የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 8/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጽንስ ማስወረድ የሚያስከትለው ጉዳትና ሞት
  • ከልክ በላይ መብላት በተበከለ ምግብ ለመመረዝ ያጋልጣል
  • የአካል ብቃትን መጠበቅ
  • የሳቅ እጥረት
  • የዓለም መሃይማን ቁጥር እየጨመረ ነው
  • የአስም ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ ነው
  • ለተፈጥሮ አደጋ የተጋለጠችው እስያ
  • ውጥረት ውስጥ የገቡ ቤተሰቦች
  • አሁንም ልጆች ትምህርት አያገኙም
  • አሥሩ ግንባር ቀደም ገዳይ ተላላፊ በሽታዎች
  • ለእግር ሕመም የሚረዳ ምክር
    ንቁ!—1998
  • ጫማህ በእርግጥ ልክህ ነውን?
    ንቁ!—2003
  • የሰላም ማስከበር ጥረቶች ለዓለም ሰላም ያመጡ ይሆን?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • 50 ዓመት ሙሉ ያልተሳኩ ጥረቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ንቁ!—1999
g99 8/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

ጽንስ ማስወረድ የሚያስከትለው ጉዳትና ሞት

በሜክሲኮ በየዓመቱ ወደ 500,000 የሚጠጉ ውርጃዎች ይፈጸማሉ በማለት በሜክሲኮ ሲቲ የጤና እና ማኅበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ፍራንሲስኮ ሐቪዬር ሴርና አልቫራዶ ተናግረዋል። ኤል ዩኒቨርሳል የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ጽንስ የማስወረዱ ተግባር በርካታ እናቶችን ለሞት የሚዳርግ ሲሆን ሌሎች ብዙ እናቶችንም የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገው ወይም ሐኪም ቤት እስከ መተኛት የሚያደርስ ጉዳት ላይ ይጥላቸዋል። በሜክሲኮ የብዙ እናቶችን ሕይወት ለሞት ከሚዳርጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው በድብቅ የሚፈጸም ጽንስ የማስወረድ ድርጊት ነው። አንዳንድ ጊዜ ጽንስን ለማስወረድ ጫፋቸው ሹል የሆኑ መሣሪያዎችን፣ የሚያስጨነግፉ መድኃኒቶችን ወይም ሥራ ሥሮችን፣ አልፎ ተርፎም ሆን ብሎ ከደረጃ ላይ መውደቅን የመሳሰሉ አደገኛ ዘዴዎች ይጠቀማሉ። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ዘዴዎች “ብዙ ደም እንዲፈስስ፣ ማኅፀን እንዲቀደድ፣ እናቲቱ መካን እንድትሆን፣ ለኢንፌክሽን እንድትጋለጥና ከነጭራሹ ማኅፀኗን እንድታጣ” በማድረግ አስከፊ መዘዝ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ሪፖርቱ ይገልጻል።

ከልክ በላይ መብላት በተበከለ ምግብ ለመመረዝ ያጋልጣል

በሜክሲኮ የሳልቫዶር ሱቢራን ብሔራዊ የስነ ምግብ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አዶልፎ ቻቬዝ ባሉት መሠረት አንድ ሰው ከልክ በላይ የሚበላ ከሆነ በተበከለ ምግብ የመታመሙ አጋጣሚ በጣም ከፍ ያለ ነው። ብዙውን ጊዜ ጨጓራችን ውስጥ የሚገኘው የጨጓራ ፈሳሽ በምንመገበው ምግብ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎችን ይገድላቸዋል። ሆኖም ከልክ በላይ ከተመገብን ተጨማሪው የምግብ መጠን በጨጓራ ውስጥ ከሚገኘው የአሲድ መጠን ስለሚበልጥ ጨጓራ ባክቴሪያዎችን የመግደል አቅሙ ይዳከማል። ዶክተር ቻቬዝ “አንድ ሰው 15 ሳንቡሳ ቢመገብና ከእነዚህ መካከል አንዱ የተበከለ ቢሆን ከተመገበው ብዛት አንጻር የመታመሙ አጋጣሚ ከፍ ያለ ይሆናል። ሆኖም ያው ግለሰብ አንድ የተበከለ ሳንቡሳ ብቻ ቢመገብ ምንም ችግር ላይፈጥርበት ይችላል” በማለት ለንቁ! ተናግረዋል።

