በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነትን እንዴት መቋቋም ይቻላል?
በብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ትዕግሥት ማጣትና በዚህም ምክንያት የሚፈጠር አምባጓሮ በዓለም ዜና ዘገባዎች ያለው ቦታ እየጨመረ መጥቷል። በብሪታንያ፣ በትላልቅ የገበያ አዳራሾች በዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎች ምክንያት ከሚፈጠር አምባጓሮና በስልክ ጭውውት መካከል ጣልቃ በመግባት ምክንያት ከሚፈጠረው ጥል በተጨማሪ የሰዎችን ትኩረት በመሳብ ላይ የሚገኘው በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነት ነው።
በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነት በጣም በመስፋፋቱ ምክንያት በ1996 በሰዎች የማሽከርከር ልማድ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ እንዳለው በብሪታንያ በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነት “እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል። በዚህም ምክንያት ባለፈው ዓመት ከአሽከርካሪዎች መካከል ግማሽ የሚያክሉት አንድ ዓይነት ስድብ ወይም ጥቃት ደርሶባቸዋል”! አንድ የአውቶሞቢል ማኅበር ከዚህ አልፎ በመሄድ “ከአሥር አሽከርካሪዎች መካከል ዘጠኙ በጎዳና ላይ ግልፍተኝነት እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ” በማለት ዘግቧል። ይሁን እንጂ ይኸው ጥናት “በማሽከርከር ላይ እንዳሉ ግልፍ ብሏቸው ትዕግሥት እንዳጡ ያመኑት ከአሥር አሽከርካሪዎች መካከል ስድስቱ ብቻ” መሆናቸውን መግለጹ የሚያስገርም ነው።
በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነት መንስኤው ምንድን ነው? እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ቢያጋጥምህ እንዴት ራስህን መጠበቅ ትችላለህ? የሌላ ሰው አነዳድ ቢያናድድህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነት በመላው ዓለም እየተስፋፋ በመሄድ ላይ በመሆኑ እንዴት ልትቋቋመው ትችላለህ?
መንስኤና ውጤት
ግልፍተኛ አሽከርካሪዎች መኖራቸው አዲስ ነገር አይደለም። ከጥንት ግልፍተኞች መካከል ሎርድ ባይረን የተባሉት እንግሊዛዊ ባለ ቅኔ ይገኛሉ። በ1817 በጻፉት ደብዳቤ ላይ በመንገድ ላይ ስላጋጠማቸው ጥል ተናግረዋል። ራሳቸው እንደጻፉት በፈረስ ሲሄዱ አንድ ሌላ የመንገድ ተጠቃሚ በፈረሳቸው ላይ “ጨዋነት የጎደለው ድርጊት” ፈጸመ። በዚህም ምክንያት ይህን ሰውዬ ጆሮ ግንዱ ላይ በቦክስ መቱት።
በብዙ አገሮች የተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን የአሽከርካሪዎች ንዴት ጨምሯል። የዩናይትድ ስቴትስ ጋዜጦች በአሽከርካሪዎች መካከል የሚፈጠረውን አምባጓሮ መንስዔ “በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነት” ብለው መጥራት የጀመሩት በ1980ዎቹ ዓመታት ነበር። በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነት በራሱ ወንጀል ሆኖ የሚያስቀጣ ባይሆንም በሌላ አሽከርካሪ አነዳድ የተናደዱ አሽከርካሪዎች ለሚፈጽሙት የኃይል ድርጊት ዋነኛ መንስኤ ሆኗል።
