a አዎን፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የተለያዩ ሕያዋን ነገሮች፣ አስገራሚ የሆነው ውስብስብ አፈጣጠራቸውና ድንቅ ንድፋቸው አንድን ትሑትና አክብሮት ያለው ሰው ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ እስከ ዛሬ የሰው ልጅ ከሚያውቃቸው ነገሮች ሁሉ የላቀ አንድ ከፍተኛ ኃይልና የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ወይም አእምሮ እንዳለ እንዲገነዘብ ያስችለዋል።—መዝሙር 8:3, 4
ጳውሎስ በአምላክ ለማመን አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎችን አስመልክቶ የተናገራቸው ተጨማሪ ቃላት ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ ናቸው። “ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፣ . . . ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን።” (ሮሜ 1:22, 25) “ተፈጥሮን” እያመለኩ በአምላክ የማያምኑ ሰዎች በይሖዋ ዓይን ሲታዩ ጥበበኞች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። እርስ በርሱ በሚጋጨው የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ግራ ተጋብተው በፈጣሪ ማመንና የፍጥረት ሥራዎቹን ውስብስብ ንድፍ ማስተዋል ተስኗቸዋል።
“በተከታታይ የተከሰቱ ታላላቅ አጋጣሚዎች”
በተጨማሪም ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ያለ እምነትም [አምላክን] ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።” (ዕብራውያን 11:6) እንዲሁ በማይጨበጥ ነገር ሳይሆን በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ እምነት የመኖራችን ዓላማ ምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ሊረዳን ይችላል። (ቆላስይስ 1:9, 10) አንዳንድ ሳይንቲስቶች ሕይወት የተገኘው “እያንዳንዳቸው አንድ ሚልዮን ዶላር የሚያስገኙ የሎተሪ ዕጣዎችን በመደዳ ሚልዮን ጊዜ” ከማሸነፍ ተለይቶ በማይታይ መንገድ አጋጣሚዎች ስለተሰካኩ ነው ብለን እንድናምን መፈለጋቸው የማይመስልን ነገር በጸጋ ተቀብለን እንድናምን ለማድረግ ከመጣር ተለይቶ አይታይም።
ብሪታኒያዊው ሳይንቲስት ፍሬድ ሆይል ለሕይወት የግድ አስፈላጊ የሆኑት ሁለት ንጥረ ነገሮች ማለትም ካርቦንና ኦክሲጅን እንዲፈጠሩ ያስቻሉት የኑክሌር አፀግብሮቶች እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሚፈለገው ትክክለኛ መጠን እንዲፈጠሩ ለማድረግ የቻሉት በድንገተኛ አጋጣሚ ነው።
ሌላ ምሳሌም ሰጥተዋል:- “የፕሮቶንና የኤሌክትሮን ክምችት ከኒውትሮኑ ክምችት ትንሽ ከማነስ ይልቅ ድንገት ትንሽ ቢጨምር ኖሮ አስከፊ ሁኔታ ይከተል ነበር። . . . በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኙት የሃይድሮጅን አቶሞች በሙሉ ወዲያው ወደ ኒውትሮኖችና ኒውትሪዮኖች ይለወጡ ነበር። ፀሐይም የኑክሌር ኃይሏ ተሟጥጦ ብርሃኗ እየደበዘዘና እየተኮማተረች በሄደች ነበር።” በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኙት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ከዋክብትም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይሆንም ነበር።
