ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ሊመጣ ይችላልን?
የጦርነትን ሰቆቃና የሚያስከትለውን መዘዝ ፈጽሞ የማታይበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። የጥይት ድምፅ ወይም የቦምብ ፍንዳታ ፈጽሞ የማትሰማበት፣ ረሃብ ያጠወለጋቸው ስደተኞች ቀዬአቸውን ጥለው ሲሰደዱ የማትመለከትበት እንዲሁም ጭካኔ የተሞላበትና ዓላማ ቢስ የሆነ ግጭት ተነሥቶ እኔም ሆንኩ የማፈቅራቸው ሰዎች እንሞት ይሆን ብለህ ፈጽሞ የማታስብበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ጦርነት በማይኖርበት ዓለም ውስጥ መኖር ምንኛ ያስደስታል!
‘ይህ ሊሆን የማይችል ተስፋ ነው’ ትል ይሆናል። ሆኖም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ሰዎች ሰላም የሰፈነበት ዓለም ይመጣል የሚለው ተስፋ በዓይነ ሕሊናቸው ብሩህ ሆኖ እየታያቸው ነው። በ1990 እና በ1991 ብሔራት ደኅንነትና ተባብሮ የመሥራት መንፈስ ወደሚሰፍንበት አዲስ ዘመን እየተሻገሩ እንዳሉ ብዙዎች ይናገሩ ነበር። በወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆርጅ ቡሽ “አዲስ የዓለም ሥርዓት” ስለ መቅረቡ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲናገሩ በዚያን ጊዜ የነበረውን ስሜት አንጸባርቀዋል።
ሰዎች እንዲህ ያለ ብሩህ ተስፋ ሊኖራቸው የቻለው ለምንድን ነው? ቀዝቃዛው ጦርነት አክትሟል። ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት የሰው ልጅ የኑክሌር ጦርነት ይነሣ ይሆናል በሚል ፍርሃት ሲቃትት ኖሯል። ይሁን እንጂ ኮሚኒዝም ከከሰመና ሶቭየት ኅብረት ከፈራረሰች በኋላ የኑክሌር እልቂት ስጋት የጠፋ ይመስላል። ዓለም ተንፈስ ብሏል።
ሰዎች በዚያን ጊዜ የወደፊቱን ሁኔታ በልበ ሙሉነት የተመለከቱበትና አሁንም ቢሆን የሚመለከቱበት ሌላ ዋነኛ ምክንያት አለ። ለአራት አሥርተ ዓመታት በምሥራቁና በምዕራቡ መካከል የተካሄደው ሽኩቻ የተባበሩት መንግሥታትን የክርክር መድረክ ብቻ አድርጎት ነበር። ሆኖም ቀዝቃዛው ጦርነት ማክተሙ የተባበሩት መንግሥታት በመላው ዓለም ሰላምና ደኅንነት እንዲሰፍን ጥረት በማድረግ የተቋቋመበትን ዓላማ ዳር ለማድረስ መንቀሳቀስ የሚችልበትን ሁኔታ ፈጥሮለታል።
በቅርብ ዓመታት የተባበሩት መንግሥታት ጦርነትን ለማስቆም የሚያደርጋቸውን ጥረቶች አጠናክሯል። የተባበሩት መንግሥታት ከ1994 በፊት በነበሩት 4 ዓመታት ውስጥ ከአባል አገራት በተውጣጣ ሠራዊት አማካኝነት ሰላም ለማስጠበቅ ያደረጋቸው በርካታ ወታደራዊ ዘመቻዎች ከዚያ በፊት በነበሩት 44 ዓመታት ካካሄዳቸው ሰላም የማስጠበቅ ተልእኮዎች የላቁ ናቸው። ወደ 70,000 የሚጠጉ ሲቪሎችና ወታደራዊ ሠራተኞች በመላው ዓለም በተደረጉት 17 ዘመቻዎች ተካፍለዋል። በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም ለማስጠበቁ ተልእኮ ያወጣው ወጪ ከእጥፍ በላይ አድጎ በ1994 ወደ 3.3 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ በቅርቡ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የዛሬ 50 ዓመት ገደማ [የተባበሩት መንግሥታት በተመሠረተበት ወቅት] በሳን ፍራንሲስኮ የተቋቋመው የጋራ ደኅንነት ሥርዓት የታቀደለትን ዓላማ ማከናወን እንደ ጀመረ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። . . . የታቀደውን ግብ የሚመታ አንድ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት በመመሥረት ላይ ነን።” ምንም እንኳ እነዚህ ሁኔታዎች ቢኖሩም የአዲሱ ዓለም ሥርዓት ዕይታ በፍጥነት እየደበዘዘ ነው። የሰው ልጅ ጦርነት የማይኖርበት ዓለምን በተመለከተ የነበረውን ተስፋ ያጨለመው ምንድን ነው? ዓለም አቀፍ ሰላም የምናገኝበት ጊዜ ይመጣል ብለን ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት ይኖራልን? የሚቀጥሉት ርዕሶች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጦር አውሮፕላኖች:- USAF photo
አየር መቃወሚያዎች:- U.S. National Archives photo