የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 7/8 ገጽ 16-17
  • ለእግር ሕመም የሚረዳ ምክር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለእግር ሕመም የሚረዳ ምክር
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ልክ፣ ፋሽንና እግር
  • ጠቃሚ ምክር ለጫማ ገዥዎች
  • ጫማህ በእርግጥ ልክህ ነውን?
    ንቁ!—2003
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1999
ንቁ!—1998
g98 7/8 ገጽ 16-17

ለእግር ሕመም የሚረዳ ምክር

“እግሬ አሠቃይቶ ሊገድለኝ ነው!” ይህ አባባል የተጋነነ እንደሆነ ግልጽ ነው። ቢሆንም የእግር ሕመም በዩናይትድ ስቴትስ እንደ ዋዛ የሚታለፍ ባለመሆኑ በሺህ ለሚቆጠሩ የእግር ሐኪሞች (podiatrists) መተዳደሪያ ሊሆን ችሏል።

ዶክተር ማይክል ካፍሊን የተባሉት የአጥንት ቀዶ ሐኪም (orthopedic surgeon) በ14 ዓመት ጊዜ ውስጥ 2,000 የሚያክሉ ቀዶ ሕክምናዎችን ካከናወኑ በኋላ አንድ አስደንጋጭ ሐቅ ሊገነዘቡ ችለዋል። “ለማመን ቢያስቸግርም እነዚህ ሁሉ ቀዶ ሕክምናዎች የተደረጉት በሴቶች ላይ ነው” ብለዋል። በተለይ ሴቶች ለእግር ሕመም የሚጋለጡት ለምንድን ነው?

ልክ፣ ፋሽንና እግር

በ356 ሴቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በአማካይ ከ10 ሴቶች መካከል ዘጠኙ ጠባብ ጫማ ያደርጋሉ! ለዚህ ምክንያቱ በከፊል የሴቶች ጫማ አሠራር ነው። የአጥንት ቀዶ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ፍራንቼስካ ቶምሰን “በአሁኑ ጊዜ ጫማ ሠሪዎች ከተረከዙ ጠበብ ብሎ ከፊት ሰፋ ያለ ጫማ ለመሥራት በሚያስችላቸው ሊነቃቀል የሚችል ፎርም መጠቀም ትተዋል” በማለት ያስረዳሉ።a

በዚህ ምክንያት ብዙ ሴቶች አዲስ ጫማ በሚሞክሩበት ጊዜ ከፊት ልካቸው ሲሆን ተረከዙ ደግሞ ይሰፋባቸዋል። ተረከዙ ልካቸው ሲሆን ደግሞ ከፊቱ ይጠባቸዋል። አንዳንዶች በተራመዱ ቁጥር ጫማቸው ከተረከዛቸው ውልቅ፣ ውልቅ እያለ ከሚያስቸግራቸው ከፊቱ ጠባብ ሆኖ ተረከዛቸውን ግጥም አድርጎ የሚይዝላቸው ጫማ ይመርጣሉ።

ጣቶችንና የእግርን ፊተኛ ክፍል ጭምቅ አድርጎ የሚይዝ ጫማ የሚያስከትለው ጉዳት እንዳይበቃ የጫማ ፋሽን አውጪዎች ተረከዙ ረዥም እንዲሆን ያደርጋሉ። ረዥም ተረከዝ ያለው ጫማ ጥሩ ፋሽን ነው ይባል እንጂ የሰውነት ክብደት በሙሉ በእግር መዳፍ ላይ ብቻ እንዲያርፍ ከማድረጉም በላይ መላው እግር ጠባብ ወደሆነው የጫማ ጫፍ እንዲገፋ ያደርጋል። ፖዲያትሪስት የሆኑት ዶክተር ዴቪድ ጋርት “ለጤና ተስማሚ ነው የሚባል ባለ ረዥም ተረከዝ ጫማ የለም” ብለዋል። አንዳንዶች ረዥም ተረከዝ ያለው ጫማ ውሎ አድሮ በእግር፣ በቁርጭምጭሚት፣ በባት፣ በጉልበትና በወገብ ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ይናገራሉ። በተጨማሪም የእግርን ጡንቻዎችና ጅማቶች ሊያሳጥር ስለሚችል በተለይ በሯጮች ላይ ከባድ ጉዳት ያስከትላል።

