የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g23 ቁጥር 1 ገጽ 3-5
  • የውኃ ምንጮች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የውኃ ምንጮች
  • ንቁ!—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የውኃ ምንጮች የተደቀነባቸው አደጋ
  • ፕላኔታችን የተፈጠረችው ለዘላለም እንድትኖር ነው
  • እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች
  • ተስፋ ለማድረግ የሚያበቁ ምክንያቶች—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
  • መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ስለተከሰተው የውኃ እጥረት ምን ይላል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • ችግሩ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነባቸው ቦታዎች
    ንቁ!—1998
  • የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ውኃ ለፕላኔታችን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2023
g23 ቁጥር 1 ገጽ 3-5
አንዲት ሴት ከወንዝ ንጹሕ ውኃ በእጇ ጨልፋ ስታወጣ።

ፕላኔታችን ትተርፍ ይሆን?

የውኃ ምንጮች

ውኃ፣ በተለይም ጨዋማ ያልሆነ ውኃ ባይኖር ኖሮ በምድር ላይ ሕይወት ሊኖር አይችልም ነበር። እንዲያውም ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ አብዛኛው የአካላቸው ክፍል ውኃ ነው። ሰዎችና እንስሳት ንጹሕ የመጠጥ ውኃ የሚያገኙት ከሐይቆች፣ ከወንዞች፣ ከረግረጋማ መሬቶችና ከከርሰ ምድር የውኃ ማቆሪያዎች ነው። እህል የምናመርተውም በእነዚሁ የውኃ ምንጮች ተጠቅመን ነው።

የውኃ ምንጮች የተደቀነባቸው አደጋ

የፕላኔታችን አብዛኛው ክፍል በውኃ የተሸፈነ ነው። ሆኖም የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት እንደገለጸው “በምድር ላይ ካለው ውኃ መካከል ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው ጨዋማ ያልሆነ ውኃ 0.5 በመቶው ብቻ ነው።” ይህ መጠን በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ ቢሆንም በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ለማቆየት በቂ ነው። ያም ቢሆን ብዙዎቹ የውኃ ምንጮች በመበከላቸው፣ የውኃ ፍጆታ በመጨመሩ እንዲሁም የአየር ንብረት በመለወጡ የተነሳ የውኃ እጥረት እያጋጠመ ነው። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በ30 ዓመት ውስጥ አምስት ቢሊዮን ሰዎች በውኃ እጥረት የተነሳ ለችግር ሊዳረጉ ይችላሉ።

ፕላኔታችን የተፈጠረችው ለዘላለም እንድትኖር ነው

ምድር የውኃ አቅርቦት እንዳይነጥፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ተፈጥሯዊ ሂደቶች አሏት። በተጨማሪም አፈር፣ በውኃ ውስጥ ያሉ ፍጥረታት እንዲሁም የፀሐይ ብርሃን ተባብረው በመሥራት ውኃን ያጣራሉ። ፕላኔታችን ለዘላለም የመኖር አቅም እንዳላት የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎችን እስቲ እንመልከት።

  • አፈር በርካታ በካይ ንጥረ ነገሮችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ከውኃ ማስወገድ እንደሚችል ተደርሶበታል። ለምሳሌ በረግረጋማ መሬቶች ላይ የሚበቅሉ አንዳንድ ተክሎች ናይትሮጅን፣ ፎስፈረስ እና ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን እንደሚያጣሩ ተስተውሏል።

  • ሳይንቲስቶች በተፈጥሮ የሚመጡ ብክለቶችን ለማስወገድ የሚረዱ በርካታ ሂደቶች እንዳሉ ደርሰውበታል። እነዚህ በካይ ንጥረ ነገሮች በሚፈስ ውኃ ውስጥ ሲያልፉ ይበረዛሉ፤ ከዚያም በባክቴሪያዎች አማካኝነት ይወገዳሉ።

  • ጨዋማ ባልሆነ ውኃ ውስጥ የሚኖሩ ክላም እና መስል የተባሉ ፍጥረታት በቀናት ውስጥ ውኃን ከተለያዩ ጎጂ ኬሚካሎች ማጣራት ይችላሉ። እንዲያውም እነዚህ ፍጥረታት ውኃን የሚያጣሩበት መንገድ ከውኃ ማጣሪያ ማዕከላት ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።

  • ፕላኔታችን በውኃ ዑደት አማካኝነት ውኃ ከምድር እንዳይወጣ ታደርጋለች። ይህ ዑደት ከሌሎች ተፈጥሯዊ ሂደቶች ጋር በመቀናጀት ውኃ ከከባቢ አየራችን እንዳይወጣ ወይም በሌላ መንገድ እንዳይነጥፍ ይከላከላል።

    ይህን ታውቅ ነበር?