የአካል ብቃትን መጠበቅ

የካናዳ ጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤት ዘ ፊዚካል አክቲቪቲ ጋይድ በሚል ርዕስ በቅርቡ ያወጣው ጽሑፍ “ጤንነትህን ለመጠበቅ ከባድ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ አያስፈልግህም” በማለት ገልጿል። ዘ ቶሮንቶ ስታር ሪፖርት እንዳደረገው “በየቀኑ በተለያዩ ሰዓቶች ላይ የ10 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው በድምሩ አንድ ሰዓት ገደማ የሚሆን ቀላል የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ አካላዊ ብቃትህንና የልብህን ጤንነት መጠበቅ ትችላለህ።” ጥሩ እንደሆኑ የተነገረላቸው አንዳንዶቹ እንቅስቃሴዎች ምንድን ናቸው? በእግር መሄድ፣ ደረጃ መውጣት፣ አትክልት መኮትኮትና መንጠራራት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው። ወለል መጥረግን ወይም መወልወልን የመሰሉ የቤት ውስጥ ሥራዎችም ከእነዚህ ጋር የሚመደቡ ሲሆን ቅልጥፍናን ይጨምራሉ። ጤና ጥበቃው ያወጣው ጽሑፍ “አካላዊ እንቅስቃሴን የዕለታዊ ኑሮ ክፍል በማድረግ” በየዕለቱ የ60 ደቂቃ ግብ ላይ መድረስ እንደሚቻል ገልጿል። የካናዳ የቤተሰብ ሐኪሞች ኮሌጅ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ፍራንሲን ለሚር “ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማታደርግ ከሆነ ከሚያጨሱ ሰዎች እኩል ጤንነትህ ለአደጋ የተጋለጠ ሊሆን እንደሚችል ጥናቶች አመልክተዋል” በማለት ተናግረዋል።

የሳቅ እጥረት

በቅርቡ ሳቅን አስመልክቶ በስዊዘርላንድ በተደረገ አንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የቀረበ መረጃ እንደጠቆመው የኢኮኖሚ ችግር በነበረባቸው በ1950ዎቹ ዓመታት አንድ ሰው በቀን ለ18 ደቂቃ ያህል ይስቅ ነበር። የኢኮኖሚ ብልጽግና በታየባቸው በ1990ዎቹ ዓመታት ግን አንድ ሰው በቀን ውስጥ የሚስቀው ለ6 ደቂቃ ብቻ ነው። ሳቅ እየቀነሰ የመጣው ለምንድን ነው? “ጠበብት እንደሚሉት ከሆነ ለዚህ ምክንያቱ ሰዎች በቁሳዊ ሀብትና በሥራ ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስና በግል ስኬታማ ለመሆን የሚያደርጉት ያልተቋረጠ ጥረት ሲሆን ይህም ገንዘብ ደስታ ሊገዛ አይችልም የሚለውን ጥንታዊ ብሂል እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ነው” ሲል የለንደኑ ሰንዴይ ታይምስ ገልጿል። በመሆኑም ደራሲው ማይክል አርጋይል እንደ ደመደሙት “ለገንዘብ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ብዙም እርካታ የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ የአእምሮ ጤንነት የላቸውም። ይህ የሆነው ገንዘብ ውስጣዊ እርካታ የማይሰጥ በመሆኑ ሊሆን ይችላል።”

የዓለም መሃይማን ቁጥር እየጨመረ ነው

“በዓለም ላይ ካለው 5.9 ቢልዮን ሕዝብ መካከል አንድ ስድስተኛ የሚሆነው ማንበብም ሆነ መጻፍ አይችልም” በማለት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አባባል የመሃይማኑ ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል። ለምን? ምክንያቱም በአስከፊ የድህነት ማጥ ውስጥ በሚገኙ አገሮች ከሚኖሩት አራት ልጆች መካከል ሦስቱ ትምህርት ቤት ገብተው አይማሩም። በዓለም ዙሪያ ተንሰራፍቶ ከሚገኘው የኢኮኖሚ ችግር በተጨማሪ በጎሣዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች ትምህርት ቤት ገብተው እንዳይማሩ ዕንቅፋት ሆኖባቸዋል። ጦርነት ትምህርት ቤቶችን ከማውደሙም በተጨማሪ ልጆች ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ ሳይሆን ለውትድርና እንዲመለመሉ ያደርጋል። ከዚህም በላይ መሃይምነት በማኅበረሰብ ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮችም የበኩሉን አስተዋጽዖ ያበረክታል። ዩኒሴፍ ዘ ስቴት ኦቭ ዘ ዎርልድስ ችልድረን 1999 በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት ላይ በመሃይምነትና ብዙ ልጆች በመውለድ መካከል ቀጥተኛ ዝምድና እንዳለ ገልጿል። ለምሳሌ ያህል በደቡብ አሜሪካ በምትገኝ በአንዲት አገር “መሃይማን የሆኑ እናቶች በአማካይ 6.5 ልጆች ሲኖሯቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተከታተሉ እናቶች ግን በአማካይ ያሏቸው ልጆች ቁጥር 2.5 ብቻ ነው” በማለት ታይምስ ገልጿል።