የሴቶች እግር ከሚደርስበት ጉስቁልና ጋር የመላመድ ችሎታ የለውም። እንዲያውም አንዲት ሴት ለአቅመ ሔዋን ከደረሰች በኋላ እንኳን የፊት እግሯ ሰፋ ከማለቱ በስተቀር ለበርካታ ዓመታት በእግሯ ቅርጽ ላይ ብዙ ለውጥ አይታይም። በተለይ በተረከዟ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አይኖርም። ዶክተር ቶምሰን እንደሚሉት “ተረከዝ ያለው አጥንት አንድ ብቻ ሲሆን በ84 ዓመቷም ሆነ በ14 ዓመቷ ያለው መጠን አንድ ዓይነት ነው።” ይህም ከአውራ ጣቷ እስከ ተረከዟ የሚመቻት ጫማ ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆንባት የሚያደርግ ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል።

ጠቃሚ ምክር ለጫማ ገዥዎች

ታዲያ ሴቶች የጫማ አሠራርም ሆነ ፋሽን የእግራቸውን ምቾት የሚጻረር ሆኖ እያለ የእግር ሕመም እንዳይደርስባቸው ሊከላከሉ የሚችሉት እንዴት ነው? መፍትሔው ከጫማ ሱቅ ይጀምራል። አንዳንድ ባለሞያዎች የሚከተሉትን ምክሮች ይሰጣሉ:-

● እግር በትንሹ አበጥ ስለሚል በቀኑ መገባደጃ አካባቢ ጫማ መግዛት።

● የአንዱን እግር ጫማ ብቻ ሳይሆን የሁለቱንም እግሮች ጫማ መሞከር።

● ተረከዝ ላይ ልክ መሆኑንና የጫማው ጫፍ ርዝመት፣ ስፋትና ከፍታ በቂ መሆኑን ማረጋገጥ።

● ጫማው ምቹ ሳይሆን ለጊዜው ብቻ ምቹ ሆኖ እንዲሰማችሁ የሚያደርግ ወፍራም ምንጣፍ ከእግራችሁ ስር አለመኖሩን ማረጋገጥ።

● ፕላስቲክ ከሚመስሉ ወይም ከሰው ሠራሽ ቆዳ የተሠራ ጫማ አለመግዛት። እንደነዚህ ያሉት ቆዳዎች እንደ ለስላሳ ቆዳ ስትሄዱባቸው አይመቻችሁም።

● ረዥም ተረከዝ ያለው ጫማ የምትገዙ ከሆነ ተጨማሪ የቆዳ ገበር ደርቡበት። ረዥም ተረከዝ ያለውን ጫማ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ አድርጉ። በቀኑ ውስጥ አጭር ተረከዝ ያለው ጫማ ቀይሩ።

ከላይ ከተመለከቱት ምክሮች በተጨማሪ ጫማ ለመግዛት በምትለኩበት ጊዜ ምንጊዜም ምቾት ያለው መሆኑን አረጋግጡ። ብዙ ጊዜ እንደሚባለው ወደፊት ይሰፋል ብላችሁ አትግዙ። ዶክተር ካፍሊን “ጫማው ያዝ የሚያደርጋችሁ ከሆነ ሻጩ ትንሽ ከሄዳችሁበት በኋላ ይሰፋል ብሎ እንዲያሳምናችሁ በፍጹም አትፍቀዱ” በማለት ይመክራሉ። “እንዲህ ያለው ጫማ እግራችሁን ያቆስላል እንጂ እንደተባለው አይሰፋም።”

