የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 7/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሊቀ ጳጳሱ ዝግመተ ለውጥን ደገፉ
  • ትዳር እየፈራረሰ ነው
  • በቂ እንቅልፍ ያጡ ልጆች
  • ባትሪ የማያስፈልገው ራዲዮ
  • ገዳይ ዝናብ
  • የአፍሪካን ዝሆኖች ማሠልጠን
  • ከደም የተዘጋጁ ተጨማሪ ምግቦች
  • በየዕለቱ ፍራፍሬ ተመገብ
  • የልጆች ጦር ሠራዊት
  • በተመሳሳይ ስም ከሚቸረቸሩ የሐሰት መድኃኒቶች ተጠበቁ
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—2000
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—2003
  • ሰውነትህ እንቅልፍ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—1995
  • የዝሆን ጥርስ ምን ያህል ተፈላጊ ነው?
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1997
g97 7/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

ሊቀ ጳጳሱ ዝግመተ ለውጥን ደገፉ

በቅርቡ ሊቀ ጳጳስ ጆን ፖል ዳግማዊ የሰውን ልጅ ዝግመተ ለውጥ በተመለከተ በተለያዩ ወገኖች የተደረጉት ምርምሮች “ወደ አንድ ነጥብ መምጣታቸው ይህንን ጽንሰ ሐሳብ የሚደግፍ” እንደሆነ በመጥቀስ አንድ መግለጫ አውጥተዋል። ሎሴርቫቶሬ ሮማኖ እንዳለው ከሆነ ጆን ፖል ዳግማዊ ይህንን ቲዮሪ ሙሉ በሙሉ ተስማምተው ባያጸድቁትም ሊቀ ጳጳስ ፒየስ አሥራ ሁለተኛ በ1950 “‘የዝግመተ ለውጥ እምነት’ ሊጤን የሚገባው ጥሩ መላምት ነው” በማለት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያስተላለፉትን ደብዳቤ ዳግም አጠናክረዋል። ሊቀ ጳጳሱ ሰዎች የማትሞት ነፍስ አለቻቸው የሚለውን የፕላቶ ትምህርት በመጥቀስ አምላክም በዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ የተጫወተው ሚና እንዳለ ለማሳየት ሞክረዋል። ሊቀ ጳጳስ ፒየስ አሥራ ሁለተኛ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያስተላለፉትን ደብዳቤ በድጋሚ በመጥቀስ እንደሚከተለው ብለዋል:- “የሰው ልጅ ሰብዓዊ አካል የሚያገኘው ቀደም ሲል ከነበረ አካል ከሆነ መንፈሳዊ የሆነችውን ነፍስ የፈጠራት አምላክ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም።”

ትዳር እየፈራረሰ ነው

በአሁኑ ጊዜ በካናዳ ውስጥ ለሚካሄደው እስታትስቲካዊ የሕዝበ ነክ ጥናት ትንተና አስተባባሪ ሆነው የሚያገለግሉት ዣን ዱማስ “ትዳር በተቋምነት ደረጃ ያለውን ሕልውና ሲያጣ በዓይናችን እየተመለከትን ነው” ብለዋል። ዘ ቶሮንቶ ስታር እንደዘገበው በካናዳ ውስጥ በተለይ ደግሞ በክዊቤክ የባለ ትዳሮች ቁጥር እያሽቆለቆለ ነው። አንዳንዶቹ ከትዳር የሚሸሹት የወላጆቻቸው ትዳር መጥፎ አመለካከት ስለቀረጸባቸው እንደሆነ ሪፖርቱ ገልጿል። ለ25 ዓመታት የተሰበሰበው ውህብ (ዳታ) እንደሚያሳየው በ1969 ከተጋቡት ባልና ሚስት መካከል 30 በመቶዎቹ እስከ 1993 ድረስ በትዳራቸው አልዘለቁም። በቅርቡ የተጋቡ ባልና ሚስቶችም በመፋታት ላይ መሆናቸውን እስታትስቲካዊ መረጃዎች ያሳያሉ። በካናዳ ውስጥ በ1993 ከተፈጸሙት ፍቺዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከተጋቡ ገና አምስት ዓመት ያልሆናቸው ሲሆን ይህ ቁጥር በ1980 ከነበረው በአንድ አራተኛ ጨምሯል። ኦንታሪዮ በሚገኘው የግዌፍ ዩኒቨርሲቲ የትዳርና የቤተሰብ ሕክምና ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ማርሻል ፋይን “ይህ ዓለም ለወጣቶች አስተማማኝ ቦታ የሆነ አይመስልም” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በቂ እንቅልፍ ያጡ ልጆች