    አፈር—ተፈጥሯዊ የውኃ ማጣሪያ

    አፈር ወደ መሬት በሚሰርገው ውኃ ውስጥ ያሉ ብረት ነክ ንጥረ ነገሮችን፣ መርዛማ ኬሚካሎችን፣ ተፈጥሯዊ ቆሻሻዎችንና ሌሎች በካይ ነገሮችን ያጣራል። ውኃው የከርሰ ምድር ማቆሪያዎች ውስጥ በሚደርስበት ጊዜ በጣም ንጹሕ ከመሆኑ የተነሳ ለመጠጥነት እንኳ ሊውል ይችላል።

    አፈር የተበከለ ውኃን የሚያጣራው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫ። የዝናብ ውኃ በአፈር፣ በድንጋይና በሸክላ ጭቃ ውስጥ አልፎ የከርሰ ምድር የውኃ ማቆሪያ ጋ ይደርሳል።

    ፊዚካላዊ ማጣሪያ

    የአሸዋ እና የድንጋይ ቅንጣቶች ጥቅጥቅ እንዳለ ወንፊት አንዳንድ በካይ ንጥረ ነገሮችን ይዘው ያስቀራሉ።

    ባዮሎጂካላዊ ማጣሪያ

    አፈር ውስጥ የሚኖሩ ባክቴሪያዎች ለሰዎች መርዛማ ሊሆኑ የሚችሉ ንጥረ ነገሮችን ያረክሳሉ። እንዲያውም አንዳንድ ባክቴሪያዎች መርዛማ የሆኑ ዘይቶችን ወደ ካርቦንዳይኦክሳይድ እና ወደ ውኃ መቀየር ይችላሉ።

    ኬሚካላዊ ማጣሪያ

    መጠነኛ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ያላቸው አፈሮች ተቃራኒ ቻርጅ ያላቸውን መርዛማ ኬሚካሎች ስበው መያዝ ይችላሉ። ለምሳሌ ኔጌቲቭ ቻርጅ ያለው የሸክላ አፈር ፖዘቲቭ ቻርጅ ያለውን መርዛማ አሞኒየም ከውኃ ማስወገድ ይችላል።

እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች

ፎቶግራፎች፦ 1. አንድ ሰው ዘይት የሚያፈሰውን የመኪናውን ክፍል ሲጠግን። ከመኪናው የሚንጠባጠበው ዘይት መሬት ላይ እንዳይፈስ ከሥር ዕቃ አስቀምጧል። 2. አንድ ሰው ኬሚካል የያዙ ዕቃዎችን በተገቢው መንገድ ሲያስወግድ።

መኪናችን ዘይት የሚያፈስ ከሆነ በመጠገን እንዲሁም መርዛማ ነገሮችን በትክክለኛው መንገድ በማስወገድ የውኃ ምንጮች እንዳይበከሉ መከላከል እንችላለን

ባለሙያዎች በቻልነው አጋጣሚ ሁሉ ውኃ መቆጠብ እንዳለብን ይመክራሉ። የውኃ ብክለትን ለመቀነስ ደግሞ መኪናችን ዘይት የሚያፈስ ከሆነ ቶሎ እንድንጠግን፣ ያልተጠቀምንባቸውን መድኃኒቶች መጸዳጃ ቤት ውስጥ እንዳንደፋ እንዲሁም መርዛማ ነገሮችን በፍሳሽ ማስወገጃ ውስጥ እንዳንለቅ ያሳስባሉ።

መሐንዲሶች ጨዋማ ውኃን ወደ መጠጥ ውኃ ለመቀየር የሚያስችሉ አስደናቂ መንገዶችን ፈልስፈዋል። ዓላማቸው የንጹሕ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን መጨመር ነው።

ሆኖም እየተደረጉ ያሉት ጥረቶች አመርቂ አይደሉም። ጨዋማ ውኃን ወደ መጠጥ ውኃ የመቀየሩ ሂደትም ቢሆን የሚያዋጣ አይመስልም፤ ምክንያቱም ብዙ ወጪ የሚያስወጣ ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ኃይል ይጠይቃል። በ2021 ስለ ውኃ አጠቃቀም የወጣ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚገልጸው “በዓለም ዙሪያ እየተደረገ ያለው ጥረት በእጥፍ ማደግ አለበት።”

ተስፋ ለማድረግ የሚያበቁ ምክንያቶች—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“አምላክ . . . የውኃ ጠብታዎችን ወደ ላይ ይስባል፤ ጭጋጉም ወደ ዝናብነት ይለወጣል፤ ከዚያም ደመናት ያዘንባሉ፤ በሰው ልጆችም ላይ ዶፍ ያወርዳሉ።”—ኢዮብ 36:26-28

አምላክ ለምድር የውኃ ምንጮች ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችሉ ተፈጥሯዊ ዑደቶችን አዘጋጅቷል።—መክብብ 1:7

እስቲ አስበው፦ ፈጣሪያችን ውኃን ለማጣራት የሚያስችሉ ሂደቶችን ካዘጋጀ ሰዎች በዚህ ወሳኝ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ያደረሱትን ጉዳት ለማስተካከል ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው አለው ብሎ ማመን ምክንያታዊ አይመስልህም? በገጽ 15 ላይ የሚገኘውን “አምላክ ፕላኔታችን እንደምትተርፍ ቃል ገብቷል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

የውኃ ሞለኪዩሎች ጎልተው ሲታዩ።

ውኃ በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችሉ ለየት ያሉ ባሕርያት አሉት። አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር ይገልጣሉ—ውኃ የሚለውን ቪዲዮ ከ​jw.org ላይ ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