ሆይል እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል:- “እነዚህ . . . ኢ ሕይወታዊ ባሕርይ ያላቸው አጋጣሚዎች ባይከሰቱ ኖሮ ካርቦንን በዋነኛነት የያዙ ንጥረ ነገሮች አይኖሩም ነበር፤ እነሱ ከሌሉ ደግሞ ሰብዓዊ ሕይወት ሊኖር አይችልም። እነዚህ ድንገተኛ አጋጣሚዎች በርካታ ከመሆናቸውም በላይ እጅግ አስገራሚ ናቸው።” አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “[ለሕይወት የግድ አስፈላጊ የሆኑት] እንዲህ ዓይነቶቹ ነገሮች አስደሳች አጋጣሚ የሆነውን የፍጥረት ዝግጅት የሚያስተሳስሩ ነገሮች ይመስላሉ። ይሁንና ለሕይወት የግድ አስፈላጊ የሆኑ የማይመስሉ በርካታ አጋጣሚዎች በመኖራቸው የተወሰነ ማብራሪያ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።”—በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
እንደሚከተለውም ብለዋል:- “ችግሩ እነዚህ በአጋጣሚ ተስተካክለው የተቀመጡ የሚመስሉት ነገሮች በእርግጥ በአጋጣሚ የተከሰቱ መሆን አለመሆናቸውን በሌላ አባባል ሕይወት በአጋጣሚ የተገኘ ነው አይደለም የሚለውን ነገር መወሰኑ ነው። ይህን ጥያቄ ማንሳት የሚፈልግ አንድም ሳይንቲስት ባይኖርም ጥያቄው መነሳቱ ግድ ነው። ምናልባት እነዚህ ነገሮች በትክክል ሊከናወኑ የቻሉት የማሰብ ችሎታ ያለው አካል አልሞ ስላደረጋቸው ይሆን?”
ፖል ዴቪስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሆይል በእነዚህ ‘በተከታታይ የተከሰቱ ታላላቅ አጋጣሚዎች’ በጣም ከመገረማቸው የተነሣ ‘የኑክሌር ፊዚክስ ሕግጋት በከዋክብት ውስጥ የሚያከናውኑትን ነገር በማሰብ ሆን ተብለው የተዘጋጁ ነገሮች ይመስላሉ’ ለማለት ተገድደዋል።” ታዲያ እነዚህ ‘ተከታታይ የሆኑ ታላላቅ አጋጣሚዎች’ እንዲከሰቱ ያደረገው ማን ወይም ምንድን ነው? ስፍር ቁጥር በሌላቸው ልዩ ልዩ ዕፅዋትና እንስሳት የተሞላችውን ፕላኔታችንን ያስገኘው ማን ወይም ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ
መዝሙራዊው ሦስት ሺህ ከሚያክሉ ዓመታት በፊት በአድናቆት ስሜት ተውጦ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፣ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች። ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፤ በዚያ ስፍር ቁጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፣ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ።”—መዝሙር 104:24, 25
ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ብሏል:- “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።” (ራእይ 4:11) ሕይወት የተገኘው በጭፍን ዕድል ወይም በሚልዮን የሚቆጠሩት የሕይወት ዓይነቶች በሙሉ የከፍተኛ ዕጣ ባለ ዕድል በመሆናቸው አይደለም።
ሐቁ አምላክ ‘ሁሉን ነገር ፈጥሯል፤ ስለፈቃዱም ሆነዋል፣ ተፈጥረውማል’ የሚለው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለፈሪሳውያን እንደሚከተለው ብሏቸዋል:- “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው . . . የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን?” ኢየሱስ ፈጣሪን ያውቀው ነበር! የይሖዋ ዋና ሠራተኛ እንደመሆኑ መጠን በፍጥረት ሥራዎች አብሮት ተካፍሏል።—ማቴዎስ 19:4, 5፤ ምሳሌ 8:22–31
ይሁን እንጂ ስለ ፈጣሪ የሚናገረውን ይህንን መሠረታዊ እውነት መገንዘብና መቀበል እምነትና ትሕትና ይጠይቃል። ይህ እምነት እንዲሁ በጭፍን መነዳት ማለት አይደለም። በተጨባጭና ጉልህ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው። አዎን “[የአምላክ] የማይታየው ባሕርይ . . . ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ . . . ግልጥ ሆኖ ይታያልና።”—ሮሜ 1:20