ኤዥያዊክ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው በአውስትራሊያና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የእንቅልፍ ስፔሺያሊስቶች በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ ልጆች ከቴሌቪዥን፣ ከዓመፀኛነት ወይም ከስንፍና ይልቅ ብዙ የሚወቀሱት ጠዋት ቶሎ ከአልጋቸው ለመውጣት ባለመፈለጋቸው ሳይሆን እንደማይቀር ገምተዋል። አውስትራሊያዊው የእንቅልፍ ኤክስፐርት ዶክተር ክሪስ ሴተን እንዳሉት ብዙዎቹ በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች እንቅልፍ የሚናፍቁበት ምክንያት ከሆርሞን ለውጦችና ከሰውነት እድገት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። የአንድ ልጅ የእንቅልፍ ፍላጎት ከዘጠኝ ዓመት ዕድሜው ጀምሮ ይጨምራል። ይሁን እንጂ ከ17 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ባላቸው 3,000 የዩናይትድ ስቴትስ ተማሪዎች ላይ በተደረገ አንድ ጥናት 85 ከመቶ የሚሆኑት የሚገባቸውን ያክል እንቅልፍ እንዳላገኙ ተረጋግጧል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ከዚህ የተነሣ ተማሪዎቹ በተለይ ጠዋት በመጀመሪያዎቹ የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች ወቅት ያለማቋረጥ እንቅልፍ እንቅልፍ ይላቸዋል። የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄምስ ቢ ማስ አስተያየታቸውን ሲሰጡ “በቂ እንቅልፍ ከማጣታቸው የተነሣ ሰው ጎትቶ ያመጣቸው የሚመስሉ ልጆች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል። ኤክስፐርቶች በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች በአንድ ሌሊት ቢያንስ የስምንት ሰዓት ተኩል እንቅልፍ ሊያገኙ ይገባል ብለው ያምናሉ።

ባትሪ የማያስፈልገው ራዲዮ

በአብዛኛው የአፍሪካ ገጠራማ ክፍል ያለውን የኤሌክትሪክ ችግርና በጣም አነስተኛ የሆነውን የባትሪ አቅርቦት ለመቋቋም በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን የሚገኝ አንድ ትንሽ ፋብሪካ በእጅ የሚሽከረከር የኃይል ምንጭ ያላት ትንሽ ራዲዮ እያመረተ ነው። ዘ ኒው ዮርክ ታምስ እንዳለው “እጀታዋን ጥቂት ጊዜ ደህና አድርገህ ታሽከረክራታለህ፣ ግማሽ ሰዓት ያለ ምንም ችግር ትሠራለች።” አዲሷ ሞዴል የምሳ ዕቃ የምታክልና ሁለት ኪሎ ግራም ክብደት ያላት ብትሆንም ብዙ ተቀባይነት የምታገኝ ትመስላለች። የፋብሪካው የሽያጭ ክፍል ኃላፊ ሲያና ማሉማ እንዳሉት ራዲዮዋ በቀን ውስጥ ከአምስት እስከ አሥር ሰዓት ለሚያክል ጊዜ ብትሠራ በዓመት ውስጥ ለባትሪ የሚወጣውን ከ500 እስከ 1,000 የአሜሪካን ዶላር ታድናለች። ማሉማ “ራዲዮ አፍሪካውያን ትልቅነታቸውን ከሚለኩባቸው ሦስት ነገሮች አንዱ ነው” ብለዋል፤ የቀሩት ሁለቱ ደግሞ ብስክሌትና ሞተር ብስክሌት ናቸው። “አትሳሳቱ” በአንድ ራዲዮ ምክንያት “ሚስትም ታገኙ ይሆናል” ሲሉም አፋቸውን ሞልተው ተናግረዋል።