በአሁኑ ጊዜ ጎዳናዎቻችን ‘ከሁሉ በፊት እኔ’ በሚለው ዝንባሌ ተውጠዋል። በማሽከርከር ልማድ ላይ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች “ጠብ ወይም አምባጓሮ የሚፈጥሩ ሰዎች፣ ሁልጊዜ ለማለት ይቻላል፣ የሌላ ሰው ፀረ ማኅበራዊ ጠባይ ተጠቂዎች እንደሆኑና ራሳቸው ምንም ዓይነት በደል እንዳልፈጸሙ ያምናሉ” ብለው እንደሚደመድሙ ዘ ታይምስ የተባለው የለንደን ጋዜጣ ዘግቧል። አንድ አሽከርካሪ ምንም ዓይነት መጥፎ አነዳድ ቢኖረው ትክክለኛ እንደሆነ ይሰማዋል። ሌላው አሽከርካሪ ትንሽ ጨዋነት የጎደለው ድርጊት ሲፈጽም ግን ቁጣው ይገነፍላል።
በተጨማሪም አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ በተለይ በወጣቱ ዘንድ የተለመደ መሆኑ በጎዳና ላይ ለሚያጋጥም ግልፍተኝነት መብዛት አስተዋጽኦ አድርጓል። አንድ የሆስፒታል አማካሪ እንዳሉት ኮኬይን መውሰድ “የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ ከመንዳት አይለይም።” አደንዛዥ ዕፅ የሚወስዱ አሽከርካሪዎች አብዛኛውን ጊዜ የራሳቸውን ችሎታ ከመጠን በላይ ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። በዚህ ምክንያት አንዳንዶች ተሽከርካሪያቸውን በአደገኛ ፍጥነት ይነዳሉ። ሌሎች ደግሞ የማመዛዘን ችሎታቸው ስለሚቃወስ ከሥርዓት ውጭ ይነዳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ውጥረትና ጭንቀት በአንድ አሽከርካሪ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት አስብ። የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ካሪ ኩፐር በ1990ዎቹ ዓመታት ለታየው በጎዳና ላይ ለሚያጋጥም ግልፍተኝነት ምክንያቱ በአብዛኛው ዕለታዊ ኑሮ የሚያስከትለው ውጥረትና ጫና እንዲሁም አለመረጋጋት እንደሆነ ገልጸዋል። አንድ የሮያል አውቶሞቢል ክለብ ቃል አቀባይ “አሽከርካሪዎች ያለባቸው ውጥረት እየጨመረ መጥቷል፣ በዚህም ምክንያት በጎዳና ላይ የሚፈጠሩ አምባጓሮዎች በዝተዋል” ብለዋል። በአሁኑ ጊዜ ከቤታቸው ወደ ሥራ ሲመላለሱ በርካታ ሰዓት ጎዳና ላይ የሚያሳልፉ አንዲት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደ ቀድሞው ታጋሽ እንዳልሆኑ አምነዋል። “ከዚህ በፊት ከቁብ የማልቆጥራቸው ጥቃቅን ነገሮች አሁን በጣም ያናድዱኛል” እንዳሉ ዘ ሳንደይ ታይምስ ዘግቧል። አንተም እንደዚህ ይሰማህ ይሆናል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ?
በጎዳና ላይ ግልፍተኝነትን ከማነሳሳት ተቆጠብ
ሌሎች አሽከርካሪዎች ፍጹም አለመሆናቸውን ተገንዘብ። አልፎ አልፎ ሕጎችን መጣሳቸው አይቀርም። በምታሽከረክርበት ጊዜ ይህንን እውነታ ግምት ውስጥ አስገባ። ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሁኔታዎችን አስቀድመህ አስብ። ለምሳሌ በርካታ መስመሮች ባሉት አውራ ጎዳና ላይ በቀስታ መንዳት በሚቻልበት የጠርዝ መስመር ላይ እየነዳህ ነው እንበል። በዚህ ጊዜ ከአውራ ጎዳናው ጋር የሚገናኝ ታጣፊ መንገድ ታያለህ። ከፊት ለፊትህ አንድ ተሽከርካሪ ከተገንጣዩ መንገድ ወደ ዋናው መንገድ ሲገባ ትመለከታለህ። በቅድሚያ መስመር ውስጥ የገባሁት እኔ ነኝና መስመሩን ይዤ የመሄድ መብት አለኝ ትላለህ? ከተገንጣይ መንገድ ለገባ ተሽከርካሪ ለምን መንገድ ትለቃለህ? ቦታ እያለህ ሌላው ተሽከርካሪ ወደ ዋናው መንገድ ለመግባት እንዲችል ስትል ብቻ ለምን መስመርህን ትለቃለህ? ግን አስብ። መስመሬን ሳላቆም በመጣሁበት ፍጥነት እነዳለሁ ብትል ምን ይሆናል? ምናልባት ወደ ዋናው መንገድ የሚገባውም አሽከርካሪ እንዳንተው ያስብ ይሆናል። ከሁለት አንዳችሁ ቅድሚያ መስጠት ይኖርባችኋል። አለበለዚያ ከባድ አደጋ ይፈጠራል።
በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነት እንዳይነሳ የሚፈልግ አሽከርካሪ የሚመጣውን ሁኔታ በቅድሚያ ያስተውልና ለሌላኛው አሳቢነት በማሳየት ይነዳል። የሚቻል ከሆነ መንገዱን ይለቅለታል። በተጨማሪም ሌላው አሽከርካሪ ያሳየውን ጨዋነት ሳይገነዘብለት ቢቀርም አይቆጣም። የእንግሊዝ የማሽከርከር ችሎታ ማሻሻያ ተቋም ተወካይ ከሦስት አሽከርካሪዎች መካከል አንዱ አደገኛ የሆነ የዝንባሌ ችግር እንዳለው ገምተዋል። እነዚህ አሽከርካሪዎች ጥሩ የማሽከርከር ችሎታ ቢኖራቸውም ጨዋነት ይጎድላቸዋል። ተወካዩ “ጎበዝ ሾፌሮች፣ ግን አመለቢሶች” ብለዋቸዋል።
ብዙ አሽከርካሪዎች አንዳንድ ጊዜ ሌሎች የመንገድ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ፈጽመው ይዘነጋሉ። ይሁን እንጂ ይህ የአጸፋ እርምጃ እንድትወስድ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ሊከተል የሚችለውን ውጤት አስብ። ባንተ እልከኝነት ምክንያት የመኪና ግጭት ተፈጥሮ ብዙ ተሽከርካሪዎች ቆመው እንዲውሉ እንደማትፈልግ የታወቀ ነው። የራስህ ስሜት እንዲያሸንፍህ አትፍቀድ። ስለማሽከርከር ጥናት ያደረጉ አንድ ሰው “በመንገድ ላይ ለሚያጋጥምህ የጠብ አጫሪነት ድርጊት ጨርሶ ምላሽ መስጠት የለብህም” ሲሉ መክረዋል። በጎዳና ላይ ግልፍተኝነትን ከሚያነሳሱ ሰዎች መካከል አትሁን!
ጥቃት ደርሶብሃልን?
ግልፍተኛ አሽከርካሪ አጋጥሞት የማያውቅ አሽከርካሪ ያለ አይመስልም። በቁጣ መንፈስ እጃቸውን ጨብጠው ማወዛወዛቸው፣ ጮክ ብለው መሳደባቸውና መጥፎ አነዳዳቸው ሊያስፈራ ይችላል፤ ያስፈራልም። ከሁሉ የሚሻለው መከላከያ ከጠብ መራቅ ነው። አንድ አሽከርካሪ ሌላ አሽከርካሪ ሊቀድመው ሲፈልግ በጣም ፈራ። ከዚያም በንዴት የጦፈው አሽከርካሪ ቀደመውና ከፊት ለፊቱ ግትር አለበት። እንዲያውም የተጠቃው አሽከርካሪ መኪናዎቹ ካሁን ካሁን ተጋጩ ብሎ እስኪሰጋ ድረስ በጣም ዝግ ባለ ፍጥነት መንዳት ጀመረ። እስከ ተወሰነ ርቀት ድረስ ደጋግሞ እንዲህ ካደረገ በኋላ የተጠቃው አሽከርካሪ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ሌላ መንገድ በመሄድ ከሁኔታው አመለጠ።
ሌሎች አሽከርካሪዎች ሊቀድሙህ እንደሚፈልጉ ከተመለከትህ በተቻለህ መጠን እንዲቀድሙህ ፍቀድ። መስመሬን ይዤ የመሄድ መብት አለኝ የሚል ድርቅ ያለ መንፈስ ከመያዝ ተቆጠብ። እየታወቀህ ሌሎችን አስቆጥተህ ከሆነ ይቅርታ ጠይቃቸው። ሳታውቅ እንኳን ብታስቆጣቸው ያዘንክ መሆንህን በምልክት አሳያቸው። የለዘበ ቃል ቁጣ እንደሚያበርድ አስታውስ።
ይህ ሁሉ ሆኖ በሆነ ምክንያት በጎዳና ላይ ጥቃት ቢደርስብህ አጸፋ አትመልስ። ፎከስ የተባለው መጽሔት “ለተደረገብህ ነገር አጸፋውን አትመልስ” ሲል ይመክራል። “በመኪናህ ውስጥ ጉዳት ለማድረስ ሊያገለግል የሚችል መሣሪያ አትያዝ።” ሌሎች ምክሮች እነሆ:- የመኪናህን በሮችና መስኮቶች ቆልፍ። የዛተብህን ሰው ፊት ለፊት አትመልከት።