ያለን ሳይንሳዊ እውቀት ውስን በመሆኑ አምላክ ነገሮችን እንዴት እንደፈጠረ ማስረዳት አንችልም። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ስለ ሕይወት አጀማመር ሁሉንም ነገር ማወቅም ሆነ መረዳት እንደማንችል አምነን መቀበል ይኖርብናል። ይሖዋ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላትም ይህንኑ የሚያስታውሱን ናቸው:- “አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና . . . ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ሐሳቤ ከሐሳባችሁ መንገዴም ከመንገዳችሁ ከፍ ያለ ነው።”—ኢሳይያስ 55:8, 9
ሕይወት የተገኘው ስፍር ቁጥር የሌላቸው የዕድል ጨዋታዎች ሁሉ በመስመራቸው ነው በሚለው ጭፍን የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ወይም ደግሞ ዓላማ ባለውና ይህንን ሁሉ ባዘጋጀው ፈጣሪ በይሖዋ አምላክ ማመን የአንተ ምርጫ ነው። በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ነቢይ እንደሚከተለው ማለቱ ትክክል ነው:- “እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፣ አይታክትም፣ ማስተዋሉም አይመረመርም።”—ኢሳይያስ 40:28
እንግዲያው አንተ የምታምነው በምንድን ነው? የሚኖርህ እምነት ወደፊት በሚኖርህ ተስፋ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርት “ነፍስን” ከአዝጋሚ ለውጥ ሂደት ጋር አያይዞ ለመግለጽ አሳሳች የመከራከሪያ ሐሳብ ቢያቀርብም የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እውነት ከሆነ ሞት ከናካቴው ተረስቶ መቅረት ማለት ይሆናል ማለት ነው።b መራራውን ሞት ላለመቀበል ሲባል የተፈጠረው የማትሞት ነፍስ አለች የሚለው ሐሳብ እውነትነት የለውም።—ዘፍጥረት 2:7፤ ሕዝቅኤል 18:4, 20
መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑንና የፈጠረንም ሕያው የሆነው አምላክ እንደሆነ የሚያምኑ ሁሉ ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ በተመለሰች ምድር ላይ ከሞት ተነስተው ፍጹም ሕይወት በማግኘት ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። (ዮሐንስ 5:28, 29) ታዲያ እምነትህን የምትጥለው በማን ላይ ነው? ተዓማኒነት በሌለው የዳርዊን የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ የዕድል ጨዋታ ላይ? ወይስ በዓላማ ሥራውን ባከናወነውና እንደዚያ ማድረጉን በቀጠለው ፈጣሪ ላይ?c
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “አምላክ ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ በዓይን ባይታይም እንኳ ዓለምን ከፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ከሠራቸው ነገሮች በግልጽ መረዳት ይቻላል።”—ሮሜ 1:20፣ ጀሩሳሌም ባይብል
