የአራዊት ማዛጋት
አንድ ሰው በሰው ፊት ሲያዛጋ ሰዎች ነውር እንደሆነ ይሰማቸዋል ወይም ደግሞ በጣም ደክሞታል ብለው ያስቡ ይሆናል። ማዛጋት ነውር ሆነም አልሆነ ጠቀሜታ አለው። ማዛጋት ሳይታወቀን አየር ወደ ውስጥ የምንስብበት ሂደት ነው። ብዙውን ጊዜ ቀን ባደረግናቸው እንቅስቃሴዎች ስለምንደክም ምሽት ላይ አለዚያም ጠዋት ከእንቅልፍ ስንነሳ እናዛጋለን። በጣም ስናዛጋ ብዙ ኦክስጅን ወደ ሰውነታችን ስለምናስገባ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ሰውነታችን ሊታደስ ይችላል። ብዙውን ጊዜ ይህ ራሳችንን ከእንቅልፍ የምናላቅቅበት አንዱ መንገድ ነው።
ሁልጊዜ ጥሩ አየር ለማግኘት ባይሆንም እንኳ እንስሳትም እንደሚያዛጉ ታውቃለህ? ብዙውን ጊዜ ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት በጣም አስደናቂ ነው። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ጊዜ ዝንጀሮዎች አንድ መልእክት ለማስተላለፍ ሲፈልጉ ያዛጋሉ። አፋቸውን በሰፊው መክፈታቸውና በሚያስፈራ መልኩ ጥርሳቸውን ማሳየታቸው ለአንድ ተቀናቃኝ ወንድ ዝንጀሮ ወይም አደጋ ያደርስብናል ብለው ላሰቡት ወገን የሚሰጥ የማስጠንቀቂያ ምልክት ነው። መልእክቱ:- ‘እገነጣጥልሃለሁ። እንዳትጠጋኝ!’ የሚል ነው።
በተጨማሪም በአፍሪካ ሜዳማ ስፍራዎች የሚገኙት አዳኝ የድመት ዘሮች ወደ አደን ከመሄዳቸው በፊት እንደሚንጠራሩና እንደሚያዛጉ ተስተውሏል። እንደ ሰዎች ሁሉ እነዚህ የድመት ዘሮችም ማዛጋታቸው ወደ ሳንባቸው ተጨማሪ አየር የማስገባት ተግባር ያከናውናል። ይህም በደም ውስጥ የሚኖረውን የኦክስጅን መጠን ከፍ ያደርገዋል። ከዚያ በኋላ ልብ ኦክስጅኑን ወደ ተለያዩ የአካል ክፍሎች በፍጥነት በማሰራጨት የሚያድኑትን እንስሳ በአጭር ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት ለማሳደድ የሚያስችል ኃይል እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።
በጣም የሚገርመው ዓሦችም እንኳ ሲያዛጉ መስተዋላቸው ነው! ኢንሳይድ ዚ አኒማል ዎርልድ የተሰኘው መጽሐፍ ስለ ዓሦች ሲገልጽ አንዳንድ ጊዜ “በፍጥነት ለመንቀሳቀስ ሲዘጋጁ ያዛጋሉ። . . . በተጨማሪም ዓሣ በደስታ ሲፈነጥዝ ወይም አንድ ጠላት ሲመለከት ወይም ምግብ ሲያገኝ፣ በአጠቃላይ ፈጣን እርምጃ መውሰድ በሚያስፈልግበት ጊዜ ሁሉ ያዛጋል።”
ምናልባት ከሁሉ ይበልጥ አስገራሚ የሆነው የጉማሬ ወይም የብሄሞት ማዛጋት ሳይሆን አይቀርም። ይህ እጅግ ግዙፍ የሆነ ፍጡር ዋሻ የሚያክለው አፉ ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ 150 ዲግሪ ይከፈታል! አንድ በዕድሜ የገፋ ጉማሬ የሚያዛጋው በክልሉ ውስጥ ላሉት ሁሉ አለቃቸው ማን እንደሆነ ለማሳየት ነው። በተጨማሪም ወደ እርሱ የወንዝ ክልል ለመግባት የሚቃጣ ሲኖር ትላልቅ ጥርሶቹን በማሳየት ለማስጠንቀቅ ያገለግላል።
በእንቅልፍ መጫጫን ምክንያት የሚፈጠረው፣ ለማስፈራራት ወይም ኃይልን ለማደስ ተብሎ የሚደረገው ማዛጋት፣ እንደ አንበሳ ግሳት ማራኪነት ያለው ባይሆንም ጠቀሜታ አላቸው። ይህ የእንስሳቱን ዓለም ያዘጋጀው ፈጣሪ ያለውን ዕፁብ ድንቅ የፈጠራ ችሎታ ከሚያሳዩት ምሳሌዎች አንዱ ብቻ ነው!