ድካም የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ስውር ወጥመድ
በጀርመን የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ሰዓታት እየነጎዱ ሲሄዱ የኃይለኛው ሞተር አሰልቺ ጉርምርምታና በጎዳናው ላይ የሚሽከረከሩት 14 ጎማዎች የሚያሰሙት ለጆሮ የሚታክት ድምፅ አንድ ላይ ተዳምረው የከባድ መኪናው አሽከርካሪ ከድካም ጋር የሚያደርገውን ትግል ያከብዱበታል። የመኪናው የፊት መብራቶች የፈነጠቁት ብርሃን የጎዳናውን መስመሮች ወደ ኋላ እየተወ ሲሄድ ያሳየዋል። ድንገት፣ ተሳቢው ወደ ግራና ወደ ቀኝ በመወዛወዝ መንገዱን መሳት ይጀምራል።
አሽከርካሪው መሪውን በኃይል በመጠምዘዝ 40 ቶን የሚመዝነውን መኪና ወደ መንገዱ ይመልሰዋል። ሙሉ በሙሉ ሲነቃ ባለፉት ጥቂት ሰኮንዶች የሆነውን ሁኔታ ፈጽሞ ማስታወስ ይሳነዋል። ክፉኛ ከተጫጫነው ድካም ጋር እየታገለ ነው።a
መኪናውን በማሽከርከር ላይ እያለ ድካም ክፉኛ የተጫጫነው ሰው በቀላሉ ሊያሸልብ ይችላል። በዛሬው ጊዜ ካሉት የተጨናነቁ መንገዶች አንጻር ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ማሸለብ በሌሎች መንገድ ተጠቃሚዎችም ላይ እንኳ ሳይቀር ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል በደቡብ አፍሪካ ከጥር 1989 እስከ መጋቢት 1994 ባሉት ጊዜያት ውስጥ ከደረሱት የከባድ መኪና አደጋዎች መካከል ከ35 በመቶ በላይ የሚሆኑት አደጋዎች የተከሰቱት አሽከርካሪዎቹ መኪናቸውን እየነዱ በማንቀላፋታቸው ምክንያት ነው።
የአሽከርካሪዎችን ጠባይና ሁኔታ የሚያጠኑት ፕሮፌሰር ጂ ሽቶከር፣ ፋርሹሌ ለተባለው የጀርመን መጽሔት በሰጡት አስተያየት ድካም እየጨመረ ሲሄድ ድብታና የአልኮል መጠጥ የሚያመጣቸውን ዓይነት ውጤቶች ያስከትላል ሲሉ ገልጸዋል። እርግጥ ፕሮፌሰሩ የሰጡት አስተያየት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አሽከርካሪዎች የሚመለከት ነው።
የድካም መንስኤዎች
በብዙ አገሮች ውስጥ ያለው ሕግ አንድ የከባድ መኪና አሽከርካሪ ከምን ያህል ሰዓት በላይ መንዳት እንደሌለበት የሚገልጽ አልፎ ተርፎም የሚደነግግ ሆኖ እያለ ከድካም ጋር የተያያዙ አደጋዎች በብዛት የሚከሰቱት ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች በመንዳት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሥራዎችንም በመሥራት የሚያሳልፉትን አጠቃላይ የሥራ ሰዓት መመልከት ይኖርብናል። እነዚህ የሥራ ሰዓቶች ረጅምና ቋሚ የሆነ ሥርዓትን ያልተከተሉ ናቸው።
አብዛኞቹ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የተሰጣቸውን ሥራ ሙሉ በሙሉ ሳያጠናቅቁ ማረፍ የሚባል ነገር አይታያቸውም፤ በመሆኑም የጫኑትን ሸቀጥ በማንኛውም ዓይነት የአየር ጠባይ ተጉዘው ለደንበኞቻቸው ማድረስ እንዳለባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። የሥራ ብቃታቸው የሚለካው በሚጓዙት ርቀትና በሚያጓጉዙት ዕቃ መጠን ነው። የሥራ ሰዓታቸው ከአማካዩ ሰዓት በእጅጉ ሊበልጥ ይችላል። በጀርመን አብዛኞቹ ሰዎች በሳምንት ውስጥ በሥራ የሚያሳልፉት ጊዜ ከ40 ሰዓት ያነሰ ሲሆን ብዙዎቹ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ግን የዚህን ዕጥፍ ይሠራሉ።