b ሐምሌ-መስከረም 1997 ንቁ! ላይ “ከዓለም አካባቢ” በሚለው ዓምድ ሥር ገጽ 30 ላይ የወጣውን “ሊቀ ጳጳሱ ዝግመተ ለውጥን ደገፉ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c ስለዚህ ጉዳይ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ሕይወት እንዴት ተገኘ?—በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንዳንድ የአዝጋሚ ለውጥ አማኞች ሕይወት ስለተገኘበት መንገድ የሚሰጡት ማብራሪያ “እያንዳንዳቸው አንድ ሚልዮን ዶላር የሚያስገኙ የሎተሪ ዕጣዎችን በመደዳ ሚልዮን ጊዜ” ማሸነፍ ይቻላል ከማለት ተለይቶ አይታይም።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ስፍር ቁጥር የሌለው ዓይነትና ንድፍ
ሦስት አፅቄዎች “ሳይንቲስቶች በየዓመቱ ከ7,000 እስከ 10,000 የሚደርሱ አዳዲስ የሦስት አፅቄ ዝርያዎችን ያገኛሉ” ሲል ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ ዘግቧል። ይሁንና “አሁንም ገና ያልተገኙ ከ1 ሚልዮን እስከ 10 ሚልዮን የሚያክሉ ዝርያዎች ሊኖሩ ይችላሉ።” ካትሪን ቪንሰንት በጻፉት የጋርዲያን ዊክሊ አምድ ሥር የተጠቀሰው ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይኛ ጋዜጣ በመዝገብ የሰፈሩት ዝርያዎች ቁጥር “ይኖራሉ ተብለው ከሚገመቱት ከ5 እስከ 50 ሚልዮን የሚያክሉ . . . ዝርያዎች አንጻር ሲታይ በጣም ጥቂት” መሆኑን ገልጿል።
እስቲ አስገራሚ የሆነውን የሦስት አፅቄዎች ዓለም በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት—ንብ፣ ጉንዳን፣ ተርብ፣ ቢራቢሮ፣ በረሮ፣ ጢንዚዛ፣ ምስጥ፣ የእሳት እራት፣ ዝንብ፣ የውኃ ተርብ፣ የወባ ትንኝ፣ ፌንጣ፣ ቅማልና ቁንጫ ጥቂቶቹ ናቸው! ዝርዝሩ ማብቂያ ያለው አይመስልም።
አእዋፍ ከ14 ግራም ያነሰ ክብደት ስላላት ወፍስ ምን ማለት እንችላለን? “እስቲ አስበው በየዓመቱ ከአላስካ ደኖች ተነስታ በደቡብ አሜሪካ ወደሚገኙት ደኖች ለመጓዝ ከ16,000 ኪሎ ሜትር በላይ የምትበር ሲሆን ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች በተሸፈኑት የተራራ ጫፎች ተሽሎክልካ፣ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ባሉባቸው ከተሞች ዳርቻዎች አድርጋና የአትላንቲክ ውቅያኖስን የተንጣለለ ውኃና የሜክሲኮን ባሕረ ሰላጤ አቋርጣ በመብረር የመልስ ጉዞዋን ታደርጋለች።” ይህች አስገራሚ ወፍ የትኛዋ ናት? “በጉዞ ችሎታዋ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት በየብስ ላይ የሚኖሩ ወፎች ሁሉ አቻ የማይገኝላት ብርቱዋ ብላክፖል ዋርብለር [ዴንድሮይካ ስትሪያታ] የተባለችው ወፍ ናት።” (ቡክ ኦቭ ኖርዝ አሜሪካን በርድስ) ይህች ወፍ ልትገኝ የቻለችው እልፍ እላፍ አጋጣሚዎች እንዲሁ ድንገት ስለተገጣጠሙ ነው? ወይስ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ያዘጋጃት ድንቅ ሥራ ነች? ብለን በድጋሚ ለመጠየቅ እንገደዳለን።
ከእነዚህ ምሳሌዎች በተጨማሪ ደግሞ ልዩ የዝማሬ ችሎታ ያላቸው አእዋፍ አሉ:- ከእነዚህም መካከል በመላው አውሮፓ እንዲሁም በከፊል አፍሪካና እስያ ደስ በሚለው ዝማሬዋ የምትታወቀው ናይትንጌል፤ በሰሜን አሜሪካ የምትገኘውና “የሌሎችን ድምፅ በመስማት ያጠናቻቸውን ሐረጎች ቀላቅላ የምትዘምረው” ሰሜናዊዋ ሞኪንግበርድ፣ “ከፍተኛ የመዘመር ችሎታ ያላትና የሰማችውን ነገር በሚያስገርም መንገድ የምትደግመው” የአውስትራሊያዋ ላይርበርድ ይገኙበታል።—በርድስ ኦቭ ዘ ዎርልድ
በተጨማሪም በጣም ብዙ አእዋፍ ያላቸው ድንቅ ቀለም እንዲሁም የክንፋቸውና የላባቸው ንድፍ በአድናቆት እንድንመሰጥ የሚያደርግ ነው። ከዚህም በላይ መሬት ላይ፣ ገደል አፋፍም ላይ ሆነ ዛፍ ላይ አንዱን ነገር ከሌላው ገምደው ጎጆአቸውን የመሥራት ችሎታቸው የሚያስገርም ነው። እንዲህ ያለው በተፈጥሮ የሚወርሱት ብልሀት ትሑት ልብ ያለውን ሰው ሊነካው ይገባል። እነዚህ አእዋፍ ሊገኙ የቻሉት እንዴት ነው? በአጋጣሚ ነው ወይስ በዓላማ?