የአስም ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ ነው

ከዓለም የጤና ድርጅት የሚወጡ ሪፖርቶች እንዳመለከቱት ባለፉት አሥር ዓመታት በዓለም ዙሪያ የነበሩት የአስም ተጠቂዎችና በሐኪም ቤት ክትትል የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር በ40 በመቶ አሻቅቧል። ለጭማሪው መንስዔ የሆነው ነገር ምንድን ነው? የቤት እንስሳ ያላቸው ሰዎች ቁጥር እየበዛ መምጣቱና በተጣበቡና ንጹሕ አየር በሚያንሳቸው ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች መበራከታቸው ለችግሩ መንስኤ እንደሆነ የአሜሪካ የደረት ሐኪሞች ኮሌጅ አባላት ይናገራሉ። “ከእንስሳት (ቆዳ፣ ጸጉርና ላባ) የሚበን ብናኝ፣ የአቧራ ቅንጣት፣ ሻጋታ፣ የሲጋራ ጭስ፣ የአበባ ዱቄት፣ የአካባቢ ብክለት የሚያስከትሉ ንጥረ ነገሮችና ከባድ ጠረን” አስም ሊቀሰቅሱ ይችላሉ በማለት ዘ ቶሮንቶ ስታር ይናገራል። ከሁሉም የከፋው ግን የድመቶች ጠጉር ብናኝ ነው። በአስም የሚሞቱት አብዛኞቹ ሰዎች ሊድኑ ይችሉ የነበሩ በመሆናቸው አስም ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ሕመም ነው በማለት ጋዜጣው ተናግሯል። በአሁኑ ጊዜ በካናዳ 1.5 ሚልዮን የሚሆኑ የአስም ሕሙማን ሲኖሩ 500 የሚሆኑት ደግሞ በየዓመቱ በበሽታው ይሞታሉ።

ለተፈጥሮ አደጋ የተጋለጠችው እስያ

“ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም ከደረሱት 10 ዋና ዋና የተፈጥሮ አደጋዎች መካከል ስድስቱ የተከሰቱት በእስያ ሲሆን ለ27,000 ሰዎች ሕይወት መቀጠፍና 38 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ለሚያወጣ ንብረት መውደም ምክንያት ሆነዋል” በማለት ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ጋዜጣ ዘግቧል። ይህም በባንግላዴሽና በቻይና የደረሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅና አጎራባች አገሮቿ በጭጋግ እንዲሸፈኑ ያደረገውን በኢንዶኔዢያ ደን ላይ የደረሰውን ሰደድ እሳት ይጨምራል። “እስያ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ይበልጥ በከፍተኛ የተፈጥሮ አደጋ ትጠቃለች” በማለት በተባበሩት መንግሥታት የእስያና የፓስፊክ አገሮች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽን ገልጿል። “በ21ኛው መቶ ዘመን በተለይ የእስያ አገሮችን የሚጠብቃቸው ፈታኝ ሁኔታ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መቀነስ ነው።”