በሌሎች አገሮችም ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። በደቡብ አፍሪካ አሽከርካሪዎች የሚከፈላቸው ደሞዝ አነስተኛ በመሆኑ ለብዙ ሰዓታት በመንዳት ገቢያቸውን ከፍ ለማድረግ ይጥራሉ። ከሕንድ የሚወጡት ዘገባዎች እንደሚያሳዩት የትራንስፖርት ኩባንያዎች አሽከርካሪዎቻቸው ጉዟቸውን ማጠናቀቅ የሚችሉበት በቂ ጊዜ የሚሰጡ ቢሆንም ብዙዎቹ አሽከርካሪዎች ገቢያቸውን ለማሳደግ ሲሉ ተጨማሪ ዕቃዎች ወደ ሌሎች ቦታዎች ያጓጉዛሉ፤ ይህ ደግሞ በማሽከርከር የሚያሳልፉትን ጊዜ ከፍ ያደርገዋል። ከዚያም ወደ ኩባንያው በሰዓቱ ለመመለስ የእንቅልፍ ጊዜያቸውን ለመቀነስ ይገደዳሉ።
በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ አንድ የከባድ መኪና አሽከርካሪ ሕጉ የሚፈቅደውን የመጨረሻውን የሰዓት ገደብ በመጠቀም በሳምንት ውስጥ ለ56 ሰዓታት ሊያሽከረክር ይችላል። ሆኖም በቀጣዩ ሳምንት ከ34 ሰዓታት በላይ እንዲያሽከረክር አይፈቀድለትም። ዕቃ በመጫንና በማራገፍ የሚያሳልፈውን ጊዜ ጨምሮ የሥራ ሰዓቱ በመቆጣጠሪያ መሣሪያ ይመዘገባል። ይህም እያንዳንዱ አሽከርካሪ ደንቡን ማክበር አለማክበሩን ለመቆጣጠር ያስችላል።
አንድ አሽከርካሪ መኪናውን በማሽከርከር በሚያሳልፈው ሰዓት ላይ ተጽዕኖ የሚያደርገው ሌላው ነገር የመኪናው ባለቤት አመለካከት ነው። መኪናው ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የፈሰሰበት በመሆኑ ቢቻል ያለማቋረጥ ዕቃዎችን በማጓጓዝ በቀን ለ24 ሰዓታት እንዲሠራ በማድረግ ትርፍ በሚያስገኝ መንገድ የመጠቀም ፍላጎት አለው። በትራንስፖርት ኩባንያዎች መካከል ያለው የንግድ ፉክክር እያደገ በመሄዱ አሠሪዎች አሽከርካሪዎቻቸው በፈቃደኝነት ለረጅም ሰዓታት እንዲሠሩ ግፊት ያሳድሩባቸዋል።
ድካም የሚመጣው የሥራ ሰዓት ረጅም በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ጉዞው ባልተለመደ ሰዓት በሚጀመርበት ጊዜም ጭምር ነው። ለምሳሌ ያህል ብዙውን ጊዜ አሽከርካሪዎች ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት እስከ አሥር ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ሥራ ይጀምራሉ። በዚህ ሰዓት አሽከርካሪዎች ጉልበታቸው የሚዳከም ከመሆኑም በላይ ንቁ ሆነው ለማሽከርከር በጣም ይቸገራሉ። ሸቀጦቹን የሚረከቡት ተቋሞች በእጃቸው ያለው ዕቃ እያለቀ ሲሄድና ሸቀጡ ‘ልክ በሰዓቱ’ እንዲደርስላቸው በሚጠይቁበት ጊዜ ግፊቱ ያይላል። ስለዚህ አሽከርካሪው ዕቃውን እንደጫነ በተቀጣጠሩበት ሰዓት ላይ ደንበኛው ቅጥር ግቢ ውስጥ መገኘት አለበት ማለት ነው። መንገዶች በተሽከርካሪዎች ሲጨናነቁ፣ መጥፎ የአየር ጠባይ ሲኖርና መንገዶች ሲጠገኑ የሚባክነውን ጊዜ አሽከርካሪው በሆነ መንገድ ማካካስ ይጠበቅበታል።
አንድ አሽከርካሪ ለምን ያህል ሰዓት ብቻ ማሽከርከር እንዳለበት የሚገልጹ ደንቦች የወጡ ቢሆንም እንኳ አልፎ አልፎ ፖሊሶች የሚያደርጉት ምርመራ ሕጉ እየተጣሰ እንዳለ ያመለክታል። ፖሊትሳይ ፌርኬር ዩንት ቴክኒክ የተባለው መጽሔት እንዳለው ከሆነ “ከባድ መኪና፣ አውቶቡስና ከባድ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ዕቃዎችን የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎችን ከሚያሽከረክሩ ሹፌሮች መካከል ከስምንቱ አንዱ ማለት ይቻላል፣ ለሥራና ለዕረፍት የተወሰነለትን ሰዓት አያከብርም።” በሀምቡርግ የትራፊክ ፖሊሶች ባደረጉት ምርመራ አንድ የከባድ መኪና አሽከርካሪ መኪናውን ያለምንም ዕረፍት ለ32 ሰዓታት እንዳሽከረከረ ታውቋል።
