ውኃ ለፕላኔታችን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር
ቀለም፣ ሽታ ወይም ጣዕም የሌለውና ካሎሪ አልባ የሆነው ውኃ በምድር ላይ ለሚገኝ ሕይወት ላለው ነገር ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ነው። ማንኛውም ሰው፣ እንስሳም ሆነ ዕፀዋት ያለ ውኃ መኖር አይችልም። ከዝሆን አንስቶ እስከ ትንሿ ሕያው ነፍስ ድረስ ያሉት ፍጥረታት ውኃ የግድ ያስፈልጋቸዋል፤ ውኃን የሚተካ ምንም ነገር የለም። በምድር ላይ ያሉት ከአምስት ቢልዮን የሚልቁ ሰዎች ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን እያንዳንዳቸው በፈሳሽ ነገሮችና በምግብ አማካኝነት በየዕለቱ ሁለት ሊትር ተኩል ገደማ የሚሆን ውኃ መውሰድ አለባቸው። ውኃ ከሌለ ሕይወት የለም።
ያለ ውኃ እህል ማምረትም ሆነ ከብት ማርባት ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው። ውኃ ከሌለ ምግብ የለም፤ ምግብ ከሌለ ደግሞ ሕይወት የለም።
ደግነቱ፣ ተዝቆ የማያልቅ የውኃ ክምችት አለ። እጅግ ውብ የሆነችው ሰማያዊ ቀለም ያላት ፕላኔታችን ከጠፈር ላይ የተነሳችው ፎቶግራፍ ሲታይ ምድር ከመባል ይልቅ ውኃ ተብላ ብትጠራ ይቀላል። እንዲያውም በዓለም ላይ ያለው ውኃ እኩል በሆነ መንገድ የፕላኔታችንን ገጽ እንዲሸፍን ቢደረግ 2.5 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ያለው ዓለም አቀፋዊ ውቅያኖስ ይፈጠር ነበር። ሰላማዊ ውቅያኖስ ብቻ እንኳ የሸፈነው ቦታ ከጠቅላላው የምድር የብስ ይበልጣል።
እርግጥ ነው፣ አብዛኛው የምድር ውኃ በባሕሮች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የባሕር ውኃ ደግሞ ጨዋማ ነው። አንድ ሰው የባሕር ውኃ ብቻ የሚጠጣ ቢሆን ሰውነቱ ከመጠን ያለፈውን ጨው ለማስወገድ በሚያደርገው ጥረት በውኃ ጥምና በሰውነቱ ውስጥ ያለው ውኃ በማለቁ ምክንያት ብዙም ሳይቆይ ይሞታል። የባሕር ውኃ ለእርሻም ሆነ ለኢንዱስትሪ የሚመረጥ አይደለም፤ አብዛኞቹን ሰብሎች ያደርቃቸዋል አንዲሁም ማሽኖችን ወዲያውኑ ያዝጋቸዋል። ስለዚህ በአብዛኛው ሰዎች በባሕር ውኃ መጠቀም የሚችሉት ጨዉን ማስወገድ ከቻሉ ብቻ ነው፤ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሂደት ነው።
በዓለም ላይ ካለው ውኃ ውስጥ ጨዋማ ያልሆነው ውኃ 3 በመቶው ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥ 99 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በግግር በረዶና በበረዶ ንጣፍ መልክ ወይም በጥልቅ መሬት ውስጥ ነው። የሰው ልጅ በቀላሉ ሊያገኘው የሚችለው 1 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ነው።
አንድ በመቶ ሲባል አነስተኛ መስሎ ሊታይ ይችላል። ወደፊት ጨዋማ ያልሆነ ውኃ እጥረት ያጋጥም ይሆን? እንዲህ ዓይነት እጥረት የሚያጋጥም አይመስልም። ፒፕል ኤንድ ዘ ፕላኔት የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ይህ [1 በመቶ] የሚሆነው ውኃ እንኳ በዓለም ዙሪያ ለሁሉም በእኩል ደረጃ እንዲደርስና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የዓለማችን ነዋሪ ሁለት ወይም ሦስት እጥፍ የሚሆን ሕዝብ ማኖር ይችላል።”
በመሠረቱ፣ በምድር ላይ ያለው የውኃ መጠን አይጨምርምም አይቀንስምም። ሳይንስ ወርልድ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ዛሬ የተጠቀምክበት ውኃ በአንድ ወቅት የአንድን ዳይኖሶር ጥም ያረካ ውኃ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያለን ውኃ በሙሉ ከዚህ ቀደም የነበረን ወይም ደግሞ ወደፊትም የሚኖረን ነው።”
ይህ ሊሆን የቻለው በዓለም ዙሪያ ያለው ውኃ ያለማቋረጥ ስለሚሽከረከር ነው፤ ከውቅያኖሶች ወደ ከባቢ አየር፣ ከዚያም ወደ ምድር፣ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ወንዞች ይገባና ተመልሶ ከውቅያኖሶች ጋር ይቀላቀላል። ሁኔታው ጠቢቡ ሰው ከብዙ ጊዜ በፊት እንደጻፈው ነው:- “የወንዝ ውሃ ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳል፤ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ውሃ ተመልሶ እንደገና ወደሚፈልቅበት ወደ ወንዞቹ መነሻ ይሄዳል።”—መክብብ 1:7 የ1980 ትርጉም
ይሁን እንጂ በምድር ላይ ጨው አልባ የሆነ የተትረፈረፈ ውኃ ቢኖርም እንኳ ብዙ የምድር ክፍሎች በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። የሚቀጥሉት ርዕሶች ችግሮቹንና እነዚህን ችግሮች በመፍታት ረገድ ያሉትን ተስፋዎች በጥልቀት ያብራራሉ።
[ምንጭ]
NASA photo