ገዳይ ዝናብ

ስዊድናዊው ሳይንቲስት ዶክተር አድሪያን ፍራንክ እንዳሉት የአሲድ ዝናብ በስካንዲኔቪያን አገሮች ውስጥ ለብዙ አጋዝኖች ሞት ቀጥተኛ ምክንያት ሆኗል። የተበከለው ዝናብ የሚያስከትለውን መዘዝ ለመከላከል ሲባል በመሬቱ ላይና በባሕሮች ውስጥ ኖራ ተጨምሯል። ይሁን እንጂ በኖራው ላይ የሚበቅሉት ተክሎች በውስጣቸው ሞሊብድነምን የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮች በከፍተኛ መጠን ይዘው ተገኝተዋል። አጋዝኖች ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ሞሊብድነም የተባለው ነጥረ ነገር ወደ ሰውነታቸው ካስገቡ በሰውነታቸው ውስጥ ያለውን የመዳብ መጠን በእጅጉ ሊቀንሰውና የበሽታ መከላከል አቅማቸውን በማዳከም ለሞት ሊዳርጋቸው ይችላል። በዚሁ የአሲድ ዝናብ ምክንያት ከ4,000 በሚበልጡት የስዊድን ሐይቆች ውስጥ ዓሣዎች በሕይወት መኖር አይችሉም፤ በኖርዌይ ደግሞ ትራውት የሚባለው የዓሣ ዝርያ ከአሁን ቀደም ከነበረው ብዛቱ በግማሽ ቀንሷል። የለንደኑ ዘ ሰንዴይ ቴሌግራፍ የብሪታንያ መንግሥት የብክለቱን ምንጭ ለመቀነስ በማሰብ ከኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ የሚወጣውን የድኝ መጠን የቀነሰ ቢሆንም የአሲድ ዝናብ ያስከተለው ውጤት ገና ለበርካታ ዓመታት መዝለቁ አይቀርም ሲል አሳስቧል።

የአፍሪካን ዝሆኖች ማሠልጠን

የእስያ ዝሆኖች በመቶ ለሚቆጠሩ ዘመናት ለሥራ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ በግዝፈት ከእነርሱ የሚያስከነዱት የአፍሪካዎቹ ዝርያዎች ለማላመድ የሚያስቸግሩና ተተናኳይ እንደሆኑ ተደርገው ይታሰቡ ነበር። ይሁን እንጂ ቢያንስ አንዱ ሙከራ ስኬት ያስገኘ ይመስላል። የአፍሪካ ዝሆኖች ዚምባቡዌ በሚገኘው የኢማየር እንስሳት መጠበቂያ ውስጥ መሬት ለማረስና እንግዶችን አስቸጋሪ ወደሆኑ ቦታዎች ለማጓጓዝ እያገለገሉ ነው። እንስሳቱን ለማለማመድ የተጠቀሙበት ዘዴ “ፍቅርና ሽልማት” ተብሎ ተጠርቷል። በአፍሪካ ውስጥ የሚታተም የአንድ ጋዜጣ ሪፖርተር ኒያሻ በመባል የሚጠራ አንድ ዝሆን ጀርባው ላይ ሙቼምዋ የተባለውን ሠራተኛ አስቀምጦ ሲያርስ ተመልክቷል። ሪፖርተሩ እንደሚከተለው ሲል ገልጿል:- “አሁንም አሁንም ኩምቢውን ወደኋላ ሲሰድ ሙቼምዋ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያለው ምግብ ጣል ያደርግለታል። በኢማየር የሚገኙት ኒያሻና ሌሎቹ የሠለጠኑ ስድስት ዝሆኖች እነርሱንም ሆነ በእርሻው መስክ ያሉትን ሌሎች እንስሳት ለመመገብ የሚያገለግሉትን እንደ በቆሎ የመሳሰሉ አዝርዕት የሚበቅሉበትን ማሳ ከሚቀጥለው የዝናብ ወቅት በፊት ለማዘጋጀት ያገለግላሉ።”