ይሁን እንጂ ያላችሁ አማራጭ ተረከዙ ላይ ልክ ሆኖ ከፊቱ ጠባብ የሆነ ወይም ከፊቱ ልክ ሆኖ ተረከዙ ሰፋ የሚል ጫማ ብቻ ቢሆንስ? ፖዲያትሪስት የሆኑት ዶክተር አኑ ጎል ለማስተካከል የሚቀልለውን መንገድ መምረጥ አለባችሁ ይላሉ። “በሁለት መንገዶች ማስተካከል ይቻላል። አንደኛው ከፊቱ ሰፋ ያለ ጫማ መግዛትና ተረከዙ ጠበብ እንዲል ከተረከዙ በኩል ዳባን ማስገባት ነው። . . . ሁለተኛው ዘዴ ከተረከዙ ልክ የሆነ ጫማ መግዛትና ፊቱን ማስወጠር ነው። ይህ ዘዴ ግን አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራው ከንጹሕ ቆዳ ለተሠሩ ጫማዎች ነው።”

ብዙ ሴቶች በቀን ውስጥ አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር የሚያክል ርቀት እንደሚሄዱ ስለሚገመት የሚያደርጉትን ጫማ በጥንቃቄ ቢመርጡ ይጠቀማሉ። አሜሪካን ኸልዝ መጽሔት እንዳለው “ለእግራችሁ ጥሩ እንክብካቤ በማድረግ፣ በተለይም ምቹ ጫማ በማድረግ በእግር ላይ የሚደርሱ ሕመሞችን በአብዛኛው ማስወገድ ትችላላችሁ።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “ፎርም” ጫማ የሚወጠርበት የእግር ቅርጽ ያለው መሣሪያ ነው።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የተለመዱ አራት የእግር ችግሮች

የአውራ ጣት መጅ። በአውራ ጣት የመጨረሻ አንጓ ላይ የሚወጣ እብጠት ነው። ይህ መጅ ከዘር የመጣ ካልሆነ ጠባብ ወይም ረዥም ተረከዝ ያለው ጫማ ከማድረግ የሚመጣ ነው። የሕመም ስሜት ከኖረው ሙቀት እንዲሰማው ማድረግ ወይም በረዶ ማስቀመጥ ለጊዜው ሊያስታግስ ይችላል። ለዘለቄታው ለማስወገድ ግን ቀዶ ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋል።

የጣት ጉብጠት። የእግርን ፊተኛ ክፍል ጭምቅ አድርጎ የሚይዝ ጫማ በማድረግ ምክንያት ጣቶች ወደ ታች ሊጎብጡ ይችላሉ። ጉብጠቱን ለማስተካከል ቀዶ ሕክምና ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል።

መጅ። አንዳንድ ጊዜ ጠባብ ጫማ በማድረግ ምክንያት መፋተግ ሲኖር በጣቶች ላይ የሚፈጠር ጉብ ያለ እብጠት ነው። በቤት ውስጥ በሚሰጥ ቀላል ሕክምና ጊዜያዊ ፋታ ማግኘት ቢቻልም አብዛኛውን ጊዜ ተጨማሪ መፋተግ እንዳይኖር እብጠቱን በቀዶ ሕክምና ማስወገድ ሊያስፈልግ ይችላል።

ካሎ። እግርን ከሚደርስበት ተደጋጋሚ መፋተግ የሚከላከል ወፍራምና በድን ቆዳ ነው። ይህን ዓይነቱን ቆዳ እንግሊዝ ጨው በተጨመረበት ሙቅ ውኃ በመዘፍዘፍ ማለስለስ ይቻላል። ይሁን እንጂ ኢንፌክሽን ሊፈጥር ስለሚችል ቆርጦ ለማንሳት መሞከር ተገቢ አይደለም።

[ምንጭ]

The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