ውጥረት ውስጥ የገቡ ቤተሰቦች

በዛሬው ጊዜ ያሉ ቤተሰቦች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ደርሶ ከነበረው ጦርነት በኋላ ከነበሩ ቤተሰቦች ይበልጥ በከፍተኛ የገንዘብና የስሜት ውጥረት ውስጥ እንደሚገኙ በቅርቡ በካናዳውያን ላይ የተደረገ አንድ ጥናት አመልክቷል። ናሽናል ፖስት የተባለው ጋዜጣ በቤተሰብ ውስጥ ለሚከሰተው ውጥረት እንደ መንስኤ አድርጎ በግንባር ቀደምትነት የጠቀሳቸው ፍቺንና የቤተሰብ መፈራረስን ነው። በቅደም ተከተላቸው መሠረት ለቤተሰብ ውጥረት ምክንያት ሆነው የተጠቀሱት ሌሎች ነገሮች ደግሞ “ወላጆች እስኪደክሙ ድረስ ለረዥም ሰዓታት መሥራታቸው፣ የሥራው ዓለም አስተማማኝ አለመሆን፣ የቀረጥ ጫናና ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ለሚያደርጉት ጥረት አድናቆት መነፈጋቸው” ናቸው። እነዚህ ውጥረቶች በነጠላ ወላጅ በሚተዳደሩ በአብዛኞቹ ቤተሰቦች ላይ እንደሚያይሉ ጥያቄው የቀረበላቸው ሰዎች ተናግረዋል።

አሁንም ልጆች ትምህርት አያገኙም

በ1948 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የጸደቀው የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ትምህርት መሠረታዊ ከሆኑት መብቶች አንዱ እንደሆነ አስታውቋል። ብዙ አመርቂ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም አሁንም እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ገና ብዙ ይቀራል። “የዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ከጸደቀ ሃምሳ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ለትምህርት የደረሱ ሆኖም ትምህርት ቤት ገብተው የማይማሩ ከ130 ሚልዮን የሚበልጡ ልጆች አሉ” ሲል የጀርመኑ ዕለታዊ ጋዜጣ አልጌማይነ ሳይቱንግ ማይንትስ ዘግቧል። “ይህም በመላው ዓለም ካሉት ልጆች 20 በመቶ የሚሆኑት መሠረታዊ ትምህርት ሳያገኙ ቀርተዋል ማለት ነው።” በጀርመን የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ራይንሃርት ሽላጊንትቫይት እንዳሉት ከሆነ በመላው ዓለም የሚገኙት ልጆች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እንዲማሩ ለማድረግ 7 ቢልዮን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል። ይህ በአውሮፓ በየዓመቱ ለአይስክሬም ከሚወጣው ወይም በአሜሪካ በየዓመቱ ለመኳኳያ ከሚወጣው የገንዘብ መጠን በጣም ያነሰ ነው፤ እንዲሁም ዓለም ለጦር መሣሪያ ከሚያወጣው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር ኢምንት ነው።

አሥሩ ግንባር ቀደም ገዳይ ተላላፊ በሽታዎች

በመላው ዓለም በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ይሞታሉ። ናቹራል ሂስትሪ የተባለው መጽሔት እንዳለው በ1997 የሚከተሉት ተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት በመዳረግ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይዘዋል። እንደ ሳንባ ምች ያሉ የታችኛዎቹን የመተንፈሻ አካላት የሚያጠቁ አጣዳፊ በሽታዎች 3.7 ሚልዮን ሰዎችን በመፍጀት በአንደኛ ደረጃ ተመዝግበዋል። በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው ሳንባ ነቀርሳ ሲሆን 2.9 ሚልዮን ሰዎችን ገድሏል። ኮሌራና ሌሎች የተቅማጥ በሽታዎች 2.5 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎችን በመግደል የሦስተኝነትን ቦታ ይዘዋል። ኤድስ 2.3 ሚልዮን ሰዎችን ገድሏል። ከ1.5 እስከ 2.7 ሚልዮን የሚደርሱ ሰዎች በወባ በሽታ እንደ ቅጠል ረግፈዋል። ኩፍኝ ለ960,000 ሰዎች መሞት ምክንያት ሆኗል። ሄፕታይተስ ቢ 605,000 ሰዎችን ለሞት ዳርጓል። ትክትክ የ410,000 ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ተነግሯል። ሌሎች 275,000 የሚያክሉ ደግሞ በመንጋጋ ቆልፍ አልቀዋል። እንዲሁም 140,000 ሰዎች ዴንጊ/ዴንጊ ሄሞሬጅክ ፊቨር በሚባል በሽታ ሞተዋል። የሰው ልጅ ምንም ያክል ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ዘመናት ያስቆጠሩት ተላላፊ በሽታዎች በአሁኑ ወቅትም በአብዛኛው የዓለም ክፍል የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለውታል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