አደጋውን መገንዘብ
ከአገር ውጪ የሚላኩ ዕቃዎችን ለ30 ዓመታት ያጓጓዘ አንድ የረጅም ርቀት ሹፌር ድካም ስለሚያስከትለው ችግር ተጠይቆ ነበር። “ኩራትና ከመጠን በላይ በራስ መተማመን አንድ አሽከርካሪ ድካም የሚባለውን ነገር ወደ ጎን ገሸሽ እንዲያደርገው ሊገፋፋው ይችላል። አደጋዎች የሚከሰቱት በዚህ መንገድ ነው” ሲል ገልጿል። የድካም ምልክቶች ገጽ 24 ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ ተዘርዝረዋል።
የመጀመሪያዎቹን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ለይቶ ማወቁ ሕይወትን ሊያድን ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ በብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ የተካሄደ አንድ ጥናት አስደንጋጭ የሆነ አኃዛዊ መረጃ አውጥቷል:- በ107 ከባድ መኪናዎች ላይ ከደረሱት አደጋዎች መካከል ስልሳ ሁለቱ ከድካም ጋር የተያያዙ ናቸው። በመሆኑም ኢንዱስትሪዎች አሽከርካሪው ማንቀላፋት በጀመረ ቁጥር ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ መሣሪያዎች የመፈብረኩን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተውታል።
አንድ የጃፓን ኩባንያ የቪዲዮ ካሜራ በመጠቀም አሽከርካሪው ዓይኑን ምን ያህል ጊዜ እንደሚያርገበግብ የሚከታተል የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ እያዘጋጀ ነው። ዓይኑ በዝግታ የሚርገበገብ ከሆነ አስቀድሞ የተቀዳ ድምፅ አደገኛ ሁኔታ ላይ እንዳለ በማሳወቅ ያስጠነቅቀዋል። አንድ የአውሮፓ ኩባንያ ደግሞ መኪናው ምን ያህል በጥሩ ሁኔታ እየተነዳ እንዳለ የሚከታተል መሣሪያ በመሥራት ላይ ይገኛል። መኪናው ወዲያና ወዲህ መወዛወዝ ከጀመረ ጋቢና ውስጥ የማስጠንቀቂያ ድምፅ ይሰማል። ይሁን እንጂ ይህን የመሰሉ ውጤታማ መሣሪያዎች ተሠርተው ጥቅም ላይ እስኪውሉ ድረስ የተወሰነ ጊዜ ማለፉ አይቀርም።
አደጋውን መከላከል
ድካም ሳይጠራና ሳይፈቀድለት በሁሉም መኪናዎች ውስጥ ዘው ብሎ የሚገባ ተሳፋሪ ነው። ጥያቄው ይህን የማይፈለግ ተሳፋሪ ማስወጣት የሚቻለው እንዴት ነው የሚለው ነው። አንዳንድ አሽከርካሪዎች ካፌን ያለባቸውን መጠጦች በብዛት ቢጠጡም ድካሙ አይለቃቸውም። ሌሎች አሽከርካሪዎች ደግሞ ሌላ የሚያነቃቃ ነገር ይጠቀማሉ። እነዚህ ነገሮች በጤና ላይ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ግልጽ ነው። በሜክሲኮ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ንቁ ለመሆን ሲሉ በጣም የሚያቃጥል በርበሬ ይበላሉ።
