50 ዓመት ሙሉ ያልተሳኩ ጥረቶች
“እኛ የተባበሩት መንግሥታት ሕዝቦች በእኛ የሕይወት ዘመን ውስጥ ሁለት ጊዜ በሰው ልጆች ላይ ይህ ነው የማይባል ሐዘን ካስከተለው ከጦርነት መቅሠፍት መጪዎቹን ትውልዶች ለማዳን እና መሠረታዊ በሆኑ ሰብዓዊ መብቶች፣ በሰዎች ውድነትና ክብር እንዲሁም ወንዶችና ሴቶችም ሆኑ ትላልቅና ትናንሽ አገሮች እኩል መብቶች እንዳላቸው እንደምናምን እንደገና ለማረጋገጥ . . . ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።”—የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መግቢያ
የተባበሩት መንግሥታት 50ኛ ዓመት ጥቅምት 24, 1995 ይከበራል። በአሁኑ ወቅት ያሉት 185 አባል አገራት በሙሉ በድርጅቱ ቻርተር ላይ የተገለጹትን የመጀመሪያዎቹን መሠረታዊ ደንቦችና ዓላማዎች ለመፈጸም ቃል ገብተዋል፤ እነርሱም፦ ዓለም ዓቀፍ ሰላምና ደኅንነት ማስከበር፣ የዓለምን ሰላም የሚያደፈርሱ የጠብ ጫሪነትን ተግባራት ማገድ፣ በአገሮች መካከል ወዳጃዊ ግንኙነት እንዲኖር ማበረታታት፣ በዘር፣ በጾታ፣ በቋንቋ ወይም በሃይማኖት ልዩነቶች እንዳይፈጠሩ በማድረግ ሰዎች ሁሉ ያላቸውን መሠረታዊ ነፃነቶች ማስከበር እና ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ችግሮችን ለማስወገድ ዓለም አቀፍ ትብብር ማድረግ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ለማምጣት ለ50 ዓመታት ከፍተኛ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ሦስተኛ የዓለም ጦርነት እንዳይቀሰቀስና የኑክሌር ቦምቦች እንደገና ፈንድተው አጠቃላይ የሆነ የሰው ዘር ጥፋት እንዳይደርስ ተከላክሏል ሊባል ይችላል። የተባበሩት መንግሥታት በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሕፃናት ምግብና መድኃኒቶችን አቅርቧል። ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ንጹሕ የመጠጥ ውኃና ከአደገኛ በሽታዎች የሚከላከል ክትባት እንዲሰጥ በማድረግ በብዙ አገሮች ውስጥ ያለው የጤና ደረጃ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ሰብዓዊ እርዳታ ተደርጎላቸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላከናወናቸው ተግባራት እውቅና ለመስጠት አምስት ጊዜ የሰላም የኖቤል ሽልማት ተሰጥቶታል። ሆኖም አሁንም የምንኖረው ከጦርነት ነፃ ባልሆነ ዓለም ውስጥ መሆኑ በጣም ያሳዝናል።
ሊደረስባቸው ያልቻሉት የሰላምና ደኅንነት ግቦች
የተባበሩት መንግሥታት ለ50 ዓመታት ከጣረ በኋላ ሰላምና ደኅንነት አሁንም ቢሆን ሊደረስባቸው ያልቻሉ ግቦች ሆነዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዘዳንት በቅርቡ ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ላይ “ይህ መቶ ዘመን ከፍተኛ ተስፋዎች፣ አጋጣሚዎችና ክንውኖች የሞሉበት ከመሆኑም በተጨማሪ ከባድ ጥፋትና ተስፋ መቁረጥ የደረሰበት ዘመን ሆኗል” ብለዋል።