ከደም የተዘጋጁ ተጨማሪ ምግቦች

በሰሜን ምሥራቅ ብራዚል አካባቢ የተፈጠረውን የተዛባ አመጋገብ ለማስተካከል ለሙከራ ፕሮቴሞል የተባለ ተጨማሪ ፕሮቲን በመሰጠት ላይ ነው። አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ይህ ተዋጽኦ በዋነኛነት የሚዘጋጀው ከቄራዎች ከተሰበሰበ የላሞች ደም ሲሆን “ከሥጋው ሳይቀር የበለጠ ንጥረ ምግብነት” እንዳለው ይነገርለታል። በጉዋቲማላም በ1990 ተመሳሳይ ሙከራዎች ተደርገው “ሀሪና ዴ ሳናግሬ” (የደም ዱቄት) የተባለ ተዋጽኦ ተዘጋጅቶ ነበር። ብራዚል ውስጥ መንግሥት ፕሮቴሞል በየቤቱ እንዲሠራጭና “በወሰዱት ልጆች ላይ ምልክት እንዲደረግ” ዝግጅት አድርጓል። ከዚህ ቀደም በብራዚል ሰሜን ምሥራቅ የሚገኙት ቄራዎች ደሙን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰው ያስወግዱት ነበር።—ዘሌዋውያን 17:13, 14

በየዕለቱ ፍራፍሬ ተመገብ

ብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል ላይ ታትሞ የወጣው በ11,000 ሰዎች ላይ የተደረገው የ17 ዓመታት ጥናት እንዳረጋገጠው ተቀጥፎ ያልሰነበተ ፍራፍሬ በየዕለቱ መብላት ለልብ ሕመም የመጋለጥን አጋጣሚ ይቀንሳል። ጥናቱ ከተካሄደባቸው ተቀጥፎ ያልሰነበተ ፍራፍሬ በየዕለቱ ከሚመገቡት ሰዎች መካከል በልብ ሕመም የሞቱት ሰዎች ቁጥር 24 በመቶ ሲቀንስ አእምሮአቸው ውስጥ ደም በመፍሰሱ ወይም የሚገባውን ያህል ደም ሳይዘዋወር ቀርቶ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ደግሞ በ32 በመቶ ቀንሶ ተገኝቷል። በየዕለቱ ፍራፍሬ ከተመገቡት ሰዎች መካከል የሞቱት ሰዎች ቁጥር አልፎ አልፎ ብቻ ፍራፍሬ ከሚመገቡት ሰዎች ቁጥር ጋር ሲወዳደር 21 በመቶ ቀንሶ ተገኝቷል። ከብሪታንያና ከስፔይን የተውጣጡ ሳይንቲስቶችን ያቀፈ አንድ ቡድን ባካሄደው ጥናት መሠረት ተቀጥፎ ያልሰነበተ ፍራፍሬ አለመብላት በአንዳንድ ሕዝቦች ዘንድ በአእምሮ ውስጥ ደም እንዲረጋ ወይም በቂ ደም ወደ አእምሮ እንዳይደርስ አስተዋጽኦ ሊያደርግና የልብ ሕመምን ለመሳሰሉት የደም ሥር ችግሮች መባባስ ምክንያት ሊሆን ይችላል። አሁን አሁን ተመራማሪዎች ለጤና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሆኖ በመገኘቱ በየዕለቱ ቢያንስ አምስት ጊዜ አትክልቶችን እንዲሁም ፍራፍሬ መብላትን ያበረታታሉ። ተቀጥፎ ያልሰነበተ ፍራፍሬ ማግኘት አስቸጋሪ ከሆነ የብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል እንዳለው በማቀዝቀዣዎች ውስጥ የቆዩ ፍራፍሬዎችንም መብላት ከዚያ የማይተናነስ ጠቀሜታ አለው።