በማለዳ ጉዞ ከመጀመር በፊት በቂ እንቅልፍ መተኛት ያስፈልጋል። በተጨማሪም አንድ አሽከርካሪ ደንቡ ከሚፈቅደው ሰዓት በላይ ማሽከርከር የለበትም። በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ ጠበብቶች አንድ አሽከርካሪ ለአምስት ሰዓት ያህል ሲያሽከረክር ከቆየ በኋላ ጥቂት ዕረፍት ቢወስድ ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። አንድ አሽከርካሪ ቀጥ ብሎ በተዘረጋ አሰልቺ ጎዳና ላይ በሚነዳበት ጊዜ አእምሮው ንቁና በትኩረት የሚከታተል መሆን አለበት። አንዳንድ አሽከርካሪዎች ራዲዮ ይሰማሉ ወይም ደግሞ ከሌሎች አሽከርካሪዎች ጋር በራዲዮ ይነጋገራሉ። አንድ የይሖዋ ምሥክር አሽከርካሪ እንደ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ያሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦችን በካሴት ይሰማል። ሌሎች ሐሳቦች ደግሞ በዚህ ገጽ ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ ሰፍረዋል።
በቂ መተዳደሪያ ለማግኘት የሚደረገው ትግል ይበልጥ እየከበደ በመሄዱ ሚዛንን መጠበቁ ቀላል አይሆንም። አንዳንድ ኩባንያዎች ወይም ሥራ አስኪያጆች የድካም ወጥመድ በአሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጥረውን አደጋ አቃልለው ይመለከቱታል። ስለዚህ በትራንስፖርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሁሉ ድካምን በተመለከተ ከላይ የተገለጹትን ነጥቦች ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ብዙውን ጊዜ አሽከርካሪዎች ከራሳቸው ተሞክሮ የቀሰሟቸው ጠቃሚ ሐሳቦች ሌሎች አሽከርካሪዎች ድብታን ለመቋቋም እንዲችሉ ሊረዷቸው ይችላሉ።
ንቁ ለመሆን የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለ መንገድ ሰውነታችን የሚያስፈልገውን ነገር በሚገባ ማሟላት ነው፤ ማንኛውንም ዓይነት የማስጠንቀቂያ ምልክት ስታዩ በአቅራቢያችሁ ያለ ልታርፉ የምትችሉበት ቦታ ፈልጋችሁ ለተወሰነ ጊዜ አሸልቡ። ከዚያ በኋላ እንደገና ጉዟችሁን ትያያዙታላችሁ። የስውሩ ወጥመድ የድካም ሰለባ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ በወንድ ጾታ መጠቀም የመረጥነው በጀርመን ውስጥ ከባድ መኪና የሚያሽከረክሩ ሴቶች ቁጥር በጣም አነስተኛ በመሆኑ ነው።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]
አፋጣኝ እርምጃ የሚሹ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች
• ዓይንህን የማቃጠል ስሜት ይሰማሃል? ወይም ደግሞ ዓይኖችህ ቡዝዝ ብለዋል?
• የቀን ሕልም ታልማለህ ወይም ደግሞ በሐሳብ ጭልጥ ብለህ ትሄዳለህ?
• መንገዱ ጠባብ እንደሆነና የመሀሉን መስመር ብቻ ተከትለህ መሄድ እንዳለብህ ይሰማሃል?
• በጉዞው ወቅት ያሳለፍካቸውን አንዳንድ ነገሮች ማስታወስ ተስኖሃል?
• መሪውንና ፍሬኑን እንደልብህ ማዘዝ አቅቶሃል?
ከእነዚህ ጥያቄዎች ለአንዱም እንኳ ቢሆን የምትሰጠው መልስ አዎ የሚል ከሆነ ወዲያውኑ እረፍት ማድረግ ይኖርብሃል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]
ረጅም ርቀት ስትጓዝ
• በቂ እንቅልፍ ተኛ
• በሚያነቃቁ ነገሮች አትተማን
• በየመሀሉ እረፍት አድርግ፤ ሰውነትህን ለማፍታታት የሰውነት እንቅስቃሴ አድርግ
• ቀጥ ብለው የተዘረጉ አሰልቺ መንገዶች ይበልጥ አደገኞች መሆናቸውን አስታውስ
• ርቦህ እያለ ጉዞ አትጀምር። ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ይኑርህ፤ ቀላልና ጤናማ የሆነ ምግብ ተመገብ
• ብዙ ፈሳሽ ጠጣ፤ ሆኖም አልኮል መጠጣት የለብህም