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እስከ 1994 ማብቂያ ድረስ “150 የሚያህሉ ጦርነቶች ወይም አነስተኛ ግጭቶች በመካሄድ ላይ ሲሆኑ ይበልጡን ሲቪሎች የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመሞታቸውም በተጨማሪ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሆነዋል” በማለት ዘግቧል። የተባበሩት መንግሥታት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ባደረገው ሪፖርት መሠረት ከ1945 ጀምሮ በታጠቁ ኃይሎች መካከል በተነሡ ግጭቶች ከ20 ሚልዮን በላይ የሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማድሊን ኦልብራይት “በአሁኑ ጊዜ የአካባቢ ግጭቶች በብዙ መንገዶች በይበልጥ የአውሬነት ፀባይ የሚታይባቸው ሆነዋል” ሲሉ ገልጸዋል። በየቀኑ በዜና ማሰራጫዎች ስለ ሰብዓዊ መብቶች ረገጣና ስለ ዘር መድልዎ ይሰማል። ብዙ ብሔራት እርስ በርሳቸው ከመቀራረብ ይልቅ ተቻችለው የሚኖሩ ይመስላሉ።
በተባበሩት መንግሥታት የብሪታኒያ አምባሳደር የሆኑት ሰር ዴቪድ ሐኔይ “የተባበሩት መንግሥታት ከ1945 ጀምሮ እስከ 1980ዎቹ ድረስ በአብዛኛው አልተሳካለትም” ሲሉ አምነዋል። የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ሰላምን በማስከበር ረገድ በአባል አገራት መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ የግዴለሽነትና የመታከት ሁኔታ ይታያል ሲሉ አማረዋል። ብዙዎቹ አባል አገራት “ለተባበሩት መንግሥታት ትኩረት አይሰጡትም” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ተጽዕኖ
የተባበሩት መንግሥታት የቱንም ያህል ኃያል መስሎ ቢታይም የሚያደርጋቸው ጥረቶች ብዙውን ጊዜ በፖለቲከኞችና በመገናኛ ብዙሃን በተዛባ መልኩ ይቀርባሉ። የተባበሩት መንግሥታት የአባላቱን ድጋፍ ካጣ ምንም ኃይል አይኖረውም። ይህም ሆኖ ብዙ የተባበሩት መንግሥታት አባላት ያለ ሕዝብ ድጋፍ የተባበሩት መንግሥታትን አይደግፉም። ለምሳሌ ያህል ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው “ብዙ አሜሪካውያን የተባበሩት መንግሥታት በሶማልያና በቦስኒያ እንዳልተሳካለት ሲመለከቱ ድርጅቱ ገንዘብ አባካኝ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው የሚል እምነት አድሮባቸዋል።” ይህ የሕዝብ አመለካከት ደግሞ አሜሪካ ለተባበሩት መንግሥታት የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ እንድትቀንስ ሐሳብ ለማቅረብ አንዳንድ አሜሪካውያን ፖለቲከኞችን አነሣስቷቸዋል።
የዜና ማሰራጫ ድርጅቶች የተባበሩት መንግሥታትን ክፉኛ ለመተቸት አያመነቱም። “ጨርሶ ችሎታ የሌለው፣” “ሥራው ሁሉ የተጓተተ፣” “አጥጋቢ ውጤት የማያስገኝ” እና “የተሽመደመደ” እንደሚሉት ያሉትን ቃላት የተባበሩት መንግሥታትን የተለያዩ ክፍሎች ለመግለጽ ያለገደብ ተጠቅመዋል። በቅርቡ ዘ ዋሽንግተን ፖስት ናሽናል ዊክሊ ኤድሽን “የተባበሩት መንግሥታት ራሱን ከገሀዱ ዓለም ጋር አስማምቶ ለመኖር የሚታገል ጎታች ቢሮክራሲ ሆኗል” በማለት ገልጿል።
ሌላ ጋዜጣ ዋና ጸሐፊውን ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊን ጠቅሶ በሩዋንዳ ውስጥ በደረሰው እልቂት ግራ መጋባታቸውን ገልጿል። “ይህ ውድቀት የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ውድቀት እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ውድቀት ብቻ አይደለም። ሁላችንም ለዚህ ውድቀት ተጠያቂዎች ነን” ብለዋል። በ1993 አንድ ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም የተባበሩት መንግሥታት “ከሁሉ የበለጠ የሰላም ጠንቅ የሆኑትን የኑክሌር የጦር መሣሪያዎች መስፋፋት ማገድ አልቻለም” በማለት ገልጾ ነበር። የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ የተባበሩት መንግሥታትን “ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ወሬ ብቻ ሆኖ ቆይቷል” ሲል ተችቶታል።