የልጆች ጦር ሠራዊት

በእንግሊዝ ማንቸስተር የሚታተመው ጋርዲያን ዊክሊ መጽሔት እንደዘገበው በ26 አገሮች ውስጥ የተደረገ አንድ ጥናት በዓለም ዙሪያ ዕድሜያቸው እስከ ሰባት የሚደርስ ሩብ ሚልዮን የሚሆኑ ልጆች በታጠቁ ሠራዊቶች ውስጥ ተሰልፈው ይዋጋሉ። የተባበሩት መንግሥታት ለሁለት ዓመት ያካሄደው ጥናት ሳይጠናቀቅ የተጠናቀረው ይህ ሪፖርት እንደሚጠቁመው እነዚህ ጨቅላ የጦር ምልምሎች ራሳቸው ብዙ ጭካኔ የተፈጸመባቸው፣ ብዙውን ጊዜም ዘመዶቻቸው ሲሰቃዩና ሲገደሉ በዓይናቸው ያዩ ልጆች ናቸው። ከዚያም በኋላ ሌሎችን በሞት እንዲቀጡ፣ በድብቅ ግድያ እንዲፈጽሙና በስለላ እንዲሠሩ ይደረጋሉ። በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ “አብዛኞቹ ሕፃናት ወታደሮች ለማምለጥ የሚሞክሩ ልጆችን ወይም ትላልቅ ሰዎችን እንዲያሰቃዩ፣ አካላቸውን እንዲቆርጡ ወይም እንዲገድሉ ይደረጋሉ።” ከውጊያው በፊት አልኮል ወይም አደንዛዥ ዕፅ የተሰጣቸው ልጆች “የማይሞቱ ወይም ጥይት የማይመታቸው ይመስል” ወደ ጦር አውድማው ለመግባት ሲጣደፉ ታይተዋል።

በተመሳሳይ ስም ከሚቸረቸሩ የሐሰት መድኃኒቶች ተጠበቁ

ዓመታዊው የሽያጭ ገቢው 16 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር የደረሰው በተመሳሳይ ስም የሚቸረቸሩት የሐሰት መድኃኒቶች ንግድ እያደገ ሄዷል። የፓሪሱ ጋዜጣ ለ ሞንድ እንዳሠፈረው “የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ ገበያ ላይ ከሚውሉት መድኃኒቶች መካከል 7 በመቶዎቹ የሐሰት መድኃኒቶች እንደሆኑ ገምቷል።” ይህ ቁጥር በብራዚል ውስጥ እስከ 30 በመቶ፣ በአፍሪካ ደግሞ እስከ 60 በመቶ ይደርሳል። እነዚህ የሐሰት መድኃኒቶች አንዳንዶቹ ኃይላቸው ከእውነተኛው መድኃኒት ጋር ሲወዳደር እጅግ ደካማ ሲሆን ሌሎቹ ጭራሽ ምንም ጥቅም የሌላቸው አልፎ ተርፎም መርዘኛ ነገር የያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ለ ሞንድ በኒጀር የተከሰተውን የማጅራት ገትር ወረርሽኝ በምሳሌነት ጠቅሷል፤ በዚህ ወቅት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ክትባት ከተሰጣቸው በኋላ የተወጉት ንጹህ ውኃ እንደነበር ተደርሶበታል። እንዲሁም በናይጄሪያ 109 የሚያክሉ ሕፃናት ፀረ ቀረት (አንቲፍሪዝ) የተጨመረበት ሽሮፕ በመጠጣታቸው ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይኸው ጋዜጣ “አንዳንድ ጊዜ ሐኪም ቤቶችም ሳይቀሩ የምርት ውጤቶችን ይበልጥ በቅናሽ ዋጋ ስለሚያቀርብ ወደ ጥቁር ገበያው ዞር ይላሉ” በማለት ዘግቧል። በብዙ አገሮች ውስጥ የጤና ጥበቃ ባለ ሥልጣኖች ሕግን የማስከበሩ ጉዳይ ደካማ ወይም ደግሞ በሙስና የታሠረ በመሆኑ ለዚህ ችግር መፍትሔ ማግኘት ተስኗቸዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