በጎዳና ላይ የሚያጋጥምን ግልፍተኝነት ስለመቋቋም ከላይ የተሰጡት ሐሳቦች አዲሶች አይደሉም። የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት በጥንት ዘመን ከሰጠው ከሚከተለው ምክር ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው:- “በክፉዎች ምክንያት አትበሳጭ። ኃጢአት በሚሠሩም አትቅና። አትቆጣ፤ አትናደድም።”—መዝሙር 37:1, 8 የ1980 ትርጉም
ምንም እንኳ በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ቢሄድም በአንተ ውስጥ ግን እንዲያድግ አትፍቀድ!
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጎዳና ላይ የሚያጋጥም ግልፍተኝነትን መቆጣጠር
የአሽከርካሪዎች ማኅበር እንዳለው በጎዳና ላይ የሚያጋጥምን ግልፍተኝነት በማስወገድ ረገድ “የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ከሚደረጉ ግንባታዎች ያላነሰ አስፈላጊነት አለው።” የራስህንም ሆነ የሌሎች መንገድ ተጠቃሚዎችን የማሽከርከር ችሎታ በምክንያታዊነት መመልከት በጎዳና ላይ የሚያጋጥምን ግልፍተኝነት ለመቋቋም በጣም አስፈላጊ ነው። የሌሎች ስህተት ገሐድ ሆኖ የሚታይህ ቢሆንም የራስህን የማሽከርከር ስህተት ደግሞ ችላ አትበል። የመንገድ ላይ ሕጎችን ሆን ብለው የሚጥሱ አሽከርካሪዎች መኖራቸውን አምነህ ተቀበል። በምታሽከረክርበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ንቁ መሆንህን አረጋግጥ። ድካም ውጥረት ያስከትላል። ለጥቂት ጊዜ እንኳን ትኩረት ማጣት ሕይወት ሊያሳጣ የሚችል አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
በተጨማሪም የሚከተለውን ምክር ተመልከትና ከጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ምሳሌዎች ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ልብ በል።
• ያሳፈርካቸው ሰዎች መቆጣትህን ለመመልከት ችለዋልን? ምናልባት ረጋ በል፣ አትቆጣ ብለውህ ይሆናል። ምክራቸውን ችላ ብለህ ምን አገባችሁ፣ የምነዳው እኔ! ብለህ አትመልስላቸው። የእርጋታ መንፈስ ለጤና ጥሩ እንደሆነና ረዥም ዕድሜ እንዲኖርህ ሊረዳህ እንደሚችል አስታውስ! “ሰላም ያለው አእምሮ ለሰውነት ጤንነትን ያስገኛል።”—ምሳሌ 14:30 የ1980 ትርጉም
• ለሌላው አሽከርካሪ አሳቢነት በማሳየት ሊነሳ የሚችለውን ችግር አስወግድ። “ጠቢብ ሰው ይፈራል፣ ከክፉም ይሸሻል። ሰነፍ ግን ራሱን ታምኖ ይኮራል።”—ምሳሌ 14:16
• ይቅርታ ለመጠየቅ ምልክት በማሳየት ወይም ይቅርታ በማለት ሊነሳ የሚችለውን ቁጣ አብርድ። “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች።”—ምሳሌ 15:1
• ሌሎች ግልፍተኞች መሆን ይቀናቸው ይሆናል። አንተ ግን እነርሱን መምሰል የለብህም። “ከቁጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን።”—ምሳሌ 22:24
• በሌሎች ጠብ ውስጥ አትግባ። “ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው።”—ምሳሌ 17:14