ይህ በስፋት የተሰራጨው ቅሬታ የተባበሩት መንግሥታት ባለ ሥልጣናትን በጣም ከማስጨነቁም በላይ ይበልጥ ግራ እንዲጋቡ አድርጓል። ሆኖም ይህ ሁሉ ግራ መጋባት ቢኖርም የተባበሩት መንግሥታት 50ኛ ዓመት የሚከበርበት ወቅት ብዙዎች ብሩህ አመለካከታቸውን የሚያድሱበትና አዲስ ጅምር እንደሚቀይሱ ተስፋ የሚያደርጉበት ጊዜ ይመስላል። አምባሳደር ኦልብራይት የተባበሩት መንግሥታት ያሉትን ድክመቶች ቢያምኑም “ባለፈው ጊዜ ምን እንዳደረግን ከማውራት ይልቅ ወደፊት ምን እንደምንሠራ መነጋገር ይኖርብናል” ሲሉ የብዙዎችን አመለካከት አንጸባርቀዋል።
ዓለም ወዴት እያመራ ነው? ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ይመጣ ይሆን? የሚመጣ ከሆነ የተባበሩት መንግሥታት በዚህ ረገድ ምን ሚና ይጫወታል? ከዚህም በላይ ፈሪሃ አምላክ ያለህ ሰው ከሆንህ ‘አምላክ በዚህ ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?’ ብለህ መጠየቅ ይኖርብሃል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ያልተሳኩ ጥረቶች
ጦርነት፣ ድህነት፣ ወንጀልና ምዝበራ እስካሉ ድረስ ሰላምና ደኅንነት ሊገኙ አይችልም። በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት እነዚህን አሃዞች አውጥቷል።
ጦርነቶች፦ “ከ1989 እስከ 1992 የጦር መሣሪያ የታጠቁ ኃይሎች ካደረጓቸው 82 ግጭቶች መካከል 79ኙ የአገር ውስጥ ጦርነቶች ሲሆኑ ብዙዎቹ አንዱ ጎሣ ከሌላው ጎሣ ጋር ያደረጓቸው ግጭቶች ነበሩ፤ የጉዳቱ ሰለባ ከሆኑት ውስጥ 90 በመቶዎቹ ሲቪሎች ነበሩ።” የተባበሩት መንግሥታት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል (ዩ ኤን ዲ ፒ አይ)
የጦር መሣሪያዎች፦ “አይ ሲ አር ሲ [ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ] በ48 አገሮች ውስጥ ያሉ ከ95 በላይ የሆኑ ፋብሪካዎች በየዓመቱ ከ5 እስከ 10 ሚልዮን የሚደርሱ ፈንጂዎችን እንደሚያመርቱ ገምቷል።”—የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩ ኤን ኤች ሲ አር)
“በአፍሪካ ወደ 30 ሚልዮን የሚጠጉ ፈንጂዎች በ18 አገሮች ውስጥ ተበታትነው ይገኛሉ።”—ዩ ኤን ኤች ሲ አር
ድህነት፦ “በመላው ዓለም ከአምስት ሰዎች መካከል አንዱ ማለትም ከአንድ ቢልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከመጨረሻው የድህነት ደረጃ በታች የሚኖሩ ከመሆናቸውም በላይ በየዓመቱ ከ13 እስከ 18 ሚልዮን የሚደርሱ ሰዎች ከድህነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች እንደሚሞቱ ይገመታል።”—ዩ ኤን ዲ ፒ አይ
ወንጀል፦ “ከ1980ዎቹ ጀምሮ የወንጀል ዘገባዎች በየዓመቱ በ5 በመቶ ጨምረዋል፤ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በየዓመቱ 35 ሚልዮን ወንጀሎች ይፈጸማሉ።”—ዩ ኤን ዲ ፒ አይ
ምዝበራ፦ “የሕዝብ ምዝበራ የተለመደ ሆኗል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ አገሪቱ በየዓመቱ ከምታስገባው ገቢ 10 በመቶ ከሚሆነው ጋር የሚመጣጠን ገንዘብ እንደሚጭበረበር ተገምቷል።”—ዩ ኤን ዲ ፒ አይ