የሰው ልጅ አንጎል “በሰው ልጅ አንጎል ውስጥ ከአሥር ትሪሊዮን እስከ አንድ መቶ ትሪሊዮን የሚደርሱ ጋጥሚያ ሕዋሳተ ነርቮች ሊኖሩ የሚችሉ ሲሆን እያንዳንዳቸው የሚደርሳቸውን የኤሌክትሪክ መልእክት እንደሚመዘግቡ ትናንሽ የሒሳብ መኪናዎች ናቸው።” (ዘ ብሬን) አንጎላችንን እንዲሁ እንደ ቀላል ነገር እናየው ይሆናል እንጂ በራስ ቅል የታቀፈ ውስብስብ ዓለም ነው። ሰዎች ማሰብ፣ ማመዛዘን እንዲሁም በሺህ የሚቆጠሩ ቋንቋዎችን መናገር እንዲችሉ የሚረዳውን ይህን አካል ልናገኝ የቻልነው እንዴት ነው? ዕድላቸው በሰመረላቸው ሚልዮን አጋጣሚዎች አማካኝነት? ወይስ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ባወጣው ንድፍ?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
የአንጎልን ውጫዊ ገጽታ የሚያሳይ ቀለል ብሎ የቀረበ ሥዕላዊ መግለጫ
ሴንሰሪ ኮርቴክስ
የመላውን ሰውነት የስሜት መልእክቶች ያስተናግዳል
ኦሲፕታል ሎብ
የእይታ መልእክቶችን ያስተናግዳል
አንጎለ ገቢር (Cerebellum)
ሚዛንንና ቅንጅትን ይቆጣጠራል
ፕሪሞተር ኮርቴክስ
የጡንቻዎችን ቅንጅት ይቆጣጠራል
ሞተር ኮርቴክስ
ሆነ ብለን የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ይቆጣጠራል
ፍሮንታል ሎብ
የማመዛዘን ችሎታን፣ ስሜትን፣ ንግግርንና እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ይረዳል
ቴምፖራል ሎብ
ድምፅን ያስተናግዳል፣ ከመማር፣ ከማስታወስ ችሎታ፣ ከቋንቋና ከስሜት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይቆጣጠራል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
አክሶን ተርሚናል
ኑውሮትራንስሚተርስ
ዴንድራይት
ጋጥሚያ ህዋሳተ ነርቭ (Synapse)
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
ህዋሰ ነርቭ (Neuron)
ዴንድራይትስ
ዘንገ ነርቭ (Axon)
ዴንድራይትስ
ጋጥሚያ ህዋሳተ ነርቭ
ህዋሳተ ነርቭ
ዘንገ ነርቭ
“በአንጎል ውስጥ ከአሥር ትሪሊዮን እስከ አንድ መቶ ትሪሊዮን የሚደርሱ ህዋሳተ ነርቮች ሲኖሩ እያንዳንዳቸው የሚደርሳትን የኤልክትሪክ መልእክት እንደምትመዘገብ ትንሽ የሒሳብ ማሽን ሆነው ይሠራሉ።”—ዘ ብሬይን
[ምንጭ]
ጨረቃና ፕላኔቶች:- NASA photo